ሀገራችን ኢትዮጵያ በተግባቦት መንፈስ ሀገራዊ አንድነትን ለመፍጠር የምክክር ኮሚሽን አቋቁማ፤ ከዛም አለፍ ሲል የተለያዩ የምክረ ሀሳብ መድረኮችን አዘጋጅታ የአንድነት ጎዳናዎቿን በማሰናዳት ላይ ትገኛለች። ከሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን አንጻር ስንቃኘው ያለፉትን ሁለትና ሦስት ዓመታት ሀሳብ በማሰባሰብና ምቹ የአንድነት ጎዳናዎችን በመጥረግ ሂደት ላይ ተጠምዶ ቆይቷል። አሁን ላይ ደግሞ ቅድመ ዝግጅቱን አጠናቆ ለውይይት የሚያበቃውን የመጨረሻ ምዕራፍ ተግባር ላይ እንደሚገኝ ነው መረጃዎች የሚጠቁሙት።
ከዚህ አኳያ ሲታይ አሁን እንደ ሀገር ከምንግዜውም በላይ ራሳችንን ለተግባቦት የምናዘጋጅበት ጊዜ ላይ ነን። ምክንያቱም ባለመግባባትና ያለፈን በማስታወስ የከፈልናቸው ዋጋዎች ዛሬም ጥዝጣዜአቸው አልሻረም። የባለፈው ጊዜ ጦርነት፣ የባለፈው ጊዜ የብኩርና ሽሚያ ዛሬ ላይ ብዙ ዋጋዎችን እየከፈልን እንደሆነ እኔና እናንተ ምስክሮች ነን።
በመሆኑም ይሄንን ችግር መሻገር የሚያስችለንን ምክክር ካላደረግን፤ እንዲሁም ከልብ በሆነ ስሜት ለይቅርታና እርቅ ራሳችንን ካላዘጋጀን በዚሁ አግባብ ችግሩን ካልተሻገርን፤ የሚመጣው ካለፈው የሚብስ ነው የሚሆነው። ያለፉት የእውነትም ሆኑ የሐሰት ትርክቶችን ዘግተን በአዲስ መነቃቃት መጪውን ስንቀበል ነው የጥንቱ ኃያልነታችን የሚመለሰው።
እኛን እና ታሪካችንን በተመለከተ ሁልጊዜም አንድ እውነት አለ። ፍቅርን የቋጠረ፣ አንድነትን ያቀለመ አብሮነት መነሻችን እና መድረሻችን ነው። ዓለም ያወቀንና የተቀበለን በዚህ ማንነታችን በኩል ነው። በዚህ ረገድም የገባን ብዙ ቢሆንም፤ እንደገባን አለመኖራችን ግን እየጎዳን ነው። በትላንት ጉያ ውስጥ ያሉ የጀግንነትና የሉዓላዊነት፣ የነፃነትና የዘመናዊነት ቀንዲሎቻችን፣ የአብሮነት ውጤቶቻችን እንደሆኑ እያወቅን እንኳን ለዚህ ክብር ዋጋ ስንከፍል አንታይም።
ኢትዮጵያ ለፍቅር ማደያ ናት። እኛ ለሰላምና ለአብሮነት መነሻ ታሪኮች ነን። አሁን ላይ ብርቅ የሆኑብን ዘመናዊነትና ሥልጣኔዎች፣ ፊተኝነትና ቀዳማዊነት ከእኛ ተነስተው ወደ ዓለም የተሰደዱ ናቸው። ታዲያ ለምን ራቁን? ለምንስ ሸሹን? ከተባለ፤ መልሴ፣ ከፍቅር ስለራቅን ነው የራቁን፤ ከአንድነትና ከአብሮነት ስለሸሸን ነው የሸሹን የሚል ሆናል።
በመሆኑም ወደዚህ የፍቅር ሰገነታችን፤ የአንድነት መድረካችን ለመመለስ ሰፊ የመነጋገሪያ ሜዳ ያስፈልገናል። ዘረኝነትና ብሔርተኝነት ደብዝዘው ኢትዮጵያዊነት ብቻ የሚቀነቀንበት ፖለቲካ፣ ራስወዳድነትና ጥቅመኝነት ኮስሰው አብሮነት የሚጎመራበት መድረክ ያሻናል። ምክንያቱም አዕምሯችንን አጽድተን ልዩነቶቻችንን እስካላጠበብን ድረስ ችግሩ ከመባስ ባለፈ የሚሻል ሕመም አይኖረንም። ሳይቃጠል በቅጠል..የሚለው አባባል እዚህ ጋ መነሳቱ ግድ ነው። የባሰ ዋጋ ሳንከፍል፣ ከዝቅታ ወደ መደፋት፣ ከድጡ ወደማጡ ሳንገባ አብሮነታችንን የምንመልስበትን እድል መፍጠር ይጠበቅብናል ።
ከየትኛውም በጎ ነገር በላይ እድሎቻችን በመነጋገር ውስጥ ነው ያሉት። የሰው ልጅ ወደዚች ምድር ሲመጣ በፍላጎት፣ በምኞት እንዲሁም በተለያየ ሀሳብ ተከሽኖ ነው። አይደለም ከሌላው ጋር ከራሳችን ጋር እንኳን የማንግባባበት ጊዜ አለ። ይሁን እንጂ ተነጋግረን እንድንግባባ፣ ተመካክረን አብረን እንድንኖር ልዕለ አዕምሮ ተሰጥቶናል።
አእምሮ ልዩነቶችን ለማስታረቅ ትልቁ አቅም ነው። የይቅርታና የፍቅር ዋጋን ለማሰላሰል ጥልቁ ጉልበት ነው። ጥላቻን በፍቅር ለመቀየር፣ በእርቅና በምክክር ወደአብሮነት ለመመለስ ነው ኃይል ነው። ለጥላቻ እየበረታ ለፍቅር የሚደክም አዕምሮ አልተሰጠንም። እንዲያውም ሚዛን ላይ እናውጣው ካልን የተሰጠን አዕምሮና ልብ ከፍቅር ውጪ ጥላቻን የማያውቅ ነው። ታላቁ የነፃነት አባት ኔልሰን ማዴላ ይሄን እውነት ሲገልጸው ‹ፍቅር ተፈጥሯዊ፣ ጥላቻ ግን በትምህርት የምናገኘው ነው› ብሎ ነው።
ከዚህ የነፃነት ታጋይ አስተምህሮም ሆነ ከሌላ ዓለማዊና መንፈሳዊ ንጻሬ አኳያ ስናየው በመካከላችን ያለው የእኔ የእኔ ሽኩቻ እንደፖለቲካ ባሉና ራስን ብቻ ከመጥቀም አባዜ ከሚመነጩ፣ ርህራሄ አልባ እሳቤዎች የተፈጠሩ እንደሆኑ መረዳት ይቻላል። ያለፉትን በርካታ ዓመታት አዕምሯችን ለአንድነት የሚሆን ዋጋ ሲከፍል አልታየም። በጥሎ ማለፍ ውስጥ የጎለመሰ ነው። የጥሎ ማለፍ እሳቤ ደግሞ ትውልዱን መሰል ኢ-ሰብዓዊ ልምምዶችን እያስተማረ ሀገርን ባዶ የሚያስቀር ነው።
ፖለቲካችን አሁን ላሉብን ማኅበራዊ ነውጦች ጣት የሚቀሰርበት የመጀመሪያው ተጠያቂ ነው። ይሄ የብዙዎቻችን እምነት ቢሆንም ፖለቲካውን ለማጥራት ጥረት ስናደርግ ግን አንታይም። የሚመጣውም ሆነ የሚሄደው ፖለቲከኛ ሥልጣንን ለሕዝብ ሰጥቶ ሀገርን በማገልገል መንፈስ ውስጥ መጥቶ የሄደ ፖለቲከኛ የለም። ይሄን አይነቱ ራስን ማዕከል ያደረገ ልምምድ ትውልዱን ለራስ ወዳድነትና ለጥቅመኝነት ዳርጎታል።
ሀገር የፖለቲካ መልክ ናት። እኔና እናንተ ሳንቀር እንኳን ከማኅበረሰባችን በላይ ፖለቲካ ጸንሶ የወለደን የፖለቲከኞቻችን የአስተሳሰብ ውጤቶች ነን። እዛ መንደር መነጋገርና መግባባት ቢኖር እኔና እናንተ መንደር ተነጋግሮ መግባባት አይቸግረንም። ፖለቲከኞቻችን ያሸረጡትን የራስወዳድነት ሽርጥ አውልቀው አንድነትን ይልበሱ። ያኔ ሕዝብ ማቁን አውልቆ ፀዓዳውን ይለብሳል። ዓላማችን በእርቅና በተግባቦት ኢትዮጵያን ማስቀጠል ከሆነ፣ ለጥላቻ የበረታ አዕምሯችን ለፍቅር እንዲንበረከክ እናለማምደው። ሕዝብ ተኮር በሆነ ብዙኃነት በፖለቲካችን አናት ላይ የፍቅር ፀሐይ ትውጣ።
ይቺ ሀገር የእኔና የእናንተ አንድነት ካላጸናት፣ የውጪ ርዳታና ድጎማ አያጸናትም። ሁሉም በክፍተቶቻችን እየገቡ መፍትሔ አልባ መለያየትን የሚፈጥሩብን ናቸው። በነጠረና ብዙኃነትን በተላበሰ ምክረ ሀሳብ ቀዳዳዎቻችንን ደፍነን መጪውን ጊዜ እስካልተቀበልን ከዝቅታ የሚታደገን አይኖርም። በጀመርንው የምክክር መድረክ ላይ ሀሳብ በመስጠትና በመቀበል ኢትዮጵያን ማሻገር ለነገ የማንለው ኃላፊነታችን ነው።
ታላላቅ ሥልጣኔዎች ከሃሳብ የሚጀምሩ ናቸው። ዘመን ተሻጋሪ በሆነ የብዙኃነት እውነት ምድርን ያቆነጁ ተግባራት እንኳን መነሻቸው ሀሳብ ነበር። የነሶቅራጠስና የነአርስቶትል ተራማጅ አመለካከት ዛሬም ድረስ ሕይወታችን ሆኖ በእያንዳንዳችን ልብ ውስጥ የሚኖረው ምክንያታዊነትን ባዘለ መንገድ ነው። ሀሳቦቻችን ምክንያታዊነትን ያዘሉ ከሆኑ ወደ ከፍታ የማይሄድበት ምንም ምክንያት የለም። ሀሳቦቻችን ለአንድነት መንገድ በሚዘጋ ራስወዳድነት ውስጥ ከሆኑ ግን በምንም መፍትሔ አናገኝም።
አጉል መሻት ከሸነቆረው የዘረኝነትም ይሁን የጥላቻ ቀዳዳ መውጫችን ምክረ ሀሳብ ነው። በሀሳብ ካልተሸናነፍን በምንም ብንሸናነፍ ልክ አንሆንም። ያለፉ ታሪኮቻችን የጦርነት እና የኃይል መድረኮች ነበሩ። ኮሽ ባለ ቁጥር ጦር እየተማዘዝን ስንገልና ስንሞት ነበር። በዚህም እልፍ የወየቡ ታሪኮችን ከመጻፍ ጎን ለጎን ለዛሬ ጉስቁልና መነሻ የሚሆኑ ቁርሾዎችን ፈጥረናል። ከሀሳብ ጎሎ በኃይል ለበረታ አእምሮ ገሎ ከመሞት በቀር ጀግንነት የለውም። ተነጋግረን በመግባባት ተነጋግሮ የሚግባባ ትውልድ እንፍጠር። ላለውም ሆነ ለሚመጣው ትውልድ በኩረ መነሻዎቹ እኛ ነንና ታርቀን እርቅን፣ ተፋቅረን ፍቅርን፣ አንድ ሆነን አንድነትን ልናስተምረው ይገባል።
ሀሳብ የሌላት ሀገር ማር የሌለው ቀፎ ናት። ቀፎ ማር እንዲሰጥ አበቦች ባሉበት፣ ለምለምና ለንቦች ምቹ በሆነ ቦታ ይሰቀላል። ይሄ ካልሆነ ግን ንቦች ወደቀፎው አይገቡም፣ ቀፎውም ማር አይዝም፤ በተስፋ ብቻ ማር መቁረጫ ቀን እንቆጥራለን። ልክ እንደቀፎው ሀገር ሰላምና ብልጽግና፣ አንድነትና ፍቅር እንዲኖራት የሀሳብ ሥልጣኔ፣ የእርቅና የምክክር ባሕል ያስፈልጋታል። አሁናዊው የሀገራችን ሁኔታ ከአበባ እንደራቀው ማር አልባ ቀፎ ነው። ቀፎው ማር እንዲይዝ የቦታ ለውጥ ያስፈልገዋል። ሀገራችን ሰላም እንድትሆን የምክክር መድረክ ያስፈልጋታል።
ትግላችን ከሌሎች ሀገርና ሕዝቦች ጋር ቢሆን ጥሩ ነበር። እኛ ግን የምንታገለው ከራሳችን ጋር ነው። እያወደምን ያለነው የራሳችንን ታሪክ ነው። እያበላሸን ያለነው የራሳችንን ትውልድ ነው። በእኛው እኛው እየተጎዳን ብዙ ዘመናትን ተሻግረናል። ሰው ከራሱ ጋር እንዴት ይጣላል? የሰሉ የክፋት አንደበቶቻችን ፍቅርን እንዲዘምሩ፣ ለመለያየት የበረቱ ምላሶቻችን ስለአንድነታችን ደጅ እንዲጠኑ ከፊታችን ያለውን ሀገራዊ ምክክር እንጠቀምበት።
ሕልሞቻችን መግባባትን ካለበሱ ከምኞት ባለፈ ፍሬ አይሰጡንም። በብሔር ደፈጣ የመጣ ንበት ረጅም ጎዳና ከድህነትም ሆነ ከኋላቀርነት አልታደገንም። የፉክክር ቤት ሳይዘጋ ያድራል እንደሚባለው በጋራ ጉዳያችን ላይ ፉክክር ውስጥ የገባንበት ሁኔታ ነው የሚስተዋለው። የሚመጣው ካለው ካልተሻለ፣ ያለው ካለፈው ካልበረታ የተሻለ ነገር ማለማችን ፋይዳ አይኖረውም። በፉክክር ጉዟችን ካለውሀ ባዷቸውን ያስቀመጥናቸው ብዙ ማድጋዎች አሉን። ሊያጠግቡንና ሊያረኩን የሚችሉ ታሪክና እሴቶቻችን ወዳጅነትን አጥተን ደብዝዘን አደብዝዘናቸዋል።
በሀሳብ ልውውጥ በሀሳብ የበረታ ትውልድ መሥራት ከየትኛውም ዓበይት ጉዳያችን ፊተኛው ነው። ለሁሉም ግፍ ያለፉትን ሀምሳ ዓመታት እናነሳለን። እኛም እኮ የዚህ ትውልድ አንድ አካል ሆነን እየኖርን ነው። አሁን ላለችው ኢትዮጵያና አሁን ላለው ትውልድ ምን እያደረግን ነው? ወቃሽ ከመሆን እና ያለፈውን ከመተቸት ውጪ ምን የሚያስመሰግን ሥራ ሠራን? የቆምነው እኮ በዛ ዘመን የፍቅርና የአብሮነት ክንድ ነው። የምንጠራው እኮ አባቶቻችን ባጸኑት የአንድነት ስም ነው። እንጂማ ምን ስም አለን? ከጥላቻና ከመገፋፋት ሌላ ምን ያተረፍነው ነገረ አለ?
የሄደው እንዳለ ሁሉ የሚመጣም ትውልድ አለ። ለመመስገንም ሆነ ለመተቸት ጊዜው የእኛ ነው። ያለፈውን የፖለቲካ ሥርዓት እንደኮነንን ሁሉ መጪው ትውልድ እኛ ባነወርነው ሀምሳ ዓመታት ላይ የእኛን ትውልድ ጨምሮ እንዳያስነውረን ዛሬን በጎ እንሥራ። ትናንሽ ቀዳዳዎቻችን ሰፊ እስኪሆኑ ሳንጠብቅ በቶሎ መድፈንን እንልመድ። አንዳንድ ንትርኮች ትላንት ላይ ተቋጭተው ቢሆን ዛሬ ላይ በዚህ ልክ አይበድሉንም ነበር። የዛሬ ትናንሽ መመላለሶች ነገ ላይ የበረቱ ሆነው ዋጋ እንዳያስከፍሉን ማሰቡም ተገቢ ነው።
ትውልዱ የፍቅር ውርስ ያስፈልገዋል። ወንድማማቾች በቀይ ምንጣፍ ላይ ተያይዘው ሲራመዱ እንዲያይና ለዛ ክብር ራሱን እንዲያዘጋጅ ምልክት እንስጠው። ከዛሬ አርቆ የተስፋ ነገን እንዲያይ የመነጋገር ውርስን እናውርሰው። በፖለቲካውም ሆነ በፖለቲከኞቻችን ስጋት የወደቀበት ትውልድ እየተፈጠረ ነው። ተስፋ እንጂ ስጋት ማንንም አጽንቶ አያውቅም። ክፍተቶቻችን በፍቅር ተሞልተው፣ በእርቅና በምክክር ታርቀው ጦርነትን እርም የሚል ትውልድ ዘርተን እናብቅል።
ያለፈውን ትተን መጪውን የምንቃኝበት በፍቅር ጀምሮ በፍቅር የሚያበቃ አዲስ ታሪክ ያስፈልገናል። የቂም በቀል ሳይሆን የወንድማማችነት ውርስ ነው የሚያስፈልገው። ሀገር ሰላምን ባነገቡ በላቁ ሀሳቦች ካልተማገረች የዘላቂነት ዋስትና አይኖራትም። ይሄ ጊዜ ከመቼውም በላይ ራሳችንን ከጦርነት ነፃ የምናወጣበት፣ የወንድማማቾች ግፊያ የሚያበ ቃበት ነው። ስለሀገራችን ሁሉንም በጎ መስዋዕት የምንከፍልበት ነው።
የምንገፋፋው ባልገባንና ባልተረዳንው ያለፈ ታሪክ እንደሆነ ግን ታውቃላችሁ? በሀገራችን ጥቂቶች የሚነዱት እልፍ መንጋ አለ። መንጋው ከኋላ ሆነው ለሚነዱት መጠቀሚያ ነው። እናም አልገባንም የምንለው በምክንያት ነው። ሳይገቡን ከምንጣላባቸው ይልቅ ገብተውን የሚያዋድዱን እልፍ የጋራ በረከቶች አሉን። ወደገቡንና የጋራችን ወደሆኑት ፀጋዎቻችን እስካልተመለስን ድረስ ባልገቡን ነገሮች ዋጋ መክፈላችን ይቀጥላል።
ትውልዱን በነገር መርዘን ጎራዴ የምንማዘዘው ምንም ባገባን መሆኑ የምንጊዜም አግራሞቴ ነው። ታሪክ ያዛነፋቸው እና እኛው ራሳችን ያዛነፍናቸው የመለያየት ቁርሾዎች ለማንም እንደማይጠቅሙ ከተረዳን ሰንበትበት ብለናል። እንዳረዳዳችን ግን ከማይጠቅመን የኩርፊያና የመለያየት መንፈስ ውስጥ ስንወጣ አንታይም። ዛሬም ድረስ በነዛ ባልገቡን ነገሮች ስር ቆመን ዋጋ ከፍለን ዋጋ የምናስከፍል ነን።
በሀገራችን ሰማይ ላይ የተስፋ ፀሐይ እንድንወጣ ምሥራቅ መሆን አለብን። ምሥራቅ በሌለበት ፀሐይ አትኖርም። ምሥራቅ ካለ ጀምበር አለች። ጀምበር ካለ ትንሳኤ አለ። በእርቅና በምክክር ለሀገራችን የፀሐይ መውጫ አድማስ ሆነን ትውልዱን የፍቅር ፀሐይ እናሙቀው የመጨረሻ መልዕክቴ ነው።
በትረ ሙሴ (መልከ ኢትዮጵ)
አዲስ ዘመን ሰኞ ጥቅምት 19 ቀን 2016 ዓ.ም