ከጥንታዊ የአትሌቲክስ ውድድሮች መካከል አንዱ የሆነው የቦስተን ማራቶን፤ ከዘመናዊው ኦሊምፒክ ምስረታ አንድ ዓመት በኋላ (እአአ 1897) ነበር መካሄድ የጀመረው። በዚህ ሩጫ ሴቶች ተሳታፊ እንዲሆኑ የተፈቀደላቸው ግን ከ75 ዓመታት ቆይታ በኋላ ነው። ይህ ሁኔታ ያልተዋጠላት አሜሪካዊቷ አትሌት ካትሪን ስዊዘር ግን እአአ በ1967 የፈጸመችው ገድል ዛሬ ላይ ላለው የሴት ስፖርተኞች ተሳትፎ በር የከፈተ ነው ሊባል ይችላል። በወቅቱ አትሌቷ ርቀቱን ለመሸፈን ፈቃድ ሳታገኝ በሩጫው ላይ በመሳተፏ አቋርጣ እንድትወጣ በአዘጋጆቹ መገፍተርና መዋከብ ደርሶባት ነበር።
ይሁንና ዓላማዋ ሴቶች እንደሚችሉ ማሳየትና ትኩረት እንዲያገኙ ማድረግ በመሆኑ በደረሰባት ሁኔታ ሳትደናገጥ አስደናቂውን ታሪክ በወርቃማ ቀለም ለማጻፍ ችላለች። የበርካታ ሴት ስፖርተኞች ተምሳሌት የሆነችው የቀድሞዋ አትሌት ስዊዘር ‹‹ብቃትና ተሰጥኦ የትም አለ፤ አስፈላጊው ነገር እድል ማግኘት ነው›› የሚል አባባል አላት። በእርግጥም ባመነችበት ነገር ወደኋላ አትልምና ሌሎችም ይህንኑ መተግበር እንዳለባቸው መሰሎቿን ታስገነዝባለች። በእርግጥ ይህ ሁኔታ የአትሌቷ ገጠመኝ ብቻም አይደለም፤ ይልቁንም ሴት ስፖርተኞች ባለፈው ዘመን የተጓዙበት ጎዳና ነው።
የዓለም ስፖርት ታሪክ የሴቶች ተሳትፎ ከወንዶች የዘገየ መሆኑን ያትታል። የስፖርታዊ ውድድሮች ሁሉ ቁንጮ የሆነው ኦሊምፒክም ጭምር የሴቶችን እኩል ተሳትፎ ለማረጋገጥ ለዓመታት አዝግሟል። ከክርስቶስ ልደት አስቀድሞ መካሄድ የጀመረው ይህ ጥንታዊ ውድድር፤ ከአካላዊ እንቅስቃሴና የፉክክር መድረክነቱ ባለፈ የሰው ልጆችን በእኩልና በሚዛናዊነት ማሳተፍ መቋጫ ሃሳቡ ነው። ይሁንና በሴቶች ተዋጽኦ እና በሚወዳደሩባቸው ስፖርቶች ልዩነቶችን ማጣጣም የቻለው በቅርቡ ነው።
ከሁለት ዓመት በፊት ጃፓን በታሪኳ ለሁለተኛ ጊዜ ያዘጋጀችው የቶኪዮ ኦሊምፒክ በታሪካዊነቱ ከኦሊምፒክ የክብር መዝገብ ላይ ሊሰፍር ችሏል። ይህ ከሆነበት ምክንያት አንዱ ደግሞ ከተወዳዳሪ አትሌቶች መካከል 49 ከመቶ የሚሆኑት ሴቶች በመሆናቸው የጾታ ምጣኔው ለመጀመሪያ ጊዜ ለእኩልነት የቀረበ በመሆኑ ነው። ይህም ማለት በኦሊምፒኩ ተካፋይ ከነበሩት 206ቱ ብሄራዊ የኦሊምፒክ ኮሚቴዎች፤ ሴት ስፖርተኞችን ያላካተተ አልነበረም። ተስፋ ሰጪ የሆነው ይህ ሁኔታ ሊፈጠር የቻለው ግን እጅግ ረጅምና አስቸጋሪ ርቀትን ተጉዞ መሆኑ ግን ሊዘነጋ አይገባውም።
የታሪክ መዛግብት እንደሚያትቱት ከሆነ ጥንታዊው ኦሊምፒክ የሚከወነው ግሪካውያኑ አማልዕክቶቻቸውን ለመዘከር በመሆኑ ሴቶች መሳተፍ አይችሉም ነበር። ክልከላው ከተሳትፎ ባለፈ በክብረበዓሉ የሚከወኑ ውድድሮችን ሲመለከቱ ቢገኙ ከባድ ስቃይን አልፎም ሞትን ሊያስፈርድባቸው የሚችል ነው። የሴቶች ብቸኛው ተሳትፎ በፈረስ ስፖርት እንዲሁም የአማልክቶቻቸው አምላክ የሆነው ዜውስ ባለቤት በሆነችው ሄሪያ በተሰየመው የሴቶች ኦሊምፒክ የተገደበ ነበር። ለዘመናት በዚህ ሁኔታ አንዳቸው ለሌላኛቸው ባእድ ሆነው የዘለቁት ሴቶች እና የኦሊምፒክ ተሳታፊነት በዘመናዊው ኦሊምፒክም መንጸባረቁ አልቀረም። ምክንያቱ ደግሞ እአአ በ1896 የተጀመረው ዘመናዊው ኦሊምፒክ የተካሄደው በወንድ ስፖርተኞች መካከል በመሆኑ ነው።
በእርግጥ በመካከለኛው ዘመንም ከግሪክ ባለፈ ባሉ ሀገራት የሴቶች ስፖርታዊ ተሳትፎ ከአካላዊ ብቃት እና ከጉልበት ጋር የሚያያዝ በመሆኑ እዚህ ግባ የሚባል አልነበረም። በሮማውያን እንዲሁም በሌሎች አውሮፓውያን ዘንድም አልፎ አልፎ የሚታይ ቢሆንም ቀጣይነት ግን አልነበራቸውም። እስከ 18ኛው ክፍለ ዘመን በነበረው ወቅትም ቢሆን የሴቶች ሚና በቤት ውስጥ ስራዎችና ቤተሰብን በመምራት ኃላፊነት ላይ የተገደበ በመሆኑ በስፖርቱ የነበራቸው እንቅስቃሴ እምብዛም ነበር። የነበሩትም ቢሆኑ በአካላዊ እንቅስቃሴ እና ፉክክር ላይ የተመሰረተ ከመሆን ይልቅ በተስተካከለ አቋምና ቁንጅና ጋር የተያያዘ እንደነበረም መዛግብቱ ያወሳሉ። ስፖርታዊ ውድድሮች በሚካሄዱባቸው ሜዳዎች ላይ ሴት ስፖርተኞች መታየት እንዲሁም በተለያዩ ስፖርታዊ ሁነቶች ውስጥ ተሳትፏቸውን እያረጋገጡ የመጡትም ከ19ኛው ክፍለዘመን አጋማሽ ወዲህ ነው።
ዘመናዊው ኦሊምፒክ በወንዶች ብቻ የተጀመረ ቢሆንም ‹‹የዘመናዊው ኦሊምፒክ አባት›› በመባል የሚጠሩት ፈረንሳዊው ፒየር ደኩበርቲን ስህተቱን ወዲያው ነበር የተገነዘቡት። የወቅቱን ሁኔታም ‹‹አካታች ያልሆነ፣ የማይስብ፣ ውበት የጎደለውና ትክክል ያልሆነ›› ሲሉ ገልጸውታል። እኚህ ከዘመናቸው እጅግ የቀደሙት የስነትምህርት ጠቢብ ኋላ ላይ ‹‹ሁሉም ስፖርቶች ሊከወኑ የሚገባቸው እኩልነትን መሰረት አድርገው ነው›› በማለትም ተገቢ ያሉትን ሁኔታ በተግባር አንጸባርቀዋል።
ሴቶች በኦሊምፒክ መድረክ ለመጀመሪያ ጊዜ የታዩት በፈረንሳይ ፓሪስ በተካሄደው ቀጣዩ ኦሊምፒክ ሲሆን፤ የቴኒስ እና ጎልፍ ደግሞ በወቅቱ ውድድር ለማድረግ የተፈቀዱ ስፖርቶች ነበሩ። በኦሊምፒክ ታሪክ ውድድሯን በበላይነት በመፈጸም የመጀመሪያውን የወርቅ ሜዳሊያ ያጠለቀችው እንስትም እንግሊዛዊቷ ቻርሎቴ ኩፐር እንደሆነችም ታሪክ ያወሳል። እአአ በ1912 ደግሞ በውሃ ዋና ስፖርት ሴቶች እንዲወዳደሩ ቢደረግም በወቅቱ ከጾታ ጋር ተያይዞ በህብረተሰቡ ዘንድ የነበረውን ሁኔታ በግልጽ ሊያመላክት የሚችል አወዛጋቢ ሃሳብ ተነስቶ ነበር። ይኸውም ዋናተኞቹ ለውድድሩ ምቹ የሆኑ አልባሳትን ከመጠቀም ይልቅ ዘወትር እንደሚያደርጉት ቀሚስ ለብሰው ይወዳደሩ የሚለው ነበር።
ሌሎቹ ስፖርቶችም ቀስ በቀስ ወደ ኦሊምፒክ የተጠቃለሉ ሲሆን፤ ኢትዮጵያ በዚህ መድረክ በተለይ የምትታወቅበት ስፖርት አትሌቲክስ እንዲሁም ጂምናስቲክ እአአ ከ1928 አንስቶ የሴቶች ተሳትፎ እንዲኖራቸው ተወስኗል። ይሁንና በጊዜው በተካሄደው የ800 ሜትር ሩጫ ውድድር በርካታ ተወዳዳሪዎች ራሳቸውን በመሳታቸው እአአ እስከ 1960 በዚህ ርቀት እንዳይሮጡ ታግዶ ነበር የቆየው። በቀጣይ ዓመታትም የተለያዩ ስፖርቶች በጥቂቱ ከመካተት ባለፈ እአአ በ1996 የሴቶች ብቻ የሆነ ውድድር ተጀምሮም ነበር በኦሊምፒክ። ነገር ግን ይህ ‹‹ሶፍትቦል›› የተባለና ከ‹‹ቤዝቦል›› ጋር ተመሳሳይነት ያለው ውድድር ብዙም ሳይቆይ ከመድረኩ ሊሰረዝ ችሏል።
በባህሪያቸው የተለዩት የፈረስ ግልቢያ እንዲሁም የጀልባ ቀዘፋ ስፖርቶች ደግሞ ለአሸናፊነት የሚደረገው ፍልሚያ በወንዶችና ሴቶች መካከል የሚከወን ነው። የቴኒስ እና ባድሜንተን ስፖርቶችም በቀደመው ዘመን በተመሳሳይ ሁለቱም ጾታዎች በድብልቅ ይወዳደሩባቸው ነበር።
ሴቶች በኦሊምፒክ ውድድር እንዲያደርጉበት የተደረገው የመጨረሻው ስፖርት ቦክስ ሲሆን፤ እአአ በ2012 ለንደን አዘጋጅታ በነበረችበት ወቅት ነው። ከዚህም በኋላ ለወንዶች ብቻ የተፈቀደ አልያም ሴቶች ያልተካተቱበት የኦሊምፒክ ስፖርት የለም። በሌላ በኩል በኦሊምፒክ ይታይ የነበረው አሉታዊ ጉዳይ ሀገራት ሁለቱንም ጾታዎች ያማከለ ተሳትፎ ያለማድረጋቸው ነበር። ለአብነት ያህል እአአ የለንደን ኦሊምፒክ እስከተካሄደበት ጊዜ ድረስ ሶስት ሀገራት (ኳታር፣ ብሩኔ እና ሳውዲ አረቢያ) በታሪካቸው ሴት ስፖርተኞችን በኦሊምፒክ መድረክ አሳትፈው አያውቁም ነበር። ነገር ግን ዓለም አቀፉ የኦሊምፒክ ኮሚቴ ባደረገው ጥረት ሀገራቱ ሁለቱንም ጾታ ያማከለ ተሳትፎ ማድረግ ጀምረዋል። ይኸውም የለንደኑን ኦሊምፒክ በመድረኩ የሴት ስፖርተኞች ተሳትፎን አንድ እርምጃ ያራመደ በሚል እንዲመዘገብ አድርጓል።
ከተሳትፎ ባለፈ ሴት ስፖርተኞች ብቃታቸውን በማስመስከር ሀገራቸውን ማስጠራትና ለመሰሎቻቸውም ተነሳሽነትን በመፍጠር ስኬታማ ሆነዋል። እአአ በ2016ቱ የሪዮ ኦሊምፒክ ከተዘጋጁ ሜዳሊያዎች መካከል 44 ከመቶ የሚሆነው በሴት አትሌቶች የተወሰደ ሲሆን፤ ይኸውም በታሪክ ከፍተኛው ነው። በግለሰብ ደረጃ አራት ሜዳሊያዎችን በአንድ ኦሊምፒክ በመውሰድ ባለ ክብረወሰን የሆነው ወንድ አትሌት ታሪኩን ካጻፈ 12 ዓመታት በኋላ ጀርመናዊቷ ፋኒ ብላንከርስ-ኮን ስኬቱን መጋራት ችላለች። ሩሲያዊቷ ማሪያ ጎርኮቪስኪያ ደግሞ በአንድ ኦሊምፒክ 2 የወርቅ እና 5 የብር በጥቅሉ 7 ሜዳሊያዎችን ለብቻዋ በመሰብሰብ ተጠቃሽ ናት። በዚህ ወቅት መሰል ስኬትን የግላቸው ያደረጉ በርካታ እንስት ስፖርተኞች ስለመኖራቸው ልብ ይሏል። ሊታሰቡ የማይችሉ አስደናቂ ተሳትፎ ካደረጉት መካከል እንግሊዛዊቷ የፈረስ ግልቢያ ተወዳዳሪ ሎርና ጆንስቶን ቀዳሚዋ ስትሆን የ 1972ቱ ኦሊምፒክ ላይ ስትሳተፍ እድሜዋ 70 ዓመት ከ5 ቀን ነበር።
ሴት ‹‹አትችልም›› በሚል የምትገለጽበት ጉዳይ በተለይ ከጉልበት ጋር የተያያዘ መሆኑ እሙን ነው። ይሁንና አቅምንና ብልሃትን በሚጠይቀው ስፖርት በሁለቱም ጾታ ተመሳሳይ ደረጃ በሁለቱም ጾታዎች በመከወን እኩል መሆናቸውን የሚያረጋግጥ ዘርፍ ነው። ይህም በርካታ ሴቶችን በኢኮኖሚ፣ በመሪነት፣ በብቃት ኃላፊነትን በመውሰድ፣ … እያሳየ ይገኛል። ለርካታ ሀገራትም የኦሊምፒክን ሜዳሊያ ባጠለቁ ሴቶች ተጨማሪ ክብር ሊያገኙ ችለዋል። በዚህ ረገድ ማሳያ ከሆኑት ሀገራት መካከልም ኢትዮጵያ ተጠቃሽ ናት። እንደ ሌላው ዓለም ሁሉ የሴቶች ተሳትፎ የዘገየ ቢሆንም ባስቆጠሯቸው ሜዳሊያዎች ግን ከወንዶቹ የላቁ መሆናቸውን መረዳት ይቻላል።
ይህንን ሁኔታ የተረዳውና ሴቶችን ማበረታታት የዘወትር ተግባሩ የሆነው ዓለም አቀፉ የኦሊምፒክ ኮሚቴም የሴቶች ስፖርት ላይ እንደ ዩኔስኮ እና የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ሁሉ እየተንቀሳቀሰ ይገኛል።
ኦሊምፒክ ኮሚቴ የስራ አስፈጻሚ ቦርድ ለጉዳዩ በሰጠው አትኩሮት በማማከር ከሚሰሩ ኮሚሽኖች መካከል የጾታ እኩልነትን በሚመለከት የተቋቋመ ኮሚቴ አለው። በየአራት ዓመቱም አዳዲስ የኮሚቴ አባላትን በመምረጥም ቀጣጥነት ያለውን ስራ ይሰራል።
ብርሃን ፈይሳ
አዲስ ዘመን የካቲት 29 ቀን 2015 ዓ.ም