በአገሪቱ ሀሳቦች ሀሳብ ከመሆን አልፈው ተገቢውን ድጋፍ አግኝተው እንዲያድጉና እንዲበለጽጉ በማድረግ ረገድ በርካታ ተግባሮች እየተከናወኑ ይገኛሉ። ይህን ተከትሎም ዲጅታል ቴክኖሎጂን ጥቅም ላይ በማዋል የህብረተሰቡን የዕለት ተዕለት ኑሮ ቀላል የሚያደርጉ አገር በቀል የፈጠራ ውጤቶች ብቅ ብቅ እያሉ ይገኛሉ።
ሀሳብ ያላቸው ዜጎች ሀሳብ እንዲያድግ በመደገፍ ሀሳባቸውን ወደ ቢዝነስ የሚለውጡባቸው ሁኔታዎች እየተመቻቹ መሆናቸውን ተከትሎ ያላቸውን እውቀት ተጠቅመው ዲጂታል ኢኮኖሚን ለመገንባት የሚደረገውን ሂደት ለመደገፍ ጥረት እያደረጉ ያሉ ስታርታፖች በየቢዝነስ ዘርፎቹ ተሰማርተው ይታያሉ።
በመንግሥት በኩል የስታርታፕ ምህዳር እንዲሰፋ በማድረግ ረገድ በርካታ ሥራዎች እየተሰሩ ናቸው። በዚህም የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴርና የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር ከተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የልማት ድርጅት ጋር በመተባበር የስታርታፕ ኢኮሲስተም ተዋንያን የምክክር መድረክና የዲጅታል ስታርታፕ ኢግዚቢሽን የካቲት 13 እና 14 በሳይንስና አርት ሙዚየም አዘጋጅተው ነበር። በኢግዚ,ቢሽኑ የተሳተፉ ስታርታፓች እንዳሉት፤ በስታርታፓች እየተፈጠሩ ያሉ ስራዎች ለማህበረሰቡ መረጃ በማድረስ፣ ሊደርስበት የሚችለውን እንግልት በመቀነስ አስተዋጽኦ እያበረከቱ ናቸው። ስራ ከመፍጠራቸው በተጨማሪ ለሌሎች ዜጎችም የስራ እድል እየፈጠሩ ይገኛሉ።
ዩቶጵያ ኢ-ፋርማሲ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር በኢግዚቢሽኑ ተሳትል፤ የድርጅቱ የጥሪ ማዕከል ሠራተኛ ወጣት ቢቂላ ወንድሙ እንደገለጸው፤ አግዚቢሽኑ በአይነቱ ልዩ የሆነ የመድኃኒት ግብይትን ቀላል የሚያደርግ በኢትዮጵያውያንና በአሜሪካውያን የበለጸገ መተግበሪያና ጽረገጽ ይዘው ቀርበዋል። ይህ ዲጅታል ፕላትፎርም አርቲፊሻል ኢንተለጀስን ጨምሮ ዘመኑ የደረሰበትን ቴክኖሎጂ በመጠቀም የዲጅታል መድኃኒት መፈለጊያ፣ ማዘዣ እና የፋርማሲ መረጃ አገልግሎት የሚሰጥ ሞባይል መተግበሪያም አለው።
በዚህ ‹‹ሃሎ መድኃኒት›› የተሰኘ መተግበሪያ አንድ ሰው መድኃኒት ሲፈልግ በስልክ ቁጥር 9640 በመደወል ወይም መተግበሪያውን ከጉግል ወይም ከአፕስቶር በማውረድ የሐኪም ማዘዣውን እስካን አድርጎ ወደኛ ሲልክ እኛ በአቅራቢያው መድኃኒቱ የሚገኝበትን ፋርማሲ አፈላልገን በደቂቃ ውስጥ እንዲያገኝ እናደርጋለን ሲል ወጣት ቢቂላ ይናገራል። ስለመድኃኒቶቹ የጎንዮሽ ጉዳትና ተያያዥ ጥያቄዎች የሚያነሳም ከሆነ አስተማማኝ መረጃ ማግኘት የሚችልበት ሁኔታ መፈጠሩን ይገልጻል። ቤቱ ሆኖ የመድኃኒት አቅርቦት የሚፈልግ ሰው ካለ ደግሞ ያለበት ድረስ የሚፈልገውን መጽኃኒት እናቀርባለን ይላል።
ከዚህ በተጨማሪ ከፋርማሲ ፋርማሲ የመድኃኒት የዋጋ ልዩነት ስላለ መድኃኒቱ ያለባቸውን ፋርማሲዎች የመድኃኒት ዋጋ በመጥቀስ ሰዎች በተሻለው ዋጋ መድኃኒት እንዲያገኙ የሚያደርግ መተግበሪያ መሆኑንም ያብራራል።
ወጣት ቢቂላ እንደሚለው፤ ዲጅታል መተግበሪያውን ተግባራዊ ለማድረግ ፋርማሲዎችን ወደዚህ ሲስተም ለማስገባት ብዙ ጥረቶች ተደርገዋል። አሁን በአዲስ አበባ በየክፍለ ከተማው አሥር የሚጠጉ አባል ፋርማሲዎች አሉ። ቁጥራቸው እየጨመረ ይሄዳል። ህብረተሰቡ ግንዛቤ ስለሌለው እንጂ አገልግሎቱን ይፈልገዋል።
ለዚህም ማሳያው በተለይ መድኃኒት ፍለጋ ደክመው ያጡ ሰዎች እኛ ዘንድ ደውለው ይህንን አይነት መድኃኒት ብዙ ቀን ፈልገን አጣን፤ እናንተ ታገኙት ከሆነ እባካችሁን አፋልጉን ሲሉ ይጠይቃሉ ያለው ወጣት ቢቂላ፣ ‹‹እኛ በ10 እና በ15 ደቂቃ ፈልገን ስናገኝላቸው እንዲህም አለ እንዴ! በማለት በመገረም ጭምር እንደሚናገሩ ጠቅሶ፣ ተጠናክሮ አንዲቀጥል እየጠየቁ መሆናቸውን እንደሚገልጹም ይናገራል። ህብረተሰቡ የመተግበሪያውን ጥቅም ባወቀ መጠን የአገልግሎቱ ፈላጊ እንደሚሆን ይገልጻል።
ድርጅቱ ለስድስት ሠራተኞች የሥራ እድል የፈጠረ ሲሆን፤ ዲጅታል ቴክኖሎጂን በመጠቀም የአገራችንን የጤና አገልግሎት አሰጣጥ ተደራሽነትና ጥራት ለማዘመን ይሰራል። ወደፊት ተለምዷዊ አካሄዶችን ወደ ዲጅታል በመቀየር ቀላል በሆነ መልኩ ሕይወት መምራት እንዲቻል እንሰራለን የሚለው ወጣት በቂላ፤ ይህንንም ወደ ክልሎች ድረስ በማስፋት ሰዎች መድኃኒት እያለ በመድኃኒት እጦት የሚደርሰባቸው እንግልት መቀነስ እንደሚያስፈልግ ያመለክታል።
ሰዎች ስለመድኃኒት ማንኛውንም የተሟላ መረጃ ማወቅ ከፈለጉ ሃሎ መድኃኒት ማለት ይችላሉ የሚለው ወጣት ቢቂላ፤ ሁልጊዜም ከጠዋቱ ሁለት ተኩል ጀምሮ እስከ ምሽቱ አንድ ተኩል በቀጥታ /ኦንላይን/ አገልግሎት ማግኘት ይችላሉ ብሏል።
ሌላኛዋ የፍሪላንስ ሥራ ድርጅት መስራችና ጀነራል ማናጀር ቤዛዊት አድማሱ በበኩሏ በትርፍ ጊዜ የሚሰሩ ሥራዎችን የሚያመቻት ኦንላይን ፕላትፎርም ያለው ‹‹ፍሪላንስ ሥራ ዶት ኮም›› የተሰኘ ጽረገጽ ይዛ በኤግዚቢሽኑ ቀርባለች። ‹‹ፍሪላንስ ሥራ›› የተሰኘው ዲጅታል መተግበሪያ ባለሙያዎች (ፕሮፌሽናሎች) እና የፍሪላንስ ሥራን ያገናኛል። ይህን ሥራ የጀመርነው ያቀረብነው ሀሳብ ተቀባይነት አግኝቶ ድጋፍ ከተደረገልን በኋላ ወደ ቢዝነስ እንዲዳብር ተደርጎ ነው የምትለው ቤዛዊት፤ እንደ ስታርታፕ የጀመሩት መሆኑንና ዓመት እንዳልሞላውም ትናገራለች። ዛሬም በዚህ ኤግዚቪሽን የተሳተፉት የተባበሩት መንግሥታት የልማት ድርጅት (UNDP) የገንዘብ ድጋፍና በሥራ ፈጠራና ክህሎት ሚኒስቴር በተደረገላቸው ድጋፍ መሆኑን ትገልጻለች።
ቤዛዊት እንደምትለው፤ ጽረገጹ ተሰርቶ ሥራ ከጀመረ አንስቶ ወደ አንድ ሺ የትርፍ ጊዜ ሥራ ፈላጊዎችን (ፊሪላንሰሮች) አሉት። ድርጅቱ በጽረገጹ በተለያየ የትምህርት መስክ ተምረው ልምድ ያላቸው ባለሙያዎችን ግለታሪክ አደራጅቶ አስቀምጧል።
አሳሪዎች የአጭር ጊዜ ሥራ ማሰራት ሲፈልጉ ጽረ ገጽ ላይ ይገቡና የሚፈልጉትን ሲመርጡ እኛ ሁኔታዎችን እናመቻቻለን። በሁለቱ መካከል ያለውን ስምምነትም እንከታተላለን የምትለው ቤዛዊት፣ ሥራው ተሰርቶ እስከሚያልቅ ድረስ የድጋፍና የክትትል ስራ እንደሚሰሩ ታብረራራለች። የትርፍ ሰዓት ሥራ ተጠቃሚውም ሆነ አሰሪው ደስተኛ ሆነው ክፍያቸውን ፈፅመው እንዲሄዱ እንደሚያደርግ ጠቅሳ፣ ሥራዎች ቀላል እንዲሆኑ ለማድረግ የሚያስችል መተግበሪያ መሆኑን ትጠቁማለች።
እንደ እሷ ገለጻ፤ መተግበሪያው ለባለሙያዎች እዚያ ቦታ የግድ ተቀጥረው መሥራት ሳይጠበቅባቸው በትርፍ ጊዜያቸው፣ በእረፍት እና በበዓል ቀናት በአንድ ከተማም ባይሆኑ በርቀት በክልሎች ሆነ ከአገር ውጪ በሙያቸው እየሰሩ ገቢ የሚያገኙበትን ሁኔታ የሚያመቻች ነው።
እስካሁን ጀማሪ እንደመሆናችን መጠን ያሰራናቸው ጥቂት ሰዎችን ቢሆንም፣ ሁሉም ግን ደስተኞች ናቸው የምትለው ቤዛዊት፤ ለአብነት አንድ እናት ቤቷ ቁጭ ብላ ልጇን እያሳደገች እውቀቷ በጣም የሚፈለግ ድርጅት ደግሞ እኛ ጋ መጣና ሥራ ተሰጣት እሷም ቤቷ ልጇ አጠገብ ሆና በሚመቻት ሰዓት ሥራውን ሠርታ አስረከበች፤ ተከፈላት። ያቺ እናት በጣም ደስተኛ ነበረች ስትል አብራርታ፣ ፍሪላንስ ስራ እንደዚህ አይነት እርካታ የሚፈጥር ሥራ መሆኑን አስታውቃለች። አሰሪውም የሚፈልገውን እውቀት በፈለገበት ጊዜ ማግኘቱ ሌላ እርካታ እንደሚፈጥር ትናገራለች።
በዚህ ሥራ ላይ ብዙ ተግዳሮቶች እንዳሉም ጠቁማለች። በኛ አገር እንደዚህ አይነት ሥራ መሥራት አልተለመደም፤ ሥራዎችን ኮንትራት እንኳን ወስዶ በሰዓቱ ያለማስረከብ ችግሮች መኖራቸውን ትናገራለች። በኮቪድ ወቅት በርቀት መሥራት እንደሚቻል ተለማምደናል የምትለው ቤዛዊት፤ ያ ወቅት ቴክኖሎጂን ተጠቅሞ ሥራዎችን ሠርቶ ማስረከብ እንደሚቻል አሳይቶናል ትላለች።
ቤዛዊት ‹‹ በቴክኖሎጂ ረገድ ብዙ የሚቀሩ ነገሮች ቢኖሩም፣ በተቻለ መጠን ደንበኞች ላለማስከፈት ማድረግ የምንችለውን እናደርጋለን›› ስትል ገልጻለች። ሠርተው ስኬታማ የሆኑትን እንደ ማሳያ ልምዳቸውን እንዲያካፍሉ እንደሚያደርጉም ነው የተናገረችው።
አሁን ላይ በኦንላይን የሚሰሩ ሥራዎች በጣም እየተለመዱ ናቸው። በአገር ውስጥ ብቻ ሳይሆን በዓለም አቀፍ ደረጃም ሥራዎች እየተሰሩ ናቸው። ቴክኖሎጂውን አንዱ እየተጠቀመ አንዱ ደግሞ በጊዜ ባለማስከረብ እየተጎዳ መሆኑን ሲያየው ሰው ራሱ ወደ መስመር እየገባ ይመጣል።
በአገሪቱ አሁን የኢንተርኔት ተደራሽነትም በጥሩ ሁኔታ ላይ ይገኛል። ሳፋሪኮም መምጣቱም ትልቅ እድል ይፈጥራል። እንደ ድሮ ወደ ውጪ መውጣት ሳያስፈልግ በቤቱ በሞባይል ስልኩ ላይ ኢንተርኔት በመጠቀም ብዙ ነገሮችን በቀላሉ ማግኘት ይቻላል። በዚህ ረገድ ወደፊት በመጓዝ የስኬታችንን ልምድ እያካፈልን ከተጓዝን ለውጥ ይመጣል ስትል ታብራራለች።
እስካሁን ከመቶ በላይ ሥራዎችን መፍጠር ችለናል የምትለው ቤዛዊት፤ አንድ ሰው በተደጋጋሚ ሥራዎች የሰራበት ሁኔታ መኖሩን ትናገራለች። አሁን ከፕላትፎርማችን ላይ ሥራ ለመውሰድ ዝግጁ የሆኑ አንድ ሺ የሚጠጉ ሥራ ፈላጊዎች መኖራቸውን ጠቅሳ፤ እንደ ኩባንያ የተመዘገቡ አጋሮችና ደንበኞች ያሏቸው መሆኑን ጠቁማለች። ባለሙያዎች ደግሞ ተቀጥረው ከሚሰሩበት ውጪ ሌላ እውቀት ካላቸው መስራት የሚችሉት ሥራ በመዘርዘር ፖስት ሲያደርጉት ቀጣሪዎች ያዩታል እና ሥራ ያገኛሉ። ሰዎች www.freelansira.com የተሰኘውን ፕላት ፎርማችንን ተጠቅመው እንደቀጣሪም እንደፊሪላንሰርም ሊመዘገቡ ይችላሉ ብላለች።
ሌላኛዋ ‹‹ማረፊያ አለ›› የተሰኘ ፕላትፎርም ይዛ የቀረበችው ጽዮን ፍቃዱ ይህ ዲጅታል ቴክኖሎጂ ሰዎችን ከእንግልትና ከአላስፈላጊ ወጪ እንደሚታደግ ትናገራለች። እንደ ‹‹ማረፊያ አለ›› ለህብረተሰቡ ከፍተኛ ጠቀሜታን የሚሰጥ ሕይወትን ቀላል የሚያደርግ ነው። ጽዮን ገለጻ፤ በዚህ የቴክኖሎጂ ዘመን ማንኛውም ሰው ቴክኖሎጂን ተጠቅሞ ታክሲ፣ ምግብ እንዲሁም ሌሎች አስፈላጊ አገልግሎቶች ባለበት ሆኖ ማግኘት ይችላል።
‹‹እኛ ይዘን የመጣነው አገልግሎት ደግሞ መኝታ፣ ማረፊያ ገስት ሀውሶችን፣ ትላልቅ ሆቴሎች፣ ሎጆች እና የመሳሰሉትን ሁሉንም አጠቃሎ የያዘ ስለሆነ ሰዎች የት ማረፍ እንዳለባቸው ሳይጉላሉ ወስነው ከከተማ ሲወጡም ሆነ እዚሁ ከተማ ውስጥ ሆነው ሊሆን ይችላል የት መሄድ እንዳለባቸው አስቦ ለመውጣት የሚያስችል ነው›› ስትል ታብራራለች።
እንደ እሷ ገለጻ፤ ‹‹ማረፊያ አለ›› የተሰኘው ፕላትፎርም አገልግሎት ፈላጊዎች ሆቴሎችን በተለያየ አማራጮች እንዲሁም በቦታቸውና በዋጋቸው መምረጥ የሚችሉበት ነው። ይህ ፕላትፎርም በአዲስ አበባና ከአዲስ አበባ ውጭ ወደ 65 ከተሞች የሚገኙ የሆቴሎችን ዳታ የያዘ መተግበሪና ድረገጽ አለው። በተጨማሪም 9717 የስልክ አገልግሎትም የሚሰጥ ሲሆን፤ ሰዎች የማረፊያ አገልግሎቶችን በመፈለግ የሚደርስባቸውን መጉላላት ይቀንሳል።
እነ ጽዮን ሥራውን ከጀመሩ አንድ ዓመት ሞልቷቸዋል፤ አሁን ተደራሽነታቸውም በከፍተኛ ሁኔታ ሰፍቷል። ሁለት ሺ አምስት መቶ የሚጠጉ ሆቴሎችን መረጃም ይዘዋል። በዚህ አጭር ጊዜ ውስጥ 50ሺ የሚጠጉ ሰዎች መተግበሪያውን አውርደው እየተጠቀሙት ነው። የድረ ገጽ እና የስልክ መስመሩን የሚጠቀሙ ደንበኞችም አሉ።
አሁን ይህንን አገልግሎት እየተጠቀሙ ያሉት የአገር ውስጥ ደንበኞች መሆናቸው የምትናገረው ጽዮን፤ አድማሱን ለማስፋት እየተሰራ እንደሆነ ትገልጻለች። መተግበሪያው ላይ የተለያዩ ማስታወቂያ ቦታዎችን በመሸጥ እንጠቀማለን። ወደፊት የምንፈጥራቸው የክፍያ ሲስተሞች ይኖራሉ የምትለው ጽዮን፣ በዚህ ድርጅት ሥር ለ25 ሰዎች የሥራ እድል መፍጠር ተችሏል ትላለች።
በኤግዚቢሽኑ መክፈቻ ላይ የተገኙት የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ባይሳ በዳዳ እንደተናገሩት፤ የአገር በቀል ቴክኖሎጂ ፈጠራ ውጤቶች ለአገር ኢኮኖሚ እድገት ወሳኝ ሚና አላቸው። ከዚህ አኳያ የአገር በቀል የፈጠራ ሥራዎችን የሚያበረታቱ ልዩ ልዩ የህግ ማዕቀፎችን እየተዘጋጁ መሆናቸውን አመላክተዋል። ምርትና ምርታማነትን የሚጨምሩ እንዲሁም የማህበረሰቡን አኗኗር የሚያቀሉ የፈጠራ ሥራዎች ከመቼውም ጊዜ በበለጠ ትኩረት ተሰጥቷቸዋል።
የስራና ክህሎት ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ንጉሱ ጥላሁን በበኩላቸው፤ አዳዲስ ስራ ፈጣሪዎችን ከማበረታታትና የገበያ ትስስር ከማስፋት አንጻር የዲጂታል ግብይት ወሳኝ ሚና እንዳለው ተናግረዋል። እንደ አገር የህብረተሰቡን ማህበራዊ ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴዎች የሚያግዙ የፈጠራ ሥራዎች እያደጉ መምጣታቸውንም ጠቅሰው፣ እነዚህ የፈጠራ ሥራዎች ወደ ተግባር ተለውጠው ውጤት እንዲያመጡ ሁሉም ባለድርሻ አካላት የበኩላቸውን መወጣት እንዳለባቸው አስገንዝበዋል።
ወርቅነሽ ደምሰው
አዲስ ዘመን የካቲት 28 ቀን 2015 ዓ.ም