በአገራችን የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ አገልግሎት እየተስፋፋ ይገኛል።በአሁኑ ወቅት በርካታ አገልግሎቶች በዚሁ ቴክኖሎጂ እየተሰጡ ናቸው።አገልግሎቱ የዘመነ፣ እንግልትን የሚያስቀር፣ ፈጣን፣ ወዘተ. መሆኑ ተመራጭ እንዲሆን እያደረገውም ነው።አንዳንድ ተቋማት የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ አገልግሎትን የግድ እስከማድረግም ደርሰዋል።መንግሥት የዲጂታል ኢኮኖሚን ለመገንባት እየሠራ እንደመሆኑም ቀጣይ አገልግሎቶች በዚሁ መንገድ የሚፈጸሙ እንደሚሆኑ ይጠበቃል፡፡
በዘርፉ ከከፍተኛ ትምህርት ተቋማትና ከመሳሰሉት በርካታ ወጣቶች እየተመረቁ ሲሆን፣ የአገልግሎቱ እየተስፋፋ መምጣት ለእነዚህ ምሩቃንና ሌሎች የዘርፉ ሰልጣኞች የሥራ ዕድሎች እየተፈጠረ ነው።ይህ ብቻም አይደለም በዘርፉ የተመረቁ ወይም የሰለጠኑ ልምዶችን እያካበቱ ሥራ እስከመፍጠር ደርሰዋል፤ በዘርፉ ውጤታማ የሆኑ ሙያተኞች ድርጅቶችን፣ ኩባንያዎችን እስከመክፈት የደረሱበትም ሁኔታ ይታያል።
እኛም በዘርፉ ተሰማራቶ ውጤታማ የሆነውንና ለሌሎችም አርአያ ይሆናል ያልነውን የዘርፉን ባለሙያ የዛሬ የስኬት እንግዳችን አድርገነዋል።እንግዳችን አዲስ አበባ ከተማ ሸራተን ሆቴል ከተሰራበት ስፍራ ፍልውሃ አካባቢ ነው የተወለደው።ያደገውም፣ የተማረውም በዚሁ አካባቢ ነው።ይህ የዛሬው የስኬት እንግዳቸውን አቶ መርእድ በቀለ ይባላል፤ አቶ መርዕድ የአይ ኢ ኔትዎርክ ሶሉሽንስ መስራችና ዋና ሥራ አስፈጻሚ ነው።
አቶ መርዕድ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርቱን፣ ጥበብ መንገድና ጆንኤፍ ኬኔዲ፣ ሁለተኛ ደረጃውን ደግሞ በዳግማዊ ምኒልክ ትምህርት ቤት ነው የተከታተለው።ጎበዝ ከሚባሉት ተማሪዎች መካከል እንደነበር ይናገራል።ከአንደኛ ክፍል ጀምሮ የአንደኝነት ደረጃውን አሳልፎ አልሰጠም።በ12ኛ ክፍል ብሔራዊ መልቀቂያ መፈተናም በሰባት የትምህርት ዓይነቶች ‹ኤ› በማምጣት በስኬት ነው ያጠናቀቀው።‹‹ዶክተር እሆናለሁ፤ ፓይለት እሆናለሁ ወዘተ…›› የልጅነት ምኞቶቹ ነበሩ።
በወቅቱ ባስመዘገበው ከፍተኛ ውጤት የመገናኛ ብዙሃንን ቀልብ ስቦም እንደነበር ጠቅሶ፣ በአንድ ሬዲዮ ጣቢያው ቃለ መጠይቅ ሲያደርግለት ሦስት ነገሮችን የመሆን አማራጭ እንደነበረው መግለጹን ያስታውሳል።‹‹አንደኛ ኤሌክትሪካል ኢንጅነር፣ ሁለተኛ ወደ ሶሻል ሳይንስ ከተሳብኩ ኢኮኖሚስት፤ ሦስተኛው የቲዮሎጂስት ፍላጎት ስላለኝ ቲዮሎጂስት የመሆን ፍላጎት አለኝ›› በማለት የወደፊት ፍላጎቱን በወቅቱ ለጣቢያው ተናግሮ እንደነበር ይገልጻል።
እንግዳችን የመጀመሪያ ምርጫውን አገኘ።በመቀሌ ዩኒቨርሲቲ ተመድቦ የኤሌክትሪካል ኢንጅነሪንግ ትምህርቱን በዚያው ተከታተለ።በመቀሌ ዩኒቨርሲቲ ቆይታው ያገኛቸውንና ፍላጎቱን ለማሳካት ያስቻሉትን የተለያዩ ዕድሎች በአግባቡ እንደተጠቀመባቸው ይናገራል።
በትምህርት ቆይታው ያደረጋቸው ጥረቶች ሁሉ ለዛሬ ስኬቱ እንዳደረሱት ይገልጻል።ዛሬ በኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂው ዘርፍ አንቱ ለመባል በቅቷል።በዘርፉም ብዙ ሙያተኞችን አፍርቷል።
በኤሌክትሪካል ኢንጅነሪንግና እና በኮምፒዩተር ኢንጂነሪንግ የመጀመሪያ ዲግሪውን ከመቀሌ ዩኒቨርሲቲ ያገኘው አቶ መርዕድ፣ በዩኒቨርሲቲው የትምህርት ቆይታው ከተከታተለው ትምህርት አብላጫው ከኮምፒዩተር ሳይንስ ጋር የተያያዘ ስለነበር ውስጣዊ ፍላጎቱ ለሆነው ለኮምፒዩተር ዕውቀት ያደላ እንደነበር ያስታውሳል።
በዩኒቨርሲቲ ቆይታው ወቅትም ዝንባሌው ለኮምፒዩተር ኢንጅነሪንግ ያደላ ነበር።የሦስተኛ ዓመት ተማሪ በነበረበት ወቅት ከጓደኞቹ ጋር የአይ ሲቲ ክለብ በማቋቋም የክለቡ ፕሬዚዳንት ሆኖ አገልግሏል።በሚያስመዘግበው የላቀ ውጤት እንዲሁም ለዘርፉ ባለው ውስጣዊ ፍላጎት የተነሳ ለዩኒቨርሲቲው አገልግሎት ለመስጠት እንዲሁም ለዘርፉ ያለውን ፍላጎትና እምቅ ችሎታ አውጥቶ እንዲጠቀም ዕድል ሰጥቶታል፡፡
በዩኒቨርሲቲው ኔትዎርክ ላይ የመሥራትና የማስተማር ዕድልም አግኝቶ ነበር።በክረምት ወቅትም እንዲሁ የልምምድ ጊዜውን ያሳለፈው በአዲስ አበባ ከተማ ውስጥ የኔትዎርክ ሥራ በሚሠራ መስሪያ ቤት ነው።ይህም ገና ተማሪ እያለ በኔትዎርክ ሥራ ዓለም አቀፍ የምስክር ወረቀት እንዲያገኝ አስችሎታል።እነዚህ መልካም አጋጣሚዎች ተደማምረው በኔትዎርክ ኢንጅነሪንግ ዘርፍ እንዲሰማራና አሁን የደረሰበት ደረጃ እንዲደርስ አግዘውታል፡፡
ከመቀሌ ዩኒቨርሲቲ በጥሩ ውጤት ያጠናቀቀውና ጥሩ የሥራ ልምድንም ያካበተው አቶ መርዕድ፤ በዩኒቨርሲቲው የላቀ ውጤት ካስመዘገቡ አራት ተማሪዎች መካከል አንዱ በመሆኑ በዩኒቨርሲቲው የመቅረት ዕድልም ገጥሞት ነበር።ይሁንና የቴክኖሎጂ ኢንዱስትሪውን የመቀላቀል ከፍተኛ ፍላጎት የነበረው በመሆኑ በተመረቀ ማግስት የኔትዎርክ ኢንጂነር ሆኖ ልምምድ ሲያደርግበት ለነበረው ተቋም ተቀጥሮ ለአንድ ዓመት አገልግሏል።
በዘርፉ አዳዲስ ዕውቀቶችን መጨመር የሚያስችለውን ዓለም አቀፍ ስልጠና ለማግኘት ፍላጎት የነበረው አቶ መርዕድ፤ ለዚህም ምቹና አስተማማኝ መንገድ የመንግሥት መሥሪያ ቤት መሆኑን በማመን ይሠራበት ከነበረው የግል ድርጅት ደመወዝ ቀንሶ ወደ መንግሥት ተቋም አምርቷል።ቀደም ባለው ጊዜ አይ ሲቲ ዴቨሎፕመንት ኤጀንሲ ይባል የነበረው፤ በአሁኑ ወቅት ኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር መስሪያ ቤት የመንግሥትን የዳታ ሴንተር በማልማት ከፍተኛ የኔትዎርክ ባለሙያ በመሆን አገልግሏል።
በመንግሥት መስሪያ ቤት ከአንድ ዓመት አገልግሎት በኋላ በዘርፉ የሚሰጠውን ስልጠና እንግሊዝ አገር ሄዶ የመሰልጠን ዕድል አግኝቷል።በመርፌ ቀዳዳ የመሽሎክ ያህል ጠባብ የሆነውን ዕድል ውጤታማ ሆኖ በማለፍ ነው ስልጠናውን ያገኘው፡፡
እጅግ ፈታኝና ጠባብ ዕድል የነበረውን ስልጠና ለማግኘት ፈተናውን በጃፓን አገር መውስድ የግድ ነበርና ወስዷል።ፈተናውን ከሚወስዱ ሰዎች መካከልም የሚያልፉት ሦስት በመቶ ያህሉ ብቻ ቢሆኑም፣ አቶ መርዕድ ግን ጥሩ ውጤት በማምጣት ፈተናውን ማለፍና ዓለም አቀፍ ስልጠናውን ከእንግሊዝ አገር ማግኘትና በዚህም ብቸኛው ኢትዮጵያዊ መሆን ችሏል።
ከመንግሥት አገኘዋለሁ ብሎ የተማመነውን የስልጠና ዕድል ማግኘት የቻለው አቶ መርዕድ፤ ሙሉ ወጪውን መንግሥት ሸፍኖለት ነው የሰለጠነው።መንግሥትም ወጪውን ሸፍኖ ማስተማሩ ተመልሶ አገሩን በማገልገል እንዲክሰው በሚል ነው።ያም ባይሆን በአገሩ የመሥራት ቀና ልብ ያለው በመሆኑ፤ በገባው ቃል መሠረት ወደ ኢትዮጵያ ተመልሷል።በተለያዩ የዓለም አገራት ከፍተኛ ተከፋይ ሆኖ መሥራት የሚያስችለውን የምስክር ወረቀት ያገኘው ብቸኛው ኢትዮጵያዊ ቢሆንም፣ ህልሙ በቴክኖሎጂው ዘርፍ አገሩን ወደ ላቀ ደረጃ ማሻገር በመሆኑ በአገሩ በዘርፉ ተሰማርቶ ትውልድ እያፈራ ይገኛል።
ከውጭ አገር ትምህርት ሲመለስ ኢትዮ ቴሌኮም ትልቅ የኔትዎርክ ማስፋፊያ ሥራ እየሠራ ነበር።አቶ መርዕድም በያዘው ከፍተኛ የምስክር ወረቀት ምክንያት ኢትዮ ቴሌኮምን ተቀላቀለ።በዚሁ አጋጣሚም ዕድለኛ በመሆን ዓለም አቀፍ ተከፋይ መሆን ቻለ፡፡
ከኢትዮ ቴሌኮም መደበኛ ሥራው በተጨማሪም ሞያዊ ዕውቀቱንና አገልግሎቱን የሚፈልጉ በርካታ ተቋማት እንደነበሩ የሚያስታውሰው አቶ መርዕድ፤ በተለይም ኢሚግሬሽን፣ ባንኮችና የተለያዩ ተቋማት አገልግሎቱን በስፋት ይጠቀሙ ነበር።የአገልግሎቱ ተጠቃሚዎች ቁጥራቸው ሲበራከት በኢኮኖሚ እየደረጀ መጣ።ይህም የኢኮኖሚ ነፃነት እንዲያገኝ በር የከፈተለት ከመሆኑም በላይ በተጨማሪ የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ኩባንያ መገንባት አስችሎታል፡፡
‹‹በዘርፉ ያካበትኩት ሞያዊ ክህሎት ወደ ቢዝነሱ እንድገባ መንገድ ጠርጎልኛል›› የሚለው አቶ መርዕድ፤ የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ኩባንያውን አስቦና አቅዶ እንደ አንድ የቢዝነስ ዘርፍ የገባበት አለመሆኑን አጫውቶኛል።ከኢትዮ ቴሌኮም ሥራ በተጨማሪ በቤት ውስጥ በግሉ ይሠራ የነበረውን ሥራ የሙሉ ጊዜ ሥራው ያደረገውም የኢትዮ ቴሌኮም ፕሮጀክት ሲጠናቀቅ እንደሆነ ያስታውሳል፤ በ2011 ዓ.ም ቢሮ ተከራይቶ አምስትና ስድስት ሠራተኞችን በመያዝ ነው ኩባንያውን ያቋቋመው፡፡
ሥራ ስለበዛበት ብቻ ኩባንያ ያቋቋመው አቶ መርዕድ፤ ኩባንያውን ለመምራት ደግሞ አሜሪካን አገር በሚገኝ አንድ ዩኒቨርሲቲ በኦን ላይን የቢዝነስ አድሚኒስትሬሽን ትምህርትን ተምሯል።ይህን ጊዜ ከኢንጅነሪንግ ውጪ የሆነውን የአስተዳደር ሙያን በመማር የአስተዳደር ሥራ ምን እንደሚመስል በመረዳት ኩባንያውን መምራት ችሏል።በዚሁ ሂደት ውስጥም ባለቤቱ የላቀ ድርሻ የነበራት መሆኑንም አጫውቶናል፡፡
የተማረውንና ያነበበውን ሁሉ ወደ ተግባር የመቀየርና የመሞከር ልምድ ያለው አቶ መርዕድ፤ የተማረውን በሠራተኞቹና በኩባንያው ላይ ተግባራዊ በማድረግ ውጤታማ መሆን ችሏል።ዕለት ዕለት በሚያደርገው ያላሰለሰ ጥረትም ኩባንያ እያደገና እየተደራጀ ሄዷል።ከአምስት ሠራተኞች አስር፣ ሃያ፣ ሰላሳ፣ አርባና ሃምሳ እያለ ተቋሙ በራሱ መቆም የጀመረው ‹‹አይ ኢ ኔትዎርክ ሶሉሽንስ›› ተቋማዊ ሥርዓት በመገንባት ሥራን በጥራትና በፍጥነት የሚሠራና የጀመረውን የሚጨርስ ስመ ጥርና ደንበኞች የሚተማመኑበት ኩባንያ መሆን ችሏል።
ሁሉም ነገር ወደ ቴክኖሎጂ እየተቀየረ በመጣበት ወቅት ወደ ሥራው መግባት የቻለው አቶ መርዕድ፤ ቴክኖሎጂ በአገር ውስጥ ያመጣውን ለውጥ ተሳታፊ በመሆን የማየት ዕድል ያጋጠመው የመጀመሪያው ሰው መሆኑን ይናገራል።አገሪቷ ቴክኖሎጂን በስፋት መጠቀም የጀመረችበት ወቅት እንደመሆኑ የአፍሪካ ህብረትን ጨምሮ ለኢትዮጵያ አየር መንገድ፣ ባንኮች፣ ዩኒቨርሲቲዎችና በሌሎችም ትላልቅ ተቋማት ውስጥ የቴክኖሎጂ ውጤቶችን ተደራሽ በማድረግ ‹‹አይ ኢ ኔትዎርክ ሶሉሽንስ›› አሻራውን ማኖር ችሏል።
ቴክኖሎጂው ገና እየተስፋፋ በመሆኑ በዘርፉ የሥራ ልምድ ያለው ሰው ገበያው ላይ ለማግኘት እንደሚቸግር የገለጸው አቶ መርዕድ፤ የሚቀጥራቸው አብዛኞቹ ሠራተኞችም ልምድ የሌላቸውና ሰልጥነው የሚሠሩ መሆናቸውን ያመለክታል።
በ‹‹አይ ኢ ኔትዎርክ ሶሉሽንስ›› ሰፊ ቁጥር ያላቸው ሠራተኞች የሥራ ልምድ የሌላቸው በመሆናቸው የተቋሙን የሥራ ባህል በቀላሉ የመለማመድ ዕድል ያገኛሉ።ተቋሙ የሚከተለው የሥራ ባህልም የአሜሪካ አገር የሥራ ባህል መሆኑን ጠቅሶ፣ ለአብነትም ጠዋት አንድ ሰዓት ተኩል ላይ ሥራ ይጀምራሉ፤ ዕለት ተዕለትም ማን ምን እንደሚሠራ በግልጽ ይታወቃል ውጤቱም የሚታይ ይሆናል ሲል ያብራራል።
በአሁኑ ወቅትም 165 ለሚደርሱ ሠራተኞች የሥራ ዕድል መፍጠር የቻለው ‹‹አይ ኢ ኔትዎርክ ሶሉሽንስ›› እያንዳንዱ ሠራተኛ በየዕለቱ በሚያስመዘግበው ውጤት ተለክቶ ተጨማሪ ተከፋይ ይሆናል።ይህም የበለጠ ለመሥራትና ሠራተኛው ለሥራ የሚኖረውን ትጋት የሚጨምርለት ይሆናል።ይህንን የሥራ ባህል ከትምህርት ቤት የሚወጡ አዳዲስ ሠራተኞች በቀላሉ ተግባራዊ ማድረግ እንደሚችሉ አቶ መርዕድ አጫውቶናል፡፡
የ‹‹አይ ኢ ኔትዎርክ ሶሉሽንስ›› እሴትና ተልዕኮው የአፍሪካን ሕይወት በጥሩ የሥራ ሥነምግባርና በሥርዓት አስተሳስሮ መቀየር የሚል እንደሆነ የሚናገረው አቶ መርዕድ፤ በዚህ ውስጥ ሁለት ዋና ዋና ነጥቦች ስለመኖራቸው ይገልፃል።አንደኛው ሥነሥርዓትን የተከተለ የሥራ ባህልን መፍጠር ሲሆን ሁለተኛው ጠንካራ ሥርዓት መዘርጋት የሚል ነው።እነዚህን ሁለት ጉዳዮች ተግባራዊ ማድረግ ከተቻለ የአፍሪካን ሕይወት መቀየር ይችላል የሚል ዕምነት አለው።ወደ ተቋሙ የሚገቡ ሠራተኞችም በዚሁ መንገድ መቃኘት እንዲችሉ ስልጠና የሚሰጣቸው ይሆናል።
‹‹በአስተዳደጌ ውስጥ ትልቅ ድርሻ ካላቸው ቤተሰቦቼ በተጨማሪ በጎ ምግባርን ተግባራዊ ማድረግ እንድችል በሰንበት ትምህርት ቤት የነበረኝ ቆይታም አግዞኛል›› የሚለው አቶ መርዕድ፤ ለሠራተኞቹ አርአያ በመሆን ከሠራተኞቹ እኩል እንደሚሠራና በሥራውም ተመራጭና ቀዳሚ ለመሆንና ይህን ጠንካራ የሥራ ባህል ለሌሎችም ለማስተላለፍ አብዝቶ ይተጋል።
ማህበራዊ ኃላፊነትን በመወጣት ረገድም ለወጣቶች ነፃ ስልጠና ይሰጣል።ሥልጠናውን ካገኙት መካከልም ገሚሶቹን በድርጅቱ የሚቀጥራቸው ሲሆን ሌሎቹም ስልጠናውን አግኝተው በተለያየ ቦታ የመቀጠር ዕድል ይኖራቸዋል።ከተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች ጋርም በጋራ በመሥራት ለተማሪዎች ስልጠና ይሰጣል።ለአብነትም በሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ለሴት ተማሪዎች ስልጠና ሰጥቷል፤ የሕይወት ልምዱን አካፍሏል።
‹‹አይ ኢ ኔትዎርክ ሶሉሽንስ›› ከመቋቋሙ አስቀድሞ በዘርፉ የተሰማሩ አገር በቀል ተቋማት ባለመኖራቸው ከኬንያ፣ ከሕንድና ከተለያዩ አገራት ዶላር ተከፍሏቸው ይመጡ እንደነበር ያነሳው አቶ መርዕድ፤ ለዚህም በመቶ ሺዎች ዶላር ይወጣ ነበር ብሏል።በአሁኑ ወቅት የእሱ ኩባንያ ሰፊ አገልግሎት እየሰጠ በመሆኑ ለዘርፉ ይወጣ የነበረውን ዶላር በማስቀረት የድርሻውን መወጣት ችሏል።
ይህ ብቻ አይደለም።ኬንያ በመሄድ አገልግሎት በመስጠት ዶላር ማምጣት የምንችልበት ደረጃ ላይ ደርሰናል ይላል።በ14 ዓመታት ጊዜ ውስጥ ከመቶ በላይ የሚደርሱ ፕሮጀክቶችን ማጠናቀቅ የቻለው ‹‹አይ ኢ ኔትዎርክ ሶሉሽንስ››፣ ሥነምግባር ያላቸው ሠራተኞችን እንዲሁም ጥሩ የሥራ ባህልንና የሥራ አካባቢን መፍጠር እንደቻለም አስታውቋል።
‹‹ትልቅ ነገርን ማሰብና መመኘት፤ ግን ደግሞ በትንሹ መጀመር›› የሚል ዕምነት ያለው አቶ መርዕድ፤ ትልቅ ራዕይ ሰንቆ በየዕለቱ ትንሽ ትንሽ በመሥራት ካሰበበት መድረስ እንደቻለም አጫውቶናል።በቀጣይም ‹‹አይ ኢ ኔትዎርክ ሶሉሽንስ›› ከአገር ውስጥ ባለፈ ኢትዮጵያን ሊያስጠራ የሚችል ጠንካራ ተቋም እንደሚሆን ያለውን ዕምነት ገልጿል።
አቶ መርዕድ በቀለ
‹‹አንደኛ ኤሌክትሪካል ኢንጅነር፣ ሁለተኛ ወደ ሶሻል ሳይንስ ከተሳብኩ ኢኮኖሚስት፤ ሦስተኛው የቲዮሎጂስት ፍላጎት ስላለኝ ቲዮሎጂስት የመሆን ፍላጎት አለኝ
አዲስ ዘመን የካቲት 25 ቀን 2015 ዓ.ም