ኢትዮጵያን በዓለም መድረክ በሰፊው ካስተዋወቁ ክስተቶች መካከል አንዱና ዋነኛው የአድዋ ድል ነው። የአድዋ ድል ከዚህም ያለፈ ታላቅ ፋይዳ አለው። የጥቁር ህዝቦች የነፃነት ቀንዲል በሚልም ይጠራል። ድሉ ለነጻነታቸው የታገሉ ጥቁር ህዝቦች ነፃነታቸውን እውን ማድረግ እንዲችሉ ተነሳሽነት ፈጥሮላቸዋል። ለጥቁር ህዝቦች ሁሉ መኩሪያና መመኪያ የሆነው ይህ ታላቅ ድል፣ ለጥቁር ህዝቦች ነፃነትም አይነተኛ ሚና የነበረውና የፓንአፍሪካኒዝም ንቅናቄን ማቀጣጠል ያስቻለ ክስተት እንደሆነም የታሪክ ምሁራን ያስረዳሉ።
በሐረማያ ዩኒቨርሲቲ የታሪክ መምህርና ተመራማሪ እንዲሁም የገዳ ጥናት ተቋም ዳይሬክተር ዶክተር ረታ ዱጉማ፤ አውሮፓውያኑ አፍሪካን ለመቀራመት በነበራቸው ከፍተኛ ፍላጎት የትኛውን አፍሪካ አገር ማን ይውሰድ በሚል ተከፋፍለው እንደነበር በማስታወስ፣ ‹‹አብዛኞቹን የአፍሪካ አገራት በቅኝ ሲገዙ ኢትዮጵያን ግን አልቻሏትም›› ይላሉ። አውሮፓውያኑ እጅግ ዘመናዊ የጦር መሳሪያዎችንና የተደራጀ ወታደር ይዘው አፍሪካን በኃይል ለመቆጣጠር በመጡ ጊዜ አፍሪካውያን የገጠሟቸው በባህላዊ መሳሪያዎች እንደነበር ይገልጻሉ።
እርሳቸው እንዳሉት፤ በወቅቱ ጣልያን ኢትዮጵያን ለመውረርና አገሪቷን ለመከፋፈል ሙከራ ባደረገ ጊዜ ህዝቡ በአንድነት ከጫፍ እስከጫፍ በነቂስ ወጥቷል። አገልጋዮች፣ ሴቶች፣ መኳንንቶችና መሳፍንቶች ሳይቀሩ ባደረጉት ተጋድሎም ድሉ የኢትዮጵያውያን መሆን ችሏል። ወቅቱ አብዛኛዎቹ የአፍሪካ አገራት ተሸንፈው በቅኝ የተያዙበት እንደነበር ያስታወሱት ዶክተር ረታ፤ ኢትዮጵያ ጣልያንን ድል የማድረጓ ዜና በተሰማ ጊዜ በአውሮፓውያኑ ዘንድ ከፍተኛ መደናገጥ ተፈጥሮ እንደነበር ያስታውሳሉ።
በኢትዮጵያ ድል አድራጊነት ተጽዕኖ የተፈጠረባቸው ጣልያኖችም ‹‹ቪቫ ምኒልክ፤ ቪቫ ጣይቱ›› ‹‹በርታ ምኒልክ፤ በርቺ ጣይቱ›› ይሉ እንደነበርም ታሪክ ያመለክታል። ጣልያኖች ከአገራቸው ውጭ ሄደው በዘመናዊ መሳሪያና በተደራጀ ወታደር ባደረጉት ጦርነትና በደረሰባቸው ሽንፈት የተነሳ በወቅቱ በነበረው የጣልያን መንግሥት ላይ ትችት እንደቀረበበትም አስታውሰዋል።
በቦንጋ ዩኒቨርሲቲ የታሪክና የስነቅርስ መምህር አቶ ሰለሞን ኪዳኔ ‹‹የአድዋ ድል በታሪክ ውስጥ ትልቅ የታሪክ እጥፋትን ፈጥሮ ያለፈ ነው›› ሲሉ ይገልጻሉ። እሳቸው እንዳሉት፤ የአድዋ ድል ሁሌም የሚወሳ የጥቁር ህዝቦች የማንነት መገለጫ ነው። አውሮፓውያን በተለይም በ19ኛው ክፍለ ዘመን ለአፍሪካ የነበራቸው አመለካከትና አፍሪካን የሚስሉበት መንገድ እጅግ ዝቅ ያለ እንደነበር ጠቅሰው፣ ያ ዘመን አፍሪካን የጨለማው አህጉር በሚል የፈረጁበት ወቅት እንደነበር ያስታውሳሉ።
በዚያ ወቅት የተገኘው የአድዋ ድልም ከኢትዮጵያ አልፎ ለአፍሪካውያን ትልቅ ብርሃን መሆን የቻለና በተለይም ቅኝ ገዢዎችን በከፍተኛ ድንጋጤ ውስጥ የከተተ ክስተት ነው ይላሉ። የአድዋ ድል የአፍሪካውያን የነጻነት ቀንዲል ነው የተባለውም በዚሁ ምክንያት መሆኑን በማስታወስ፤ ‹‹የአድዋ ድል የኢትዮጵያውያንን ስነልቦና ከመገንባት ባለፈ የቅኝ ግዛትን ተጽዕኖ በሚገባ የተረዱትና የሚያውቁት አፍሪካውያን በተገኘው ድል እጅጉን ኮርተዋል። አሁንም ይኮራሉ›› ሲሉ ያብራራሉ።
‹‹እንደ አለመታደል ሆኖ ከቅኝ ግዛት በፊት አፍሪካ በባሪያ ንግድ ብዙ ዋጋ ከፍላለች›› የሚሉት መምህር ሰለሞን፤ የባሪያ ንግድ ሲያበቃ ከኢንዱስትሪው አብዮት በኋላ የሰው ጉልበት ዋጋ ሲያጣና በማሽን ሲተካ አውሮፓውያን ፖሊሲያቸው አፍሪካን በአፍሪካ መበዝበዝ ያውም በቅኝ ግዛት የሚል እንደነበር አስታውሰው፤ ‹‹ይሁንና አውሮፓውያኑ ከሰው ተራ የማይቆጥሩት ጥቁር ያሸንፈናል የሚል ግምት ያልነበራቸው በመሆኑ በአድዋ ድል ከፍተኛ የሆነ የመደናገጥና የስነልቦና ጫና ተፈጥሮባቸው አልፏል። በወቅቱም ጣልያን በመሸነፏ ምክንያት የተፈጠረው የፖለቲካ ቀውስ የመንግሥት ለውጥ ለማድረግ ያስገደደ ነበር›› ሲሉ ያብራራሉ።
እንደ መምህር ሰለሞን ማብራሪያ፤ ይህን ታላቅ ድል ተከትሎም አፍሪካውያን በተለያዩ እንቅስቃሴዎች ራሳቸውን ከአውሮፓውያን ቅን ገዢዎች ነጻ ለማድረግ ታግለዋል። ከእነዚህም እንቅስቃሴዎች መካከል ኢትዮጵያኒዝም የተባለው ንቅናቄ በዋናነት ይጠቀሳል፤ ትግሉ ብዙ አፍሪካውያንን ዋጋ ከማስከፈል ባሻገር በስኬት የተመዘገበው ብቸኛው ድል የአድዋ ድል መሆኑን አንስተዋል።
ድሉ ከሚታሰበው በላይ ፋይዳው የጎላ መሆኑን ያነሱት መምህር ሰለሞን፤ ‹‹በተለይም አፍሪካውያን ጥቁሮች ነጮችን እንዴት ማሸነፍ ቻሉ በሚል ተገርመው ነበር። ምክንያቱም በወቅቱ ነጮች በቴክኖሎጂና በሌሎች ዘርፎች የተሻሉ ነበሩ። ከአድዋ ድል በኋላ ግን ‹‹ጥቁር ነጭን ማሸነፍ ይችላል፤ጥቁርም እንደ ሰው እኩል ነው››የሚል ከፍተኛ የሆነ የሞራል ስንቅና የስነልቦና መነቃቃት ተፈጥሯል። ‹‹የታሪክ እጥፋት› ነው የሚባለውም በዚሁ ምክንያት ነው›› ሲሉ ያብራራሉ።
ኢትዮጵያ ጣልያንን ድል በማድረጓ የተገኘው የአድዋ ድል በቅኝ ግዛት ሥር ለወደቁ አፍሪካውያን ከፍተኛ አቅም፣ ጉልበትና የሞራል ስንቅ ሆኗል›› የሚሉት ዶክተር ረታ፤ ድሉ ለፓንአፍሪካኒዝም ይበልጥ መቀጣጠል መነሻ የሚሆን መሰረት የጣለ ነው ይላሉ። ነጮችን ማሸነፍ እንደሚቻል ያሳየ ድል በመሆኑ እህትና ወንድም የሆኑ አፍሪካውያን በአንድነት ሆነው ለውጥ ማምጣት እንደሚችሉ አሳይቷል። በተለይም በወቅቱ በአፍሪካም ሆነ በአውሮፓ ውስጥ ሆነው በባሪያ ንግድ ለተያዙ አፍሪካውያንና ለአፍሪካ አገራት ትልቅ ሞራል በመሆን ከፍተኛ ንቅናቄ ፈጥሯል ሲሉ ያብራራሉ።
በ20ኛው ክፍለ ዘመን አካባቢ በተለያዩ አፍሪካ አገራት በቅኝ ገዢዎች ላይ የተጀመሩ ንቅናቄዎች እንደነበሩ ያነሱት ዶክተር ረታ፤ የአድዋ ድል ለእነዚህ ንቅናቄዎች ጭምር መሰረት እንደሆነ ነው የተናገሩት። ጣልያኖች በድጋሚ ሲመጡም በርካታ አገራት ለኢትዮጵያ ድጋፍ በማድረግ ከኢትዮጵያ ጎን ቆመው እንደነበር ጠቅሰው፣ በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ ከቅኝ ግዛት ነጻ የመሆን ፍላጎት የነበራቸው አብዛኞቹ ሚሲዮናውያን ቤተ ዕምነቶች ኢትዮጵያኒዝም በሚል ከፍተኛ ንቅናቄ አድርገው እንደነበር ነው ያመለከቱት። የኢትዮጵያኒዝም ንቅናቄ በተለይም በአፍሪካ ውስጥ በደቡብ አፍሪካ ተፈጥሮ እንደነበርም አንስተዋል።
ጣልያኖች ኢትዮጵያን ለሁለተኛ ጊዜ ለመውረር በመጡ ጊዜ ከአፍሪካውያን በተጨማሪ ሌሎች የዓለም አገራት ኢትዮጵያን ‹‹የጥቁር ተስፋችን›› በሚል በተለያየ መንገድ ሲደግፉ እንደነበር የጠቀሱት ዶክተር ረታ፤ ይህም ኢትዮጵያ ለጥቁር ህዝቦች የነጻነት ቀንዲል ተምሳሌት በመሆኗ ነው ይላሉ። የአድዋ ድል በተለይም በቅኝ ግዛት ሥር ለነበሩ አፍሪካውያን ትልቅ የሞራል ስንቅ ያስታጠቀ በመሆኑ ሁሌም ሲዘከር ይኖራል ብለዋል።
ዶክተር ረታ እንዳሉት፤ በአድዋ ድል ይበልጥ የተቀጣጠለው የፓንአፍሪካኒዝም ንቅናቄ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ትስስርን በመፍጠር፤ የአፍሪካውያንን ችግር በአፍሪካውያን የመፍታት፤ እንዲሁም ኢኮኖሚያዊ ትስስር የመፍጠር አቅምን ለማረጋገጥ ከፍተኛ ድርሻ አለው። በፓንአፍሪካኒዝም ንቅናቄ አፍሪካ ክብሯና ነጻነቷ እንዲጠበቅ፣ ኢኮኖሚያዊ ትስስር እንዲፈጠር፣ ፖለቲካዊ ችግሮች እንዲቃለሉ ብዙ ተሰርቷል ።
የተባበረችና አንድ የሆነች አፍሪካን ለመፍጠር በሚል እሳቤ በንቅናቄው የተሰሩ ሥራዎች እንዳሉ ሁሉ እንቅፋት የሆኑ በርካታ ችግሮች ስለማጋጠማቸውም ዶክተር ረታ ጠቁመዋል። በተለይም የቅኝ ግዛቱ ካበቃ በኋላ አስተሳሰቡ በተለያየ መልኩ ያደገ በመሆኑ ጠባሳ ጥሎ አልፏል። በመሆኑም ምዕራባውያኑ የራሳቸውን ፍላጎት ለማስፈጸም መሪዎችን የማስቀመጥ አዝማሚያና ፍላጎቶችን በማሳደር በተለያዩ አገራት እጃቸውን እያስገቡ አገራትን በጥብጠዋል ይላሉ።
እነዚህና መሰል ችግሮች በመፈጠራቸው ምክንያት የፓንአፍሪካኒዝም ንቅናቄ በሚፈለገው መጠን ጠንካራ መሆን ባይችልም ጉልህ አስተዋጽኦ እንደነበረው፣ ከፍተኛ መነቃቃትንና ሰፊ ግንዛቤን በመፍጠር ረገድም በጎ ተጽዕኖ ማምጣቱን ያመለክታሉ። የፓንአፍሪካኒዝም ንቅናቄ ግቡን መምታት እንዲችል አሁን ላይ የተጀማመሩ እንቅስቃሴዎች እንዳሉ ሆኖ ነው በቀጣይ ብዙ ርቀት በመሄድ ግብን ማሳካት እንደሚገባም አስገንዝበዋል።
በመሰረታዊነት የአፍሪካንና የጥቁርን አንድነት ለማምጣት የተጀመረው የፓንአፍሪካኒዝም ንቅናቄ ከአፍሪካ ውጭ በነበሩ ጥቁር ጃማይካውያን የተጀመረ ስለመሆኑ የሚገልጹት መምህር ሰለሞን፤ ፓንአፍሪካኒዝም ጥቁሮች ያለምንም ገደብ የሚስተናገዱበት አፍሪካን አንድ የማድረግ እሳቤ ያለው መሆኑን ያስረዳሉ። ለዚህም የአድዋ ድል እንደ ስንቅ ሆኖ ያገለገለ መሆኑንም ይገልፃሉ።
አፍሪካን አንድ በማድረግ ማዋሃድ በሚል የተጀመረው የፓንአፍሪካኒዝም እንቅስቃሴ ለአፍሪካ አንድነት ድርጅት መመስረትም ትልቅ ድርሻ እንደነበረው አንስተዋል። እሳቸው እንደሚሉት፤ አፍሪካውያን ከነጻነት በኋላ ዘርፈ ብዙ ችግሮች ገጥሟቸዋል። ቅኝ ግዛት ጥሎት ያለፈው ጠባሳ ብዙ ችግሮችን ፈጥሯል። ድህነትን ጨምሮ በምግብ ራስን አለመቻል፣ በርካታ መፈንቅለ መንግሥቶች፣ የድንበር ግጭቶችና ሌሎች ፖለቲካዊ ቀውሶች አጋጥመዋቸዋል። ስለሆነም ፓንአፍሪካኒዝም በታሰበው ልክ ውጤታማ መሆን አልቻለም ይላሉ።
‹‹ይሁንና በቅርቡ በተካሄደው በ36ኛው የአፍሪካ የመሪዎች ስብሰባ ላይ የፓንአፍሪካኒዝም እንቅስቃሴ እንደገና መነሳቱ ለአፍሪካውያን ትልቅ ኩራት ነው›› የሚሉት መምህር ሰለሞን፤ አሁን ያለው ጅማሬ መልካም ነው ይላሉ። ያለፈውን ከመውቀስ ይልቅ ካለፈው ችግር በመማር አፍሪካውያን የጋራ ችግራቸውን በጋራ ለመፍታት የሚያደርጉትን ጥረት አጠናክሮ መቀጠል እንደሚገባም ያስረዳሉ።
እሳቸው እንዳሉት፤ ለአፍሪካውያን ችግር አፍሪካዊ መፍትሔ በማፈላለግም ኢትዮጵያ ምሳሌ ሆናለች። ለእዚህም ከሰሜኑ ጦርነት ጋር በተያያዘ የተወሰደው እርምጃ ጥሩ ጅምር ነው። ኢትዮጵያ ግንባር ቀደም በመሆን አፍሪካዊ የዲፕሎማሲ መፍትሔ ማምጣት ችላለች። የአፍሪካን ችግር አፍሪካዊ በሆነ መፍትሔ ለመፍታት የተደረገው ጥረትም የአድዋን ድል መሰረት በማድረግ የተጀመረው የፓንአፍሪካኒዝም ንቅናቄ አንዱ ማሳያ አድርጎ መውሰድ ይቻላል።
አፍሪካውያን ኢትዮጵያ ላይ ትልቅ ተስፋ አላቸው የሚሉት አቶ ሰለሞን፤ ለኢትዮጵያ ያላቸው ክብርም ከፍተኛ እንደሆነም ያነሳሉ። ኢትዮጵያውያን ግን ይህንን በልኩ እንዳልተረዱት በመጥቀስ አፍሪካውያን ለኢትዮጵያ የሰጡትን ቦታ በሚገባው ልክ መረዳት እንደሚገባ ያስገነዝባሉ። ‹‹አፍሪካውያን ወንድም እህቶች ለሰጡት ፍቅርና ቦታ በወጉ ምላሽ ሊሰጥ ይገባል። በቀጣይም አሁን በፖለቲካው የተገኘውን ድል በኢኮኖሚው በመድገም ኢኮኖሚያዊ ትስስሩን አጠናክሮ ለመቀጠል ኢትዮጵያ የማንቂያ ደውል መሆን አለባት›› በማለት ይገልፃሉ።
አድዋን ታላቅ ድል ያሰኘው የህዝቦች መተባበር፣ የህዝቦች በአንድነት መቆምና መነሳት መሆኑን ያነሱት ዶክተር ረታ፤ አሁን በአገሪቱ ያሉትን ዘርፈ ብዙ ችግሮች በአንድ ልብና ሀሳብ ሆኖ በጋራ መቆም ከተቻለ እንደ አድዋ ሁሉ ችግሮቹን ድል መንሳት እንደሚቻል ጠቅሰው፤ የአድዋ ድል የሚያስተምረንም ይህንኑ ነው ይላሉ።
የዶክተር ረታን ሃሳብ የተጋሩት መምህር ሰለሞን በበኩላቸው፤ አሁን ያለው ትውልድ የአድዋን ድል ምሳሌ ማድረግ እንደሚኖርበት ይገልጻሉ፤ በሃይማኖት፣ በብሔርና በተለያዩ ሃሳቦች መከፋፈሉን በመተው ታሪክን መማሪያ እንጂ ቂም መወጣጫ ባለማድረግ እንዲሁም አንድነትን በማጠናከር ኢትዮጵያን ወደ ብልጽግና ጉዞ ማሻገር እንደሚገባ አጽንዖት ሰጥተው አስገንዝበዋል።
ጥቁሮች ለዓላማቸው መሳካት በአንድነት ከታገሉ ጠላትን ማሸነፍ እንደሚችሉ ጽኑ እምነት እንዲያዝ ማድረግ ያስቻለው የአድዋ ድል፤ አውሮፓውያኑ ትምህርት ያገኙበት መሆኑን ይናገራሉ፤ ወራሪ ቅኝ ገዥዎች የአገዛዝ ፖሊሲያቸውን ጭምር እንዲመረምሩ አድርጓል ባይም ናቸው።
በወቅቱ የነበሩት የአሜሪካና የአውሮፓ ጋዜጦችና መጽሔቶች ጭምር አቋማቸውን በመቀየር ድሉ ታላቅ ገድል መሆኑንና ዳግማዊ አፄ ምኒልክም ታላቅ መሪ እንደነበሩ መመስከራቸው ይታወሳል።
ፍሬሕይወት አወቀ
አዲስ ዘመን የካቲት 25 ቀን 2015 ዓ.ም