በአይናችን ብሌን የመጣው ሕገ ወጥ ግብይት ፤

ሕገ ወጥ የግብይት ስርዓቱ ሲድህ ሲድህ በማንደራደርበት በሀገራችን የአይን ብሌን ማዳበሪያ ላይ ደርሷል። የህልውናችን መሠረት፣ የግብርናችን የጀርባ አጥንት የሆነው ማዳበሪያ ላይ እጁን አስገብቷል። መቼም አይደፈርም። አይነካም። አይሞከርም። ብለን በምንተማመነው የማዳበሪያ ግብይትና ስርጭት እጁን ማስገባት ከቻለ ነገ ተቋሞቻችንና መዋቅሮቻችንን እንደማይቆጣጠር ምን ዋስትና አለን ።

ከጨረታ፣ ከግዥ፣ ከማጓጓዝ እስከ ስርጭት በየደረጃው ባለ የመንግስት መዋቅር ይሳለጣል ብለን በምናምነው የማዳበሪያ ግብይት ካች አምና እና አምና ጥቂት ሕገ ወጦች አልፎ አልፎ የታዩበት ዘንድሮ እልፍ አእላፍ ሆነው ሲራኮቱበት ታዝበናል። ስድ የተለቀቀው ሕገ ወጥ የግብይት ስርዓት ከሕዝባችን 85 በመቶ የሚሆነው ዜጋችን ኑሮውን በመሠረተበት፤ ለሀገሪቱ ጥቅል ብሔራዊ ምርት ድርሻው 47 በመቶ በሆነው ግብርና አንገት ላይ ሸምቀቆውን እያስገባ ነው። በጊዜ አደብ እንዲገዛ ካልተደረገ በመሠረታዊ የፍጆታ ሸቀጣ ሸቀጦች ላይ እንዳደረገው ሸምቀቆውን ስቦ ያንቀዋል። ይህን አደረገ ማለት በ117 ሚሊየን ሕዝብ እና በሀገር ጉሮሮ ላይ ቆመ ማለት ነው።

በተለይ ከአለፉት ሁለት አስርት ዓመታት ወዲህ ያለ አፈር ማዳበሪያ ግብርና የሚታሰብ አይደለም ። መሬቱ ማዳበሪያ ለምዷል። ይህን የተረዱ የሕገ ወጥ ግብይቱ ተዋናዮች ገበሬው መሬቱ ጦም ከሚያድር የተጠየቀውን እንደሚከፍል እርግጠኛ ስለሆኑ በግብይት ሰንሰለቱ ሰርገው በመግባት ከሙሰኛ አመራር፣ የልማት ጣቢያ ሰራተኛና ስነ ምግባር ከጎደላቸው ከሕብረት ስራ ማህበራት አመራሮች ጋር በመመሳጠር፤ እንዲሁም ዘንድሮ የተፈጠረውን የአቅርቦት መዘግየትና መስተጓጎል እንደ ጥሩ አጋጣሚ በመጠቀም መንግስት በከፍተኛ ድጎማ ለገበሬውን ያቀረበውን ማዳበሪያ በሁለትና በሶስት እጥፍ እስከ መቸብቸብ ደርሰዋል።

ያለው ውስን ማዳበሪያ በወቅቱ እንዳይከፋፈል በማድረግና ሰው ሰራሽ እጥረት በመፍጠር ቀውስ ፈጥረዋል። ሕገ ወጥ የግብይት ስርዓቱ መንግስት በወቅቱ ማዳበሪያን ካለማቅረቡ ጋር አብሮ የማዳበሪያ እጥረቱ ተባብሶ በሀገራችን ታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ ገበሬውን ሰልፍ እስከማስወጣት ደርሷል። ለሴራ ትንተና በር ከመክፈቱ ባሻገር ወደ መልካም አስተዳደር ችግርነት ተሸጋግሯል። ሕገ ወጥ የግብይት ስርዓቱ ሀገሪቱ በሌላት የውጭ ምንዛሬ አቅም ከ1 ቢሊየን ዶላር በላይ ወጭ አድርጋ የገዛችውን ማዳበሪያ እንደ ዘይቱና ሲሚንቶው ለመቆጣጠር ዕንቅስቃሴ መጀመሩን ታዝበናል።

አልቀመስ ባለው፣ ሸማቹን ባማረረውና ኑሮውን ባመሰቃቀለው የኑሮ ውድነት ላይ ቤንዚን አርከፍክፏል። በሚቀጥለው ዓመት የኑሮ ውድነቱና የዋጋ ግሽበቱ አሁን ካለበት እንደሚባባስ ለመተንበይ ነብይ መሆን አይጠይቅም። ከዓመት ዓመት ክንዱ እየፈረጠመ የመጣው ሕገ ወጥ የግብይት ስርዓት ነገ የህልውናችንና የሰላማችን ስጋት መሆኑ አይቀርምና መንግስት ነገ ዛሬ ሳይል ስርዓት ሊያሲዘው እና በግብይት ስርዓቱ የሕግ የበላይነትትን ሊያረጋግጥ ይገባል። ካልሆነ እንደ ጣሊያኑ የሲሲሊ ማፍያ በመንግስት ውስጥ ያለ ሌላ መንግስት መሆኑ አይቀርም።

መንግስት መሠረታዊ የፍጆታ ምርቶችን፣ ነዳጅንና ማዳበሪያን በብዙ ቢሊየኖች እየደጎመ በሌለ የውጭ ምንዛሬው ቅድሚያ ሰጥቶ እያስገባ ሕገ ወጥ የግብይት ስርዓቱ ግን አመድ አፋሽ እያደረገው እና ከሕዝብ ጋር እያቃቃረረው ስለሆነ አበው ሳይቃጠል በቅጠል እንዲሉ መንግስት ከዳተኝነት አባዜ ወጥቶ ሕገ ወጥ የግብይት ስርዓቱን በፖለቲካዊ ቁርጠኝነት ታግዞ ሊያስተከክለው ይገባል። የግብይት ስርዓታችን ጤናማ ቢሆን ኑሮ የዋጋ ግሽበቱም ሆነ የኑሮ ውድነቱ እዚህ ደረጃ ባልደረሰ። የሀገራችንን የዋጋ ግሽበት የተለየ የሚያደርገውም እሴት በማይጨምሩ ሕገ ወጦች የታነቀ መሆኑ ነው።

ይህ ማለት ግን የፍላጎትና የአቅርቦት አለመጣጣም፤ አለማቀፉ የዋጋ ግሽበትና የዩክሬን በራሽያ መወረር ለዋጋ ግሽበቱም ሆነ እሱን ተከትሎ ለመጣው የኑሮ ውድነት አስተዋጾ የለውም ማለት አይደለም። ዝቅ ብዬ ዋቢ ያደረግሁት አስደንጋጭ ጥናት እንደሚያትተው ደላላው ወይም የሕገ ወጥ ግብይቱ ተዋናይ በሀገራችን ለሚስተዋለው የዋጋ ግሽበት 60 በመቶ ድርሻ አለው። መንግስት ይሄን አጉራ ዘለል የግብይት ስርዓት ከቁጥጥር ውጭ መሆኑ ሳይባባስ አደብ ቢያስገዛ የዋጋ ግሽበቱን 60 በመቶ የመቀነስ ዕድል አለው ማለት ነው።

የኢትዮጵያ ፖሊሲ ጥናት ኢንስቲትዩት በዚያ ሰሞን አንድ አስደንጋጭ የጥናት ውጤት ይፋ አድርጓል። ኢትዮጵያ ምግብ ውድ ከሆነባቸው የአፍሪካ ሃገራት ከቀዳሚዎቹ ተርታ መሰለፏንና ከዓለም 8ተኛ ደረጃ፤ ከዚምባቡዌ ቀጥላ ኢትዮጵያ በአፍሪካ ከፍተኛ የዋጋ ግሽበት ያለባት ሃገር እንደሆነች አርድቶናል። አጠቃላይ የዋጋ ግሽበቱ 49.1 በመቶ ሲሆን የምግብ የዋጋ ንረት ከፍተኛውን ድርሻ ይዟል፡፡ ይህም ከክልል ክልል የተለያየ ሲሆን በአማራና ደቡብ ክልል ያለው የዋጋ ግሽበት ከሃገራዊ ምጣኔው ከፍ ያለ ነው፡፡

ከተቀረው ዓለም የሀገራችንን የኑሮ ውድነት ለየት የሚያደርገው ማለትም ከፍላጎትና አቅርቦት አለመመጣጠን ባሻገር እሴት የማይጨምሩ ደላሎች በገበያ ሰንሰለቱ ከማሳ እስከ ገበያ መሰግሰጋቸው፤ መንግስትም ተገቢውን ቁጥጥርና የእርምት እርምጃ አለመውሰድ የዋጋ ንረቱን አባብሶታል ይላል ጥናቱ።በዚህም ምክንያት ምርት አምራቹ ከሚሸጥበት 58 በመቶ ዋጋው ከፍ ብሎ ሸማቹ ጋር እንዲደርስ አድርጓል፡፡ ይህ ማለት ዛሬ በሀገራችን ከሚስተዋለው የዋጋ ግሽበት 60 በመቶ ያህሉ የተከሰተው በደላሎች አማካኝነት መሆኑን ጥናቱ ያመላክታል። በሕግና በስርዓት ሊስተካከል በሚችል የግብይት ሰንሰለት ሸማቹ ምን ያህል ፍዳውን እያየ መሆኑንም ቁልጭ አርጎ አሳይቶናል።

የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር ከስንት ውትወታ በኋላ ሕገ ወጥ ደላላን ከግብይት ሰንሰለቱ የሚያስወጣ መመሪያ አዘጋጀሁ ቢለንም ስራ ላይ ባለመዋሉ የሀገሪቱ የግብይት ሰንሰለት የደላላ መፈንጫ እንደሆነ ቀጥሏል። በዚያ ሰሞን በሲሚንቶና በስንዴ ላይ አሁን ደግሞ ማዳበሪያ ላይ የሚስተዋለው ትንቅንቅ የግብይት ሰንሰለቱን ስብራት አደባባይ አውጥቶታል። የአማርኛው ሪፖርት ያለፈው እሮብ እትም የማዳበሪያ ግብይት የገባበትን ቅርቃር እንዲህ አስነብቦናል።

አምና ለመኸር ምርት እንዲውል ከ12.8 ሚሊዮን ኩንታል በላይ የአፈር ማዳበሪያ ተገዝቶ፤ የግብርና ሥራዎች ኮርፖሬሽን መጋቢት 21 ቀን 2014 ዓ.ም እንዳስታወቀው፣ ከጥር ወር ጀምሮ ለ2014 ዓ.ም መኸር የተገዛው ማዳበሪያ ወደ ኢትዮጵያ መግባት ጀምሮ ነበር። ከጥር እከከ መጋቢት ጅቡቲ ወደብ ድረስ የተባለው ማዳበሪያ መጠን 3,724,030 ኩንታል ነበር፡፡ ጅቡቲ ደረሰ ከተባለው ማዳበሪያ ውስጥ ደግሞ አብላጫው ወይም ሦስት ሚሊዮኑ እስከ መጋቢት ወደ አገር ውስጥ ገብቶ ነበር፡፡ የግብርና ሥራዎች ኮርፖሬሽኑ በቀን እስከ 70 ሺሕ ኩንታል ማዳበሪያ በመኪናና በባቡር እየተጫነ ወደ አገር ቤት ይገባ ነበር ብሏል፡፡ በዚህ የተነሳ ዋጋው ከካች አምናው አንፃር በዓለም ዋጋ መጨመር ሳቢያ ጭማሪ ይታይበት እንጂ የማዳበሪያ አቅርቦት እጥረት እንደሌለ ነበር ኮርፖሬሽኑ በጊዜው ያስታወቀው፡፡

ይሁን እንጂ የማዳበሪያ አቅርቦትን በተመለከተ የተጠየቁ ገበሬዎች በወቅቱ ማዳበሪያ ተቸገርን የሚል ስሞታ በተለያዩ አጋጣሚዎች ሲያሰሙ ነው የታዩት፡፡ አርሶ አደሮቹ እንደተናገሩት፣ በኩንታል ከ2,000 ብር በማይዘል ዋጋ ይገዙት የነበረ ማዳበሪያ በእጥፍና በሁለት አጥፍ አድጎ ከ4,000 እስከ 6,000 ብር ለመግዛት መገደዳቸውን ገልጸዋል፡፡ አንዳንድ አርሶ አደሮች ዋጋው በሁለት እጥፍ ጨምሮ ማዳበሪያ ለመግዛትም ቢሆን ትውውቅ፣ ዝምድናና ምልጃ እንደሚጠይቅ ነበር የተናገሩት፡፡

አምና በኢትዮጵያ ዋናው ችግር የማዳበሪያ ዋጋ ተወደደ የሚል ነበር የአርሶ አደሮች ቅሬታ፡፡ ዘንድሮ ደግሞ ይህ ችግር ተባብሶ ማዳበሪያ አጣን ወደሚል ተሸጋግሯል፡፡ አምና በማዳበሪያ ዋጋ የተቸገረ ገበሬ ዘንድሮ ግን ማዳበሪያ ማግኘቱ በራሱ ስቃይ እንደሆነበት ሲያማርር ተደምጧል፡፡ ለዘንድሮ መኸር የግብርና ሚኒስቴር 12.8 ሚሊዮን ኩንታል ማዳበሪያ ግዥ መፈጸሙን በመጋቢት ወር አስታውቆ ነበር፡፡ በጊዜው 4.4 ሚሊዮን ኩንታሉን ወደ ክልሎች የማጓጓዙ ሥራ 90 በመቶ መገባደዱን ሚኒስቴሩ ገልጾ ነበር፡፡

የግብርና ሚኒስቴር ያን ጊዜ የዘንድሮ የማዳበሪያ አቅርቦትና ሥርጭት በዓይነት፣ በመጠንና በወቅቱ እንዲዳረስ የተሻለ የዝግጅት ሥራ ስለመሥራቱም ሲናገር ተደምጧል፡፡ ይሁን እንጂ የመኸር ወራት ሲቃረብ ማዳበሪያ አጣን የሚለው የአርሶ አደሩ ብሶትና ምሬት ከአምናውም የባሰ ሆነ፡፡ በግንቦት፣ በሰኔና እስከ ያዝነው ሐምሌ ተከናወነ የሚባለው የማዳበሪያ አቅርቦትና ሥርጭት የግብርና ሚኒስቴርም ሆነ ሌሎች ባለድርሻ አካላት በሚያዝያና በመጋቢት ካስነገሩት መረጃ ፈጽሞ የሚቃረን ሆኖ ነው የተገኘው፡፡ ለአብነት ያህል እስከ ግንቦት ወር ግዥ የተፈጸመበት ተብሎ የተቀመጠው የማዳበሪያ አኃዝ 12.87 ሚሊዮን ኩንታል፤ ለዘንድሮው መኸር ሊገዛ መታቀዱ ሲነገር የቆየው ግን 15 ሚሊዮን ኩንታል ነበር፡፡

እስከ ግንቦት 30 ድረስ 6.25 ሚሊዮን ኩንታል ማዳበሪያ ጅቡቲ ወደብ መግባቱም፤ በመጋዘኖች ተከማችቶ የቆየ ወይም የከረመ 2.2 ሚሊዮን ኩንታል ማዳበሪያ ስለመኖሩም፤ በወቅቱ ሁለቱ ተደማምረው በአጭር ጊዜ ውስጥ 8.45 ሚሊዮን ኩንታል ማዳበሪያ ወደ ኅብረት ሥራ ማኅበራት ይሠራጫል ተብሎም ነበር፡፡ የሰኔ ወር ሲመጣ ግን 7.59 ሚሊዮን ኩንታል ማዳበሪያ ወደ ኅብረት ሥራ ማኅበራት መውረዱ ነው የተነገረው፡፡

ለኅብረት ሥራ ማኅበራቱ ከተሰጠው ማዳበሪያ ውስጥም ቢሆን ለገበሬዎች ተሠራጭቷል የተባለው 5.74 ሚሊዮን ኩንታሉ ብቻ እንደሆነ፤ ቀሪው 2.7 ሚሊዮን ኩንታል ማዳበሪያ በእጃችን ላይ ይገኛል የሚል መግለጫ በግብርና ሚኒስቴርና በሚመለከታቸው ወገኖች ሲነገር ቆይቷል፡፡ ወደ 15 ሚሊዮን ማዳበሪያ ተገዝቶ እንደሚሠራጭ ከመጋቢት ጀምሮ ሲናገሩ የቆዩት አካላት፣ እስከ ሰኔ 5.74 ሚሊዮን ኩንታል ብቻ ገበሬው ዘንድ ስለመድረሱ ብቻ ነው ማረጋገጫ የሰጡት፡፡

ይህ የማዳበሪያ አቅርቦት መዘግየት በስተኋላ ያሳሰባቸው የሚመስሉት የግብርና ሚኒስቴር ሰዎች፣ የዛሬ ወር ገደማ በ15 ቀናት ውስጥ 2.9 ሚሊዮን ኩንታል ማዳበሪያ እናስገባለን በሚባልበት ጊዜ ግን ጉዳዩ እጅግ አርፍዶ ሁኔታውም ከቁጥጥር ውጪ መሆን ጀምረ፤ ማዳበሪያ ከአምናውም ዋጋው ብሶበት በኩንታል ከአሥር ሺሕ ብር በላይ ከመሸጡ ባሻገር በአንዳንድ አካባቢዎች የማዳበሪያ ኮንትሮባንድና ሕገወጥ ግብይት ተንሰራፋ። መንግሥት ከሌለው ሀብት ወጪ በማድረግ የዘንድሮ መኸር ገበሬው እንዳያልፍበት ሲል እስከ 21 ቢሊዮን ብር ደጉሞ ማዳበሪያ እያስገባ ስለመሆኑ ደጋግሞ ቢለፍፍም፤ ችግሩ ግን ከባድ ቀውስ ወደ መፍጠር ተሸጋግሮ፤ በተለያዩ ክልሎች ማዳበሪያ ይቅረብልን የሚሉ የገበሬዎች ቁጣና ተቃውሞ መሰማት ጀመረ፡፡

የግብርና ሚኒስቴር ሚኒስትር ደኤታ ዶ/ር ሶፊያ ካሳ በኩላቸው ከአንድ ወር ቀደም ብሎ የተለያየ መጠን ያለው ማዳበሪያ በግብርና ሚኒስቴርና በግብርና ሥራዎች ኮርፖሬሽን በኩል ለክልሎች ተሠራጭቷል ብለዋል፡፡ ለምሳሌ ደቡብ ክልል 780 ሺሕ ኩንታል፣ ሲዳማ ክልል 140 ሺሕ ኩንታል፣ ቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል 111 ሺሕ ኩንታል፣ እንዲሁም ደቡብ ምዕራብ ክልል 149 ሺሕ ኩንታል ማዳበሪያ እንዲደርሳቸው መደረጉን ተናግረዋል፡፡ በማዳበሪያ ግዥ ሥርዓቱ ውስጥ ያልተካተቱ ክልሎችና አካላት ደግሞ በድምሩ 450 ሺሕ ኩንታል ማዳበሪያ ደርሷቸዋል ተብሏል፡፡

በሰፋፊ እርሻ ልማት የተሰማሩ፣ የስኳር ኮርፖሬሽን፣ ሚድሮክ ኢንቨስትመንትና ሌሎችም የግብርና አንቀሳቃሾች ከዚሁ 450 ሺሕ ኩንታል እንደሚደርሳቸው ነው የተነገረው፡፡ ጥያቄው ታዲያ የት ገባ የሚል ነው። ማዳበሪያው በተለይ ዘንድሮ እየገባ ያለው ዘግይቶ ቢሆንም፤ ከጅቡቲ ተጭኖ ቀጥታ ወደየክልሎች የሚጓጓዝ ከሆነ፤ ማን ቀሽቦ ለሕገ ወጥ ደላላዎችና ነጋዴዎች አስረከበው፤ ከዚህ አደገኛ አዝማሚያ የመውጫ መንገዳችንስ ምንድን ነው፤ የዘንድሮ ችግር በሚቀጥለው እንደማይደገም ምን ዋስትና አለ፤ ዋስትናው የግብይት ስርዓቱን በደንብ ፈትሾ የማያዳግም የእርምት መውሰድና መንግስትም ግብይቱን አበክሮ ማጠናቀቅ ነው።

በኢትዮጵያ በህገ-ወጥ መንገድ በሚካሄደው የግብይት ስርዓት አገሪቱ በየዓመቱ አስከ ዘጠኝ ቢሊዮን ብር የሚደርስ ገቢ እያጣች መሆኑን፤ በዓለም ታዋቂ ከሆነው የምጣኔ ሀብታዊ መፅሄት “ዘ-ኢኮኖሚስት” ጋር በመተባበር በተዘጋጀውና በአህጉራዊ የንግድ እንቅስቃሴ ችግሮች፣ መንስኤዎቻቸውና መፍትሄዎቹ ዙሪያ በመከረ ጉባኤ ላይ መመልከቱ የችግሩን አሳሳቢነት ያረጋግጣል። በኢትዮጵያ ከሚካሄደው አጠቃላይ የአገር ውስጥ ግብይት ስርዓት ውስጥ40 በመቶ ያህሉ በህገ-ወጥ መንገድ በሚገቡ ምርቶች የተያዘ ነው። በዚህም አገሪቱ ከግብይቱ ስርዓቱ ማግኘት የነበረባትን ዘጠኝ ቢሊዮን ብር በየዓመቱ ታጣለች።

ይህ ገቢ ለ72 ሺ ዜጎች የስራ እድል በመፍጠር አገራዊ ኢኮኖሚውን በከፍተኛ መጠን ያግዝ ነበር ተብሏል። እንደ ኢዜአ ዘገባ 45 በመቶ የትንባሆ ምርቶች፣ 48 በመቶ የጨርቃ ጨርቅ ምርቶች እንዲሁም 30 በመቶ መድሃኒት በህገ-ወጥ መንገድ ወደ አገር ውስጥ በመግባት ገበያውን የሚያውኩት ቀዳሚ ሸቀጦች ናቸው። በዚሁ ህገ ወጥ የግብይት ስርዓት አማካኝነት ወደ አገር የሚገቡ ጊዜ ያለፈባቸው መድሃኒቶችም የህብረተሰቡን ጤና ስጋት ላይ የሚጥሉ መሆናቸውንም ጥናቱ አመልክቷል።

ሻሎም !

አሜን።                                            

በቁምላቸው አበበ ይማም (ሞሼ ዳያን)

አዲስ ዘመን ሐሙስ ሐምሌ 20 ቀን 2015 ዓ.ም

Recommended For You

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *