**ጣሊያን ሞኙ…. የሀበሻን ልክ አያውቅማ…ባንዳ ሁሉ ባንዳ ይመስለዋል እንዴ?….አይሁዳዊው ይሁዳ ጌታውን ስሞ በሰላሳ ዲናር ሸጠው፤ ኢትዮጵያዊው ይሁዳ ግን ሀገራቸውን ለማዳን ሲሉ የጄኔራሉን ጉልበት ስመው ሄዱ…የኢትዮጵያን አርበኛ አበላለሁ ብሎ የሞት ድግስ ደገሰ አሉ….የማን ዘር ጎመን ዘር!…. አሰናባሪው ባሻ አውአሎምስ የሀበሻ ልጅ አይደሉ… …ከጮማውም፣ከቀዩም፣ከሽንጡም፣ከሻኛውም እየቆረጡ፤ ከጠላውም፣ከጠጁም እየቀዱ በአናት በአናቱ አስጋፋት…. ደጋሹ ጣሊያንም በስካርና በቁንጣን ፈንድቶ በራሱ ድግስ ሞተ… ባሻ አውአሎም የዘረጉትን የመረጃ ሰንሰለት፣ ጣሊያኖቹ በራሳቸው አንገት አጠለቁትና እንደ አንበሳ ገብተው እንደ ውሻ ተጎትተው ወጡ…**
በጦርነት ውስጥ የጠላትን መረጃ ማግኘት የአሸናፊነቱን ቁልፍ ለመጨበጥ ግማሹን መንገድ እንደሚሄድ ይቆጠራል። ያውም በዛኛው ዘመን ደግሞ በቃላቶች ብቻ ተገልጾ የሚታለፍ አይደለም። ምንም አይነት ዘመናዊ የመገናኛ ዘዴ እንኳን በሌለበት በዚያ ዘመን በድፍረት ከጠላት መንደር ሰርስሮ መግባትና ገብቶም መረጃውን ይዞ በተሳካ መንገድ ለመውጣት ምናልባትም ባሻ አውአሎምን መሆን ይጠይቃል። ለመሆኑ ባሻ አውአሎም ማናቸው? የሠሩትስ ገድል ምንድነው? በዓድዋ ድል ማግስት የእኚህን ዝነኛ ሰላይ ገድል እንመልከት።
ባሻ አውአሎም በሞሳድና በሲአይኤ የስለላ ተቋማት ውስጥ የስለላን ጥበብ ተምረው የወጡ ምሑር ሰላይ አይደሉም። ይልቁንስ የኤርትራ ግዛት እንደዛሬው ከኢትዮጵያ እቅፍ ሳትወጣ በፊት በትግራይ ድንበር አካባቢ ተወልደው ያደጉና በፋሽስት ወረራ ወቅት፣ በነበራቸው ልዩ የስለላ ብቃት የፋሽስቱን ጦር ከአፈር ለመቀላቀል በስለላ ጀልባ ላይ እየቀዘፉ፣ ከፋሽስት መንደር ወደ አርበኛው፣ ከአርበኛው ወደ ፋሽስቱ መንደር ከማዶ ማዶ ሽርጉድ ሲሉ የነበሩ ድንቅ አሰናባሪ ሰላይ ናቸው። ታሪክ ዘነጋቸው እንጂ የስለላን ምንነት ሳያውቁ ተፈጥሮ በሰጠቻቸው እውቀት ብቻ የሠሩት ሥራ ዛሬ ዓለማችን ላይ ከሚወራላቸው ታላላቅ ሰላዮች ከሠሩት ቢበልጥ እንጂ አያንስም። በሀገራዊ ወኔና ፍቅር ብቻ ተነሳስተው የጥቁር ሕዝብ ሁሉ ኩራት ለሆነው የዓድዋ ድል ይህ ነው የማይባል አስተዋጽኦ አበርክተዋል።
በግራም ነፈሰ በቀኝ ግን በወቅቱ የነበረው የኢትዮጵያ እና የፋሽስት ጣሊያን ጦርነት ባሻ አውአሎምን ታሪካዊ ሰላይና የሀገር ባለውለታ አድርጓቸዋል። ቀደም ሲል ባሻ አውአሎም የራስ አርአያ ጀግና ወታደር የነበሩ ሲሆን፣ ራስ አርአያ ሲሞቱም የራስ መንገሻ ወታደር ሆኑ። ባሻ የሚለውንም ማዕረግ የሰጧቸው ራስ መንገሻ ነበሩ። ለሠሩት ታሪካዊ ሥራ ግን በትውልዶች ሳይዘመርላቸውና በቅጡ ሳይወራላቸው ኖረዋል።
ባሻ አውአሎም የሠሩት ገድል ምናልባት ከአንድ የጦር ጀኔራል የሚስተካከል ነው ቢባል ማጋነን አይሆንም። ለመሆኑ ባሻ አውአሎም የሠሩት ትልቅ ገድል ምንድነው? ጊዜው ለየካቲት 23/1888ዓ/ም ተቃርቧል። በወቅቱ ደግሞ የጣሊያኗ ፋሽስት ጦር ጄኔራሎች እየረገፉባት ስታፈራርቃቸው የነበረበት ጊዜ ነው። የዚያን ጊዜ ደግሞ ጦሩን የሚመራው ተረኛ ጄኔራል፣ ጄኔራል ባራቶሪ ነበር። ይህ ሰው እጅግ በጣም ብዙ የሚባሉ የኢትዮጵያ ሀገራቸውን ጡት ነካሽ ባንዳዎችን በየስርቻው አሰማርቶ ነበር። ምክንያቱ ደግሞ ስለ ኢትዮጵያ ከኢትዮጵያዊ በላይ የሚያውቅ የለምና እየሰለሉ መረጃን እንዲያመጡለት አደረገ። እንዳለመታደል ሆኖ ደግሞ ሰላቶው ፋሽስት ለስለላ ከመረጣቸው መሐከል ባሻ አውአሎም አንደኛው ናቸው። ጄኔራሉም የስለላ መረቡን በመዘርጋት እጩዎቹን አሰማራቸው። የእናት ሆድ ዥንጉርጉር እንዲሉ አብዛኛዎቹ በጥቅማጥቅም ተታለው የእውነትም የኢትዮጵያን ጦር እየሰለሉ መረጃን ሲያቀብሉ ነበር። በተቃራኒው ደግሞ ባሻ አውአሎምና ጥቂት መሰሎቻቸው ደግሞ የባራቶሪ አሽከር ሆነው በመቅረብ ለእናት ሀገራቸው ቆሙ። ለሁሉም ምሳሌ መሆን የቻሉና ነጥረው በመውጣት ታምርን መስሥራት የቻሉት ግን ባሻ አውአሎም ነበሩ።
እናም የታላቁ ሰው ታምራዊ ጀብዱ ሲጀምርም እንዲህ ነበር። ጄኔራል ባራቶሪ የኢትዮጵያ አምላክ አይሁንልህ ሲለው ከሁሉም አብዝቶ የሚቀርበውና የሚያምነው ባሻ አውአሎምን ነበር። አስጠርቶም የመታነቂያ ገመዱን ከትልቅ የስለላ አደራ ጋር ሰጣቸው። ባሻም አይሆንም ሀገሬንማ አሳልፌ አልሰጥህም አላሉትም። ይልቁንስ ደስ አላቸው። ባራቶሪም ይሁዳ ጌታውን በሠላሳ ዲናር የሸጠበትን ታሪክ ሳያስታውስ አልቀረም። “የሰው ልጅ ለጥቅሙ ሲል ሰማያዊ ፈጣሪውን ከሸጠ ይሄ ድሃ ሀገሩን የማይሸጥበት ምን ምክንያት ሊኖር ይችላል” ሲል በልቡም የተሳለቀበት ይመስላል። ኢትዮጵያዊ ማን እንደሆን አያውቀውማ፣ ምን ያድርግ። እናም ከፊት ድሉን አሻግሮ እያየ አውአሎምን በፈገግታ ወደ ስለላው ሜዳ ሸኛቸው። አይሁዳዊው ይሁዳ ጌታውን ስሞ ሸጠው። ኢትዮጵያዊው ይሁዳ ግን ሀገራቸውን ከቀኝ ገዢው ለማስለቀቅ የባራቶሪን ጉልበት ስመው ሄዱ።
ከፋሽስቱ የጦር መንደር ወጥተውም ስለጉዳዩ እያሰላሰሉ ወደ አጼ ምኒሊክ ቤተ መንግሥት አቀኑ። ከዚያም ደርሰው የገጠማቸውን ነገር ለንጉሡ ገለጹላቸው። አጼ ምኒሊክም ይህንን ነገር ከአውአሎም አንደበት ሰሙ። ከዙፋናቸው ብድግ ብለው ከወለሉ ላይ ጎርደድ ጎርደድ እያሉ በሀሳብ ባሕር መቅዘፍ ጀመሩ። ወዲያው ባለቤታቸውና የቀኝ እጃቸው የሆነችውን እቴጌ ጣይቱን አስጠሯት። አጼ ምኒሊክ፣ እቴጌ ጣይቱ እና ባሻ አውአሎም ለሦስት አንድ ድንገተኛ ታላቅ ስብሰባ ማካሄድ ጀመሩ። ባሻ አውአሎም ይዘውት በመጡት መረጃ ዙሪያ ብዙ መከሩ፣ አወጡ፣ አወረዱ በስተመጨረሻም አንድ ሀሳብ ከመሃከላቸው ዱብ አለ። የፋሽስቱ ጄኔራል የአጼ ምኒሊክን ዙፋን በመረከብ የኢትዮጵያን በእጁ ለማድረግ እጅጉን ስለቋመጠ። ትልቅ የሠርግ ድግስ ደግሶ የጥሪ ካርድ በታኙን ባሻ አውአሎምን በመጠባበቅ ላይ ነው። አጼ ምኒሊክም ጥሪ አክባሪ ናቸውና መቼም አክብሮ ለጠራቸው የጣሊያን ጦር ስለ ምላሹ ተማከሩበት። የምላሹንም ድግስ በምን አይነት መልኩ መሆን እንዳለበት ሦስቱም ከተማከሩ በኋላ አውአሎምም ሌላኛውን የሠርግ ምላሽ፣ የጥሪ ካርድ በልባቸው በመያዝ የአጼውን ቤተመንግሥት ቅጥር ግቢ ለቀው ዳግም ወደ ጄኔራሉ ባራቶሪ ተመለሱ።
ጄኔራሉ፣ ባሻ አውአሎም አንድ የምሥራች ይዘው እንደሚመጡ እርግጠኛ ሆኖ ነበር። በጉጉት እየጠበቃቸው የነበሩት አውአሎም ከባራቶሪ ዘንድ ደረሱ። በኩራትም ጠጋ ብለው ደስ የሚያሰኝ ጮማ ወሬ ይዘው እንደመጡ ገለጹለት። ይሄኔ ባራቶሪ በደስታ ጮቤ ረገጠ። ወሬውንም ለመስማት ተጣደፈ። ‘እህሳ ባሻዬ በል ንገረኛ’ አለ። ባሻ አውአሎም ያንን ትኩስ ጮማ ወሬ በቢላ እየቆረጡና በአዋዜ እያጠቀሱ ማጉረሱን ቀጠሉ። “ምን መሰለህ ጌታዬ የፊታችን እሁድ በኢትዮጵያውያን ዘንድ የሚከበር አንድ በዓል አለ። እለቱ የጊዮርጊስ ታቦት የሚወጣበት ቀን ነው። እንደአጋጣሚ ሆኖ ደግሞ በዓሉ ከሰንበት ጋር ተገናኝቷል። ይህ ደግሞ ሌላ የማይገኝ እድል ነው። ከምንም በላይ ለፈጣሪያቸው ቅድሚያ ስለሚሰጡ በዚህ እለት ላይ ጦር ማንሳት ይቅርና ሥራ እንኳን አይሠሩም። በመሆኑም ንጉሡና ከፊሉ ሠራዊቶቻቸው ለክብረ በዓሉ ይወጣሉ። የተቀሩትም ቢሆን ቀለብ ፍለጋ በየቦታው ይበተናሉ። ስለዚህ ያለምንም መንፈራገጥ ንጉሡን ማርከህ ሀገሪቱን በቁጥጥርህ ስር ማድረግ ትችላለህ። ታዲያ ከዚህ የተሻለ ጊዜና ቦታ ከየት ታገኛለህ ፍጠን እንጂ’ በማለት አውአሎም ቀና ሲሉ፣ ከባራቶሪ ፊት ላይ ጸሐይን የሚያስንቅ ወገግታ ተመልክተው ‘አዬዬ ጣሊያን ሞኙ ሰው አማኙ’ ሲሉ በልባቸው ተረቱበት። ጄኔራሉ በጥርጣሬ ምንም ጊዜ ለማባከን አልፈለገም። ወዲያው ጦሩ ለ23ቱ የጊዮርጊስ እለት እንዲዘጋጁ አዘዘ።
በሠርጉ ደጋሽ የፋሽስቱ ጦር እና በጥሪ አክባሪው የኢትዮጵያ አርበኛ በጉጉት ስትጠበቅ የነበረችው የካቲት 23 ቀን ደረሰች። ለዚህች እለት ሽር ጉድ ሲል የከረመው የባራቶሪ ጦር ወፎች ሳይንጫጩ ገና በማለዳው ዘመናዊ ጦሩንና ጓዙን ሸክፎ ተሰናዳ። አሁን የቀረው ብቸኛው ነገር ቢኖር የጄኔራላቸው ፊሽካ ብቻ ነው። ምሽቱ አልነጋልህ ብሎት ያለ እንቅልፍ ያደረው ጄኔራሉም የጦር ሜዳ ካባ ጥሩሩን ለብሶ ተነሳ። ሙሽሪቱን ኢትዮጵያን የራሱ ለማድረግ በልቡ እየቸኮለ ‘በሉ እንግዲህ እንሂድ’ አለ። በሰላቶ ጀሌዎቹም ታጅቦ በሚሠራው ጀቡዱ ከፋሽስት መንግሥት ስለሚቸረው ክብርና ዝና እያሰበ ጉዞውን ጀመረ። ባሻም በልባቸው ከት ብለው እየሳቁ የመስዋዕቱን በግ እየነዱ ወደ ዓድዋ ተራሮች ይዘዋቸው ወጡ።
በሌላ በኩል ደግሞ ጀግናው የኢትዮጵያ አርበኛ ከዓድዋው የድግስ ስፍራ ላይ ድብቅ ድንኳኑን ጥሎ በመመሸግ ሠርገኛውን የፋሽስት ጦር በመጠባበቅ ላይ ነበር። ሳሩን እንጂ ገደሉን መመልከት የተሳነው ፋሽስቱም ዘመናዊ የጦር መሣሪያውን እያንጓዘዘ፣ ሲነዳ መጣ። ጀግናው ባሻ አውሎአም ልክ ከሠርጉ ደጅ ላይ መድረሳቸውን ሲያዩ ድንገት በሚያስበረግግ ድምጽ ‘ዘራፍ’ አሉና ጎራዴያቸውን መዘው አጠገባቸው የነበረውን ሰላቶ እንካ ቅመስ አሉት። ይሄኔ አንድ..ሁለት..ሶስት..እያሉ ለቁጥር የሚያዳግቱ የኢትዮጵያ አርበኛ ሠራዊት ከየት መጡ ሳይባል፣ ከሰማይ የወረዱ እስኪመስል ድረስ ከመሸጉበት ጎሬ እየወጡ የፋሽስት ጣሊያንን ጦር እንደጉንዳን ሰፈሩበት። ያንን ሁሉ ዘመናዊ የጦር መሣሪያና መድፍ ተሸክሞ የመጣው የባራቶሪ ጦር መላቅጡ ጠፍቶት ተርበደበደ። ጀግናው የኢትዮጵያ አርበኛ የፋሽስቱን አንገት እየቀላ ከላዩ ላይ ቁጭ ብሎ ከወዲህ ይሸልላል፣ ይፎክራል፣ ከወዲያ ቀረሮቶውን እየነፋ ሲያሻው በፈረስ ይጋልብበታል። አንዴ ህልም፣ ሌላ ጊዜ እብደት ሲመስላቸው በግራ መጋባት የናወዙት ባራቶሪና ጦሩ የሚያደርጉትን ቢያጡ የያዙትን መሣሪያ ዛፍ ይሁን ሰው ብቻ ባገኙት ነገር ላይ ሁሉ ያንዠቀዥቁት ጀመሩ። ወይ ፍንክች ሀበሻን አያውቁትም ኖሯል። የዘመናዊው መሣሪያ የተኩስ እሩምታ መች ሊያስፈራው፤ አጥንቱ ከመሣሪያው ብረት የጠነከረ፣ ደሙም ከመድፉ እሳት የባሰ የሚያቃጥል መሆኑን አልተረዳም። እራሱ በደገሰው ድግስ ጥሪ አክባሪው የኢትዮጵያ አርበኛ ከስፍራው ተገኝቶ ሠርግና ምላሹን አንድ አደረገው። ድል ያለውን የጣሊያንን ድግስ፣ ድል ባለ ሽንፈት አሽገው ስጦታውን ለፋሽስቱ መንግሥት ላኩለት። የድግሱ አሰናባሪ የነበሩት ጀግናው ሰላይ ባሻ አውአሎምም የሰላቶውን አንገት እየቀሉ በሽለላና ፉከራው ቢደክሙም፣ ነገር ግን ምንም ሳይሆኑ ከጦርነቱ ተርፈው በሰላም ተመለሱ። ለሰሩት ገድልም ንጉሡ አጼ ምኒሊክ የእንጥጮ ወረዳ ግዛትን እንዲያስተዳድሩ በሽልማት መልክ ሰጧቸው። የጥቋቁር ወርቆች ደማቅ ታሪክም በዓለም ሁሉ እየዞረ እጅን በአፍ አስጫነ። ይሄው ዛሬም በኩራት ‘ዓድዋ’ እንላለን። ትላንት፣ ዛሬ፣ ነገም፣ ሁሌም ዓድዋ!!!
ሙሉጌታ ብርሃኑ
አዲስ ዘመን የካቲት 26 ቀን 2015 ዓ.ም