ኢትዮጵያ የግብርናውን ዘርፍ ምርትና ምርታማነት በማሳደግ በመልካም ጉዞ ላይ ትገኛለች። እንዲያም ሆኖ ግን
የምግብ ዋስትናን በማረጋገጥ በኩል የምርት አቅርቦትና ፍላጎት ክፍተት ሲስተዋል ቆይቷል። ይህን ክፍተት ለመሙላት
እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ ሌሎች የምግብ ምርቶችን ጨምሮ ስንዴን ከውጭ ታስገባ ነበር።
መንግስት ይህን የአቅርቦትና ፍላጎት ክፍተት ለመሙላት፣ አገሪቱ ከውጭ የምታስገባዋን ስንዴ ለማስቀረት፣
ከዚህም አለፍ ብላ ስንዴ ለጎረቤት አገሮች ለማቅረብ፣ ግብርናው ወደ ኢንዱስትሪ ለሚደረገው ሽግግር ያለውን ፋይዳ
በመመልከት በዘርፉ መጠነ ሰፊ ስራዎችን በመስራት አሁንም ምርትና ምርታማነት ለማሳደግ የሚያደርገውን ርብርብ
አጠናክሮ ቀጥሏል። ይህን ተከትሎም የምርትና ምርታማነት ዕድገት እየተመዘገበ ነው።
በመኸርና በበልግ ከሚካሄደው የእርሻ ስራ በተጨማሪ በበጋ ስንዴ መስኖ ልማት እየተከናወነ ያለው ተግባርና
እየተመዘገበ ያለው ውጤት ለእዚህ በአብነት ይጠቀሳል። አገሪቱ ባለፈው የመኸር ወቅት ብቻ ከ110 ሚሊየን ኩንታል
በላይ ስንዴ ማምረት ችላለች። በተመሳሳይ ዓመት ከበጋ መስኖ ስንዴ ልማት 26 ሚሊየን ኩንታል አምርታለች፤ በ2015
በጀት ዓመት በበጋ መስኖ ስንዴ ልማት 52 ሚሊዮን ኩንታል ለማምረት አቅዳ መስራቱን ተያይዛዋለች።
በበጋ ስንዴ መስኖ ልማት በግብርናው ዘርፍ እየታየ ያለው ለውጥ አገሪቱ በግብርናው ዘርፍ ታሪክ መስራት
እንደምትችል ጠቁሟል። የስንዴ ምርት መጠን እየጨመረ መምጣት፣ ዓመታዊ የስንዴ ፍጆታዋን ሸፍና ከውጭ ስንዴ
ለማስገባት ታወጣ የነበረውን እስከ ሰባት መቶ ሚሊየን ዶላር ወጪ ማስቀረቷ፣ ስንዴ ለጎረቤት አገሮች መላክ ውስጥ
መግባቷ ሲታሰብ በእርግጥም አገሪቱ በግብርናው ዘርፍ ታላቅ እምርታ ማስመዝገብ እንደምትችል ያሳያል።
ግብርናው ከተበጣጠሰ ማሳ የአስተራረስ ዘዴ የእርሻ ስራውን በሜካናይዜሽን በማስደገፍ ማከናወን እንዲቻል
አስተዋጽኦ ወደ ሚያደርገው ኩታ ገጠም እርሻ እየተሸጋገረ መሆኑ፣ የምርምር ዘርፍ ውጤቶችን መጠቀም መቻሉ፣
የውሃ አማራጮችን በሚገባ ስራ ላይ ማዋል መጀመሩና የመንግስት ቁርጠኝነት ለምርትና ምርታማነቱ በከፍተኛ ሁኔታ
እየጨመረ መምጣት አስተዋጽኦ ካበረከቱት መካከል ሊጠቀሱ ይችላሉ።
በአገሪቱ ምርትና ምርታማነት ቢጨምርም፣ በሌላ በኩል ደግሞ ድርቅ ዜጎቿን እየጎዳባት የምትገኝ አገር ናት።
እርግጥ ነው አገሪቱ የድርቅ አደጋ ተጋላጭነትን ለመቀነስ በተፋሰስ ልማት እና በሴፍቲኔት መርሀ ግብር ላይ ስትሰራ
ቆይታለች። በዚህም የዜጎችን የድርቅ ተጋላጭነት መቀነስ የተቻለባቸው አካባቢዎች እንዳሉ ይታወቃል። ከድርቁ
መመላለስ እና ብርታት ጋር በተያያዘ ግን ድርቅ የሚያስከትለው ችግር አሁንም ቀጥሏል።
ባለፉት ዓመታት በሶማሌና አሮሚያ ክልሎች በተከሰተው ድርቅ በርካታ ህዝብ ለተረጂነት መዳረጉ እንዲሁም
በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ እንስሳት ማለቃቸው ይታወሳል። ዘንድሮም በኦሮሚያ ክልል ቦረና ዞን በተከሰተ ድርቅ ዜጎች
እርዳታ ለመጠበቅ ተገደዋል፤ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ከብቶችም ማለቃቸውን ነው መረጃዎች ያመለከቱት።
ድርቁ በአጠቃላይ በዓለም የአየር ንብረት ለውጥ ሳቢያ የተከሰተ ቢሆንም፣ አደጋው በዜጎች ያደረሰው ችግር
ሲታሰብ የድርቅ ተጋላጭነትን በመቀነስ ላይ በስፋት እንዳልተሰራም ይጠቁማል። ችግሩ እያደረሰ ያለው ጉዳት አሁንም
የተጠናከረ የድርቅ ተጋላጭነትን የሚቀንስ ስራ መስራትን እንደሚፈልግ ድርቁ ቦረና ዞን ካደረሰው ጉዳት መረዳት
ይቻላል።
አሁን በድርቁ ጉዳት ለደረሰባቸው አርሶ እና አርብቶ አደሮች የርዳታ አቅርቦት እየደረሳቸው ይገኛል። በቀጣይም
በተጠናከረ መልኩ መድረስ ይኖርበታል። ይህ ጊዜያዊ መፍትሄ ነው፤ ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት ርብርብ ማድረግም
ያስፈልጋል። እስከ አሁን ሲከናወኑ የቆዩ የድርቅ ተጋላጭነትን የመቀነስ ስራዎችን ማጠናከሩ አንድ ስራ ነው፤ አገሪቱ
የድርቅ አደጋ ተጋላጭነትን የመቀነስ ስራውን በእጅጉ ማስፋት የግድ በሚላት ሁኔታ ውስጥ ትገኛለች።
ለዚህ ደግሞ በበጋ ስንዴ መስኖ ልማት የተገኘውን ተሞክሮ በተለይ የውሃ ልማት ስራዎቹን ወደ ድርቅ ተጋላጭ
አካባቢዎች ማስፋት ያስፈልጋል። የበጋ ስንዴ መስኖ ልማት ለማካሄድ ወንዞችን፣ የጥልቅ ውሃ ጉድጓዶችን፣ ሀይቆችን
ለመስኖ ልማት ማዋል ውስጥ ተገብቷል። በዚህም የሚታይ ለውጥ ማምጣትም ተችሏል። በልማቱ የተገኘውን ተሞክሮ
በማስፋት ድርቅን የመቋቋም አቅምን መገንባት ይገባል።
ድርቅ የሚመላለስባቸውን አካባቢዎች ማጥናት፣ ለበጋ መስኖ ስራ ላይ የዋሉ የውሃ አማራጮችን በእነዚህ
አካባቢዎች ማፈላለግና ማልማት ላይ በትኩረት መሰራት ያስፈልጋል። በተለይ በክረምት ወቅት በከንቱ የሚፈሰውን ውሃ
ማቆር ላይ በስፋት መስራት፣ ለእዚህም ትላልቅ ግድቦችን መገንባት፣ በዚህ የሚጠራቀመውን ውሃም ወደ ተለያዩ የአርሶ
አደሩና አርብቶ አደሩ አካባቢዎች በማድረስ በእርሻ ስራ በስፋት ማሰማራት፣ ከብቶቻቸውን መታደግ ያስፈልጋል።
በቦረና በእንድ ወቅት ተጀምረው የነበሩ የጥልቅ ውሃ ጉድጓድ የማልማት ስራዎች ምን ደረጃ አንደደረሱ በመመርመር
እና ተሞክሮ በመቅሰም፣ መስፋት ያለባቸውን በማስፋፋት፣ የድርቅ ተጋላጭነትን ለመቀነሱ ስራ ማዋል ያስፈልጋል።
አገሪቱ ያላት ሰፊ የውሃ አቅም ሀብት አውጥቶ በመጠቀም ለውጥ ማምጣት እንደሚቻል የበጋ ስንዴ መስኖ ልማት
እንዲሁም የአትክልትና ፍራፍሬ ልማት ስራዎች ይመሰክራሉ። ለዚህ ስራ የማንንም አገር ተሞክሮ ፍለጋና ቅመራ መሄድ
አያስፈልግም። አገሪቱ የራሷ አገር በቀል ተሞክሮዎች ሞልተዋታልና። እነዚህን ተሞክሮዎች ማስፋት ብቻውን የድርቅ
ተጋላጭነትን በመቀነስ የዜጎችን ህይወትና የእንስሳት ሀብትን በወሳኝ መልኩ መታደግ ይቻላል።
በግብርናው ዘርፍ ታስቦባቸው የማያውቁ እንደ በጋ ስንዴ መስኖ ልማት ባሉት ላይ በመስራት ውጤታማ መሆን
ተችሏል፤ በድርቅ አደጋ ተጋላጭነት ቅነሳ ላይም ተመሳሳይ ስራ በማከናወን ዘላቂ መፍትሄ ማስቀመጥ ይገባል።
በእዚህ በኩል የቆላማ አካባቢዎችና የመስኖ ልማት ሚኒስቴር ወደየትም የማይገፋው ሰፊ የቤት ስራ ከፊቱ
ተቀምጦለታል። ለድርቅ ተጋላጭ የሆኑ አካባቢዎችን በጥናት መለየት ይኖርበታል፤ የውሃ አማራጮችን እንዲሁ በጥናት
በመለየት ማልማትና በየአርሶ እና አርብቶ አደሩ መንደር ማድረስ ላይ መስራት ይጠበቅበታል። ለእዚህም የመንግስትን፣
የለጋሾችን፣ የመላ ሕዝቡን ተሳትፎና ትብብር ማጎልበት ያስፈልጋል!
አዲስ ዘመን የካቲት 28 ቀን 2015 ዓ.ም