ተቀራራቢ የፖለቲካ አላማና ርዕዮት ዓለም ያላቸው ተፎካካሪ ፓርቲዎች በመዋሃድ ቁጥራቸውን ወደ ሶስትና አራት ዝቅ አድርገው ለቀጣዩ ምርጫ ዴሞክራሲያዊነት እንዲዘጋጁ እየተከናወነ ባለው ተግባር ፓርቲዎች መዋሀድ ጀምረዋል፡፡ ይህ ውህደታቸው በጠንካራ የፖለቲካ መሰረት ላይ ከተገነባ አዋጭ ነው ሲሉ የፖለቲካ ምሁራን ይገልጻሉ።
የባህርዳር ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካል ሳይንስ ረዳት ፕሮፌሰር አቶ ውህበእግዜር ፈረደ እንዳሉት፤ ተፎካካሪ ፓርቲዎቹ እርስ በእርሳቸው እንዲሁም ከገዢው ፓርቲ ጋር የጀመሩት ውህደት ጥሩ የሚባል ቢሆንም፤ በአንድ አቋም ርዕዮተ ዓለምና የትግል አቅጣጫ መሰረት በዘላቂነት የሚሄድ ሊሆን ይገባል ።
‹‹በአገሪቱ በርካታ ተፎካካሪ ፓርቲዎች ባሉበት ሁኔታ በአጠቃላይ የምርጫ ስርዓት ውስጥ በቂ ድምጽ ማግኘት አይቻልም፤ ወደ ውህደት መቅረብ ጥሩ አማራጭ ነው›› ያሉት ረዳት ፕሮፌሰሩ፤ ውህደት ሲባል ግን ዝም ብሎ አብሮነት መሆን እንደሌለበት ይጠቁማሉ፡፡ ‹‹ፓርቲዎች ይመሩበት በነበረው መርሀ ግብር ላይ ውይይት በማድረግ አቋማቸውን ወደ አንድ ማምጣት ካልቻሉ የመዋሃዱ አሳማኝነትና ዘላቂነት አጠያያቂ ይሆናል››ያሉት ረዳት ፕሮፌሰሩ፤ መጀመሪያ ይሆናል» ያሉት ረዳት ፕሮፌሰሩ፣ መጀመሪያ በመስመራቸውና በርእዮተ ዓለም ዙሪያ ውይይት ማድረግ እንዲሁም አባሎቻቸውንም ማሳመን እንደሚገባቸው አመልክተዋል፡፡
የፖሊሲ ጥናት ኢንስቲትዩት መሪ ተመራማሪ ዶክተር ግርማ ተሾመ እንዳሉት፤ በርካታ ተፎካካሪ ፓርቲዎች የሚያነሷቸውም ጉዳዮች ተመሳሳይ ናቸው። በመሆኑም ሰብሰብ ማለቱ በጣም ይደገፋል፡፡ተመሳሳይ መርሃ ግብር፣ ቋንቋ እንዲሁም ርእዮተ ዓለም የሚከተሉ ፓርቲዎች ውህደት መፍጠራቸው ለአገርም ለህዝብም ጠቀሜታው ከፍተኛ ነው።
ዶክተር ግርማ እንደተናሩት፤እነዚህ ፓርቲዎች ሁሉም ለማለት በሚቻል ሁኔታ የተራራቀ ሃሳብ ያላቸው አይደሉም፤አካሄድ ላይ ካልሆነ በስተቀር ልዩነት የላቸውም። በመርሀ ግብርና በዓላማ ሲታይም ብዙዎቹ ተመሳሳይ ናቸው። ልዩነት ቢኖርም እንኳን የሰጥቶ መቀበል መርህን በመከተል በድርድር መቀራረብና መፍታት ይቻላል፡፡
ከሚዋሀዱት ፓርቲዎች መካከል የአንዱ ሃሳብ ብቻ ተይዞ የሌላኛውን አለመያዝ ውጤታማነት ላይ ችግር ያመጣል የሚሉት ዶክተር ግርማ፤ በመጀመሪያ ዴሞክራሲን በውስጣቸው መለማመድ ከዚያ መወያየት ለመቀራረብና አንድ ለመሆን ወሳኝ መንገዶች ያመለክታሉ።
«አሁን ላይ ለሚታዩት አንዳንድ ግጭቶች መንስኤያቸው የተለያዩ የፖለቲካ አማራጮች የትግል መስመሮች እንዲሁም ጥቅምና ፍላጎቶች ናቸው፤ እነዚህን ሁሉ በፓርቲዎች ጥምረትና ህብረት ወደ አንድ ለማምጣት የሚደረገው አካሄድ ጥሩ ነው። ውጤታማ የሚሆነው ግን በትግል መስመርና በርእዮተ ዓለም በፍላጎትና በመግባባት ላይ ሲመሰረት ነው» ይላሉ።
ረዳት ፕሮፌሰር አቶ ውህበእግዜር ውህደት ሲባል አንዱ በአንዱ ውስጥ መግባት ካለመሆኑም በላይ የተዋሀዱ ፓርቲዎች ከሚይዙት አርማ ጀምሮ የማንን ይዞ ይቀጥሉ የሚለው እራሱ በርካታ ሂደቶች ያሉትና መስማማትን የሚጠይቅ ነው ይላሉ። አሁን እየተዋሀዱ ያሉ ፓርቲዎች የመጀመሪያውን እንቅስቃሴ አደረጉ እንጂ ገና ብዙ ሂደቶች እንደሚቀሯቸውም ይገልጻሉ፡፡
ውህደቱ በመሰረታዊነት ብሔራዊ ጥቅምን በዘላቂነት ሊፈታ እንዲሁም የኢትዮጵያን የፖለቲካ ምስቅልቅሎሽ ሊያስወግድ በሚችል መርህ መሰረት መካሄድ እንዳለበት ጠቅሰው፤ ፓርቲዎች በዘላቂነት ጠንክረው ሊወጡ የሚችሉበት ውህደት ሊኖር እንደሚገባ ይናገራሉ፡፡ ይህን ማድረግ ካልተቻለ ግን ውህደቱ ጊዜያዊ ጋብቻ ሊሆን እንደሚችል፣ ይህ ደግሞ ውስጣዊ ችግርን በመፍጠር በአገር ላይ ያልተረጋጋ ሁኔታ እንደሚያስከትል ይጠቁማሉ፡፡
በድርድርና ሰጥቶ በመቀበል መርህ አካሄዳቸውም ሆነ መርሀ ግብራቸው ላይ ተወያይተውና ተከራክረው ለህዝብ ጥቅም የሚበጀውን በመመካከር በጋራ አሸናፊነት ለመቀጠል መስማማት እንደሚጠበቅባቸው ያመለክታሉ፤ ለደጋፊዎቻቸውም አንድ መሆናቸውንና የአካሄድ ስልት መቀየራቸውን ማሳየት ይገባቸዋል።
እንደ ረዳት ፕሮፌሰሩ ማብራሪያ፤ውህደቶች ቀጣይነት እንዲኖራቸው በፓርቲዎች ውስጥ ያሉ አካላት በተዋረድ ውይይቶችን ማድረግ አለባቸው፤ አመራሩ ብቻ ውሳኔውን የሚያሳልፍ ከሆነ ደጋፊዎቹ አብረውት አይቀጥሉም። ካልተወያዩ አመራሩ ሲዋሀድ ደጋፊው ደግሞ ሌላ ፓርቲ ይዞ ብቅ ይላል። ውህደቱም ቀጣይነት አይኖረውም። መፍትሔው መጀመሪያ ሃሳቡ ሲጠነሰስ መጀመር ያለበት ከታች ነው። አመራሩ ባመነበት ልክም ደጋፊው እንዲያምን ማድረግና ፍላጎታቸውንም ማክበር ያስፈልጋል፡፡
ኢህአዴግን የመሰረቱት አራቱ ብሔራዊ ድርጅቶች በጋራ የሚመሩበት የራሳቸው መርህ እንዳላቸው ለአብነት በመጥቀስ፣ በቅርቡ ውህደት የፈጸሙት የኦሮሞ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ(ኦዴፓ)እና የኦሮሞ ዴሞክራቲክ ግንባር (ኦዴግ) መሰረታዊ ድርጅቶቹ በሚከተሉት መርህና መርሀ ግብር ውስጥ ይገባሉ ወይስ የኢህአዴግ አካል ሆነው ይቀጥላሉ ? የሚለውን ጥያቄ ሊመለስ ይገባል ሲሉ ያብራራሉ። ይህ አካሄድ ምናልባትም በቀጣይ ከእያንዳንዱ ብሔራዊ ፓርቲ ጋር የሚዋሀዱትን የሚመለከት ወሳኝ ሃሳብ መሆኑንም ይናገራሉ።
ፓርቲዎች እያደረጉ ያሉት ውህደት አሁን አገሪቱ ከምትፈልገው የፖለቲካ መስመር አኳያ የሚፈለግ ቢሆንም፤ ወደ ውህደት ከመሄዳቸው በፊት ግን ጥምረት መመስረት አይችሉም ነበር ወይ? የሚለውም ሊጠየቅ ይገባል ሲሉ ረዳት ፕሮፌሰሩ ይጠቁማሉ፡፡ በቀጣይ ኢትዮጵያ ውስጥ ምንም ዓይነት ዴሞክራሲያዊ ምርጫ ቢካሄድ ሊፈጠር የሚችለው መንግስት የጥምር መንግስት ነው የሚሉት ረዳት ፕሮፌሰሩ፤ ይህ ሁኔታ የተሳካና ህዝቡም ሳይወዛገብ ድምጹን ለማን መስጠት እንዳለበት እንዲወስን እነርሱም ውድድሩን በብቃት ማሸነፍ እንዲችሉ የግድ ለገዥውም ሆነ ለተፎካካሪ ፓርቲዎች ወደ ውህደት መሄዱ ግዴታ ነው ሲሉ ያብራራሉ።
ዶክተር ግርማ በአንዳንድ ፓርቲዎች ዘንድ ውህደት፣ ሌሎቹ ዘንድ ደግሞ ጥምረት አዋጭ ሊሆን እንደሚችል ይገልጻሉ፡፡አብዛኞቹ በአገሪቱ ያሉ ፓርቲዎች ተመሳሳይ፣ለአንድ አካባቢ ህዝብ የቆሙና በስም ብቻ የሚለያዩ መሆናቸውን አመልክተው፤ ውህደት የሚያስኬድ መሆኑን ይገልጻሉ።
በኢትዮጵያ የመጣውን ለውጥ ተከትሎ መንግስት በወሰደው እርምጃ በርካታ ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች በስደት ከሚኖሩበት አገር ወደ አገራቸው ገብተዋል፡፡ በአገሪቱ የሚንቀሳቀሱ ተፎካካሪ ፓርቲዎችም እንዲሁ በነጻነት የሚንቀሳቀሱበት ሁኔታ ተፈጥሮላቸዋል፡፡
ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች ከ70 በላይ እንደሚደርሱ መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡ በቅርቡም ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ከፓርቲዎቹ ጋር ባደረጉት ምክክር ተፎካካሪ ፓርቲዎች ወደ ሶስትና አራት ተሰባስበው ቢንቀሳቀሱ ምርጫው ዴሞክራሲያዊ እንዲሆንና ለዴሞክራሲ ስርአት ግንባታም እንደሚጠቅም አስታውቀዋል፡፡
ሰሞኑን ኦዴፓና ኦዴግ ውህደት የፈጸሙ ሲሆን፤ ቀደም ሲል የአማራ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ(ኦዴፓ) ከአማራ ዴሞክራሲያዊ ኃይሎች ንቅናቄ (አዴሃን)ጋር ውህደት መፈጸሙ ይታወሳል፡፡
ተፎካካሪ ፓርቲዎች ውህደት መፍጠር የሚገባቸው በመጀመሪያ በራሳቸው መካከል ያለውን መተማመን ካጎለበቱ በኋላ መሆን ይኖርበታል፡፡ መዋሃድ የእነርሱ በጎ ፈቃደኝነት ቢሆንም፤ ማን ከማን ጋር የሚለውም ጉዳይ ከግምት ውስጥ መግባት አለበት፡፡ ምርጫን ብቻ ታሳቢ በማድረግ ሳይሆን ጠንክሮ በሁለት እግር ለመቆምም መዋሃድ አማራጭ የሌለው ጉዳይ ነው፡፡
አዲስ ዘመን ህዳር 25/2011
እፀገነት አክሊሉ