ግማሽ ክፍለ ዘመን ያስቆጠረው የኢትዮጵያ እና የቻይና ግንኙነት ዘርፈ ብዙ መልክ እንዳለው ይታመናል። ስትራቴጂካዊው የሁለቱ ሀገራት ግንኙነት ዛሬ ላይም ተጠናክሮ በንግድ ግንኙነቱ መሰረቱን በመጣል ላይ ይገኛል። በተለይም ቻይና፣ ልክ ለሌሎቹ የአፍሪካ ሀገር እንደተሰጠው አይነት እድል ኢትዮጵያም ምርቶቿን ከቀረጥ ነጻ ወደ ቻይና እንድታስገባ መፈቀዷ የሁለቱን ሀገራት ወዳጅነት ከፍ እንደሚያደርገውም እየተነገረ ነው።
በተያዘው ወር አጋማሽ በገንዘብ ሚኒስትሩ አቶ አህመድ ሺዴ የተመራ ልዑክ ለይፋዊ የሥራ ጉብኝት ወደ ቻይና ባቀናበት ወቅት ኢትዮጵያ እና ቻይና የኢንቨስትመንትና የኢኮኖሚ ትብብርን ለማሳደግ የሚያስችል ቡድን ለማቋቋም የስምምነት ሰነድ ተፈራርመዋል። ይህን ተከትሎ ቻይና የኢትዮጵያ የወጪ ምርቶች ከቀረጥ ነጻ እንዲገቡ ፍቃድ መስጠቷንና ፈቃዱም ቻይና በቅርቡ ይፋ ባደረገችው ‹‹የአፍሪካ ልዩ ቀረጥ ማሻሻያ›› ማዕቀፍ ስር እንደሚተገበር በኢትዮጵያ የቻይና አምባሳደር ዣኦ ዢዩዋን በትዊተር ገጻቸው ካሰፈሩት መረጃ ማወቅ ተችሏል።
በተመሳሳይ ኢትዮጵያ ከቻይና ጋር ያላት ግንኙነት ስትራቴጂካዊና ወሳኝ መሆኑን ከኢፌዴሪ ገንዘብ ሚኒስቴር የትዊተር ገጽ የተገኘው መረጃ ያሳያል። ቻይና የኢትዮጵያ ወሳኝ የልማት አጋር መሆኗንም መረጃው ያመለክታል።
የኢትዮጵያ ምርት ወደ ቻይና ገበያ ከቀረጥ ነጻ እንዲገባ ቻይና መፍቀዷ እና የሁለቱ ሀገራት የንግድ ግንኙነት በተመለከተ ያነገጋገርናቸው የምጣኔ ሀብት ባለሙያዎች እንደሚሉት፤ ቻይና የኢትዮጵያ ምርት ወደ ሀገሯ ገበያ ከቀረጥ ነጻ እንዲገባ መፍቀዷ ለሁለቱ ሀገሮች ወዳጅነትም ሆነ ለኢትዮጵያ የበለጠ ጥቅም አለው። ይሁንና በቻይና ይሁንታ የተገኘው ነጻ እድል ብቻውን ስኬታማ ስለማያደርግ ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪ ለመሆን ከተገኘው ከቀረጥ ነጻ እድል በስተጀርባ ወደ ቻይና ገበያ የሚላኩ ምርቶች ላይ በጥራትም በብዛትም ከፍተኛ ስራ ሊሰራባቸው ይገባል።
በጉዳዩ ዙሪያ ካነጋገርናቸው የምጣኔ ሀብት ባለሙያ አምባሳደር ጥሩነህ ዜና አንዱ ናቸው። እርሳቸው በቻይና ገበያ ከቀረጥ ነጻ የሆነ እድል ማግኘት በአግባቡ መጠቀም ከተቻለ ትርጉሙም ሆነ ጥቅሙ ብዙ ነው ይላሉ። አንደኛ የሁለቱን ሀገራት ግንኙነት መልካም መሆኑን የሚያመላክት ሲሆን፣ ሁለተኛው ደግሞ የተሰጠው እድል ትልቅ በመሆኑ የኢትዮጵያን የገበያ መዳረሻ ያሰፋል ብለዋል።
ይሁንና ይላሉ አምባሳደሩ፣ ‹‹ኢትዮጵያ ሁልጊዜም ቢሆን ገበያ የሚችግራት አገር አይደለችም። እንዲያም ሆኖ ግን ከቀረጥ ነጻ የሆነ የገበያ እድል ማግኘት በጣም አስፈላጊም ወሳኝም ነው። ምክንያቱም በዓለም ላይ ውድድር ስላለ ዋጋው ዝቅ ማለቱ ለገበያ መሳብ አንዱ እድል ነው ይላሉ።
በተመሳሳይ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የኢኮኖሚክስ ትምህርት ክፍል የሶስተኛ ዲግሪ ተማሪ የምጣኔ ሀብት ባለሙያው አቶ ሞገስ ቱፋ በበኩላቸው፤ ነጻ እድል ማግኘቱ አንድ በጎ ነገር ነው። ይሁንና የተሰጠውን እድል በአግባቡ ለመጠቀም ሁለንተናዊ ዝግጁነት ያስፈልጋል። ይኸውም በነጻ እድል የተሰጠው የምርት አይነት ወደ ቻይና ገበያ ሲላክ ጥራቱን የጠበቀ አድርጎ መስራት የግድ ይላል ሲሉ ይናገራሉ።
የመጀመሪያው ነገር የተጠቃሚዎችን ፍላጎት ማለትም የእድል ሰጪ ሀገርን ፍላጎት በማሟላት የእድሉ ተጠቃሚ መሆን የግድ ነው። ስለሆነም ከጥራት ጋር ተያይዘው ያሉ ነገሮች በትኩረት ሊሰራባቸው ያስፈልጋል። ምርቱ ወደተላከበት ሀገር ደርሶ መፈተሹ ስለማይቀር ሲታይና ሲመረመር ጥራቱ የተጠበቀ ምርት እንዲሆን መስራት የግድ እንደሚል ተናግረዋል።
እርሳቸው እንደሚሉት፤ አንድ ምርት ሲመረት ማሟላት የሚገባው የጥራት ደረጃዎች አሉ። ጥራት ማለት የተጠቃሚውን ፍላጎት ማሟላት ነው። በኢትዮጵያ ለምሳሌ ወደምርት ከመግባታችን በፊት መሟላት ይገባቸዋል ተብሎ በሕግ የተቀመጡ የቴክኒክ ጉዳዮች አሉ። የኢትዮጵያ የጥራትና ደረጃዎች ኤጀንሲ የሚያስቀምጣቸው የጥራት ደረጃዎች አሉ። የኢትዮጵያ ደረጃዎች ቁጥጥር ባለስልጣንም የሚሰጣቸው ደረጃዎችም ይኖራሉ። እሱ ደረጃ ከዓለም አቀፉ ደረጃዎች ጋር በመሆን የተሰራ ደረጃ ነው።
ይሁንና ይህ የተባለው ደረጃ ተሟልቶ ቢገኝም ቻይና እንደገና የራሷ መስፈርት ሊኖራት ይችላል። ስለዚህ የኢትዮጵያ ምርት እነዚህን ሁለቱንም ደረጃዎች በማጣመር የሚሰራ ከሆነ እሰየው ነው ሲሉ ያስረዳሉ። ነገር ግን ይህ ሲደረግ ጥራትን ለማስጠበቅ ሲባል ከመጠን በላይ ወጪ በምርቱ ላይ ወጥቶ ካለን የማምረት ልምድ፣ ካለን ማሽነሪ እንዲሁም ካለን የሰው ኃይል ጋር ሲደማመር ዋጋውን ከፍ ሊያደርገው ይችላልና ጥንቃቄ የሚያሻው መሆኑን ያመለክታሉ። ጥራቱን ጠብቆ ዋጋውም ለተወዳዳሪነት በሚያበቃ መልኩ ማምረት ከተቻለ ግን መልካም እድል መሆኑን ያስረዳሉ።
ቻይና የሰጠችው እድል በጣም ትልቅ እድል ነው ያሉት አምባሳደር ጥሩነህ፤ ኢትዮጵያ አሁንም ቢሆን ከአግዋ በስተቀር የገበያ እድል እንዳላት ግን አልሸሸጉም። ኢትዮጵያ ከጦር መሳሪያ በስተቀር ሌላውን ምርት በነጻ ታስገባለች የሚል ስምምነት ላይ የተደረሰበት የአውሮፓ የገበያ እድል (Everything but Arms) (EBA) አለ በማለት ማሳያ አስቀምጠዋል።
ይህ የሚያሳየው ኢትዮጵያ የጦር መሳሪያ አምርታ የምትሸጥበት ጊዜ ላይ ስላልሆነች ከጦር መሳሪያ ውጪ ሁሉንም ምርት ወደእዛ ማስገባት ትችላለች ማለት ነው ይላሉ። እንዲህም ሲባል ችግር የለም ማለት አይደለም። ምክንያቱም ኢትዮጵያ የምትልካቸው ምርቶች ሁሉ የራሳቸውን መስፈርት ካላሟሉ መከልከላቸው አይቀርም ባይ ናቸው። ለምሳሌ ጥራታቸውን ካለመጠበቅ የተነሳ በቀላሉ የአውሮፓንም ሆነ የቻይናን ገበያ መቆጣጠር አይችሉም። ለምሳሌ የሚላኩ ምርቶች ምግብ ነክ ከሆኑ በጤና ላይ የሚያደርሱት እክል ሊኖር ይችላል። ስለዚህ ጥራታቸውን የጠበቁና ደረጃቸውን ያሟሉ መሆን ይጠበቅባቸዋል። ለምሳሌ አንዱን ምርት ብቻ ወስደን ለማየት ብንሞክር ስጋ ብንልክ በጣም ከፍተኛ ጥቅም እናገኛለን። በዚህ ዘርፍ እነ ኬንያ አብዝተው ይጠቀማሉ ሲሉ ሁኔታውን ያመለክታሉ።
የምጣኔ ሀብት ባለሙያው አምባሳደር እንደሚሉት፤ በኢትዮጵያ በኩል ስጋ ለመላክ የሚያስችል አቅም ቢኖረንም ከጥራት ጉድለት የተነሳ ማግኘት የሚገባንን ጥቅም ማግኘት አልቻልንም። በተለይም ያሉንን ከብቶች በሽታ ስለሚያጠቃቸው በሽታ በመከላከል ላይ አልሠራንም። የኢትዮጵያ መንግስት ከብት እርባታ ላይ ለመስራት ተነሳሽነቱ እንዳለውና በትኩረት እንደሚሰራም ይናገራል። ነገር ግን በሽታን ከማጥፋት ጋር የተሰራው ነገር በቂ አይደለም።
ለዚህም ዋና ምክንያት ከተባለ አንድ አርሶ አደር በዓመት ከበሽታ የተነሳ አራት ያህል ከብት እንዲሚሞትበት ሲናገር መደመጡ ነው። እንዲህ አይነቱ በሽታ እና ችግር እስካለ ድረስ ስጋ ወደ አውሮፓ ገበያ መላክ አንችልም። ይህ ችግር እስካልተፈታ ድረስ ደግሞ ወደቻይናም ለመላክ ያስቸግራል ሲሉ አምባሳደሩ ያስረዳሉ።
ስለዚህ ይላሉ አምባሳደሩ፣ ከቀረጥ ነጻ እድል ቢገኝም ከሌሎች ችግሮች ማለትም ጤና እና ጤና ነክ የሆኑ ችግሮችን ከሚፈጥሩ ነገሮች መጠበቅና ችግሩን ማሻሻል የግድ ይላል። ምክንያቱም ከጥራት ጉድለት ጋር ተያይዞ የሚመጣው እንከን ሸቀጣችንን ማገዱ አይቀርም። በዚህ ችግር ምክንያት ከምንጠቀመው እድል እንዳንስተጓጎል በትኩረት መስራትን ይጠይቃል። የአውሮፓን እድል የነሳሁበት ምክንያት ቀደም ሲል የተሰጠውን እድል አሟጥጠን መጠቀም ያልቻልንበት ምክንያት ጥራት መሆኑን ለማሳየት ይረዳኝ ዘንድ ነው ብለዋል።
የምጣኔ ሀብት ባለሙያው አቶ አቶ ሞገስ ደግሞ በሌላ በኩል፤ መታየት ያለበት ጉዳይ አለ ይላሉ። እርሳቸው አንድ ምርት ሲመረት የወጣበትን ወጪ አስልቶ ወደቻይና ማጓጓዝ ምን ያህል ትርፋማ ነው የሚለው መለካት አለበት ባይ ናቸው። የውጪ ገበያ እድል ብቻ ስለተገኘና የውጭ ምንዛሬ ስለሚፈለግ ብቻ በብዙ ድጎማዎች አዋጭ ሳይሆኑ እንዲሁ የሚገባበት ጊዜ ነበር። ለምሳሌ ወደ ኤክስፖርቱ ዘርፍ የሚገቡ ድርጅቶች ወይም አምራቾች ከኢትዮጵያ መንግስት ብዙ ጥቅማጥቅሞችን ያገኛሉ። እሱ ሲደመርበትና እዛ የተላከበት ሀገር የሚሸጥበት ዋጋ ሲነጻጸር ሽያጩ ኪሳራ ነው ማለት ያስደፍራል ሲሉ እውነታውን ያሳያሉ።
አቶ ሞገስ፣ ለዚህ አባባላቸው በምክንያትነት የጠቀሱት፤ እዚህ የሚደረግላቸው ጥቅማጥቅሞች ለምሳሌ ጥሬ እቃ ሲያስገቡ ግብር አለመክፈል ይሆናል፤ ይህንና መሰል ጥቅማጥቅሞችን ያገኛሉ። ይህ ሁሉ ወጪ ተደማምሮ ምርቱ ዋጋ የሚያወጣ ከሆነ አዋጭ ነው ማለት ይቻላል ብለዋል።
ሌላው በቻይና ያሉ ድርጅቶች በሀገራቸውም ሆነ ከሀገራቸው ውጪ በጣም ተወዳዳሪ ናቸው። ወደ እኛዎቹ ሲመጣ የዚያን ያህል በሀገር ውስጥ ውድድር የለም። ውጪ ሲሄዱ ደግሞ የሚገጥማቸው ውድድር በጣም ከፍተኛ ነው። ቻይና ደግሞ እድሉን የምትሰጠው ለኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን ለአፍሪካ ሀገሮችም ጭምር ነው። ስለዚህ ውድድሩ በእኛና በእነዛ የአፍሪካ ሀገራት መካከል ይሆናል። ስለዚህ የእነርሱንም ውድድር በአግባቡ ለመወጣት መስራትና መከታተል ያስፈልጋል። በተለይም የተሻለ ልምድ የሚኖራቸውም ከሆነ ከእነርሱ መውሰድ መልካም መሆኑን አስገንዝበዋል።
እንደ እርሳቸው ገለጻ፤ ኢትዮጵያ በአሁኑ ሰዓት የተፈቀደላትን ምርት በጥራት የማቅረብ ቁመና ላይ ናት ማለት አያስደፍርም። ምክንያቱም መሟላት የሚገባቸው በርካታ ነገሮች አሉ። በጥቂቱ ለመጥቀስ ያህል ምርትን በአግባቡ ለማምረት የመብራት መቆራረጥ መኖር የለበትም። ይህ ችግር ደግሞ አሁንም ያልተፈታ ነው። ውሃም እንዲሁ ነው። ስለዚህ ከእነዚህ ሁሉ ችግሮች ወጥተን በአንድ ግብ ለአንድ ዓላማ መስራት ያስፈልጋል። ቁመናችን በዚህ ልክ ሆኖ ቢሆን ኖሮ ኤክስፖርታችን ከጊዜ ወደጊዜ እየወረደ አይመጣም ነበር። እስካሁንም እያገኘን ያለነው ከብዛት እንጂ ከጥራት አይደለም።
ቻይና ምርቶቿን በሀገራችን በዝቅተኛ ዋጋ ታቀርባለች፤ ለምሳሌ ብረታብረትን መውሰድ ይቻላል። ስለዚህ እኛ በምናመርተው ምርት እዚሁ ሀገራችን ውስጥ እንኳ መወዳደር አንችልም። ቻይናም ይዛ የምትመጣው ምርት ይኖራልና ለእዛም መዘጋጀት ያስፈልጋል ሲሉ አስገንዝበዋል። ከአሁን በፊት ሚዛኑ የሚደፋው ወደ እነርሱ ነው። ከአፍሪካ ጋር ለሚደረገውም የንግድ ልውውጥ ዝግጅት ያስፈልጋል ባይ ናቸው። በቅርቡ በመዲናችን የተካሄደው የአፍሪካ መሪዎች ጉባኤ ላይ የአፍሪካ ሕብረት ውሳኔ አንዱ ይህ ነውና ብለዋል።
ቻይና ቀደም ሲል ኢትዮጵያ 1 ሺ 644 ምርቶች ከቀረጥ እና ኮታ ነጻ ማስገባት እንደምትችል ፈቃዱን ያሳወቀችው ታኅሣሥ 3 ቀን 2015 ዓ.ም. መሆኑ የሚታወስ ነው። የአሁኑ የተሰጠው እድል ደግሞ ተጨማሪ የተሰጠ ነው።
አሜሪካ የአፍሪካ ሀገራት ከቀረጥ ነጻ ወደግዛቷ እንዲያስገቡ ከፈቀደችው የአጎዋ እድል ኢትዮጵያን በጥቅምት ወር 2014 ዓ.ም ላይ በፕሬዚዳንቷ አማካይነት መሰረዟ የሚታወስ ሲሆን፣ በወቅቱም የኢፌዴሪ የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር በአሜሪካ መንግስት ውሳኔ የተደረሰው ክልከላ እንዳሳዘነው በወቅቱ ማሳወቁ ይታወሳል።
አቶ ሞገስ፣ የቁጥጥር ባላስልጣኑ ወደውጭ በሚሄዱ ምርቶች ላይ በቅርበት ክትትል ማድረጉን ከሌላው ጊዜ በተሻለ መልኩ ትኩረት ሊሰጥበት ይገባል ይላሉ። በሁለትና በሶስት አምራቾች ብቻ የወጪ ገበያውን እድል መጠቀም ውጤት አያመጣምና በዚህ ዙሪያ መንግስት በትኩረት ተከታትሎ የተፈለገውን ውጤት ለማምጣት መስራት ይጠበቅበታል ብለዋል።
አምባሳደር ጥሩነህ፣ ጥራትን ለማምጣት መስራት እንችላለን ይህ የማይቻል ነገር አይደለም፤ ይህ ፊዝክስ አይደለም፤ ይሁንና አልሠራንም። ትኩረት አድርገን ብንሠራና የእንስሳት በሽታን ለማስወገድ ብንችል ከእንስሳት ሀብታችንም ልናገኝ የምንችለው ጥቅም በጣም ከፍተኛ ነው። እንስሳትን በተመለከተ በሽታው ላይ ከመስራት በዘለለ ደግሞ በዝርያ ማሻሻልና አያያዝ ላይም እንዲሁ መሰራት ይኖርበታል። መንግስት እያደረገ ያለው እንቅስቃሴ በአሁኑ ወቅት ከበፊቱ ይልቅ የተሻለ ነው ብለዋል።
በተጨማሪም አርሶ አደሩ ምርቱን እንዲያሻሻል ከወትሮ በተሻለ መንቀሳቀስ የግድ እንደሚል ጠቅሰው፤ 60 በመቶ ያህሉ መሬት በደንብ አልታረሰምና ያለውን መሬትም ለመጠቀም መታተር ብሎም ለአርሶ አደሩ ቴክኖሎጂውን ማቅረብ እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል። አርሶ አደሩ ያመረተውንም ምርት ሳይበላሽ የሚያቆይበትን መሳሪያ ማበጀት አስፈላጊነቱን አስረድተዋል።
አስቴር ኤልያስ
አዲስ ዘመን የካቲት 28 ቀን 2015 ዓ.ም