ዓለም አቀፍ ይዘት ኖሮት እኤአ ከ1975 ጀምሮ በተለያዩ መሪ ሐሳቦች እየተከበረ የመጣው የሴቶች ቀን ዘንድሮም ‹‹እኔ የእህቴ ጠባቂ ነኝ›› በሚል መሪ ሐሳብ በዓለም አቀፍ ደረጃ ለ112ኛ ጊዜ፤ በኢትዮጵያ ደግሞ ለ47ኛ ጊዜ በዛሬው ዕለት ታስቦ ይውላል፡፡
ቀኑ በዚህ መልኩ ታስቦ በሚውልባት ኢትዮጵያ ደግሞ ከጠቅላላው የሕዝብ ብዛት ከግማሽ በላይ ቁጥር የያዙት ሴቶች ናቸው። ይህ ደግሞ የቁጥራችውን ያህል ቀርቶ ሲሶውን ያህል ለመስራት የሚያስችል ዕድል ቢፈጠርላቸው ለሀገር ልማትም ሆነ እድገት ላቅ ያለ አስተዋጽኦ ማበርከት እንደሚችሉ አመላካች ነው። በኢትዮጵያ የታሪክ ሁነቶችና ጉዞ ውስጥ ሴቶች የነበራቸውን ከፍ ያለ ሚና በዓድዋው የጦር ሜዳ ተጋድሎና ድል ጭምር አስመስክረዋል፡፡
ይህ እውነት እንደተጠበቀ ሆኖ ግን ለሴቶች ዕድል በማቻቸቱ ረገድ፤ ባለፉት ዘመናት በተለይም ከለውጡ በፊት ሴቶች እድሉ እንደተሰጣቸው ተደርጎ ብዙ ሲባል ቢቆይም፤ በስማቸው ከመነገድ ያለፈ ስፍራ ሲሰጥ አልታየም። ለዚህ ማሳያ የሚሆነው በየደረጃ ያለው የአመራር ተሳትፏቸው ከብዛታቸው አንጻር ሲሰላ ከወንዶች ጋር ያለው ጥግግት ሚዛን የሚደፋ ባለመሆኑ ነው።
ይሁንና ከለውጡ ማግስት የኢፌዴሪ መንግስት ሴቶችን በአቅምና ችሎታቸው እየለዩ ወደ አመራርነት መንበር በማምጣቱ ረገድ የሚያስመሰግነውን ተግባር መፈጸም ችሏል። በተለይም በመንግስት ካቢኔ እና በሌሎች ተመሳሳይ የኃላፊነት ቦታዎች ላይ የሴት አመራሩ ቁጥር ከወንድ ጋር ሲነጻጸር መሳ ለመሳ እንዲሄድ ማድረጉም የአደባባይ ምስጢር ነው፡፡
መሪነት ማለት ደግሞ የስልጣን ቦታ የመያዝ ጉዳይ ሳይሆን መምራት የመቻል ጥበብ እንደመሆኑ ስፍራ የተሰጣቸው ሴቶች በአደባባይ ጥንካሬያቸውንም ማሳየት ችለዋል። የኢፌዴሪ መንግስትም በሴቶች ችሎታ በመተማመን ወደ አመራር እርከን እንዲመጡ ያደረገበት ሂደት ለሌሎች አገራት ጭምር አርአያ እንደመሆኑ ከፍ ያለ ዓለም አቀፍ ሙገሳን ተችሯል።
በላይኛው የአመራርነት እርከን ላይ የታየው በጎ ተግባር ግን በየደረጃው እስከ ወረዳ ባሉት የአመራርነት ቦታዎች በመተግበር በኩል ሰፊ ክፍተት አለ። በመሆኑም መንግስት ሴቶችን በከፍተኛ የአመራር እርከን ለማምጣት የሄደበትን ያህል፤ ከፍተኛ ቁጥርና የኃላፊነት ሚና ባለው ብቻ ሳይሆን፤ የመንግስት የአስተዳደር ጉድለት በሚጎላባቸው የታችኛው እርከን ሴቶችን በየደረጃው ወደ ኃላፊነት ማምጣት ቢችል ሴቶች በውስጣቸው ያለውን የመምራት ጥበብ በመጠቀም በርካታ ውጤት ማስመዝገብና ትርፋማ መሆን ይቻላል፡፡
በመሆኑም በየደረጃው ባሉ የተለያዩ ተቋማት ውስጥ ሴቶች ስፍራ ተሰጥቷቸው ችሎታቸው የሚመዘንበት ሁኔታ እምብዛም ባለመሆኑ ትኩረት ተሰጥቶበት ሊሰራ፤ ከተከለሉበት አሊያም ከተደበቁበት ወጥተው ብቃታቸውን ለማሳየት የሚያስችላቸው ድጋፍ ሊደረግላቸውም ይገባል፡፡
ሴቶች የመምራት ብቻ ሳይሆን በአመራር ጥበባቸው ፈተናዎች ሲያጋጥማቸው በጥበብ የማለፍ ትልቅ ተሰጥኦ አላቸው። ምቹ በሆነ ሁኔታ ውስጥም ሆነ ባልተመቻቸ ቦታ ስራቸውን በብቃት መውጣት የሚችሉ ሴቶች መኖራቸውም ከግምት ውስጥ ገብቶ ተገቢው ስፍራ እስካልተሰጣቸው ድረስ ሀገርን ወደተፈለገው ከፍታ ማሻገር ከባድ መሆኑ ልብ ሊባል ይገባል፡፡
ሀገራችን ከድህነትና ኋላቀርነት ተላቅቃ በኢኮኖሚ ጠንካራ ከሆኑት ተርታ ለማሰለፍ የሚደረገው ሩጫ ያለ ሴቶች ተሳትፎ እንደ ‹‹ባለህበት እርገጥ›› የሚቆጠር ነውና በየደረጃው ላለው የአመራር ቦታ ሴቶችን ወደፊት ማምጣት ተገቢነቱ አጠያያቂ አይሆንም። ሴቶች በማኅበራዊው፣ ኢኮኖሚያዊውም ሆነ የሀገርን ሕልውና በማስጠበቅ ረገድ የተወጡት ከፍ ያለ ሚናም የዚህ ዐቢይ ማሳያ ነው፡፡
ከዚህ አኳያ የሀገራችንን ልማት ለማሳለጥ የሴቶች ተሳትፎ ወሳኝ ነው በሚል መፈክር ብቻ የሴቶችን ተሳትፎ ማሳደግ ብሎም የሀገራችንንም ልማት ማሳለጥ አይቻልም። ለተሳትፎ ሲባልም ‹‹ሴቶች እዚህ እና እዚያኛው ስልጣን ላይ ቢቀመጡ የተሻለ ውጤት ያስመዘግባሉ›› በሚል አስተሳሰብ ብቻም ስኬታማ ስራ መስራት አይቻልም። ሀገራችን በተያያዘችው የብልጽግና ማማ ላይ የመውጣት እቅድ ስኬታማ መሆን የሚችለው ሴቶችም ከወዲሁ መርከቡን ተሳፍረው የበኩላቸውን ማበርከት ሲችሉ ብቻ እንደሆነ ሊታወቅ ይገባል።
በማኅበረሰባችን ውስጥ አሁንም ድረስ ሴቶችን ዝቅ አድርጎ የማየት፣ የማሸማቀቅና የማናናቅ እኩይ ሁነቶች መኖራቸው እሙን ነው። ዛሬም ቢሆን በተማረችም ሆነ ባልተማረች እንዲሁም በአመራር ደረጃ ባለችም ሆነ ተራ ሰራተኛ በሆነች ሴት ላይ በተለያየ መንገድና ዓይነት ጉዳት ሲደርስባቸው መታየቱ አልቀረም።
ምክንያቱም ሴቶችን ማደናቀፍ የሀገር ልማትን እንደማደናቀፍ ብሎም ሰላምን እንደማደፍረስ ይቆጠራል። በመሆኑም በሀገር አቀፍ ደረጃ በየቦታውና በየደረጃው ላሉ ሴቶች ተገቢውን ስፍራ በመስጠት ክህሎታቸውን በአደባባይ አውጥተው እንዲያሳዩ የተጀመረው ማበረታታት ሊጠናከርና የታታሪነት እና የፀረ ሙስና ትግል ምሳሌ የሆኑትን ሴቶችን ወደ አመራርነት የማምጣቱም ተግባር ሊቀጥል ይገባዋል!
አዲስ ዘመን የካቲት 29 ቀን 2015 ዓ.ም