ዓድዋ ዛሬ ናት
ዓድዋ ትናንት
መቼ ተነሱና የወዳደቁት
የሚለው የእጅጋየሁ ሽባባው(ጂጂ) ዘፈን የቱንም ያህል ቢደጋገም የማይሰለች ጥልቅ መልዕክት ያለው ነው። ዓድዋን ዛሬ(ዘንድሮ) እያከበርን ነው። ዓድዋ ከዛሬ 127 ዓመታት በፊት(ትናንት) የተፈጸመ ታሪክ ነው። ዓድዋን ወደፊት(ነገ) እናከብረዋለን። ምክንያቱም ዓድዋ ላይ የወደቁ ጀግኖች አልተነሱም።
‹‹…ሰው ተከፍሎበታል ከደም እና ከአጥንት…›› ብላለች ጂጂ። አዎ! ዛሬ ያለንባት ‹‹ቅኝ ያልተገዛች›› የምትባለዋ ኢትዮጵያ የደምና አጥንት ዋጋ ተከፍሎባታል። ለእኛ በነፃነት መኖር እነርሱ ተሰውተዋል። ይህን ታሪክ ዓድዋ ይናገራል፤ ይመሰክራል።የትናንቱን ዓድዋ ዛሬና ነገ የምናከብረው የኢትዮጵያ የኩራት ምንጭ ስለሆነ ነው። የአፍሪካ ኩራት የሚባለው ቅኝ አለመገዛትን ለአፍሪካ አገራት ያሳየ ስለሆነ ነው።
በመስከረም 2014 ዓ.ም በ6ኛው አገር አቀፍ ጠቅላላ ምርጫ ያሸነፈው ብልጽግና የመንግሥት ምሥረታ ሲያደርግ የአፍሪካ አገራት መሪዎች መጥተው ነበር። በተጋበዙበት መድረክ ላይ የተናገሯቸው ንግግሮች ለረጅም ቀናት መነጋገሪያ ሆነው ነበር። የሁሉም መሪዎች ንግግር ሲጠቃለል፤ ኢትዮጵያ ለአፍሪካ አገራት የነፃነት ምሳሌ መሆኗን ነው። ‹‹እናት›› ሲሉ የገለጿትም ነበሩ።
ይህ ለምን ሆነ? ብለን ብንጠይቅ ብዙ ምርምር የሚያስፈልገው አይደለም። የነፃነት ተምሳሌት መሆኗ ነው። ቅኝ አለመገዛትን ያሳየች መሆኗ ነው። በሰሜን ኢትዮጵያ ተከስቶ የነበረውን ጦርነር እንኳን ሲገልጹ ‹‹ኢትዮጵያ እንዲህ ከሆነች…›› በሚል ነበር። ከእናት ምን እንማራለን? ማለታቸው ነው።
ዓድዋን ዛሬም ነገም የምናከብረው ለዚህ ነው። የሃምሳ ምናምን አገራት መውጫ በር ስለሆነ ነው። የጥቁር ሕዝቦችን አይበገሬነት ያሳየ ስለሆነ ነው። አንዳንድ ምሁራን እንደሚሉት ዓድዋ የአፍሪካ ወይም የጥቁር ሕዝቦች ድል ተብሎ ብቻ የሚገደብ አይደለም። ዓድዋ አጠቃላይ የሰው ልጅ የመብትና ነፃነት አስከባሪ የሆነ የነፃነት አርማ ነው።
በታሪክ እንደምናውቀው ቅኝ ገዢዎች አፍሪካን ብቻ ሳይሆን ከእስያና አሜሪካ አገራትም ቅኝ ገዝተዋል። ዓድዋ የእነዚህን ሁሉ የዓለም አገራት በደል ነው የደፈረ፤ ዓለም የተቀበለውን ባርነት ነው የገፈፈ፤ የሰው ልጆችን ባሪያ ያለመሆን መብት ያጎናፀፈ ነው።
‹‹Study.com›› የተባለ የጥናት ቋት ጣሊያን ቅኝ የገዛቻቸውን አገራት ይዘረዝራል። ከእነዚያ ውስጥ ግን ኢትዮጵያ ‹‹አልገዛም›› እንዳለች ይገልጻል። ጣሊያን በ1928 ዳግም ወረራ ለማድረግ ብትሞክርም እሱም እንደከሸፈባት የጥናት ቋቱ ይመሰክራል።
ዓድዋን ዛሬም ነገም የምናከብረው ለዚህ ነው። አውሮፓውያን ለአፍሪካ አገራት ያላቸው አመለካከት የምናየው የምንሰማው ነው። በዚህ የተንሸዋረረ አመለካከታቸው ውስጥ ዓድዋ እየገባ ሴራቸውን ያጋልጥባቸዋል። ምንም አያደርጉም ብለው የሚገምቷቸውን ጥቁሮች ምን እንደሚያደርጉ አሳይቷል።
የብዙ የዓለም አገራትን የነፃነት ታሪክ ካየን ከዓድዋ በኋላ ነው። እንዲያውም ከ20ኛው መቶ ክፍለ ዘመን አጋማሽ በኋላ ነፃ የወጡ ናቸው። ዓድዋ ግን በ19ኛው መቶ ክፍለ ዘመን መጨረሻ አካባቢ ነው ነፃነትን ለዓለም ያሳየ።
‹‹በእጅ የያዙት ወርቅ…›› ሆኖብን እንጂ ዓድዋ የሌላ አገር ታሪክ ሆኖ ቢሆን ኖሮ ቅናቱን አንችለውም ነበር። ይህን ድንቅ ታሪክ በዓለም አቀፍ የታሪክ ሰነዶች ማስመዝገብ ቀላል ነገር አይደለም። ዛሬ ‹‹ኃያል›› የምንላቸው አገራት ኃያል የሆኑት በምንም ተዓምር ሳይሆን ራሳቸውን አጋነው በማስተዋወቅ ነው፤ እኛ ግን እንኳን ማጋነን ያለውንም በሚገባ ማስተዋወቅ አልቻልንም።
ቅኝ አለመገዛታችን የመጣው በዓድዋ ነው። ቅኝ አለመገዛታችን ደግሞ ኢትዮጵያን በብዙ ነገር ‹‹በአፍሪካ ብቸኛዋ…›› እንድትባል አድርጓል። የራሷ ማንነት እንዲኖራት አድርጓል። ከሰሞኑ የአማርኛ ቋንቋን የአፍሪካ ሕብረት የሥራ ቋንቋ ለማስደረግ እየሰራች ያለችው ኒጀራዊት አርቲስት ራህመቶ ኪታ አማርኛ የዓለም ቋንቋ መሆን የሚገባው ነው ስትል ነበር።
ምክንያቷ ደግሞ የራሱን ፊደል የቀረጸ ጥንታዊ ቋንቋ ነው የሚል ነው። በዚሁ ጉዳይ ላይ በሰጠችው መግለጫ፤ ዓለም ላይ በርካታ ቋንቋዎች ቢኖሩም እንደ አማርኛ ጥንታዊ የሆኑ ቋንቋዎች ጥቂት በመሆናቸው መንከባከብና ማስተዋወቅ ይገባል ብላለች።
አርቲስቷ በቅርቡ የሰራችውን ‹‹ዘ ዌዲንግ ሪንግ›› የተሰኘ ፊልሟን ‹‹የጋብቻው ቀለበት› የሚል የአማርኛ ስያሜን በመስጠት ለአማርኛ ያላትን ክብር አሳይታለች። በፊልሙ የተሳተፉ ተዋንያኖችን ስም በአማርኛ አስጽፋለች። ይህን ያደረገችው የፊልም ባለሙያዎቹን ኃይሌ ገሪማ እና ሰለሞን በቀለ እንዲሁም በኒጀር የኢትዮጵያ አምባሳደር በማነጋገር ነው።
አርቲስቷ ለምን አማርኛንና ኢትዮጵያን ወደደች ከተባለ ምክንያቱ እንደተናገረችው ነው። አማርኛ ጥንታዊ ታሪኮችን የያዘ እና የራሱ ፊደል ያለው መሆኑ ነው። ይህ የሆነው ኢትዮጵያ ከጥንት ጀምሮ የራሷ በሆኑ ማንነቶች ስለቆየች ነው።
የብዙ አፍሪካ አገራት የሥራ ቋንቋ የቅኝ ገዥዎቻቸው ነው። ኢትዮጵያ ውስጥ ግን ጣሊያንኛ ከሌሎች የዓለም አገራት ቋንቋዎች በተለየ የሚታወቅበት ዕድል የለውም። የአንዳንድ ቦታዎችና ዕቃዎች ስያሜ ውስጥ እንደማንኛውም የዓለም ቋንቋዎች(ፈረንሳይኛ፣ አረብኛ…) ሊገኝ ይችላል።
የትኛውንም የዓለም ቋንቋ ማወቅ ቢቻል ጥሩ ነበር፤ ዳሩ ግን በቅኝ ገዥዎች ኃይል የራስን በማጥፋት ሳይሆን በፍላጎት ነው። ስለዚህ ኢትዮጵያ በቅኝ ገዥ በኃይል የተጫነባት ነገር የለም። ምናልባት በዘመናዊ መንገድ የመጣውን የባህል ወረራና የውጭ ናፋቂነት የምናይ ከሆነ እሱ በቅኝ ግዛት ሊባል አይችልም፤ ዜጎች ወደውና ፈቅደው፣ ተመችቷቸው የሚመርጡት ነው።
ዓድዋ ዛሬ ትናንት ነበር፤ ዓድዋ ዛሬም ነገም ነው ስንል፤ የኢትዮጵያን የትናንት ታሪክ፣ የዛሬ ምንነት እና የነገን ተስፋ የሚነግረን ነው። የትናንት አባቶች አገራቸውን በውጭ ወራሪ አናስደፍርም ብለው ከአንድ ሺ በላይ ኪሎ ሜትር በእግር ተጉዘው ዘመናዊ ጦር የታጠቀን ኃይል ዶግ አመድ አድርገው ታሪክ ሰርተዋል፤ ሉዓላዊነቷ ያልተደፈረች አገር አስረክበዋል።
ዓድዋ ዛሬ ናት ስንል የትናንቱን ክብር ዛሬም እናስጠብቃለን ለማለት ነው። የዛሬው ትውልድም የአይበገሬነትና የአገር ወዳድነት ወኔ ሊኖረው ይገባል ማለት ነው። ዓድዋ ነገም አለ ስንል ዛሬ ያስረከብነውን ነገር ይዞ ይቀጥላል ማለት ነው።
እኛ ዛሬ በአባቶቻችን ታሪክ እንደምንኮራው ሁሉ የነገው ትውልድም በዛሬዎቹ በእኛ እንዲኮራ እናድርግ ማለት ነው። ዓድዋ እንዲህ በትውልድ ቅብብሎሽ የሚቀጥል፤ የኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን የአፍሪካ፣ የአፍሪካ ብቻ ሳይሆን የጥቁር ሕዝቦች፣ የጥቁር ሕዝቦች ብቻ ሳይሆን የሰው ልጅ የነፃነት ምልክት አርማ ነው።
ስለዚህም የትናንቱን ዓድዋ ዛሬም ነገም እንዘክረዋለን!
ሚሊዮን ሺበሺ
አዲስ ዘመን የካቲት 24/2015