እኤአ 1871 ቅኝ ገዢ ሀገራት አፍሪካን ለመቀራመት በርሊን ላይ ስምምነት አደረጉ፡፡ በስምምነቱ መሠረትም የወቅቱ ቅኝ ገዢዎች የአፍሪካ ሀገራትን ቀስ በቀስ በመዳፋቸው ስር ማድረግ ጀመሩ፡፡ በዚህም ምክንያት የአፍሪካ ሀገራትም ስር ለሰደደ ጭቆና፤ባርነት፤ጉስቁልናና እንግልት ተዳረጉ፡፡
የቅኝ ገዢዎቹ አንዷ አካል የነበረውም የጣሊያን ወራሪ መንግሥት ኢትዮጵያን ለመግዛት ተነሳ፡፡ በሰሜኑ የሀገሪቱ ክፍል ቀስ በቀስ የወረራ አቅሙን እያጠናከረ በኢትዮጵያ ላይ የበላይነቱን ለማሳየት ሞከረ፡፡ ይህንኑ በተግባር ለመሞከርም የአማርኛና የጣሊያንኛ ትርጉሙ የተለያየ በሆነው የውጫሌ ውል በአንቀጽ 17 ‹‹የኢትዮጵያ መንግሥት ማንኛውንም ግንኙነት ሲያደርግ በጣሊያን በኩል ይሆናል›› የሚል ሐረግ በመሸንቆር ኢትዮጵያን በመዳፉ ስር ለማድረግ የሚያስችል አንቀጽ አሰፈረ፡፡
የወቅቱ መሪ አጼ ምኒሊክ የጣሊያንን ሴራ በመረዳት አንቀጹ እንዲስተካክል ቢወተውቱም ጣሊያን አሻፈረኝ በማለቱ የካቲት 23 ቀን 1988 ዓድዋ ላይ ጦርነት ገጠሙ፡፡ ኢትዮጵያውያንም እስከአፍንጫው ዘመናዊ መሣሪያ የታጠቀውን ወራሪ የጣሊያን ኃይልን በሰዓታት ውስጥ ድባቅ መቱት ፡፡ ለመጀመሪያ ጊዜም ጥቁር ሕዝብ በነጭ ገዢዎች ላይ የድል አክሊል ተቀዳጀ፡፡ እውነትን ከያዙና ከተባበሩ ጥቁሮች ማንኛውንም ኃይል ድል መንሳት እንደሚችሉ ለዓለም አበሰሩ፡፡
የታሪክ ምሑራን ዓድዋን ሲገልጹት “የኢትዮጵያውያን አንድነት መገለጫ፣ የመላው ጥቁር ሕዝቦችና የነፃነት ታጋዮች የድል ታሪክ ነው” ይሉታል። የዓድዋ ድል ከኢትዮጵያ አልፎ መላው አፍሪካውያን ለነፃነታቸው እንዲተጉና አንድነታቸውን እንዲያጠናከሩ መሠረት የሆነ ታላቅ ድል ስለመሆኑም ይናገራሉ። የጥቁር ሕዝቦች የአሸናፊነት ማሳያም ተደርጎም ይወሰዳል አንጸባራቂው የዓድዋ ድል።
ዓድዋ ለኢትዮጵያውያን የድል በዓል ሲሆን ለጥቁር ሕዝቦች ደግሞ የነጻነት ዓርማ ሆኖ ዝንተ ዓለም ያገለግላል፡፡ መላው አፍሪካና የካሪቢያን አካባቢ በቅኝ ገዢዎች መዳፍ ስር ወድቆ የባርነት ሕይወት በሚመራበት የጨለማ ወቅት ዓድዋ ልዩ ብርሃን ሆኖ ጭቁን ሕዝቦችን ለነጻነት ተጋድሎ አነሳስቷል፡፡
በ1871 ከተደረገው የበርሊኑ የቅኝ ግዛት ስምምነት ጀምሮም ጥቁር ሕዝቦች ለከፋ የጉልበት ብዝበዛ፤ እንግልትና ኢ-ሰብዓዊ አካኋን ሕይወታቸውን ሲገፉ ኖረዋል፡፡ በሰፋፊ እርሻዎች እግሮቻቸው ታስሮ በመንጋ እንደ እንስሳ ሌት ተቀን እንዲሠሩ ተደርገዋል፡፡ በርካቶችም ከአፍሪካና ከካሪቢያን አካባቢዎች እየተወሰዱ ለምዕራባውያን ሥልጣኔ ሻማ ሆነው ነደው ቀልጠዋል፡፡
በዚህም የተነሳ የአፍሪካ ሃገራትም የሲኦል ተምሳሌቶች ሆነው ኖረዋል፡፡ በቅኝ አገዛዝ ጦስ ምክንያት በርካታ አንጡራ ሃብት ወደ አውሮፓና ሰሜን አሜሪካ በገፍ ከመደረጉም ባሻገር አፍሪካውያን በገዛ ሀገራቸው የነጮችን የበላይነት አምነው እጅ እንዲነሱ፤ እንዲታዘዙና በአጠቃላይም የቅኝ ገዢዎች ንብረት መሆናቸውን እንዲያምኑ በርካታ ተጽዕኖዎች ይደረጉባቸው ነበር፡፡
ሆኖም የቅኝ ግዛትን ቀንበር መሸከም ያቃታቸው ጥቁር ሕዝቦች ከዓድዋ የአይበገሬነትን መንፈስ በመውሰድ ለነጻነታቸው መታገል ጀምሩ፡፡ ብዙዎችም በ1960ዎቹ ነጻነታቸውን አወጁ፡፡ በምትኩም ዓድዋ ከነጻነት በሻገርም የፓን አፍሪካኒዝም መነሻ መሠረትም ሆነ፡፡ አፍሪካውያንም ወደ አንድነትና ዕድገት እንዲያመሩ መንገዱን የሚጠርገው የአፍሪካ አንድነት ድርጅትም እውን ሆነ፡፡
የዓድዋ ድል ከአፍሪካና ከካሪቢያን ሀገሮች ባሻገርም በየቦታው ለጥቁር ሕዝቦች ነጻነት የሚሟገቱ ታዋቂ ሰዎችንም አፍርቷል፡፡ እንደ ማርቲን ሉተርን የመሳሰሉ ታዋቂ የነጻነት ታጋዮችም በዓድዋ መንፈስ ለነጻነት ታግለው አሸንፈዋል፡፡ ታሪካቸውም ዘወትር ከዓድዋ ጋር ተያይዞ ይወሳል፡፡
የዓድዋ ድል በታሪካዊዋ በየካቲት ወር የተገኘ የድል እና የነጻነት በዓል በመሆኑም በአሜሪካውያን ዘንድ የየካቲት ወር የጥቁር ሕዝቦች የታሪክ ወር ተብሎ በየዓመቱ ለመዘከር በቅቷል፡፡ አንዳንድ የአፍሪካ ሃገራትም ለቀኑ ልዩ ትርጉም በመስጠት ነጻነታቸውን በማጣጣም ላይ ይገኛሉ፡፡
በአጠቃላይ ዓድዋ የጥቁር ሕዝቦች ነጻነት የተረጋገጠበት የድል በዓል ከመሆኑም ባሻገር በቀጣይ የአፍሪካ ሃገራት ለሚመሠረቱት የኢኮኖሚ ውሕደትና ነጻነት ጉልበት ሆኖ ያገለግላል፡፡ ትላንት የጥቁር ሕዝቦች ለነጻነታቸው እንዲታገሉ እንዳነሳሳ ሁሉ ዛሬም የአፍሪካ ሀገራት የኢኮኖሚ ነጻነታቸውን እንዲያውጁ ብርታት ይሆናቸዋል!
አዲስ ዘመን የካቲት 22 ቀን 2015 ዓ.ም