የአንድን አገር ስፖርት ውጤታማና ቀጣይነት ያለው ለማድረግ መሰረቱ በታዳጊዎች ላይ ትኩረት አድርጎ መስራት መሆኑን ባለሙያዎች ደጋግመው ያነሳሉ፡፡ ለዚህ ደግሞ ትምህርት ቤቶች ትክክለኛው ቦታ ናቸው፡፡ ምክንያቱም ታዳጊዎች በትክክለኛ እድሜያቸው የሚገኙት ትምህርት ቤቶች ላይ ከመሆኑ በተጨማሪ፣ የስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራ እንዲሁም ባለሙያዎች በአንድነት የሚገኙትም በትምህርት ቤቶች በመሆኑ፡፡ ይህንን በመገንዘብ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የአትሌቲክስ ፌዴሬሽን ትምህርት ቤቶችን ማዕከል በማድረግ የታዳጊ ፕሮጀክቶች ላይ በስፋት በመንቀሳቀስ ላይ ይገኛል፡፡
ለዚህም የአዲስ አበባ ከተማ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን በጃንሜዳ እና አበበ ቢቂላ ስታዲየም ታቅፈው ለሚገኙ የታዳጊ ፕሮጀክቶች ድጋፍ እያደረገ ይገኛል፡፡ የከተማ አስተዳደሩ ፌዴሬሽን በህጻናት ፓይለት ፕሮግራሞች በወንድራድና በስብስቴ ነጋሲ አንደኛ ደረጃ ትምርህርት ቤቶች የሚገኙትን ፕሮጀክቶችን እየደገፈ መሆኑንም ጠቁሟል፡፡ በቅርቡም በፕሮጀክቱ የሚካተቱ ታዳጊዎች ምልመላ በትምህርት ቤት ደረጃ ውድድር ለማዘጋጀት ማቀዱን ፌዴሬሽኑ አስታውቋል፡፡
በትምህርት ቤት ደረጃ የታዳጊ ፕሮጀክቶችን ለማብዛት የሚደረገው ውድድር መጋቢት/2015ዓም መገባደጃ ላይ የሚደርግ ሲሆን፤ በምልመላው የተገኙ ብቃት ያላቸው ታዳጊዎች በፕሮጀክቶች ታቅፈው የሚሰለጥኑበት እድል እንደሚመቻችም ታውቋል። ለዚህ የሚሆኑትን አራት ፕሮጀክቶች ፌዴሬሽኑ በራሱ በጀት ለመያዝ በዝግጅት ላይ እንደሚገኝም ጠቁሟል።
በትምህርት ቤቶች ወድድር የሚለዩትም ከ13፣ ከ15 እና ከ17 ዓመት በታች ባሉ የዕድሜ እርከኖች ሲሆን፤ በዚህ መሰረት የሚለዩት ታዳጊዎችም ወደ ስልጠናው የሚገቡ ይሆናል፡፡ የከተማ አስተዳደሩ ወጣቶችና ስፖርት በስልጠና ክፍሉ ከዚህ ቀደም አራት ከ15 ዓመት በታች ፕሮጀክቶችን የያዘ ሲሆን፤ ፌዴሬሽኑም የሙያ ድጋፍና ክትትል እያደረገላቸው ይገኛል፡፡ ፕሮጀክቶቹን በትምህርት ቤት ደረጃ እንዲያሰለጥኑ ለስፖርት ሳይንስ መምህራን የአሰልጣኞች ስልጠናን ለመስጠትም ዝግጅቶች በመጠናቀቅ ላይ ይገኛሉ። እንደ ከተማ አትሌቲክሱን በፕሮጀክት ደረጃ ለመያዝ ክፍለ ከተሞች ፍቃደኛ መሆን ባለመቻላቸው ፌዴሬሽኑ ክፍተቱን ለመሸፈን ትምህርት ቤት አካባቢ ፕሮጀክቶችን በማስፋፋት አዲስ አበባን የሚወክሉ አትሌቶችን ለማፍ ራት እንደወሰነም ጠቁሟል፡፡
የከተማ አስተዳደሩ በፕሮ ጀክቶች ውድድር ውጤታማ የነበረ ሲሆን፤ በአጠቃላይ ውጤትም የሶስተኝነት ደረጃን በመያዝ ነበር ያጠናቀቀው። በእድሜ ተገቢነት ረገድም ተገቢውን የእድሜ እርከን ይዞ በመቅረቡ ምንም ዓይነት ችግር እንዳልገጠመው ፌዴሬ ሽኑ አስታውቋል። ለዚህም ምክንያት የሆነው ታዳጊዎቹ ወደ ስልጠና ከመግባታቸው አስቀድሞ በህክምና ባለሙያ ዎች እገዛ ትክክለኛ ዕድሜያቸው ተጣርቶ ወደ ስልጠና በመግባታቸው መሆኑ ተገልጿል፡፡ ለሚቀጥለው የትምህርት ቤቶች ፕሮጀክት እድሜ ምልመላም ተመሳሳይ ሂደትን እንደሚከተልም ፌዴሬሽኑ ጠቁማል፡፡
ስልጠና ያለውድድር ውጤታማ አይሆንምና ፌዴሬሽኑ ከተማ አቀፍ ውድድሮችን ለማዘጋጀት ቢያቅድም ብቁ የሆነ የመወዳደርያ ስፍራ አለመኖር ትልቅ እንቅፋት ሆኖበታል፡፡ ፌዴሬሽኑ በውድድር ዓመቱ አስር ውድድሮችን ለማድረግ ያቀደ ሲሆን፤ የትምህርት ቤቶች፣ የማራቶን እና የክፍለ ከተሞች እንዲሁም የገቢ ማሰባሰቢያ ውድድሮችን በቀጣይ የሚያከናውን ይሆናል፡፡ ይሁንና አዲስ አባባ ስታዲየም በእድሳት ላይ በመሆኑ እንዲሁም በአበበ ቢቂላ ስታዲየም የሜዳ ተግባር መወዳደሪያ ባለመኖሩና መሙ አስፈላጊውን መስፈርት ባለመጠበቁ ተወዳዳሪዎች ለጉዳት እንዳይዳረጉ ስጋት ስላለባቸው ውድድሮችን ማካሄድ አዳጋች እንደሆነበት ፌዴሬሽኑ ገልጿል፡፡ ያለው አማራጭ የኢትዮጵያ ስፖርት አካዳሚ በመሆኑም ውድድሮቹን እዚያ ለማድረግ መገደዱን ጠቁሟል፡፡
የአዲስ አበባ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ወይዘሮ እታፈራው ገብሬ፣ ስፖርቱ ከመንግስት ተላቆ ወደ ህዝብ እንዲገባ በተቀመጠው አቅጣጫ መሰረት ድጋፎችን ለማሰባሰብ ስራዎች እየተሰሩ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡ ፌዴሬሽኑ በራሱ ገቢ ለመመራት የሚያደርገውን ጥረት አጠናክሮ ለመቀጠል ከጎኑ ሆኖ በተለያዩ ወጪዎች ድጋፍ በማድረግ ላይ የሚገኘው ሞሃ ለስላሳ መጠጦች ፋብሪካ እንደሆነ ገልፀው፤ ተጨማሪ ስራዎችን ለመስራት የተለያዩ ድርጅቶች ድጋፍ እንዲያደርጉ ያቀረበው ጥያቄ ምላሽ እንዳላገኘ አስረድተዋል፡፡ አትሌቲክስ የአገር ምልክት ከመሆኑ አኳያ ባለሃብቱ ድጋፉን እንዲያደርግም መልእክት አስተላልፈዋል፡፡ በከተማዋ ብዙ ባለሃብት ከመኖሩ አኳያ አንዱ ባለሃብት አንድ ፕሮጀክት ቢይዝ ከተማዋን በአትሌቲክስ ውጤታማ ማድረግና ማስጠራት እንደሚቻል የጠቆሙት የፅህፈት ቤት ኃላፊዋ፣ በዚህም የማዘውተሪያ ስፍራን ችግር ለመፍታት ባለሃብቶች ከአሸዋ ሜዳዎች ስራ ጀምሮ ከፌዴሬሽኑ ጎን እንዲቆሙና እንዲደግፉ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
አለማየሁ ግዛው
አዲስ ዘመን የካቲት 27/2015