ኢትዮጵያውያን ለቅኝ ግዛት አሰፍስፎ የመጣውን የጣልያንን ወራሪ ኃይል ድል ያደረጉበትን 127ኛው የዓድዋ ድል በዓልን በደማቅ ሥነሥርዓት አክብረዋል። በዓሉ ሰሞኑን በተለያዩ ዝግጅቶች ሲከበር የሰነበተ ሲሆን፣ ትናንት ደግሞ በዳግማዊ ምኒልክ አደባባይና በዓድዋ ድልድይ በተካሄደ ሕዝባዊ ሥነ ሥርዓት እንዲሁም በመስቀል አደባባይ በተካሄደ ደማቅ ወታደራዊ ትርኢት ተከብሯል። በሌሎች የሀገሪቱ አካባቢዎች እንዲሁም በተለያዩ ሀገሮች በሚገኙ የኢትዮጵያ ሚሲዮኖችም በዓሉ በድምቀት ተከብሯል።
ዘንድሮ በዓሉ የተከበረባቸው መንገዶች በተለይ በመስቀል አደባባይ የተካሄደው ወታደራዊ ትርኢት ለድሉ የሚገባና የሚመጥን ታላቅ አከባበር ነው ብሎ መውሰድ ይቻላል። የዓድዋ ድል ታላቅ ነውና በቀጣይም ይህን የሚመጥን ከዘንድሮውም የላቀ አከባበር በእጅጉ ይፈልጋል።
የዓድዋ ድል የኢትዮጵያውያን አንድነት ጎልቶ የታየበት፣ ከኢትዮጵያም የሚያልፍ ለአፍሪካም ተምሳሌት በመሆን ያገለገለ ነው፣ ለአፍሪካውያን ከቅኝ ግዛት የመላቀቅ የነጻነት ትግል ትልቅ መሳሪያ በመሆን አገልግሏል። ነጮች በጥቁሮች ሊሸነፉ እንደሚችሉ ታይቶበታል፤ ይህም መላ ዓለምን ጭምር በእጅጉ አነጋግሯል፤ በዚህም የኢትዮጵያ ዝና ይበልጥ እንዲናኝ ያደረገ ታላቅ ገድልም ተጽፎበታል።
የዓድዋ ድል በዓል ሲከበርና ሲታወስ ትውልዶች የዚህን ታላቅ ድል ምስጢር እንዲገነዘቡ ብቻ አይደለም የሚደረገው፤ ለትውልዱ አደራም ይሰጣል። ጀግኖች አባቶች ሲዘከሩም ይህ ትውልድ እንዲጀግን አደራ ይተላለፍበታል፤ ትውልዱም እኔስ ምን ማድረግ አለብኝ፣ የት ነው የቆምኩት ብሎ ራሱን እንዲፈትሽ ይደረጋል።
ዓድዋ የብዙ ነገሮች ተምሳሌት ነውና ለታላላቅ የልማት እና የሰላም አጀንዳዎች መፈጸም መሳሪያ በመሆን ሊያገልግል ይችላል። በዓባይ ግድብ ግንባታ፣ የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት በማስከበር ተግባር የዓድዋ ድል በተምሳሌትነት በተደጋጋሚ ተነስቷል። እነዚህ አጀንዳዎች የኢትዮጵያውያንን አንድነት በእጅጉ የሚፈልጉ በመሆናቸው ነው ድሉ መጠቀሱ። በቀጣይም የሚሆነው ይህ ነው። ምክንያቱ ደግሞ የዓድዋ ድል የኢትዮጵያና የኢትዮጵያውያን ልክ በመሆኑ ነው።
ለዓድዋ ድል አስተዋጽኦ ያደረገውን አንድነትና ትብብር፣ አንድ ሆኖ መነሳት የሚያውለበልብ ኢትዮጵያዊ፣ በምንም አይነት መልኩ አንድነትን ሊንድ በሚችል ተግባር ውስጥ መገኘት የለበትም። ዓድዋን ሰሞኑን በተከበረው መልኩ የዘከሩ እና ሲዘክሩ የኖሩ ኢትዮጵያውያን ሃሳባቸው ተግባራቸው እና አካሄዳቸው ሁሉ ይሄንን ድል የሚመጥን ሊሆን ይገባል።
አፍሪካውያንም ሆኑ መላው ዓለም ኢትዮጵያንም ሆነ ኢትዮጵያውያንን የሚያውቁት በዓድዋ የልዕልና ልክ ነው። ኢትዮጵያም ኢትዮጵያውያንም በእዚሁ የዓድዋ ልክ ላይ መጽናት ይኖርባቸዋል። ይህን ለማድረግ ደግሞ በዘር፣ ሃይማኖት፣ አክራሪነትና በመሳሰሉት መከፋፈል ፈጽሞ አይገባም። ኅብረ-ብሄራዊነትን ባከበረ መልኩ ጀግኖች ኢትዮጵያውያን ያኖሩትንና ያቆዩትን የዓድዋ ድል ልክ የራስ በማድረግ የዓድዋን ድል ታሳቢ ባደረገ መልኩ ለሀገር መስራት ይገባል።
በሀገሪቱ ሰሜን ክፍል ባለፉት ዓመታት፣ የተከሰቱ ግጭቶችን በሰላማዊ መንገድ ለመቋጨትና ችግሮች እንዲፈቱ የኢትዮጵያ መንግሥት አበክሮ እየሰራ ነው። የሰሜን ኢትዮጵያው ጦርነት በተፈረመው የሰላም ስምምነት ቆሟል፤ ስምምነቱ የሚጠይቃቸው ተግባሮች እንዲፈጸሙም እየተሰራ ነው። መሳሪያ አንስተው እየተዋጉ ያሉ ሌሎች ኃይሎችም ከዚህ ድርጊታቸው ታቅበው ለሰላማዊ አማራጭ ቅድሚያ መስጠት ይኖርባቸዋል። ከዴሞክራሲያዊና ሰላማዊ አማራጭ ውጪ ያሉት አካሄዶች በሙሉ መቆም አለባቸው። ሰላማዊ አማራጭና ውይይት ገዥ ሆነው መምጣት ይኖርባቸዋል። ለኢትዮጵያ የሚመጥናትም ይሄው ነው።
ኢትዮጵያውያንን የሚጠቅመው ኅብረብሔራዊ የአንድነት መንገድ ነው። ኅብረብሔራዊ አንድነት የት እንደሚያደርስ ከዓድዋ ድል በሚገባ ትምህርት ተወስዷል፤ በዓባይ ግድብ ግንባታና የሀገርን ሉዓላዊነት ለማስከበር በተካሄዱ የሀገር ዘመቻዎችም ደምቀው ታይተዋል። ከዓድዋ ድል መማር የተቻለው የኢትዮጵያውያን ልክ ይሄ ነው።
የኢትዮጵያና ኢትዮጵያውያን ልክ የዓድዋ ድል ነው። የዓድዋ ድል በኅብረብሔራዊ አንድነት የመቆምን ፋይዳ በሚገባ አመላክቷል። በዚህ ልክ መገኘት ይገባል። በዓድዋ ድል ልክ ማሰብ፣ ማቀድ፣ መተግበርና ውጤትንም መጠበቅ ከኢትዮጵያውያን በተለይም አሁን እጅጉን ይፈለጋል!
አዲስ ዘመን የካቲት 24/2015