እስቲ ዛሬ ስለ ኳስ እናውራ! ከመደበኛው ወጣ እንበላ! ምንም እንኳ እግር ኳስን «ወጣ» ልናደርገው ብንሞክርም ፖለቲካ ካልሆንኩኝ ሲል እያየነው ቢሆንም፤ ይሁን! አንዳንዴ እንደ ርዕስ መቀየሪያ እንጠቀመው። አሃ! ቆዩ እንጂ መግቢያ መች አዘጋጀሁ። እንካችሁማ መግቢያ! መቼ እለት በቴሌቭዥን ካየሁት ዝግጅት ልጀምር፤ ምን የማይታይ አለ!
በምላችሁ ዝግጅት ላይ አዘጋጅቱ ለንግግር የጋበዘቻቸው ሰዎች ከተናገሩት ቁምነገር መካከል አንዱ የበለጠ ሳበኝ። ምን አሉ? «አበሾች ለቅሶ ቤት ሰው ለማጽናናት ሲሄዱ ጭራሽ ሃዘን ቀስቅሰው <ታሞ ነበር? እንዴት ሞተ? ብዙ ተሰቃየ?> ወዘተ እያሉ ይጠይቃሉ» አሉ። መቼም እንደ እኛ ለችግር ደራሽ አለ ብለን ባናምንም፤ ማስተዛዘኛ መንገዳችን ግን ጭራሽ ሀዘን የሚቀሰቅስ ሆኖ ተገኘ ማለት ነው።
እና ምን ብናደርግ ነበር ጥሩ? ሌላ ሌላ ጉዳይ እያነሳን የታመመውንም ሆነ ሰው የሞተበትን ሰው ከሀዘኑ እንዲወጣ ማስረሳት፤ ማረሳሳት። እና ምን ልላችሁ ፈልጌ ነው፤
ብለን ብለን የደከመንንና አይገመቴውን ፖለቲካ ለአፍታ ትተን እስቲ ስለኳስ ብናወራ ምን ክፋት አለው? አቤት መግቢያ!
እና ግን ለምንድን ነው ከ 18 ዓመት በታች የሆኑ ልጆች ስታድየም እንዳይገቡ የማይከለከለው? በተለይ አሁን አሁን «ፖለቲካ የእኔ ነው» ባይ በበዛበት ጊዜ፤ እግር ኳሱም ብሶበት ነው የሚታየው። ያድነኛል ብለው ውጠውት የባሰ አዲስ በሽታ እንደሚፈጥርና ህመሙን እንደሚያብስ «መድኃኒት» ሆነብን፤ እግር ኳስ። አሃ! ጦርነት ሆኗላ! የፖለቲካ እልህ ያለበት ሁሉ በኳስ ሲፈናከት እያየን!
ምን ሆነ መሰላችሁ! ስንት ጊዜ የአገራችን እግር ኳስ ሲታማ በጆሮዬ እሰማ የነበርኩ ልጅት ባለፈው ስታድየም መግባት። የት? እርሱን አልነግራችሁም። ያው ችግር የሌለበት ባለመኖሩ አንዱንም ልትገምቱ ትችላላችሁ፤ ግን ከአዲስ አበባ ውጪ መሆኑን ያዙልኝ። ታድያ ወደ ጨዋታው ሜዳ ስንገባ የእንግዳው ቡድን ብቻውን እንጂ አንድም ደጋፊ አልነበረውም።
«ውይ! አገር ምድሩ ሰው በሆነበት ጊዜ ደጋፊ ጠፍቶ ነው?» ብል፤
«አይ! ደጋፊዎቹ ጸበኞች ናቸውና እዚህ እንዳትደርሱ ተብለው ነው።» አሉኝ።
«እና ይህም እግር ኳስ ሆኖ በዚህም ተከፋፍለናላ!» ስል፤
«ያው የድጋፍ ጉዳይ ነው!»
«ጎሽ! እና እነዚህ ያለሜዳቸው የሚጫወቱ ተጫዋቾቹ ብቻቸውን አይፈሩም? ካሸነፉስ ማን ሊጨፍር ነው?» አልኩኝ፤ ድፍረቴኮ!
«የምን ማሸነፍ? ማን ፈቅዶላቸው? ጨዋታው ካለቀ በኋላ በሰላም ወደ ማደሪያሽ መግባት አትፈልጊም? ዳኛውም’ኮ ሰው ነው… ልጆች ይኖሩታል። ይኑርበት እንጂ!» ብለውኝ እርፍ።
አሃ! ታድያ በሕይወት ካለ፤ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን እንዲህ ባሉ አጋጣሚዎች ቡድኖች ወጪ ከሚያወጡ ለ«ባለሜዳው» ቡድን ዝም ብሎ ነጥብ እንዲሰጥ ለምን አይፈቅድም አልኩኝ፤ በልቤ ወይም በሆዴ። ፌዴሬሽኑ ግለሰብ ቢሆን ኖሮ ቀዳሚ ድንጋይ አቀባይና አስወርዋሪ ነገር መስሎ ታየኝ። እንዲህ በማለቴ መቼስ አይከፋውም። ቢከፋውም ይሁን! እንደ ህጋዊ ሰው ስሜት ያለውና ግዑዝ ያልሆነ መሆኑን አረጋግጥበታለሁ።
ብቻ ግን ጨዋታው ተካሄደና ይኼው እንግዳውን የተቀበለው ቡድን በሜዳው አንድ ጎል አገባ። ጎሉ እንኳ ኦፍ ሳይድ ነበር፤ ግን ቢሆንስ? እንደውም ለምን በእጁ አያገባም? ውጤቱን የሚወስነው ባለ ሜዳው ነው። ባለሜዳው ባለ አእምሮ ላይሆን ይችላል፤ ነገር ግን ባለ ስሜት ነው። ያውም የእግር ኳስ ስሜት አይደለም… የድብድብ ስሜት።
ከዛ በባሰ ልጆች ወደ ሜዳ እንዳይገቡ ይከልከል ያልኩት ደግሞ ለዚህ ነው፤ ስድቡ! ኧረ ስድብ! የስድብ ችሎታችን በዜማና በግጥም ተቀናብሮ ይቀርብ የለ እንዴ? ሰው እንዴት በጋራ እንደ ኅብረ ዝማሬ የስድብ ቃልን በኩራት ይናገራል? በእድሜ ትልልቅ የሆኑ ሰዎችም በሜዳው የዚህ የስድብ ተጋሪ መሆናቸውን ሳይ ደግሞ ጭራሽ አፈርኩ።
ነገሩ ለእኔ አዲስ ሆኖብኝ እንደሆነ የገባኝ ደጋግመው ስታድየም ጨዋታ ለመዘገብ የሚገቡ ባልደረቦቼ ምንም እንዳልተፈጠረ ዝም ማለታቸውን ስመለከት ነው። የሚሆነውን ሁሉ እንደ ጦጣና «ኢትዮጵያዊነት መልካምነት» ብሎ እንደሚያይ ጨዋ ሰው ሆኜ ነበር። በኅብረ ዝማሬ ከሚሳደቡት ደጋፊዎች ተቀብለው ህጻናት የማያውቋቸውን ቃላት እየተቀበሉ ያስተጋባሉ። እነዛን አስጸያፊ የስድብ ቃላት ከሽማግሌና አዋቂዎች አንደበት መስማት ሳያንስ ትርጉሙን ከማያውቁት ልጆች ሲወጣ ደግሞ ሰውነትን ውርር ያደርጋል። ኧረ ምን እየተዘራ ነው? ነገ ምን ሊታጨድ ነው ወገን!
ብቻ ግን በስድብና ትክክለኛ ባልሆነ ጎልም ቢሆን ጨዋታው በሰላም አለቀ። ሰላም አንጻራዊ አይደለ? ለካ ደግሞ መውጣትም ፈተና ነው። ጠመንጃ የታጠቁና በቁጥር በርከት ያሉ ፖሊሶች በሩ ጋር ሆነው በመከላከል ተጫዋቾቹ በእንግድነት ከተጫወቱበት ሜዳ ተንከባክበው ይዘዋቸው ወጡ። ኳስ እኛም አገር በስሙ ተጠርታና ወግ ደርሷት ጭራሽ እንዲህ አስፈሪ ትሁን? አሁን ማን ይሙት በአገራችን ከስታድየሞቻችን በላይ አስፈሪ ቀጠናስ አለ?
ከስታድየሙ ውጪ የሚታየው የፖሊስ ኃይል ከመብዛቱ የተነሳ አንድ የፖሊስ ክለብ የተጫወተ ነው የሚመስለው። እናላችሁ ወደየማረፊችን ስናቀና አንድ ጉድ ሰማሁ። ለካ ሰብሰብ ብለን ሲያዩን የእንግዳው ቡድን ደጋፊዎች መስለናቸዋል ጥርስ ነክሰውብናል። ጥርስ ይነከሳል ወይ የሚለው ሌላ ጉዳይ ሆኖ ይህን ነገር ከስታድየሙ ስወጣ መስማቴ ጠቀመ እንጂ አስቀድሞ ብሰማ ኖሮ የት ልገባ ነበር? ምንስ ልሆን ነበር?
በቃ! ከ18 ዓመት በታች የሆኑ ስታድየም ከመግባት ይከልከሉ። ስታድየሞቻችንና የሚካሄዱት ጨዋታዎች፤ ወላጆች ልጆችን ይዘው ‹ይህን ቡድን ነው የምደግፈው…› ብለው እንዲያሳዩ፣ የሚደግፉትን ቡድን መለዮ ለብሰው በነጻነትና ያለስጋት እንዲንቀሳቀሱ የሚፈቅድ አይደለም። እንደውም እንደሚባለው ከሆነ መሮጥ የሚችል ሰው ነው ጨዋታ እንዲያይ የሚመከረው! ነጻ ትግል ቢችልም ይመረጣል።
ሆድ ያባውን ብቅል እንደ ሚያወጣው ማንነትና ጸባያችንን ኳስዬ እያሳየችን ነው። እንግዳ ተቀባይነት? ኧረ ተውኝ እስቲ! እንግዲህ አንድ ሁለቴ ስታድየም ስመላለስ ነገሩን እለምደው ይሆናል ብዬ በመገመት በቅርቡ ለመድገም አስቤአለሁ። አንዳንድ ነገሮች አልቀየር ካሉና ሌላ አማራጭ ከሌለ ራስን መቀየር አስፈላጊ ነው አይደለ? አዎን! በዚህ ሃሳብ ባልስማማም ትክክል መሆኑን አልክድም።
ብቻ ግን እንዳልኩት ስታድየም መግ ባት ከ18 ዓመት በታች ለሆኑ ቢከለከል ጥሩ ነው። ቡድኖችም ተተኪ ተጫዋችና ደጋፊ እንጂ ተተኪ ተሳዳቢ ምን ያደርግላቸዋል? ነገሩ ቀላል አልመሰለኝም! እውነቱን ለመናገር የእግር ኳስ ፌደሬሽን የሚባል ነገር የእውነት እንደ ስሙ ካለ መፍትሄው በእጁ ነው ያለው። አሁን ቡድኖች ሳይሆኑ ደጋፊ አለን የሚሉት፤ ደጋፊዎች ናቸው ቡድን ያላቸው።
እናት ሉሲ ሰላምን ፍለጋ ከምትኳትነው በላይ እግር ኳስ ወዳጅነትን በቀላሉ በመፍጠር አቻ የሌለው መሣሪያ ሊሆን ይችል ነበር። አላለልንም! ኳስ ለሰላም ከማለታችን በፊት ሰላም ለእግር ኳሳችን አስፈላጊ ሆኗል። እንደውም ዘርፉ የፈጠረው የሥራ ዕድል ብዙ ነው፤ በዛ ላይ ግርማ ሞገስ ያለውና ሲጠራ የሚያስበረግግ ደመወዝ የሚከፈልበት ብቸኛው ትርፍ አልባ ዘርፍ መሆኑ ነው እንጂ ቢቀርስ ምን እንሆናለን?ወይም አንድ ሁለት ዓመት ዘግቶ የተሻለ መንገድ መፈለግ ነው። የእግር ኳስ ቡድን ደጋፊ እንዲኖረው እንጂ ደጋፊ ቡድን እንዳይፈጥር፣ በብሔርና በክልል የተደራጀና በአስተዳደሮች የአወቃቀር ተዋረድ ስር በውስጠ ታዋቂነት ተቀምጦ የእነርሱ ድንጋይ መወራወሪያ ከመሆን እንዲወጣ፤ ከማንም በላይ አቅም ያላቸው ልጆች ዓለም አቀፍ እውቅና የሚያገኙበት መድረክ እንዲሆን ለማድረግ መሰራት አለበት። ብቻ ይከልከልልን! መጠላላትን ጠላን። ሰላም!
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 13/2011
ሊድያ ተስፋዬ