ታላቁ የዓድዋ ድልና የአበበ ቢቂላ የሮም ኦሊምፒክ የማራቶን ድል ታሪካዊ ግጥምጥሞሽ ሁሌም አስገራሚና እንደአዲስ የሚነገር ነው። ጀግኖች ኢትዮጵያውያን ቅኝ ገዢው ጣሊያን ዘመናዊ የጦር መሣሪያ እስካፍንጫው ታጥቆ ለመውረር ሲመጣ እጅግ ኋላ ቀር በሆነ መሣሪያ በወኔ፣አልሸነፍ ባይነትና አስደናቂ ጀግንነት ድል ተደርጎ ተመልሷል። ይህም በጥቁር ሕዝቦች የጦርነት ታሪክ ሕያው ድል ሆኖ ከመዘከሩ ባለፈ በዓለም ፖለቲካዊ ሥርዓት ውስጥ ተዘርዝሮ የማያልቅ ተጽዕኖ ማሳደር ችሏል። የአበበ ቢቂላም የሮም ኦሊምፒክ የማራቶን ድል ተመሳሳይ ነው።
አበበ የአባቶቹን ሀገር በግፍ ለመውረር በመጣው ጣሊያኖች ሀገር በወቅቱ ዘመናዊ ሥልጠናና ዝግጅት አድርገው ምቹ የመሮጫ ጫማ ካጠለቁ አያሌ ነጮች ውስጥ በባዶ እግሩ አፈትልኮ ሌላኛውን የዓድዋ ድል ተምሳሌት ሮም ኦሊምፒክ ላይ ፈጽሟል። ይህም ድሉ በኦሊምፒክ መድረክ የጥቁር አትሌቶች ፋና ወጊ ድል ከመሆኑ ባሻገር ልክ እንደ ዓድዋ ሁሉ ጥቁሮች በስፖርቱ መድረክ ቀና ብለው እንዲሄዱ የማይፋቅ አሻራውን አሳርፏል።
በዓለም አቀፍ የስፖርት መድረኮች ጥቁሮች አሁን ላይ በየትኛውም ዓለማቀፍ መድረክ ተፎካካሪ እንዲሆኑ ከማስቻል ባሻገር በትልቅ ደረጃ ውጤታማ መሆን እንደሚችሉ ለማሳየት በርካታ ጥቁር ከዋክብት ብዙ ችግሮችን ተጋፍጠዋል። በተለይም ጥቁር አሜሪካውያን አትሌቶች በዚህ ረገድ ያዩት ፈተና ሳይጠቀስ የሚታለፍ አይደለም።
አፍሪካውያንም ቢሆኑ በርካታ መከራዎችን ተጋፍጠው ለታላቅ ክብር በመብቃት ለአሁኖቹ አትሌቶች ፋና ወጊ ሆነው እኩልነትን ማንፀባረቃቸው አይካድም። ለዚህም ታሪካዊውን ኢትዮጵያዊ የማራቶን ኮከብ አትሌት ሻምበል አበበ ቢቂላ በትልቁ የሚነሳ የጥቁር ሕዝቦች ኩራት ሆኖ እናገኘዋለን።
ኢትዮጵያውያን በስፖርቱ ብቻም ሳይሆን በዓድዋ ድል የጥቁር ሕዝቦች የነፃነት ተምሳሌትና የማዕዘን ድንጋይ ሆነዋል። የጥቁር ሕዝቦች ኩራት የሆነው የዓድዋ ድል የሚዘከርበት የካቲት ወር በመላው ዓለምም የጥቁር ሕዝቦች መታሰቢያ ሆኖ ይከበራል።
በስፖርት መድረክ ዘረኝነትን የታገሉ፤ እኩልነትን ያንፀባረቁና በድላቸው የጥቁር ሕዝቦችን አንገት ያቀኑ በርካታ ጥቁር ከዋክብቶች መኖራቸው አይካድም። ከነዚህ ከዋክብቶች ግን ተፅዕኗቸው ከፍተኛ የነበረ፤ ድላቸው በርካታ ትርጉም የነበረውና በትልቅ ደረጃ ከሚነሱት መካከል የታላቁ ዓድዋ ድል ባለቤት የሆነው የኢትዮጵያ ሕዝብ እንቁ ልጅ አበበ ቢቂላና የሮም ኦሊምፒክ ሕያው የማራቶን ድል ተጽዕኖ ቀላል እንዳልነበረ በብዙ ድርሳናት ተጽፎ ይገኛል።
1928 ፋሺስት ጣሊያን በአምባገነኑ ቤኒቶ ሞሶሎኒ በመመራት ኢትዮጵያን ከወረረ ከሃያ አራት ዓመታት በኋላም ታላቁ አበበ ቢቂላ ታላቋን ሮም በባዶ እግሩ ወሮ ዓለምን ጉድ አሰኘ። የምንጊዜም የማራቶን ንጉሡ የአፍሪካውያን ኩራትና የነፃነት ተምሳሌት እንዲሁም፤ የመጀመሪያው ጥቁር የማራቶን ኦሊምፒክ የወርቅ ሜዳሊያ አሸናፊ በጥቁሮቹ በጀግኖች መታሰቢያ ወር የካቲት የጥቁር ሕዝቦች ኩራት ሆኖ ከስልሳ ዓመት በፊት በኢትዮጵያውያን አዲስ ዓመት ዋዜማ በሮም ኦሊምፒክ የፈፀመው ታሪካዊ ጀብድ በመላው ዓለም ያሉ ጥቁር አትሌቶችን በእጅጉ ያኮራና ያነሳሳ ነበር።
ጳጉሜን 5 ቀን 1952 አስራ ሰባተኛው የሮም ኦሊምፒያድ በታላቋ ሮም ጎዳናዎች በርካቶች ዓይናቸውን ለማመን የተቸገሩበት ጀብድ በአምባገነኑ ሞሶሎኒ አገር በበርካታ ነጮች መሐል አንድ ጥቁር በባዶ እግሩ ይጽፈዋል ብሎ ማንም አልጠረጠረም። ልክ እንደ ዓድዋ ድል ሁሉ የጥቁር ሕዝቦች ተዓምርን ለመቀበል የሚተናነቃቸው ዘረኝነትን በደማቸው ያሰረፁ ነጮች እንዴት ይህ ሊሆን እንደቻለ አሁንም ድረስ ግራ ይጋባሉ። አፍሪካውያንን ያኮራ ኢትዮጵያውያንን ከልብ ያስፈነጠዘው ታሪካዊ ድል በአበበ ቢቂላ ቀጫጭን እግሮች በወርቅ ቀለም መጻፉን ግን እየተናነቃቸውም ቢሆን ሊያላምጡት ተገደዋል።
ከ83 አገራት የተውጣጡ ከ5ሺ በላይ አትሌቶች በተካፈሉበት የሮም ኦሊምፒክ፤ የዓለም ሕዝብ ትኩረት በአውሮፓውያን አትሌቶች ላይ ነው፤ ስለኢትዮጵያውያን አትሌቶች በተለይም ስለ አበበ ቢቂላ የሚያውቀው ነገር አልነበረም።አበበ ቢቂላ ወይም ሌላ አፍሪካዊ አትሌት ሊያሸንፍ እንደሚችል አልተጠበቀም። ከዚያ በፊት አንድም አፍሪካዊ በኦሊምፒክ ታሪክ ሜዳሊያ አግኝቶ አያውቅም።።
የሮም ኦሎምፒክ የማራቶን ውድድር ግን፤ የዓለምን ታሪክ ቀየረ።የውድድሩ ውጤት፤ ለኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን፤ ለመላው አፍሪካና ለዓለም ጥቁር ሕዝብ ድል ያበሰረ ችቦ አቀጣጣለ። ኢትዮጵያዊው አትሌት አበበ ቢቂላ በባዶ እግሩ ሮጦ ታላቁን የኦሊምፒክ ማራቶን በአንደኝነት ከማሸነፍም በተጨማሪ፤ 2፡5፡6.2 በሆነ ሰዓት አዲስ የዓለም ክብረወሰን አስመዘገበ። በኦሊምፒክ ታሪክ የሜዳሊያ ባለቤት ለመሆን የቻለ የመጀመሪያው አፍሪካዊ ስፖርተኛ ሆኖ ስሙ በታሪክ መዝገብ በወርቃማ ቀለም ሰፈረ።
አበበ ቢቂላ የማራቶንን ርቀት ሮጦ ያሸነፈውና ሪከርድ ያስመዘገበው፤ በባዶ እግሩ መሆኑ ደግሞ የመላ ዓለም ስፖርት አፍቃሪዎችን በእጅጉ ያስደነቀ ነበር። የአበበ በቂላን ስምና የኢትዮጵያን ዝና በመላው ዓለም ተቀርፆ እንዲቀር አድርጓል። በዓድዋ ጦርነት ላይ የዘመቱ ኢትዮጵያውያን ባዶ እግራቸውን እንደነበሩ ያስታውሳል። ጋዜጠኞች አበበ ለምን ያለ ጫማ በባዶ እግሩ እንደሮጠ ጠይቀውታል፣ “ዓለም ሁሉ እንዲያውቅ ፈልጌ ነው” ሲል የተናገረው አበበ፤ “እኛ ኢትዮጵያውያን ሁሌም የምናሸንፈው በጀግንነትና በወኔ እንደሆነ፤ ለዓለም ሕዝብ ለማሳወቅ በመፈለጌ ነው” ብሏል።የዓድዋን የጦርነት ታሪክ እያስታወሰ።
የአራት ዓመት ታዳጊ ሆኖ እናት አገሩ ኢትዮጵያ በጣሊያን ፋሺስት ስትወረር መጥፎውን ጊዜ ገና ባልጎለበተ የሕፃን አዕምሮው የሚያስታውሰው አበበ ቢቂላ፣ ሃያ ስድስት ዓመታት ጠብቆ ታላቁን የሮም ጎዳና በባዶ እግሩ ወሮ የማይደገመውን ታሪክ አኑሯል።
ከአራት ዓመት በኋላም 1956 በድጋሚ ጫማ አጥልቆ በቶኪዮ ኦሊምፒክ ክብረወሰን በማሻሻል ጭምር አሸንፎ ጥቁሮች በማይደፈረው ርቀት አሁን ላይ ቁንጮ እንዲሆኑ መሠረቱን ጣለ። እሱ በከፈተው በርም ቁጥር ስፍር የሌላቸው የማራቶን አትሌቶች ለዘመናት ለርቀቱ የተፈጠሩት እነሱ ብቻ እስኪመስሉ አሁን ድረስ በዓለም አደባባይ እያንጸባረቁ ነው።
አበበ ምናልባት ያንን ውድድር ባያሸንፍ ኖሮ የጥቁር አትሌቶች በተለይም የረጅም ርቀት ታሪክ ዛሬ ከምናውቀው ተቃራኒ ሊሆን እንደሚችል በርካቶች ይስማማሉ።
እርግጥ ነው በሮም ኦሊምፒክ አበበ ብቸኛው ተሳታፊ አልነበረም። ብቸኛው ወርቅ ያጠለቀም አትሌት አይደለም። በዚያ ኦሊምፒክ ከተሳተፉ ጥቁሮች መካከል ሌላ ባለድልም ነበር። አሜሪካዊው ጥቁር የቡጢ ተፋላሚ መሐመድ ዓሊ በቀላል ሚዛን የወርቅ ሜዳልያ ተጎናፅፎ ነበር። ቢሆንም ኦሊምፒኩ በመሐመድ ዓሊ ወርቅ ሜዳልያ እምብዛም የደመቀ አልነበረም። በወቅቱ ታሪክ የሚያስታውሰው ሌላ ክስተትም ነበር። ጊዜው ደቡብ አፍሪካ በአህጉራዊ ውድድሮች ለመጨረሻ ጊዜ ተሳትፋ የታገደችበት ነበር። የእገዳዋ ምክንያት ደግሞ ትከተለው በነበረ የአፓርታይድ ሥርዓት መሆኑ ነው። ቢሆንም የያኔ የሮሙ ኦሊምፒክ በመሐመድ ዓሊ የወርቅ ሜዳልያም ይሁን በደቡብ አፍሪካ መታገድ አይደለም የሚታወሰው።
ታዲያ በምን ይታወሳል? ያሉ እንደሆነ በውድድር ዘመኑ የማራቶን ሩጫ ያለ ጫማ ሮጦ የርቀቱ አዲስ ክብረወሰን ባስመዘገበው ኢትዮጵያዊ አትሌት ሻምበል አበበ በቂላ ነው። በወቅቱ በርካታ ሊጠቀሱ የሚችሉ ነገሮች ቢከናወኑም አበበ ግን ታሪኮችን ሁሉ ልቆ የሚታወስ ድንቅ ታሪክ አስመዘገበ።
ያኔ፣ አይደለም አበበ ቢቂላ የሚባል አትሌት፣ ኢትዮጵያ ተብላ ስለምትጠራ አገርም የሚያውቅ ነጭ ብዙም አልነበረም። ይሁን እንጂ ውድድሩ በጣሊያን መካሄዱ እና የጣሊያን ወረራ በኢትዮጵያ ድል አድራጊነት ተጠናቅቆ ድል የመጨበጧ ወሬ ገና ከዓለም አቀፍ የዜና አውታሮች የወሬ አጀንዳነት ባለመረሳቱ፣ የአበበ ቢቂላ ድል ገነነ። ለዚህም ነው ብዙዎች የአበበ ድልና ታላቁ የጥቁር ሕዝቦች የጦርነት ድል ዓድዋ የሚመሳሰልባቸው ወይም የሚገጣጠምባቸው። አበበ ቢቂላ ለመጀመርያ ጊዜ በተሳተፈበት የማራቶን ውድድር አሸነፈ። የጥረት እንጂ የአጋጣሚ ጉዳይ አይደለም።ጀግና፤ ጀግናን ያፈራል።
የዓለም አቀፍ ሚዲያዎች ሳይቀሩ ባልተጠበቀው የአትሌት አበበ በቂላ ድል ተደምመው ደጋግመው፣ በባዶ እግር ሮጦ የወርቅ ሜዳልያ ስላገኘው ኢትዮጵያዊው አትሌት ተናገሩ። በውድድሩ ማግስትም የጣሊያን ጋዜጦች ‹‹ኢትዮጵያን ለመውረር የኢጣሊያ አገር ወታደር ሁሉ አስፈልጎ ነበር፤ ኢትዮጵያ ግን አንድ ወታደር ብቻ ልካ ድፍን ሮምን ወረረችው›› የሚል ጽሑፍ ይዘው ወጡ። ይህም አጋጣሚ ብዙ ጥቁር አፍሪካውያን በዓለም አቀፍ ውድድሮች እንዲሳተፉ በር ከመክፈቱ በዘለለ ከቅኝ ግዛት ለመላቀቀ የነጻነት ትግል በማድረግ ላይ ለነበሩ የዓለም ጥቁር ሕዝቦች ሁሉ የ”ይቻላል” መንፈስና ትልቅ የስነልቦና ስንቅ ሆኗቸዋል።
የአበበ ቢቂላ አንፀባራቂ ድሎች ለአፍሪካውያን በፋና ወጊነት ጠቅሟቸዋል። በኩራችን ብለውም ሰይመውታል። አዲስ አበባ በ2000 ዓ.ም. ያዘጋጀችውን 16ኛውን የአፍሪካ አትሌቲክስ ቻምፒዮና አጋጣሚን ምክንያት በማድረግ በ50 ዓመታት ውስጥ ለአፍሪካ አኩሪ ታሪክ የፈጸሙ አትሌቶች ሲሸለሙ፤ አውራው ተሸላሚ አበበ ቢቂላ ነበር። ‹‹የአፍሪካ ማራቶን አባት›› ተብሎም በዶክመንተሪው ፊልም ላይ ተመልክቷል።
አፍሪካውያን ለአበበ ያላቸው ፍቅርና አክብሮት እስከዚህ ድረስ ነው አይባልም። የአፍሪካ አትሌቲክስ ሻምፒዮና በሴኔጋል መዲና ዳካር በ1971 ዓ.ም. ሲጀመር ወደ ዳካር ስታዲየም የሚያስገባውን መንገድ ‹‹አበበ ቢቂላ ጎዳና›› በማለት መሰየሟ ይታወሳል። ኢጣሊያም ብትሆን ለአበበ ክብሩን አልነፈገችም። የሮም ኦሊምፒክ 50ኛ ዓመትን ስትዘክር አንድ ድልድይ በስሙ ሰይማለች።
አምስተርዳም ከተማም የአበበ ቢቂላ መንገድ አላት። ‹‹ቶኪዮ ኦሊምፒያድ›› በተባለው የትረካ ፊልም ላይ የአበበ ቢቂላ የቶኪዮ ድል ተጨምሯል። ከዚሁ ፊልም የተወሰደ ክፍልም በ1968 በተሠራው ‹‹ማራቶን ማን›› በተባለው ፊልም ላይ ይገኛል። ‹‹ቪብራም›› የተባለ የአሜሪካ የጫማ አምራች ድርጅት በ2002 ‹‹ፋይቭ ፊንገርስ ቢቂላ” (Five Fingers Bikila) የተባለ ጫማ ለገበያ አቅርቧል።
ቦጋለ አበበ
አዲስ ዘመን የካቲት 23/2015