አንዳንዴ የሆነበትን ሁሉ ሲያስብ ከልብ ይከፋል ። ትናንት ሕይወትና ኑሮው እንዲህ አልነበረም ። ደስተኛና ብርቱ ነበር ። እንዳዛሬው በርካቶች ሳያገሉት፣ ሳያርቁት በፊት ቤተሰቦቹ፣ ወላጆቹ ሲኮሩበት ቆይተዋል ። እሱም ቢሆን ለእነሱ ፈጥኖ ደራሽ ነው ። እጁን አያጥፍም፤ ኪሱን አይሰስትም ። ቀድሞ የሚለው የሚናገረው ሁሉ ይሰማል ። ሀሳቡን የሚያከብሩ፣ ቃሉን የሚፈጽሙ ጥቂት አልነበሩም ።
ዛሬ ላይ ግን የነበረው እንደ ትናንቱ አልሆነም ። ተሰሚነቱ ጠፍቷል፣ ክብሩ ከእሱ ሄዷል ። ለዚህ ደግሞ ምክንያቱን አሳምሮ ያውቀዋል ። ወላጆቹን ጨምሮ ብዘዎች ፊት ያዞሩበት ጉዳይ በአንድ ልጁ ምክንያት ነው ። ይህን ሲያስብ ይበልጥ ይከፋል ። ለሆነበት፣ ለተደረገበት ሁሉ ራሱን ደጋግሞ ይጠይቃል፣ ውስጡን ያስጨንቃል ። መልስ ሲያጣ ምላሹ የተለመደ ነው ። ኀዘን ብስጭት አያጣውም ። ብቸኝነት፣ ባይተዋርነት ይከበዋል ።
ደጀን ደምስ ትውልድና ዕድገቱ ምዕራብ ጎጃም ዞን ደጋዳሞት ላይ ነው ። ዕድሜው ከፍ ሲል ከአካባቢው ርቆ የራሱን ሕይወት ጀመረ ። እንዲያም ሆኖ ወላጆቹን አልረሳም ። ጠንካራ ገበሬ ነውና በላቡ ወዝ ካገኘው በረከት ‹‹እነሆኝ›› ማለትን ለምዷል ።
ደጀን ትውልድ መንደሩን ትቶ ዓመታትን የዘለቀው ‹‹መተከል›› ከሚባል ቦታ ነበር ። አካባቢው ከእሱ ቢስማማ ጉልበቱን ከፍሎ ሌት ተቀን መትጋት ያዘ። የልፋቱን አላጣም ። የራሱ ጥሪት ኖረው፣ የአቅሙን ገንዘብ ቋጠረ ። በየጊዜው ወላጆቹን እየረዳ የሚቸረው ምርቃት በረከት ሆነለት ።
ጥቂት ቆይቶ ለፍቶ ያገኘበት፣ ሠርቶ የከበረበት፣ አካባቢ የሰላም እጦት ገጠመው ። ስፍራው የጦርነት አየር ነገሰበት ። በርካቶች ክቡር ሕይወታቸውን አጡ። ብዘዎች ቤት ንብረታቸው ወደመ ። እሱን ጨምሮ ሌሎች ደግሞ አካባቢውን ጥለው ሊሸሹ ግድ ሆነ ።
ደጀን ተመልሶ ትውልድ አገሩ ገባ ። ብቻውን አልነበረም ። ሚስቱና ከተወለደ ቀናት ያስቆጠረ ጨቅላ ልጁ አብረውት ናቸው ። አሁን እንደቀድሞው ከእጁ የሚያልፍ፣ ለሌሎች የሚተርፍ ጎበዝ አይደለም ። ጥሪት ሀብቱ የነጠፈበት፣ ቤት ንብረቱን ያጣ ተፈናቃይ ነው። ደጀንን ያገኙት ሁሉ እንደቀድሞው አልሆኑለትም። አቀባበላቸው ቀንሷል ። ፈገግታቸው ደብዝዟል። እንዲህ መሆኑ አባወራውን አስከፍቷል ። በተለይ ወላጆቹ ፊት አልሰጡትም ። የትናንት መልካምነቱን ዘንግተው በየምክንያቱ ያስቀይሙት ይዘዋል ።
ለዚህ ሰበቡ የአንድ ልጁ መታመም ነውና ደ ጀን ከ ልቡ አ ዝኗል ። ልጁ ከተወለደ ጀምሮ ጤና ኖሮት አያውቅም። አንድ ዓመት ቢሞላውም እናት አባቱን አይለይም፣ እንደ ዕድሜው በወጉ አያይም፣ እንቅስቃሴው የዘገየ ፣ ችግሩ የሰፋ ሆኗል ። ያለበት ዕድሜ ‹‹ዳዴ.›› የሚልበት፣ መውደቅ መነሳትን የሚያውቅበት ነው ። እሱ ግን ከአልጋና ከእናቱ ትከሻ አልወረደም ።
አባት የልጁ ሁኔታ ቢያሳስበው ከቀናት በአንዱ ከሆስፒታል ይዞት ሄደ ። ሀኪሞች የሕፃኑ ችግር በእርግዝና ጊዜ በጭንቅላት ውስጥ የሚከሰት ችግር መሆኑን አስረዱት ።
አባት ስለጉዳዩ ማብራሪያ ጠየቀ ። ህመሙ ጽንሱ በእናት ሆድ ሳለ በጭንላት ላይ የሚከሰትና በሕክምና ስያሜው ‹‹ሀይድሮ ሴፋለስ›› ተብሎ እንደሚጠራ ተነገረው ። ይህ ችግር ነፍሰጡር ሴት የፎሊክ አሲድን በአግባቡ ባለመውሰዷ ጋር የሚከሰት መሆኑን ተረዳ ።
ደጀን የልጁን ዕጣ ፈንታ እያሰበ ስለመፍትሄው ተጨነቀ ። ባለው ጊዜና አቅም ተጠቅሞ ልጁን ለማሳካም ሮጠ ። ሕክምናው የትኛውም ጤና ተቋም አይገኝም ። ቀዶ ሕክምና የሚያሻው፣ ክትትል የሚያስፈልገው ነው ። ምርጫ አልነበረውም ። ራሱን አበርትቶ ያለውን ቋጥሮ አዲስአበባ ከአንድ ሆስፒታል ደረሰ ። ሆስፒታሉ ለልጁ አልጋ ሰጥቶ ሕክምናው ተጀመረ ። ሕፃኑ አፋጣኝ ቀዶ ሕክምና ተደረገለት ። በጭንቅላቱ ‹‹ሸንት›› የተባለው መሣሪያ ገብቶም ወደቤቱ ተመለሰ ።
ጉዳዩ በቤተሰቡና በአካባቢው እንደታወቀ አባት ደጀን ሌላ ፈተና ገጠመው ። የልጁ ሕመም ወደሌሎች እንደሚተላለፍ ታስቦ መገለል ይደረግበት ያዘ ። ቤተሰቦቹ ልጃቸውን ከመርዳት ይልቅ ሊቀበሉት ከበዳቸው ። ትናንት ስለእሱ የነበራቸውን አክብሮት ሲያስታውስ በድርጊታቸው አዘነ ። አሁን ለራሱ ቤተሰብ እንኳን የሚተርፍ አቅም የለውም ። እንደቀድሞው የእጁን ሊሰጥ ያለውን ሁሉ ሊያበረክት አይችልም ። ዛሬ የእርዳታ ስንዴ የሚሰፈርለት፣ የእርዳታ እጆችን የሚያይ ተፈናቃይ ነው ።
ደጀን ቤተሰቦቹን ጨምሮ ለአካባቢው ነዋሪ ስለ ልጁ ችግር ሊያስረዳ ሞከረ ። ሕመሙ ለሌሎች ጤና እንደማያሰጋ ዘርዝሮ ሊያሳምን ጣረ ። ቀላል አልሆነለትም ። የሰሙት ሁሉ ፊት አዞሩበት ። ዝም አላለም ። በአካባቢው እንደሱ ልጅ ተመሳሳይ ችግር ያለባቸው ሕፃናት መኖራቸውን አውቋል ። ወላጆቻቸው ከእይታ ደብቀው ቤት ዘግተውባቸዋል ። እሱ ሕመማቸው ሕክምና እንደሚያግዘው ያውቃልና ሊረዳቸው ይፈልጋል ።
ሁሉም ይህን ሊያደርጉ አይፈቅዱም ። አብዛኞቹ የፍላጎትና የአቅም ማጣት ችግር አለባቸው ። ደጀን የአንድ ዓመት ልጁን አዲስ አበባ ወስዶ ለማሳከም ብዙ ዋጋ ከፍሏል ። በሥራ ማጣትና በችግር እየተፈተነ ለልጁ መኖር ብዙ ታግሏል ። እንደእሱ ይህን ሊያደርጉ የሞከሩ አለመኖራቸውን ሲያስብ ግን ልቡ ያዝናል ።
እናቶች በእርግዝና ጊዜ ማድረግ ስላለባቸው ጥንቃቄ ከእሱ በላይ አስረጂና እማኝ የለም ። አባወራው በልጁ የደረሰው ችግር በሌሎች ወላጆች እንዲደርስ አይሻም። የሚሰማው ቢያገኝ የራሱንና የባለቤቱን ተሞክሮ ለሁሉም ማጋራት ይፈልጋል። ብዙዎቹ ግን እውነታውን መቀበል ይከብዳቸዋል። ችግሩን ከእርግማን አያይዘው ‹‹የእግዜር ቁጣ›› መሆኑን ያምናሉ ።
ደጀን በጤናው ዘርፍ ስለፎሊክ አሲድ አስፈላጊነት ብዙ እንዳልተሠራ ይሰማዋል ። በተለይ ለገጠሯ ሴት በወጉ ግንዛቤው ሊደርስ ይገባል ባይ ነው ። በተቻለ አቅም ይህ ንጥረ ነገር በምግብ፣ በጤፍና በጨው ውስጥ መጨመር ቢችል በርካቶችን መታደግ እንደሚቻል ግንዛቤ ወስዷል ።
በተሳሳተና ባልተገባ ግንዛቤ ደጀንና ባለቤቱን የመሰሉ ወላጆች እንግልትና የበዛ መገለል እያጋጠማቸው ነው ። እንዲህ መሆኑ ሕይወትን በወጉ መርቶ፣ ቤተሰብን በነፃነት ለማሳደር እንቅፋት ይሆናል ።
ከአባት ደጀን ጋር የነበረኝን ቆይታ ጨርሼ ከሌላው አባወራ ወግ ይዣለሁ ። አቶ ጌቱ ዘሪሁን ይባላል ። የወልቂጤ ነዋሪ ነው ። ጌቱ ከአራት ዓመት በፊት የመጀመሪያ ወንድ ልጁን አግኝቷል ። የዛኔ እጅግ ደስተኛ ወላጅ ነበር ። በወቅቱ እንደአባት ለልጁ የሚፈልገውን አሟልቶ ለማሳደግ ሲጥር ቆይቷል ።
በቅርቡ ሁለተኛውን ልጁን ሲታቀፍም ደስታው ከቀድሞ የተለየ አልነበረም ። ሕፃኑ ሁለተኛ ወሩን እንደያዘ ግን የነበረው ስሜት ተቀየረ ። የልጁ ጤና ማጣት ሳቅ ፈገግታውን ነጠቀው ። ሐሳብ ዓላማውን አደበዘዘው ። ጌቱ ልጁን ለማሳየት ጤና ጣቢያ ደረሰ። ከምርመራ በኋላ የሕክምና ባለሙያዎቹ ውጤቱን ነግረው ለከፍተኛ ሕክምና ወደ አዲስ አበባ ጻፉለት የሕፃኑ ችግር በጭንቅላቱ ውስጥ የተፈጠረ የነርቭ ዘንግ ክፍተት መሆኑን ከሄደበት ሆስፒታል አረጋገጠ ።
ከአካባቢው ርቆ ለመጣው አባወራ ይህን መስማት በእጅጉ ይከብዳል ። አሁን የሕመሙን ስሜት ለይቶ የማይነግረው ጨቅላ ሁኔታ እያሳሰበው ነው ። የሰው አገር ሰው ቢሆንም ልጁን ማትረፍ ግድ ይለዋል ። ጌቱ ባለቤቱ በሆስፒታል ክትትል መውለዷን ያውቃል ። ልጁ በተወለደ የመጀመሪያዎቹ ጊዜያትም ምንም የተለየ ምልክት እንዳልነበረው እርግጠኛ ነው ። አሁን ግን ለትንሹ ልጅ ተከታታይ ሕክምና እንደሚያስፈልግ እየተነገረው ነው ።
አባት ጌቱ ልጁን ይዞ በሆስፒታሉ ሕክምናውን ጀመረ ። የሁለት ወሩ ጨቅላ የመጀመሪያው ቀዶ ሕክምና ተደረገለት ። አባወራው ከቤቱ ርቆ ከሆስፒታል አልጋ ይዞ ልጁን እያስታመመ ነው ። በዚህ ስፍራ የሰው ዓይን ይርባል፣ ጠያቂ ዘመድ ይናፍቃል ። እንዳሰበው አልሆነም።
ጌቱ በልጁ ሕመም የቤተሰቦቹን ድርጊት ታዝቧል። በወቅቱ ወላጆቹን ጨምሮ የቅርብ የሚላቸው ሰዎች ያደረባቸው ስሜት የተለየ ነው ። ለሕክምናው አዲስ አበባ በቆየባቸው ጊዜያት የት ወደቅህ? ምን ደረስክ? ያለው የለም ። ቢጨንቀው ራሱ እየደወለ ያለበትን ሁኔታ ይናገር ጀመር ። የተለየ ነገር አላገኘም። ማንም ስለእሱና ስለሚስቱ ፣ ስለሕፃኑ ደህንነት ግድ አልሰጠውም ። በእሱ ግምት እንዲህ መሆኑ ሁሉም በሕፃኑ ላይ ያደረባቸው ተስፋ መቁረጥ ነው ።
ጌቱ እንደሚለው የእሱ ልጅ ማለት ለቤተሰቦቹ እንደተለየ ፍጡር ሆኗል ። ነገ እንደሌሎች ለራሱ የሚበጅ፣ ለአገርም የሚጠቅም አይደለም ። ይህ ዓይነቱ እውነት ለአባት ጌቱ በእጅጉ ይከብዳል ። ገና ከአሁኑ በልጁ እየደረሰበት ያለው መገለል አሳዝኖታል ። እሱ ለሕፃኑ ሕይወት መሮጡ ነገውን በማሰብና ተስፋ በማድረግ ነው ።
የመጀመሪያ ልጁ አሁን አራት ዓመት ሆኖታል። ሲወለድ ጀምሮ አንዳች የጤና ችግር የለውም ። አባት ትንሹ ልጅ የገጠመውን ሕመም በሕክምና እስኪያውቀው የውስጡን ጥያቄ ለመመለስ ቸግሮት ነበር ። ይህ እውነት ከኅብረተሰቡ አመለካከት ተዳምሮም ሲያስጨንቀው፣ ሲያስተክዘው ቆይቷል። አሁን ግን ሕመሙን አውቆ በቂ ግንዛቤ ወስዷል ። የሕፃኑ ችግር በሕክምና አጠራሩ ‹‹ሀይድሮሴፋለስ›› በሚል ይታወቃል ። ሕመሙ በጭንቅላት ውስጥ ያለ የፈሳሽ መጠን መጨመር ሲሆን በአብዛኛው በእርግዝና የመጀመሪያዎቹ ጊዜያት በጽንሱ ላይ የሚከሰት ችግር ነው ።
ጌቱ ይህን እውነት ያወቀው እንደሌሎች ወላጆች አስቀድሞ ሳይሆን ከልጁ መወለድ ሁለት ወራት በኋላ ነበር። አባት የመጀመሪያ ልጁ ፍጹም ጤነኛ ነውና ስለምን ብሎ መጨነቅ፣ መጠየቁ አልቀረም ። ለልጁ ሕክምናውን ለመጀመርም ከቦታው ርቆ አዲስ አበባ መምጣት ግድ ይለዋል ። ይህ ሁሉ ለእሱና ለባለቤቱ ቀላል አልሆነም ።
አባወራው ያለዘመድ እገዛ፣ ያለቤተሰብ ‹‹አይዞህ›› ባይነትግራ በገባው ጊዜ ከጎኑ የቆመለትን አጋር አይረሳም። ‹‹ሆፕ ኢሲቤኤች›› የተሰኘ ድርጅት ነው። ድርጅቱ ከጭንቅላት ፈሳሽ መጨመርና ከአከርካሪ ህብለሰርሰር ችግሮች ጋር በሚወለዱ ሕፃናት ላይ የሚሠራ ብቸኛ ተቋም ነው ።
ይህ ተቋም እንደ አባት ደጀን እንደ ጌቱና መሰል ወላጆችን ችግር በማቃለል ይታወቃል ። ድርጅቱ የተመሠረተው በሕመሙ ተጠቂ በሆኑ ሕፃናት ወላጆችና ቤተሰቦቻቸው ነው ። ከተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች ለቀዶ ሕክምና የሚመጡ ሕፃናትና ቤተሰቦቻቸውን ተቀብሎ በማቆያዎች በማስተናገድ ችግሮቻቸውን ይቀርፋል ።
ድርጅቱ ከሕመሙ ጋር የተወለዱ ሕፃናትን ለመንከባከብ የሚያስችሉ ስልጠናዎችን በመስጠት በችግሩ ዙሪያ ግንዛቤዎችን ያስጨብጣል ። ተቋሙ በቀዶ ጥገና ወቅት የሚያስፈልገውን ‹‹ሸንት›› የተባለ የጭንቅላት ውስጥ አቅርቦት በማሟላትም የበርካታ ሕፃናትን ሕይወት በመታደግ ላይ ይገኛል።
ዛሬ ጌቱ ቀድሞ በአዕምሮው ሲመላለስ ለቆየው ጥያቄ ምላሹን አግኝቷል ። አሁን እናቶች ከእርግዝና በፊትና በኋላ ‹‹ፎሊክ አሲድ››ን በመጠቀም ችግሩን ማምለጥ እንደሚችሉ ያውቃል ። ይህ እውነት በባለቤቱና መሰል እናቶች ዳግም እንዳይከሰት ይጠነቀቃል ። ሌሎችም ከዚህ አጋጣሚ መማር እንዳለባቸው አይጠፋውም ። ችግሩ ‹‹በእኛ ይብቃ›› ለማለት ግን ግንዛቤው በስፋት ሊኖር ይገባል ባይ ነው ።
አባት ጌቱ አሁን የሕፃናቱ ችግር በሕክምና ከታገዘ መፍትሄ እንዳለው ተገንዝቧል ። ዛሬ ስለ ልጁ ያልተገባ ስሜት ላላቸው ሰዎች ሁሉ የሚሰጠውን ምላሽ ያውቃል። በአካባቢው እንደ እሱ ልጅ ተመሳሳይ ሕመም ያለባቸውን ሕፃናት ወደ ሕክምና በማምጣት የግንዛቤ ለውጥ መፍጠር እንደሚያሻም እየገባው ነው።
ከተለያዩ ቦታዎች በአንድ የተገናኙት ሁለቱ አባቶች ውስጣዊ ብሶት ተመሳሳይ ነው ። ሁለቱም በቤተሰቦቻቸውና በማህበረሰቡ መገለል አግኝቷቸዋል ። ልጆቻቸውን ከሕክምናው እስኪያደርሱም መንገዳቸው ገደል ነበር ።
አሁን የሁለቱም አባቶች አስተሳሰብ በአንድ ተጋምዷል ። ችግርን በመጋፈጥ እንጂ የችግሩን ሰለባዎችና ቤተሰቦቻቸውን በማግለል መፍትሄ እንደማይኖር አውቀዋል ። ይህ እውነት በራሳቸው ሆኖ አይተውታልና ችግሩን ተጋፍጦ ችግር ለመፍታት ግንባር ቀደም ሊሆኑ ዝግጁ ናቸው ። የቆሙት ዛሬ ላይ ነውና ብሶታቸውን የሚቀርፍ፣ ለድካማቸው የሚደርስ ጠንካራ ክንድ፣ አጋር መከታ ይሻሉ ። አሁን! ዛሬ ላይ ።
መልካምሥራ አፈወርቅ
አዲስ ዘመን የካቲት 25 ቀን 2015 ዓ.ም