አዲሱን ዓመት በአዲስ ተስፋ ለመቀበል

2016 ዓ.ም እየገባ ነው፤ “እኛስ?”። እዚህ ላደረሰን ምስጋና ይግባውና ተወደደም ተጠላ፤ ፈለግነውም አልፈለግነውም (የማይፈልግ ካለ) ከ2015 ወደ 2016 ዓ.ም ይገባል። አሁንም ጥያቄው “እንዴት እንግባ?” የሚለው ነው። “እንዴት?”፣ ከነቆፈናችን፤ ከነቂም በቀላችን፤ ከነዘር ከረጢታችን፤ ከነጥላቻና ፍርሀታችን፤ ከነ ስጋትና ጭንቀታችን፣ ከነ እንትን ፖለቲካችን? በፍፁም መሆን የለበትም።

በፍፁም – – – መሆን ያለበት ከእነዚህ ሁሉ እድፎች (ወደንም ይሁን ሳንወድ ያቆሸሹን ቆሻሾች) ፅድት ብለን ነው አዲሱን ዓመት መቀበልና መቀላቀል ያለብን። አዎ፣ ወደ ፊት ሌሎች አዳዲስ ዓመታትን የምንናፍቅ፣ የምንመኝ – – – ከሆነ ፅድት ፅድትድት ብለን ወደ 2016 ዓ.ም መግባት ብቻ ነው ያለን ምርጫ።

ጉዳዩን እንደ ገጽዋ አቅም ሰፋ አድርገን እንመልከተው። አዲስ ዓመት የትም አለ። ግጭቶችም የትም አገር ነበሩ፣ አሉ፣ ይኖራሉም። የአገራት ልዩነቶች መውጫ መንገዶቻቸው ናቸው እንጂ ሌላ ምንም አይለያቸውም። “እወቅ ያለው በ40 ቀን፣ አትወቅ ያለው በ40 ዓመት” እንዲሉ ሆኖ እንጂ ላወቀበት ግጭት ያስ ተምራል።

ለተጠቀመበት የግጭት ወቅቶች በርካታ አጋጣሚዎችን፣ እድሎችን ነው ይዘው እሚመጡት። ያወቀበት ወደ ሀብትና ንብረት ይለውጣቸዋል፤ ፍቅርና ደስታ ያሳድጋቸዋል፤ “አትወቅ ያለው – – -” እንደ ተባለው ያላወቀበት ዘላለም ዓለሙን መገዳደያ ያደርጋቸዋል። ወደ’ማያባራ ጦርነት ያስፋፋቸዋል። የተለመዱ የስልጣን ጥም ማርኪያ ብልሀት ያደርጋቸዋል። ሲወርድ እንደሚጨብጣቸው ረስቶ እየረገጠ የሚወጣቸው መሰላል ያደርጋቸዋል። ይህንን ትተን ወደ አዲሱ ዓመታችን እንምጣና ርእሳችንን ከፈትፈት እናድርገው።

የእኛ አገር ፖለቲከኞች ወቅታዊ ሁኔታና ይዞታ በስነልቦና ሊቃውንት አተያይ ቢፈተሽ በዋነኛነት ከአንድ አበይት ችግር አይዘልም። ይህን ችግር ምናልባትም በባለሙያዎች ሲተነትኑት እንደ ነጠላ ቁጨት ዘርፍ ዘርፍ እያወጡ ሊበዙ ይችሉ ይሆናል። ይበዙናም ችግሮቻችንን ያንኑ ያህል አብዝተው ያሳዩን ይሆናል። ችግር ፈጠራው ላይ በርትተን መፍትሄ ማምጣቱ ላይ ሰንፈናልና የሚባለው ሁሉ ቢባል የመቀየም ሆነ ”ለምን?” ብሎ የመጠየቅ ሞራል አይኖረንም።

ከላይ አበይት ስነልቦናዊ ችግር ያልነው፣ ይህ በዚህ ጸሐፊ እምነት ብቻ ነው፣ እርስ በእርስ ያለ መተማመን የሚያመጣው ስጋትና ስጋቱም የሚፈጥረው ፍርሀት (ፎቢያ) ነው። ይህ እውነታ እያደገ ከሄደ የዘር ጥላቻ (xenophobia) ሊለወጥ እንደሚችል ማሰብም ተገቢ ነው።

በአንድ ጽሑፌ ላይ ተጠቅሜበት እንደ ነበረው የመተማመን አለመኖር መነሻው አለማመንና አለመተማመን ሲሆን፣ የአለመተማመን ምንጩ ደግሞ ስር የሰደደ የመተማመን ፍርሀት (pistanthro­phobia) ነው። ይህም ወደ ፊት አደጋ ሊያደርስብኝ ይችላል፤ ሊክደኝ ይችላል፤ በዚህ ምድር ላይ ምንም አይነት ጥሩ ነገር የለም፤ ሰው ሁሉ ምቀኛ ነው፣ የእከሌ ብሔር የእከሌን ብሔር – – – ከሚል ስጋት የሚመነጭ ፍርሀት።

ይህ እጅግ አስከፊ ፍርሀት፣ በተለይ በስነልቦና ምሁራን ዘንድ ከፍተኛ ትኩረት የሚሰጠውና ለህክምናውም ቀን ከሌት የሚለፋበት ችግር (ህመም) ነው። አሁን ጥያቄው ይህንን ችግር፣ እንደ አገር እዚህ እኛ ጋ አለ ወይስ የለም?” የሚለው ነው። ከሌሉ እሰየው፤ ካሉ “ምን እናድርግ?” በሚለው ላይ (የሰላምና እርቅ ኮሚሽንን የመሃል ዳኛ አድርገንም ቢሆን) መነጋገር ያስፈልጋል።

ወደ ኋላ መለስ ብለን የአገራትን ልምድ ብንመለከት ሁለቱም አይነት (ተደጋጋፊ) ፍርሀቶች / እርስ በእርስ ያለ መተማመን የሚያመጣው ስጋትና ስጋቱ የሚፈጥረው ፍርሀት (ፎቢያ) እና የዘር ጥላቻ (xenophobia) ፎቢያ/ አገራትን አተራምሰዋል።

ሁለቱም አይነት ህመሞች አገራትን ደቁሰዋል። ሁለቱም አይነት በሽታዎች ኃይማኖት ተቋማት ውስጥ ሳይቀር ገብተው አጫርሰዋል። ሁለቱም አይነት ማህበራዊ እንከኖች ዛሬ ዓለማችን እያስተናገደች ላለችው ሽብርተኝነት መወለድ የየድርሻቸውን አበርክተዋል።

ችግሩ በዓለማችን ለተስተናገዱና የሚሊዮን ንፁሀንን ህይወት ለቀጠፉ ጦርነቶች በአንድም ይሁን በሌላ እጃቸው አለበት። ታዲያ የእስከዛሬው የዓለማችን ልምድ ይህ ከሆነ ጥያቄው “ከእነዚህ አጫራሽ ፍርሀቶች፣ ችግሮች ለመላቀቅ የሚደረገው ሙከራ ለምን የቅድሚያ ቅድሚያ አይሰጠውም?” የሚለው ይሆናል።

አዲስ ዓመት ነው ብለን ነው የተነሳነው። በመሆኑም ጉዳዩን ከዚህ በላይ አንለጥጠውም። ይህንን ስንል ግን ማለት ያለብንን ማለት የለብንም ማለት አይደለም። የሰነበትንበት ሁኔታ ብዙም ደረት የሚያስነፋ አይደለም። የፕሪቶሪያው ስምምነት ስድስት ወራትን እንኳን ሳያስቆጥር ወደ ሌላ እቶን ውስጥ የገባንበት ሁኔታ ነው የገጠመን።

የሚቀጥለው ስምምነት የት እንደ ሆነ ባይታወቅም የሆነ ስምምነት እንደ ሚጠብቀን ግን መጠራጠር አይቻልም። ስጋቱ አሁንም ከዛ ስምምነት በኋላ ወደ ሌላ እቶን የመግባት አለመግባታችን ጉዳይ ነው። ሁሉም በዚህች ጉዳይ ላይ ሊቆዝም፤ ከፍርሀትና እርስ በእርስ ጥርጣሬ ሊላቀቅና በአንተ ትንብስ፣ አንቺ ትብስ የመተሳሰብ ስሜት ወደ አዲሱ ዓመት ሊገባ፤ ወይም አዲሱን ዓመት ሊቀበል ይገባል።

ልብ እንበል፣ እንደ አገርና ህዝብ ከላይ የጠቀስነው ፍርሀት ከለብንና ካደገ/እርስ በእርስ ያለ መተማመን የሚያመጣው ስጋትና ስጋቱም የሚፈጥረው ፍርሀት (ፎቢያ) እና የዘር ጥላቻ (xenophobia) ፎቢያ /ምንም መትረፊያ የለንም፤ አይደለም ሁለቱ አንዱ እንኳ ሰፍሮብን ከሆነ መውጫ ቀዳዳችን ጠባብ ነው።

በ“እኛ” እና “እነሱ”፣ በ“እኔ” እና “አንተ”፤ በ“መጤ” እና “ነባር” – – – አተያይ ከተቀፈደድን፣ ምንም አትጠራጠሩ ሁለቱም ፎቢያዎች አሉብንና እግዞኦታ ያስፈልገናል። ቁጭ ብሎ መነጋገርን መተማመንን ማስፈን ይጠበቅብናል።

ሁሌም እንደሚመክረው፣ ሲወራረድም እንደ መጣው አዲስ ዓመትን በአዲስ መንፈስ መቀበል ተገቢ እንደ ሆነ ነው። አዲስ ዓመትን በሆታና እልልታ፣ በደስታና ጭፈራ፣ በአብሮነትና መተሳሰብ መቀበል ተገቢ መሆኑ ነው ሲሰበክ የኖረው። ዛሬም ያው ነው መቀጠል ያለበት።

ኢትዮጵያ አገራችን እንደ ሆነች ለማንም የምትበቃ፣ ሁሉን የታደለች አገር ነች። በጎሳ፣ በብሄር፣ በሀይማኖት፣ በመንደር፣ በጎጥ በስርጓጉጡ ሁሉ ሊጣሉባት የምትገባ አገር አይደለችም። እኛ ዜጎችም እነዚያን ሁሉ ሺህ ዓመታት በሠላም እንደ ኖሩ ሁሉ አሁንም ሆነ ወደ ፊት እነዚያኑ ማስቀጠል እንጂ ያልተፈለጉ ፍርሀቶች (ያለመተማመን ፍርሀትና በእርስ በርስ ጥላቻ መጠባበቅ) ሰለባ መሆን የለብንም።

“እንቁጣጣሽ” ትርጉሙ ጥልቅ ነው፤ ማህበረ- ባህላዊ እሴት የሆነው “እንኳን አደረሳችሁ” ትርጉሙ ከውቅያኖስ የሰፋ ነው፤ “አበባየሽ/ህ ወይ – – – ለምለም” የትም የሌለ የእኛው ለእኛው የሆነ ትውፊታችን ነው፤ በዓመት በአል ዳቦና ጠላ ከኬክና ውስኪ ይበልጣል እኮ። ታዲያ እነዚህ ሁሉ ባሉበት እንዴት ከፍርሀት፣ ከቆፈን – – – መውጣት ይሳነናል? እንዴት የእርስ በርስ ግጭት አዙሪትና ድብርት መውጣት አቃተን፤ አያቅተንም!!!

መልካም አዲስ ዓመት!!!

ግርማ መንግሥቴ

አዲስ ዘመን ማክሰኞ ነሐሴ 30 ቀን 2015 ዓ.ም

Recommended For You