የምሥራቅ አፍሪካ አገራት ለአየር ንብረት ለውጥ በብዙ መንገድ የተጋለጡ ናቸው። ይህ የአደጋ ተጋላጭነታቸው በተለያዩ ወቅቶች ለከፋ የድርቅ አደጋ ዳርጓቸዋል። በአደጋዎቹም ከፍተኛ ለሆኑ ሰብአዊና ቁሳዊ ችግሮች ተዳርገዋል።
አገራቱ ካላቸው ዓለም አቀፍ ስትራቴጂክ ጠቀሜታ አንጻር የብዙዎች ዓይን ማረፊያ ከመሆናቸው በላይ ያለመረጋጋትና የግጭት ምንጭ ናቸው፤ ይህና ሌሎችም ተግዳሮቶች ተደማምረው የደካማ ኢኮኖሚ ባለቤት አድርጓቸዋል፤ አደጋ የመቋቋም አቅማቸውን በእጅጉ ተፈታትኖታል። ዛሬም እየተፈታተነው ይገኛል።
ከዚህ ባለፈ በዓለም አቀፍ ደረጃ እየተከሰተ ያለው የአካባቢ የአየር ብክለት በአግባቡ ካልተያዘ ለአካባቢ አገራት ሕዝቦች «በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ» በመሆን፤ ያልዘሩትን እንዲያጭዱ ተጨማሪ የከፋ እርግማን ሆኖ ሊከሰት እንደሚችል ይጠበቃል።
ይህንንም በተመለከተ በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚጮኹ ድምፆች እየተበራከቱ ቢሆኑም፤ ዓለም አቀፉ ኅብረተሰብ በተለይም የችግሩ ዋነኛ ምክንያት የሆኑት አገራት ለድምጾቹ ጆሮ የመንፈጋቸው እውነታ አገራቱ በቀጣይም በተመሳሳይ አደጋ /በከፋ መልኩ ሰለባ ሊሆኑ እንደሚችሉ አመላካች ነው።
አሁን ላይም ቢሆን ከተከሰተው የአየር ንብረት ለውጥ ጋር በተያያዘ በአምስት ተከታታይ የዝናብ ወቅቶች ዝናብ ባለመጣሉ ምክንያት የአካባቢው አገራት በሆኑት በኢትዮጵያ፣ በኬንያና በሶማሊያ 31.6 ሚሊዮን ሰዎች ለድርቅ አደጋ ተጋላጭ ሆነዋል።
ድርቁ በተለይም በአገራቱ የሚኖሩ የአርብቶ አደር ማኅበረሰቦችን ለረሃብ፤ የሕይወታቸው መሠረት የሆኑ የቤት እንስሳትን ለእልቂት እየዳረገ መሆኑ፤ የማኅበረሰቡን ዛሬን ብቻ ሳይሆን ነገዎቹንም ጭምር ጽልመት እያለበሰው ነው።
በርግጥ የአካባቢው አገራት ያላቸውን ሰፊ የተፈጥሮ እና የሰው ሀብት በአግባቡ ማልማት የሚያስችል የተረጋጋ የፖለቲካ ምህዳር ቢኖራቸው፤ አገራዊ የመልማት አቅማቸው በወቅቱ ብዙ ዋጋ እያስከፈላቸው ያለውን የድርቅ አደጋ ከመታደግ ባለፈ ነገዎቻቸውን ብሩህ ማድረግ የሚያስችል ሁለንተናዊ አቅም እንዳለው ይታመናል።
አገራቱ ቀጣይ ዕጣ ፈንታ የጋራ መሆኑን ተገንዝበው፤ በመካከላቸው ያለውን ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ግንኙነቶች በማጠናከር፤ በመተማመንና በጋራ ተጠቃሚነት ላይ የተመሠረተ ግንኙነት በመፍጠር የመልማት አቅማቸውን ተጨባጭ ማድረግ የሚያስችል ቁርጠኝነት መፍጠር ቢችሉ ለሌሎች የሚተርፉበት ዕድልና አጋጣሚ ሰፊ ነው።
ከተደጋጋሚ የአየርንብረት ለውጥና ከዚህ ከሚመነጭ የድርቅ አደጋ እራሳቸውን ለመታደግ ያላቸው ዋነኛ አማራጭም ድርቅን የሚሸከም አካባቢያዊ /አገራዊ ኢኮኖሚ መገንባት ነው። ለዘለቄታውም ቢሆን ድርቅ በመጣ ቁጥር የዓለም አቀፉ ኅብረተሰብ የልመና አጀንዳ ከመሆን የሚታደጋቸውም ይኸው ነው።
አሁን ያሉበትም ወቅቱ ይህንን እውነታ በተገቢው መንገድ ተገንዝበው፤ ለዜጎቻቸው ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት ራሳቸውን በተሻለ መንገድ የሚያዘጋጁበት፤ ቀደም ባሉት ጊዜያት ይህንን አካባቢያዊ እውነታ መፍጠር እንዳይችሉ ተግዳሮት የሆኑባቸውን ፈተናዎች በአሸናፊነት ለመወጣት ከፍ ባለ ቁርጠኝነት ለመንቀሳቀስ ራሳቸውን የሚያዘጋጁበት ነው።
በተለይም አካባቢውን ከግጭት ነፃ ቀጣና በማድረግ፤ የአካባቢው አገራት ሕዝቦች ለልማት ትኩረት በመስጠት ድርቅና ድርቅን ተከትሎ የሚከሰቱ አደጋዎችን ተቋቁመው መሻገር የሚችሉበትን ኢኮኖሚ እንዲገነቡ የሚያስችሉ አስቻይ ሁኔታዎችን በጋራ መፍጠር ይኖርባቸዋል።
ለዚህ የሚሆኑ የጋራ ፕሮጀክቶችን ከመቅረጽና ወጪን ከመጋራት ጀምሮ፤ የአገራቱን ሕዝቦች በተለያዩ መንገዶች በማስተሳሰር፤ በረጅሙ የግንኙነት ታሪካቸው ይዘዋቸው የመጡትን የጋራ ማኅበራዊ እሴቶች በማጠናከር ከፍ ሊል ለተገባው ቀጣይ ግንኙነታቸው አቅም አድርገው ሊጠቀሙበት ይገባል!
አዲስ ዘመን የካቲት 26 ቀን 2015 ዓ.ም