በአንድ አገር ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ ከሚከሰቱ ተግዳሮቶች ውስጥ አንዱ እና ዋነኛው የኑሮ ውድነት ነው። ይህንን ችግር ለመፍታትም የንግዱ ማኅበረሰብ በተለይም መንግስት በከፍተኛ ኃላፊነት እንዲንቀሳቀሱ ይጠበቃል።
በአገራችንም ከለውጡ ማግስት ጀምሮ ለውጡን በከፍተኛ ሁኔታ እየተፈታተኑ ከሚገኙ መሰረታዊ ችግሮች መካከል አንዱ የኑሮ ውድነት ነው፤ የኑሮ ውድነቱ በተለያዩ ገፊ ምክንያቶች የተከሰቱ ቢሆኑም፤ በአብዛኛው ችግሮቹ ሰው ሰራሽ የመሆናቸው እውነታ የሕዝብን ኑሮ የመገዳደር አቅሙ ዕለት ተዕለት እያደገ እንዲመጣ አድርጎታል።
በአንድ በኩል በአገር አቀፍ ደረጃ ያለው የገበያ ስርአት የተበላሸ መሆን፤ በሌላ በኩል ስርአቱን አስተካክሎ ለመምራት ኃላፊነት የተሰጣቸው መንግስታዊ ተቋማትና ቢሮዎች በችግሩ ላይ የማያዳግም እርምጃ ከመውሰድ ይልቅ በተለመዱ ምክንያቶች ራሳቸውን አጥረው መገኘታቸው ለችግሮቹ መገንገን አይነተኛ ምክንያት ሆኗል።
እንዲያውም የሚመለከታቸው ተቋማት ሁሌም ለችግሮቹ እንደ ምክንያት የሚያቀርቧቸው ምክንያቶች የተለመዱና ሁሌም ችግሩ ከገበያ ሰንሰለት ጋር ይያያዛል የሚል መሆኑ ሲታይ ሕዝብን ከማሰልቸት አልፎ ተስፋ ወደመቁረጥ እያደረሰው ይገኛል፡፡ ይህም የንግድ ስርዓቱን የመቆጣጠር ኃላፊነት የተጣለባቸውን ተቋማት ችግሮችን የመፍታት አቅምና ተአማኒነት ጥያቄ ውስጥ እየከተተው ነው።
አሁን ላይ ከገጠር እስከ ከተማ አሳማኝ ባልሆኑ ምክንያቶች የሚፈጠሩ የተጋነኑ የዋጋ ንረቶች በተለይም በከተሞች አካባቢ በሚኖሩ ዜጎች ላይ እያስከተሉት ያለው መጠነ ሰፊ ችግር በዚሁ ከቀጠለ፤ ዝቅተኛ ገቢ ያላቸው ብቻ ሳይሆኑ መካከለኛ ገቢ ያላቸው ዜጎች በልቶ የማደር ጉዳይ ጥያቄ ውስጥ ሊገባ የሚችልበት ሁኔታ ሊከሰት እንደሚችል መገመት የሚከብድ አይሆንም።
በአገሪቱ ካለው ተጨባጭ እውነታ አንጻር በአሁኑ ወቅት የዋጋ ጭማሪ ያልተደረገባቸው ለገበያ የሚቀርቡ ሸቀጦች አሉ ለማለት የሚያስደፍር አይደለም፡፡ ጠዋት የገዙትን ሸቀጥ ማታ በተመሳሳይ ዋጋ ማግኘት በአብዛኛው የሚታሰብ አይደለም፤ ማታ የገዙትን እንዲሁ ጠዋት በነበረበት ዋጋ አያገኙትም። ከዚህም የተነሳ የሸቀጦች ዋጋ ከቁጥጥር ውጪ የሚሆንበት ስጋት ዕለት ተዕለት እየጨመረ ነው ።
የቀደሙትን ትተን በቅርቡ እንኳን በጤፍ ዋጋ ላይ በአዲስ አበባ እየታየ ያለው ያልተገባ የዋጋ ጭማሪ /በኩንታል ከሁለት ሺህ ብር በላይ/ መካከለኛ ገቢ ባለው ኅብረተሰብ በተለይም ዝቅተኛ ገቢ ባላቸው የመንግስት ሰራተኞችና ሌሎች የኅብረተሰብ ክፍሎች የዕለት ተዕለት ሕይወት ላይ ሊያስከትል የሚችለው ሁለንተናዊ ተጽእኖ በቀላሉ የሚሰላና በዝምታ ሊታለፍ የሚችል አይደለም።
ለግብርና በተሰጠ ትኩረት በአገሪቱ ከፍተኛ ምርት በተገኘበት ወቅት የብዙ ኢትዮጵያውያን የምግብ ምንጭ በሆነው ጤፍ ላይ የዚህን ያህል የዋጋ ጭማሪ መታየቱ በምንም ዓይነት መልኩ በተለመዱ ምክንያቶቹ አለባብሰው ሊያልፉት የሚችሉት ጉዳይ አይሆንም።
የምርት እጥረት በሌለበት ወቅት የተፈጠረው ይህን መሰል የዋጋ ንረት፤ በመንግስት በኩል ከፍያለ ትኩረት ሊሰጠው የሚገባው ነው፡፡ ችግሩ ሕዝብን ለምሬት የሚዳርግና የመኖር ህልውናውን በእጅጉ የሚፈታተን በመሆኑ በተለይም በንግድ ሰርዓቱ ላይ የሚሰሩ መንግስታዊ ተቋማት ችግሩን ከፍ ባለ ደረጃ ሊመለከቱትና የማያዳግም መፍትሄ የሚያገኝበትን መንገድ ሊቀይሱ ይገባል።
በደላላና በቆየ የተበላሸ የገበያ ስርአት እየተመካኘ መፍትሄ አልባ ሆኖ የዘለቀው ይህ ችግር፤ በቂ የትርክት እና የምሬት ጊዜዎችን አልፏል፡፡ ከእንግዲህ እነዚህን ችግሮች እንደምክንያት አድርጎ ማምጣት የሞራል ጥያቄ ሊያስነሳ የሚችል ነው።
የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር መስሪያ ቤትን ጨምሮ ሌሎች የሚመለከታቸው አካላት በህግ ከተሰጣቸው ስልጣንና ኃላፊነት አንጻር ራሳቸውን በአግባቡ በመገምገም፤ እንደ አገር ችግሮቹን ተሻግሮ መጓዝ የሚቻልበትን ሁለንተናዊ ቁመና መፍጠር ይኖርባቸዋል። ለዚህ ደግሞ ከተለመዱ ምላሾችና ዝምታዎች ወጥተው ስትራቴጂክ በሆነ መንገድና በተቀናጀ እና በተናበበ አካሄድ ዜጎች ባልተገቡ ምክንያቶች የሚከፍሉትን ዋጋ ማስቆም ይኖርባቸዋል!
አዲስ ዘመን የካቲት 30 ቀን 2015 ዓ.ም