ሰሞኑን የተፈጠሩ ከጾም ጋር የተያያዙ ሁለት ክስተቶች ሲያነጋግሩን ከርመዋል።አንደኛው ጉዳይ ሞዛምቢካዊው ፓስተር እንደ ኢየሱስ ክርስቶስ 40 ቀን ለመጾም ሲሞክር በ25ኛ ቀኑ ሞቶ መገኘቱ ነው።ሁለተኛው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ምእመናን የሚጾሙትን አብይ ጾም መግቢያ በማስመልከት “የቅበላ ኮንሰርት” አዘጋጅተናል ያሉ የምሽት ጭፈራ ቤቶች ጉዳይ ነው።ሁለቱ ክስተቶች ጾም የስጋ ረሃብ ነው ወይስ የነብስ ምግብ የሚል ጥያቄ እንዳነሳ አድርገውኛል።
የግብጽ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ፓትሪያርክ አቡነ ሺኖዳ ሦስተኛ “The Spiritual of Fasting” (የጾም መንፈሳዊነት) በሚል ርዕስ ያሳተሙት መጽሐፍ መንፈስ ይህን ጽሁፍ እንደተጫነው አስቀድሜ መናዘዝ እፈልጋለሁ።እነዚህን ሁለት ክስተቶች ለአደባባይ ያበቃቸው ስለጾም የተያዘ ትክክል ያልሆነ ግንዛቤ ይመስለኛል።ይህ ግንዛቤ ጾምን የስጋ የስቃይ መድረክ አድርጎ የሚወስድ ነው።ለሀገሩ ሊሰዋ ጦር ሜዳ ለሚወርድ ወታደር የሚደረግ ሽኝትን የሚያስንቅ ድግስና ኮንሰርት እየተዘጋጀ ያለው ለተወሰነ ጊዜ ረሃብን ሊጋፈጥ የተዘጋጀውን ስጋን ለማጽናናት ነው።ይህ በእውነት ያስተዛዝባል!
40 ቀን ለመጾም ሲሞክር በ25ኛ ቀኑ የሞተው ሰውም ጾምን የተረዳበት መንገድ ጥያቄ የሚያስነሳ ነው።አቡነ ሺኖዳ ከላይ በጠቀስኩት መጽሀፋቸው፣ “ሰው ጠቢብ ወይም ብልህ ሊባል የሚችለው ራሱን መቆጣጠር ሲችልና የሆዱን አሰራር ሲጠብቅ ነው።ብልህ ሰውነቱን ልፍስፍስ እስኪሆን ድረስ አይመግበውም፤ የሚያስፈልገውን መጠን በማሳጣትም እጅግ አያኮማትረውም” ይላሉ። ይህ ሰው በህይወት ለመቆየት ያህል እንኳን የሚያስፈልገውን ጥቂት ምግብ ራሱን ከልክሎ ነው ስጋው እስከ መጨረሻው የተኮማተረው።በአጭሩ ብልህ ባለመሆኑ ተበልቷል።ይህ ጾምን የስጋ ረሀብ አድርጎ በመቁጠር የመጣ ውጤት ነው፡፡
ስለ ጾም የተያዘውን ይህን ታማሚ ግንዛቤ ሳይንስ እንኳን አይደግፈውም።ሳይንስ ጾም ጠቃሚ መሆኑን አረጋግጧል።ሳይንስና ሃይማኖት ከሚገናኙባቸው ጥቂት ድልድዮች አንዱ ጾም ነው።አንድ ሀኪምና የሃይማኖት አባት በእኩል ደረጃ ስለ ጾም ጠቀሜታ ሲናገሩ ሊደመጡ ይችላሉ።ሳይንስ ደግሞ ከመቼ ወዲህ ነው ጾምን መስበክ የጀመረው? የሚል አንባቢ አይጣፋም።ሳይንስ ለጾም የበኩሉን እውቅና ከሰጠ ሰነባብቷል።ለምሳሌ ሩሲያዊው ሳይንቲስት አሌክሲ ሶፍሪን (Alexi Soforin) ከ92 አመታት በፊት በጾም የሚከናወን ህክምና (ትሪትመንት ባይ ፋስቲንግ) በሚል ርዕስ አንድ መጽሃፍ ጽፏል።ሶፍሪን በዚህ መጽሐፉ ለረጅም ጊዜ ከምግብ ተከልክሎ መቆየት ብዛት ያላቸው በሽታዎችን እንደሚያክም ገልጿል።በጾም ወቅት ሰውነት በቂ ምግብ አለማግኘቱ የተከማቹ ስቦች እንዲቃጠሉ እንዲሁም የታመሙና ያመረቀዙ ጡንቻዎቻችን እንዲፍታቱና እንዲዝናኑ እድል እንደሚሰጥ ጠቅሷል።
በሃይማኖቶች ሰፈር ጾም ሳይንስ ከደረሰበት ጠቀሜታው በዘለለ ትልቅ መንፈሳዊ መሳሪያ ነው።ስለ ቡዲዝም፣ ብርሃማኒዝም፣ ኮንፊሺኒዝም እና ዮጋ የሚያነብ ሰው በጾም ስጋቸውን ለነብሳቸው በማስገዛት ነብሳቸው ሙሉ ለሙሉ የበላይ እንድትሆን ማድረግ እንደሚችሉ ይገነዘባል።በታዋቂው የሃይማኖት መሪ ማህተመ ጋንዲ ህይወት ውስጥም ጾም ትልቅ ስፍራ ነበረው።ጋንዲ እጅግ ለረጅም ጊዜ ከመጾሙ የተነሳ በአንድ ወቅት ሀኪሞች ደሙ እንደ ወተት መበጣጠስ መጀመሩን ነግረውት ነበር።
ዮጋዎች በጾም አማካኝነት ጥቅም ላይ ይውል ያልነበረን ከፊል የሰውነታቸውን ኃይል ማግኘት እንደቻሉ ይናገራሉ።ይህ ኃይል ሰው ለሥጋው በሚያደርገው እንክብካቤ የሚሸሸግ በመሆኑ ከጾም በቀር በምንም መንገድ ሊገኝ እንደማይችል ያምናሉ።ሂንዱዎች ደግሞ በጾም ሥጋን ከነብስ የመለየት (ኒርቫና) ደረጃ ላይ ስለምንደርስ ከአምላካችን ጋር አንድ እንሆናለን የሚል እምነት አላቸው።እዚህ ደረጃ ላይ ለመድረስ ታዲያ ጥብቅ ምናኔ፣ ጾምና ከስጋዊ ነገሮች መከልከል ያስፈልጋል።
በሀገራችን ብዙ ተከታዮች ባሏቸው በክርስትና እና እስልምና ሃይማኖቶች ውስጥ ለጾም የሚሰጠው ቦታ ትልቅ ነው።በመጽሐፍ ቅዱስ በጊዜያዊው የስጋ ረሃብ ዘላለማዊዋ ነብስ እንደምትጠግብ ለማጠየቅ “እናንተ አሁን የምትራቡ ብፁሐን ናችሁ ትጠግባላችሁና” (ሉቃ6፡ 21) ተብሎ ተጽፏል።በክርስትና እሳቤ ሰው በተራበ ጊዜ የሚያቀርበው ልመና (ጸሎት) ይበልጥ ተሰሚነት አለው።በመንፈሳዊነት የተሞላ ጸሎት በምግብ ከተሞላ ሰውነት ሊወጣ አይችልም።ሆድህ ምግብ ተሞልቶ ከምትጸልየው ሰዓታት ከሚወስድ ጸሎት ይልቅ በረሃብ ውስጥ ሆነህ የምታቀርበው የሁለት ደቂቃ ጸሎት ጥልቀት፣ ተሰሚነትና ተቀባይነት አለው።መነኩሳትና መንፈሳውያን አባቶች ሰው የህይወት ዘመኑን ዕኩሌታ የሰውነቱን ጡንቻ ለማዳበር አውሎ፣ ቀሪ ዘመኑን ደግሞ በሂደቱ በሰውነቱ የተከማቸውን ስብ ለማጥፋት መድከሙ እንደ ምን ያለ አሳዛኝ ነገር ነው ? ብለው ይጠይቃሉ።እነሱ ጾምን ለማያውቁት እንዲህ እያዘኑ በጾም ደስታን ያደርጋሉ እንጂ የስጋ ረሃብ አድርገው አያዩትም።
ኢትዮጵያውያን ሊቃውንት ወግሪስ እና ወቅሪስ፣ የውጨጭ ሀገር ሰዎች ደግሞ (Evagrios) እያሉ የሚጠሩት በአራተኛ መቶ ክፍለ ዘመን በግብጽ ምድር የነበረ መናኒ የእርሱን መንፈሳዊ ተጋድሎና ልምምድ ለሚፈልጉ መናንያን ይጽፍ በነበረው መልዕክት፣ ጤነኛ ትሆን ዘንድ የምግብ ሸከምን አቅልል።የዛገ መስታወት ፊትን እንደሚያጠቁር ጥጋብም አስተዋዩን ያደነቁራል።ደካማ ሥጋህን አትራራለት።አንተ ከተንከባከብከው በአንተ ላይ በጠላትነት ይነሳብሃልና።የተለጎመ ፈረስ እንደሚታዘዝ ሥጋችንም ከገራነው ታዛዥ ይሆናል፤ ፈጽሞም አይናወጽም ይላል።
አቡነ ሺኖዳ ሦስተኛም እንደሚገልጹት፣ ጾም የስጋ ሥቃይ ወይም መስቀል አይደለም።ሥጋ ከነብስ ጋር የሚተባበርበት ደረጃ ላይ ለመድረስ ከፍ ከፍ የሚልበት እንጂ።የጾም ዓላማ ስጋን ማንገላታት ሳይሆን ጠባዩን መግራት ነው።ነብስ ከፍ ብላ ሥጋ ጓዙንና ሸክሙን አራግፎ አብሯት ከፍ እንዲል የምታደርግበት ነው።በጾም ወቅት ነብስና ስጋ በኅብረት መንፈሳዊ ተግባር ለመከወን ይነሳሉ።ስለዚህ ጾም የስጋ ረሃብ ሳይሆን የነብስ ምግብ ነው።
ለእስልምናም ጾም ከአራቱ የሃይማኖቱ መሰረቶች መካከል አንደኛው ነው።እስልምና መጾም የሚችል ሰው ከምግብ ከመከልከል ባለፈ ጾምን ከሚያበላሹ ነገሮች እንዲቆጠብ ግዴታ ይጥላል።የአላህ መልዕክተኛ (ሰ.ዐ.ወ) እንዲህ በማለት አስጠንቅቀዋል፣ ‹‹እኩይ ንግግሮችንና በእነርሱም መስራትን የማይተው ሰው፣ ምግቡንና መጠጡን በመተው አላህ ምንም ጉዳይ የለውም፡፡›› (ቡኻሪ 1804)።አንድ ሙሰሊም በተፈቀደለት ስጋዊ ስሜት ላይ ለተወሰኑ ሰዓታትና ቀናት ድልን ሲቀዳጅ የነፍሱ ንጉሥ ለመሆን ከመቻሉ ባሻገር ስሜቱን በአግባቡ ለመቆጣጠርና ስሜቱ ክልክል በሆኑ ስፍራዎች ላይ እንዳይውል ለመለጎም አቅም ይኖረዋል።
ከላይ ያነሳናቸው ሃይማኖታዊ እሳቤዎች በጾም አማካኝነት ነብስ ከስጋ ፍላጎቶችና ቁጥጥር ነጻ በመውጣት የተፈጥሮ እምቅ ኃይሏን እንደምታገኝ የሚያስረዱ ናቸው።
በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን “ቅበላ” ተብሎ የሚጠራው፣ ጾም ከመግባቱ በፊት ቀደም ብሎ ያለው ቀን ወይም ሰሞን ነው።በቤተክርስቲያኗ ሥርዓትና ትውፊት መሰረት አጽዋማት አቀባባል የሚደረግላቸው በዋዜማው በሚቀርብ የጸሎት ስነ ስርዓት ፣ መዝሙርና ትምህርተ ወንጌል ነው። ቅበላን ለስጋ በመራራት ኮንሰርት በማዘጋጀት የሚደረግ ተድላና ደስታ ነብስን ምግቧን አሳጥቶ ለረሃብ የሚዳርጋት ዋጋ የሚያሳጣ ተግባር ነውና ሊወገዝ ይገባል።የነብስ ምግብ ስታርተር የስጋ ተድላ ሊሆን አይችልም።
ተስፋ ፈሩ
አዲስ ዘመን የካቲት 25 ቀን 2015 ዓ.ም