ሀገራችን በድርቅና ከዚህ በሚመነጭ የረሀብ አደጋ ከሚጠቁ ሀገሮች መካከል አንዷ ናት። በዚህም በየዘመኑ በሰውና በንብረት ላይ የደረሱ ጉዳቶች ከፍተኛ እንደሆኑ የታሪክ ማህደራት ያመለክታሉ። ስሟ በዓለም አቀፍ ደረጃ የረሀብ መገለጫ እስኪመስል ድረስ ሲታይ መኖሩም የአደባባይ እውነታ ነው።
ከቅርቡ ጊዜያት ካለው እውነታ ብንነሳ በአፄ ምኒልክ (1880 – 1883)፤ በግርማዊ ቀዳማዊ አፄ ኃይለ ሥላሴ (1965/66 ዓ.ም) ፣ በደርግ (1977 ዓ.ም) በኢህአዴግ /1990/ ወቅት ከፍተኛ የድርቅና የርሃብ አደጋዎች ተከስተዋል፡፡ በዚህም ሀገር እንደ ሀገር የከፈለችው ዋጋ የየዘመኑ ሀገራዊ ጥቁር ታሪክ ተደርጎ የሚወሰድ ነው።
በእነዚህ የታሪክ ምዕራፎች ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ዜጎቻችን ለከፋ የረሀብ አደጋ ፣ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ለሞት ተዳርገዋል፤በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ የጋማና የቀንድ ከብቶች አልቀዋል። በዚህም ሀገር በየዘመኑ አንገት ለሚያስደፉ የልብ ስብራቶች ተዳርጋለች፤ የልብ ስብራቱ ትውልድ ተሻግሮም የታሪካችን ጥቁር ጠባሳ ሆኗል።
ይህን ሀገራዊ ታሪካዊ እውነታ ለመለወጥና ይህን የታሪክ ጥቁር ጠባሳ ለመፋቅ እንደ ሀገር ሁለንተናዊ በሆነ የብልጽግና ንቅናቄ ውስጥ ባለንበት በዚህም ወቅት የድርቅ አደጋ በተለያዩ የሀገራቱ አካባቢዎች ተከስቷል።
መረጃዎች እንደሚያመለክቱት በኦሮሚያ ክልል፤ በቦረና ዞኑ የሚገኙ 13 ወረዳዎች በድርቅ ተጠቅተዋል። በሶማሌ እና በደቡብ ብሄር ብሄረሰቦች ክልሎች የተለያዩ አካባቢዎች ችግሩ እንደተከሰተ ተነግሯል።
በቦረና ዞን በድርቁ ምክንያት ከሁለት ሚሊዮን በላይ እንስሳት ሞተዋል፤ 60 በመቶ የሚሆነው የወረዳዎቹ ነዋሪዎችም /807 ሺህ ሰው/ ድጋፍ ያስፈልጋቸዋል። ከነዚህም ውስጥ 167 ሺህ የሚሆኑ ደግሞ አስቸኳይና ተከታታይ ድጋፍ የሚፈልጉ ናቸው።
መንግሥት በአንድ ዙር ከ600 ሺህ በላይ ለሚሆኑ ሰዎች ከ90 ሺህ ስድስት መቶ ኩንታል በላይ ስንዴ፣ ሁለት ሺህ 66 ሊትር ዘይት እና 22 የውሃ ቦቴዎች እርዳታ አቅርቧል። ከመንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶችና አጋር አካላት ወደ 750 ሚሊዮን የሚጠጋ የገንዘብ ድጋፍ ተገኝቷል።
የችግሩ ሰለባ የሆኑ ዜጎቻችንን ለመታደግ እየተደረገ ያለው ጥረት በመንግስትና በሚመለከታቸው መንግስታዊ ያልሆኑ አካላት ቀጥሏል። በግለሰብ ሆነ በቡድን ደረጃ ድጋፎችን ለማሰባሰብ የሚደረጉ ጥረቶችም በስፋት እየተከናወኑ ነው። ይህ ይበል የሚያሰኝና ለወገን ቀድሞ ደራሽ ወገን መሆኑን በተጨባጭ ያመላከተ በጎ ተግባር ነው።
በችግሩ ውስጥ ካሉትም ሆነ ስጋት ውስጥ ከሚገኙ ተጨማሪ ዜጎቻችን አንጻር እየተካሄደ ያለው ድጋፉ ግን በቂ ነው ተብሎ የሚወሰድ አይደለም። ችግሩን በስኬት አሸንፎ ለመውጣት በቀጣይም የእያንዳንዱን ዜጋ የነቃ ተሳትፎ የሚጠይቅ ነው።
በምግብ እህል ራሳችንን ለመቻል በተለያዩ ዘርፎች /የስንዴን ምርት ጀምሮ ውጤታማ መሆን በጀመርንበት ታሪካዊ ምዕራፍ የተከሰተው ይህ የድርቅ አደጋ የብልጽግና ጉዟችንን የሚፈታተን ቢሆንም ፤ በጀመርንበት መንገድ በቁርጠኝነት እንድንጓዝ የበለጠ እልኸኝነትን የሚፈጥር ነው።
የተከሰተው የድርቅ አደጋ የቱንም ያህል ቢፈታተነን፤ ቀደም ሲል ከፈተኑንና በአሸናፊነት ከተሻገርናቸው ችግሮቻችን የበለጠ አይሆኑም። ፈተናን ሳይጋፈጥ ለብልጽግና የበቃ አንድም ሀገር የለምና ችግሩ ከማንም በላይ እኔን ይመለከተኛል በሚል የዜግነትና የኃላፊነት መንፈስ በአንድነት መንቀሳቀስ ከቻልን ብዙ ዋጋ ሳያስከፍለን ልንቆጣጠረው እንችላለን። ለዚህ ደግሞ እጅ ለእጅ ተያይዘን ለመንቀሳቀስ ትክክለኛው ጊዜ አሁን ነው!
አዲስ ዘመን የካቲት 25 ቀን 2015 ዓ.ም