ኢትዮጵያ ጥንታዊ ስልጣኔ እና ከአብዛኞቹ የዓለም ሀገራት ጋር ሲነጻጸር ረጅም የስርዓተ መንግስት ታሪክ ያላት ሀገር ነች፡፡ ይህች ጥንታዊት ሀገር በየዘመናቱ የሚያጋጥሟትን ፈተናዎች በማለፍ ያላትን ሉዓላዊነት ክብርና ሞገስ ጠብቃ ዛሬ ላይ ደርሳለች፡፡ ዓድዋን፤ መተማንና ካራማራን በመሳሰሉ የጦር አውድማዎች የሀገርን ሉአላዊነትና ዳር ድንበር አላስደፍርም ያሉ ጀግኖች ልጆቿም ደማቸውን አፍስሰው፤ አጥንታቸውን ከስክሰው ከነክብሯ ለዛሬው ትውልድ አስረክበዋል፡፡
የዛሬው ትውልድም የአያትና ቅድመ አያቶቹን አደራ በመረከብም በጦር ሜዳ ውሎውም ሆነ በልማት ዘርፉ የራሱን አሻራ በማሳረፍ ላይ ይገኛል፡፡ ለሀገሩ ሉዓላዊነት መታፈርና ለዳርድንበሩ መከበር በተጠራበት መስክ ሁሉ በመዋደቅ የቀደምት አያቶቹን ታሪክ ደጋግሞ ጽፏል፡፡ ከዚያም አለፍ ብሎ ኢትዮጵያ በዕድገት ጎዳና እንድትጓዝ የቻለውን ሁሉ እያደረገ ነው፡፡ ጀግንነት በጦር ሜዳ ብቻ እንዳልሆነ በመረዳትም የዓባይ ግድብ የመሳሰሉ ዘመን ተሻጋሪ ፕሮጀክቶቹን በራሱ ገንዘብና ዕውቀት በማገዝ ኢትዮጵያን ከብልጽግና ማማ ላይ ለማቆም በመጣር ላይ ይገኛል፡፡
በዚህ ትውልድ ጠንሳሽነት ግንባታው ከ84 በመቶ በላይ የደረሰው የዓባይ ግድብ በርካታ ፈተናዎችና አሜካላዎች ቢገጥሙትም በዚህ ትውልድ አይበገሬነት ዛሬ ከራስ አልፎ ለጎረቤት ሀገራት የኢኮኖሚ ነጻነት ብርሃን መሆን ችሏል። የኢትዮጵያን መበልጸግ የማይፈልጉ ሀገራት ግድቡን ለማሰናከልና የትውልዱንም ተስፋ አብሮ ለማጨለም ያልፈነቀሉት ድንጋይ ባይኖርም በፍትሃዊ አቋም፣ በዚህ ትውልድ በሳል አመራርና በሕዝብ ጽናትና የማያቋርጥ ድጋፍ የዓባይ ግድብ ወደፍሬ እየተቃረበ ነው፡፡ ኢትዮጵያውያንም የዓባይን ግድብ ለፍጻሜ በማቃረብ እንደ ዓድዋ ሁሉ ዛሬም ለአፍሪካ ሀገራት የኢኮኖሚ ነጻነት ብርሃን ሆነዋል፡፡
ከዚህም አልፎ ኢትዮጵያውያን ከ25 ቢሊዮን በላይ ችግኝ በመትከልም ሌላ የዘመኑን ታሪክ ጽፈዋል፡፡ በዓለም ደረጃ እየተስፋፋ የመጣውንና በቀጣይም የዓለም ሀገራት ስጋት ይሆናል ተብሎ የሚሰጋውን የበረሃማነት መስፋፋት ከወዲሁ ለመመከት ኢትዮጵያውያን እጃቸውን ከአፈር ጋር በማወዳጀት አረንጓዴና ምቹ ዓለምን ለመጪው ትውልድ ለማስረከብ ዜግነታዊ ግዴታቸውን በብቃት በመወጣት ላይ ይገኛሉ፡፡ ይህንኑ ተሞክሮም እንደ ኬንያ ያሉ በርካታ የአፍሪካ ሀገራት በመውሰድም አፍሪካን ለአየር ንብረት ለውጥ የማትበገር አህጉር ለማድረግ በመጣር ላይ ይገኛሉ፡፡ ይኼው የኢትዮጵያውያን ጥረት በቅርቡ በተካሄደው የአፍሪካ ኅብረት 36ኛው መደበኛ ስብሰባ ላይ አድናቆትን በማግኘት አንዱ የዚህ ትውልድ ደማቅ አሻራ ሆኗል፡፡
ኢትዮጵያ በዓድዋ ቅኝ ገዢዎችንና ወራሪዎችን በማሳፈር የድል እና የነጻነት ተምሳሌት ነች፡፡ ሆኖም በጦር ሜዳ የተገኘውን ድል በልማቱም መስክ በመድገም ሀገርን ከስንዴ ልመና ለማውጣት የሚደረገው ጥረት ግቡን ሳይመታ ዓመታት ተቆጥረዋል፡፡ አሁን ግን ታሪክ መቀየር ጀምሯል፡፡ይህ ትውልድ ከእርዳታ ጠባቂነት የሚያላቅቀውን ስንዴን አምርቶ ወደ ውጭ ሀገራት ለመላክ በቅቷል፡፡ በዚህ አመት ብቻ 32 ሚሊዮን ኩንታል ስንዴ ለውጭ ገበያ መቅረቡም የዚሁ ስኬት አንዱ ማሳያ ነው፡፡ ሆኖም የኢትዮጵያ ችግር በአንድና በሁለት ዓመታት የስንዴ ምርት የማይፈታና ተከታታይ በሆነ መልኩ ምርትና ምርታማነትን ማሳደግ የሚጠይቅ ነው፡፡ ስለዚህም ባለፉት አራት ዓመታት የተደረጉ ለውጦች ኢትዮጵያን ከስንዴ ልመናና ገዢነት ወደ ስንዴ ላኪነት ለማሸጋገር አብቅቷታል፡፡ ይህ ስኬት ትጋትና ትዕግስት ከታከለበት ለዘመናት የተከማቹ ችግሮች በሂደት እየተራገፉ እንደሚመጡ አመላካች ነው፡፡
በተለይም የዛሬው ትውልድ ችግሮችን በመነጋገርና በውይይት መፍታት ከቻለ አሉ የሚባሉትን ችግሮች ሁሉ ወደ ምቹ አጋጣሚ መቀየር ይቻላል፡፡ ለዚህ አብነት የሚሆነው ደግሞ ለሁለት ዓመታት ያህል በኢትዮጵያ መንግስትና በሕወሓት መካከል ሲደረገው የቆውን ጦርነት የውጭ ኃይል ሳይገባበት በምክክርና በውይይት መፍታት መቻሉ ነው፤ ተግባሩም ኢትዮጵያን በአዲስ አስተሳሰብና ጎዳና እንድትራመድ አድርጓታል፡፡ ይህ ተግባር ሀገራችን የሚገጥሟትን ችግሮች ሁሉ በራሷ አቅም የመፍታት አቅም እንዳላትም አሳይቷል፡፡ በአሁኑ ወቅት በኦሮሚያ ቦረናና ጉጂ፤ በደቡብ ክልል በአንዳንድ ቦታዎች እንዲሁም በሶማሌ ክልል የተከሰተው የድርቅ አደጋን ለመመከት ኢትዮጵያውያን እያሳዩት ያለው አንድነትና ወንድማማችነት ኢትዮጵያውያን በየጊዜው የሚገጥሟቸውን ችግሮች በጋራ ክንድ መመከት እንደሚችሉ ጥሩ ማሳያ ነው!
አዲስ ዘመን ሰኞ የካቲት 27 ቀን 2015 ዓ.ም