ብዙዎች አገር ከፍ ባለ መስዋእትነት እና በታላቅ ምጥ ተወልዳ አገር እንደምትሆን ለመረዳት የሚቸግራቸውን ያህል፤ ብዙዎች የመስዋእትነቱ እና የምጡ ባለቤት በመሆን በታሪክ ውስጥ ልዩ ስፍራ የመያዛቸው እውነታ የተለመደና ዛሬም ዓለም እየሄደችበት ያለው ያልተለወጠ የጉዞ ምዕራፍ ነው።
የቀደሙት አባቶቻችንም ቢሆኑ የዛሬዪቷን ኢትዮጵያ ለዘመናት አሻግረው ለዚህ ትውልድ ያበቁት በዚሁ የተለመደ የጉዞ ምዕራፍ ነው። በየዘመኑ እንደ አገር ያጋጠሙንን ፈተናዎች (ተግዳሮቶች) በብዙ መስዋእትነት እና በታላቅ ትግል በመሻገር፤ በአሸናፊነትና በነፃነት መንፈስ የተገነባች ታላቅ አገር በመፍጠር ነው።
ይህ በአሸናፊነት ትርክት (ከፍ ባለ የሥነ ልቦና ልዕልና) የተገነባች አገር ባለቤት የመሆናችን ምስጢር፤ ስለ አገር ከፍያለ፤ መረዳት እንዲኖረን ከማድረግ ባለፈ እንደ ሕዝብ ስለአገር መሞት ክብር መሆኑን የሚያጸና የአስተሳሰብ መሠረት ላይ እንድንቆም አድርጎናል። በየዘመኑም ስለአገር በመሞት የደማቁ ታሪኮች ባለቤት እንድንሆን አስችሎናል።
ከነዚህ በመስዋእትነት ደም ከደመቁ፤ የአትንኩኝ ባይነትና የተጋድሎ ታሪካችን አንዱ እና በዋነኛው የዓድዋ ጦርነትና በጦርነቱ በየተገኘው አንጸባራቂ ድል ነው። ይህ ከእኛ አልፎ ለዓለም ጭቁን ሕዝቦች የብሩህ ነገዎች ጸዳል፤ የነፃነት ትግል ተስፋ እርሻ የሆነው ድል፤ አባቶቻችንን ብዙ ያስከፈለ፤ የአይቻልም ትርክትን የገለበጠ፤ ዛሬም የይቻላል መነቃቃት ዘር ተደርጎ የሚወሰድ ነው።
አባቶቻችን ስለ ነፃነታቸው ያላቸውን ቀናኢነት በተግባር በመስዋእትነት በገዘፈ ታሪክ ለመላው ዓለም ያሳዩበት፤ አገርና አገረ መንግሥት የቱን ያህል በመስዋእትነት እንደሚፀና፤ ለዚህ የሚሆን ከትውልድ ትውልድ ሲሸጋገር የመጣ የዓላማ ቁርጠኝነትና የመንፈስ ጽናት ያለን ሕዝቦች እንደሆንን በተጨባጭ ያሳየንበት ነው።
ለአንድ አገር ሕዝቦች ሁለንተናዊ የጋራ ልዕልናና አንድነት ብሎም ከዚህ የሚመነጭ ኅብረትና መተሳሰብ ወሳኝ አቅም እንደሆነ፤ ይህ አቅም አገርን እንደ አገር ለማስቀጠልም መተኪያ እንደማይኖረው፤ አይቻልምን ወደ ይቻላል መለወጥ የሚያስችል የተፈተነ አገራዊ ብቃት መሆኑን ጭምር ያስመሰከርንበት ነው።
በብዙ ጭቆና እና ግፍ ውስጥ የነበሩ በመላው ዓለም የሚገኙ ጥቁር ሕዝቦች ከግፍ ዋሻ ጫፍ የብርሃን ጭላንጭል ማየት የቻሉበትን ዕድል መፍጠር ያስቻለ፤ ነገ በዛሬ የመስዋእትነት ተጋድሎ ዘር ፍሬ ተስፋ ሆኖ እንደሚወለድ ማስተዋል የቻሉበት፤ ለዚህ የሚሆን ሥነልቦናዊ ዝግጁነት እንዲፈጥሩ ያስቻለ ነው።
ከመስዋእትነት በስተጀርባ ያለውን የነፃነት ሕይወት ተስፋ አድርገው፤ ራሳቸውን ከፍ ላለ መስዋእትነት በማዘጋጀት ለቀጣይ ትውልዶች አዲስ ነገዎችን በመስዋእትነት በደመቁ ዛሬዎች መፍጠር እንደሚቻል ከተጨባጭ ተሞክሮ መረዳት የቻሉበትን ታሪካዊ አጋጣሚ መፍጠር የቻለ ክስተት ነው።
በአጠቃላይ ዓድዋና የዓድዋ የተጋድሎ የመስዋእትነት ድል፤ ዛሬም የኢትዮጵያዊነት፣ የአንድነትና የነፃነት ዜማ የሚደመጥበት፤ የጽናት፣ የሉአላዊነት ቅኔ መወድስ የሚሰማበት በመስዋእትነት ደም የተዋጀ የነፃነት ማማ ነው!
አዲስ ዘመን የካቲት 23/2015