ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ በዓለም አቀፍ ደረጃ የሳይበር ጥቃት በከፍተኛ ደረጃ እየጨመረ መምጣቱን መረጃዎች ያመላክታሉ። የሳይበር ጥቃት ከቴክኖሎጂ ጋር በተገናኘ የሚፈጸም እንደመሆኑ መጠን ዓለም በቴክኖሎጂ እየመጠቀ ባለበት በዚህ ዘመን የሚቃጣውና የሚፈጸመው የሳይበር ጥቃት በዚያው ልክ አደገኛ የሚባል ነው። በአንድ አገር ላይ ሆን ተብሎ የሚፈጸም የሳይበር ጥቃት አገሪቱን ባንዳፍታ ምስቅልቅሏን አውጥቶ ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ቀውስ ሊያስከትል ይችላል።
የሳይበር ጥቃት ሆን ተብሎ ያልተፈቀዱ የኮምፒዩተር ሥርዓቶችን፣ መሠረተ-ልማቶች እና ኔትዎርኮች ላይ አጥፊ ሶፍትዌሮችን በመጠቀም በሕገወጥ መንገድ መረጃዎች መበዝበዝ እና አገልግሎት በማስተጓጎል የሚሰነዘር ጥቃት ነው። በማህበራዊ የትስስር ገጾች ላይ ደግሞ ከባህልና ከሥነ ምግባር ውጪ ባፈነገጠ መንገድ ከሚለጠፉ ምስሎች እና መልዕክቶች ጀምሮ የመረጃ መረብ ተገን በማድረግ በተለያዩ ደረጃዎች የሚፈጸሙ የመረጃ ስርቆቶች የሳይበር ጥቃት ማሳያዎች ናቸው።
መረጃዎች እንደሚያመላክቱት የሳይበር ጥቃት በበርካታ አገራት የደረሰ ሲሆን፣ በጥቃቱም እጅግ ከፍተኛ ጉዳት ደርሷል። ለአብነትም በእ.ኤ.አ 2009 ዩክሬን ላይ የተፈጸመው የሳይበር ጥቃት ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ቀውሶች አስከትሎ እንደነበር በወቅቱ የወጡ መረጃዎች ያመላክታሉ። በአንጻሩ ደግሞ የተቃጡ ጥቃቶች የታለመላቸውን ግብ ሳይመቱ የከሸፉባቸው በርካታ ሁኔታዎችም አሉ።
ኢትዮጵያም የዚህ ጥቃት ሰለባ እየሆነች ትገኛለች። በአገሪቱ የፋይናንስ፣ የህክምና፣ የሚዲያ እና የትምህርት ተቋማትን ጨምሮ ሌሎች ወሳኝ መሠረተ-ልማቶችን ኢላማ ያደረጉ የሳይበር ጥቃት ሙከራዎች እንደሚደረጉ ከኢንፎርሜሽን መረጃ ደህነንነት አስተዳደር የተገኘው መረጃ ያመላክታል። ጥቃቶቹን በማክሸፍ በኩል በርካታ ተግባሮች መከናወናቸውን መረጃው ጠቁሟል።
በኢትዮጵያ የሳይበር ጥቃትን የመከላከል ኃላፊነት የተሰጠው የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር ነው። አስተዳደሩ በ2015 በጀት ዓመት የመጀመሪያ ስድስት ወራት የእቅድ አፈጻጸሙን አስመልክቶ በቅርቡ ለጋዜጠኞች ማብራሪያ የሰጡት የአስተዳደሩ ዋና ዳይሬክተር አቶ ሰለሞን ሶካ እንደተናገሩት፤ ተቋሙ በስድስት ወራት ውስጥ በሳይበር ጥቃት ሊከሰቱ የነበሩ በርካታ ጉዳቶች ማስቀረት ችሏል።
አስተዳደሩ እንደ አገር የሳይበር ጥቃትን ለመከላከል የሚያስችሉ በርካታ ተግባራት እያከናወነ መሆኑን የሚገልጹት አቶ ሰለሞን፤ በስድስት ወራት ጊዜ ውስጥ በኢትዮጵያ ሊደርሱ የነበሩ ጥቃቶችን በማስቀረት፣ የደረሱ ጥቃቶችን በማስቆም፣ እንዲሁም አደገኛ የደህንነት ስጋት ሊደቅኑ የሚችሉ ቴክኖሎጂዎችን በመቆጣጠር ሊደርሱ የሚችሉ ጉዳቶችን ማስቀረቱን መቻሉን አብራርተዋል።
እንደ አቶ እሳቸው ገለጻ፤ በአገራችን በስድስት ወራት ውስጥ በርካታ የሳይበር ጥቃት ሙከራዎች የተሰነዘሩ ሲሆን፣ ጥቃቶችንም በማክሸፍ ረገድ በርካታ ሥራዎች ተሠርተዋል። ጥቃቶቹ ቢደርሱ ኖሮ በግለሰብ፣ በተቋማት እና በአገር ደረጃ ሊያደርሱ የሚችሉት ኢኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊ፣ ዲፕሎማሲያዊ እና ሥነ-ልቦናዊ ክስረት በጣም ከፍተኛ ይሆን ነበር።
በአጠቃላይ አስተዳደሩ ሊደርሱ የነበሩ ጥቃቶችን በማስቀረት፣ የደረሱ ጥቃቶችን በማስቆም፣ እንዲሁም አደገኛ የደህንነት ስጋት ሊደቅኑ የሚችሉ ቴክኖሎጂዎችን በመቆጣጠር ሊደርሱ የሚችሉ ጉዳቶችን ማዳን ችሏል ያሉት ዋና ዳይሬክተሩ፣ በዚህም በ2015 በጀት ዓመት ስድስት ወራት ውስጥ በሳይበር ጥቃት ምክንያት አገሪቱ ላይ ሊደርስ የሚችል አስራ አምስት ቢሊዮን ብር ኪሳራ ማዳን መቻሉንም ነው የገለጹት።
አቶ ሰለሞን በሳይበር ጥቃት ኢላማዎች በአብዛኛው ትኩረታቸውን በባንኮችና ፋይናንስ ተቋማት ላይ ያደረጉ መሆናቸውንም ጠቅሰው፣ የፀጥታ እና ደህንነት ተቋማት፣ የሚዲያ ተቋማት፣ ቁልፍ የመንግስት ተቋማት ፣ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቶች ፣የክልል ቢሮዎች እና የህክምና እና ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የጥቃት ዒላማዎች እንደነበሩ አብራርተዋል።
የሳይበር ጥቃት በመከላከል ላይ ሊሠሩ የሚገባቸው ጉዳዮች ተጠናክረው መቀጠል እንዳለባቸው የሚገልጹት አቶ ሰለሞን፤ አስተዳደሩ እንደ አገር የአገሪቱን የዲጂታል ሉአላዊነት ለማረጋገጥ የሚሠራው ሥራ እንደተጠበቀ ሆኖ ከሌሎች አጋር አካላት ጋር በመሆን የሳይበር ምህዳሩን ደህንነት የማረጋገጥ ድርሻውን አጠናክሮ እንደሚቀጥል ይገልጻሉ።
የሳይበር ደህንነት ተጋላጭነት
በ2015 በጀት ዓመት የመጀመሪያው ስድስት ወራት ውስጥ የተከሰተውን የሳይበር ደህንነት ተጋላጭነት በተለያዩ ዘርፎች በሚገኙ 64 ተቋማት (27 የመንግሥት እና 37 የግል) ላይ የተጋላጭነት ዳሰሳ ተደርጓል። ዳሰሳው ከተደረገባቸው ከእነዚህ ተቋማት የዌብ፣ የኔትዎርክ መሠረተ ልማት፣ የሞባይል መተግበሪያዎችን ጨምሮ በተለያዩ መሠረተ ልማቶች 340 የሳይበር ደህንነት የተጋላጭነት የአደጋ ደረጃ (Vulnerability risk level) ክፍተት መገኘቱን እና መድፈን መቻሉ ተመላክቷል።
የሳይበር ደህንነት ተጋላጭነት ስጋቱ ከደረጃ አንጻር ሲታይ 97 ከፍተኛ፣ 154 መካከለኛ እና 89 ዝቅተኛ ደረጃ የተመዘገቡ ናቸው። አጠቃላይ በእነዚህ ሲስተሞች ላይ ሥራው ባይሰራ የሚያመጣው ኪሳራ በብዙ ሚሊዮን ብር የሚገመት ነው። አጥቂዎች የተገኙትን ክፍተቶች ቢጠቀሙባቸው ሲስተሞቹ ምስጢራዊነትን፣ ታማኝነትንና ተጠያቂነትን ሊያጡ ይችሉ አንደነበር ተመላክቷል።
የሳይበር ደህንነት ስጋት
በአገራችን 2ሺ145 የሳይበር ጥቃቶች እና የጥቃት ሙከራዎች እንደተፈፀሙና ከእነዚህ መካከልም 2ሺ049 ምላሽ የተሰጠባቸው እና የተቀሩት በሂደት ላይ እንዳሉ ተጠቅሷል። በዚህም በመንፈቅ ዓመቱ የሳይበር ጥቃት ሙከራን የመመከት አፈፃፀም 91ነጥብ5 ከመቶ ማድረስ መቻሉም ተጠቁሟል።
በእነዚህ ስድስት ወራት ከተከሰቱት የጥቃት ዓይነቶች እና ኢላማዎች በስፋት የተሞከሩት የሳይበር ጥቃት ዓይነቶች መካከል የድረገጽ ጥቃት፤ ማልዌር፤ የመሠረተ ልማት ቅኝት (Scan)፤ የመሠረተ ልማት ማቋረጥ (DDOS)፤ ሰርጎ መግባት ሙከራ እንደየቅደም ተከተላቸው ከፍተኛ የጥቃት ሙከራ የተደረገባቸው ናቸው።
ለአብነት የሳይበር ጥቃት የተሞከረባቸውን ብንመለከት 14 የድረገጽ ጥቃት እና 381 ሙከራዎች የተደረጉ ሲሆን፣ በማልዌር ጥቃት ሁለት የተሳኩ ጥቃቶች እና 545 ሙከራዎች ተደርገዋል። የመሠረተ ልማት ቅኝት (Scan) ስንመለከት የተሳካ ጥቃት ባይኖርም 869 ሙከራዎች ተደርገዋል። መሠረተ ልማት ማቋረጥ (DDOS) እና ሰርጎ የመግባት ሙከራ የተደረገ ሲሆን፣ የተሳካ ጥቃት ባይኖርም እንደየቅደም ተከተላቸው 57 እና 197 የጥቃት ሙከራዎች መደረጋቸው ተገልጧል። የተለያዩ የኢሜል (ፍራውድ-ክፍያ እንዲፈጸም ማድረግ፣ አካውንት መንጠቅ) ሶሻል ሚዲያ (ስም ማጥፋት፣ አካውንት መንጠቅ፣ ገንዘብ መሰብሰብ) በተመለከተ 80 የተሳኩ ጥቃቶች መፈጸማቸውም ተጠቅሷል።
የተሞከሩ ጥቃቶች ቢደርሱ ኖሮ የመሠረተ-ልማቶችን በማቋረጥ፤ ተቋማት የሚሰጧቸውን አገልግሎቶች ለተወሰኑ ጊዜያት በማስተጓጎል ሥራዎች እንዳይሠሩ በማድረግ፣ አገልግሎት አሰጣጥ ላይ ተጽዕኖ በማሳደር ገቢ የማስተጓጎል፤ የዳታዎች መሰረቅ እና መጥፋት፤ ዳታዎችን በመመስጠር የቤዛ ክፍያ ገንዘብ መጠየቅ፤ የግንኙነት መንገዶችን በመጥለፍ እና የክፍያን መንገድ በመጠቀም ገንዘብን በማጭበርበር እና በመውሰድ ጉዳት ይደርስ እንደነበር ተመላክቷል።
የሳይበር ጥቃቶች ክብደት ሊያደርሱ ይችሉ ከነበረው ጥፋት መጠን ስንመለከት በጣም ከፍተኛ፣ ከፍተኛ እና መካከለኛ በሚባል ደረጃ ተቀምጠዋል።
የመረጃ እና መገናኛ ቴክኖሎጂዎች ቁጥጥር
በአገር አቀፍ ደረጃ ከሚደረገው የሳይበር ደህንነት አደጋ የመቀነስ እና በሚገባ የማስተዳደር ሥራዎች መካከል ወደ አገር ውስጥ የሚገቡ እና የሚወጡ እንዲሁም በተለያየ ምክንያት የሚወገዱ የመረጃ እና የመገናኛ ቴክኖሎጂዎችን መቆጣጠር ይገኝበታል። የቁጥጥር ሥራው የሚካሄደው በአገሪቱ መግቢያ እና መውጫ ኬላዎች ላይ እና ድንገተኛ አካላዊ የመስክ ፍተሻዎች በማድረግ ነው። በዚህ መሠረት ወደ አገር ውስጥ ለማስገባት ፈቃድ ከተጠየቀባቸው 2ነጥብ 158 የተለያዩ ዓይነት ቴክኖሎጂዎች 297 የሚሆኑት የደህንነት ስጋት የሚያስከትሉ በመሆናቸው አደገኛ ተብለው የተለዩ ቴክኖሎጂዎች ወደ አገር እንዳይገቡ ተደርገዋል።
የሳይበር ደህንነት አደጋ/Risk
አገር አቀፍ የሳይበር ደህንነት አደጋ ደረጃን ለማመላከት በተመረጡ የሚዲያ ተቋማት፣ የፀጥታ እና ደህንነት እንዲሁም ቁልፍ መሠረተ ልማት የሚተዳደሩ ተቋማት ላይ ትኩረት በማድረግ የሳይበር ደህንነት ስጋትን እና ተጋላጭነትን በማጣመር መሥራቱን ለማመላከት ተሠርቷል።
እንደ አጠቃላይ የሳይበር ጥቃት የተሰነዘረባቸው አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ይሰጡት የነበረው አገልግሎት እንዳይቋረጥ በማድረግ የቀረው የገንዘብ ኪሳራ፣ የደንበኞች እንግልት፣ የተጋላጭነት ዳሰሳ በማድረግ የተገኙ ክፍተቶችን መሸፈን ተችሏል። ማስቀረት የተቻሉ ጥቃቶችን መረጃ በመመስጠር የቤዛ ክፍያ ገንዘብ የተጠየቀባቸውን ዳታ ሪኮቨር በማድረግ የቀረ ወጪ፣ እና በመሠረተ ልማቶች ላይ ሊደርስ የነበረውን ጥቃት በማስቀረት የታሰበውን ጉዳት በማስቀረት እንዲሁም ጉዳቱ ደርሶ ቢሆን የድህረ ክስተት ምርመራ ወጪ እና መልሶ ግንባታ ወጪ የሚያስቀሩ ሥራዎች ተሠርተዋል።
ከዚህ በተጨማሪም ማህበራዊ እና ፖለቲካዊ ምስቅልቅል በመፍጠር በማህበረሰቡ እርስ በርስ እና ከመንግሥት ጋር ያለውን መስተጋብር ለማበላሸት የተደረገ ጥቃት ከሚኖረው ኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊ፣ ኢንቨስትመንት፣ የፀጥታ እና ደህንነት፣ ቁልፍ የመንግሥት ተቋማት የግንኙነት እና የዳታ ልውውጥ መስተጋብር ተአማኒነቱ፣ ምሉዕነቱ እና እንደተጠበቀ ማድረግ ተችሏል። በዳታ ማፈትለክ አልያም መበላሸት ምክንያት ይመጣ የነበረው ጫና እና ተቋማት ላይ በተደረገ የሳይበር ደህንነት አደጋ//Risk ደሰሳ እና የተቀመጡ መፍትሔዎች መተግበር ወይም በመተግበር ላይ መሆን የተቋማቱን የሳይበር ተቋማቱን የሳይበር ደህንነት ቁመና የማሳደግ ሥራ በመሥራቱ መከላከል የተቻሉ የሳይበር ደህንነት ጉዳቶች እና የመሳሰሉት መሆናቸው ከአስተዳደሩ የተገኘው መረጃ ያመላክታል።
እንደ መውጫ
ከጊዜ ወደ ጊዜ አሳባቢ እየሆነ ያለው የሳይበር ጥቃት በማንኛውም የቴክኖሎጂ መሠረተ ልማት ተጠቅሞ ሥራውን በሚሠራ ግለሰብ፣ ተቋምና ቡድን ላይ ሊሰነዘር ይችላል። የሳይበር ጥቃት በአብዛኛው ሲስተሞች፣ የኮምፒዩተር ሥርዓቶች እና መጠቀሚያ መሣሪያዎችን ክፍተት በመጠቀም የሚሰነዘር ነው። ጥቃቱ ፈጻሚዎች (መረጃ ጠላፊዎች) የግለሰቦችን ኮምፒዩተር፣ የስልክ፣ የባንክ ካርድ እና ማንኛውንም ኢንተርኔት ላይ ያኖሩትን መረጃ በመበርበር ጥቃት ሊሰነዝሩ የሚችሉበት ሁኔታ መኖሩ ይታወቃል። እንደዚህ ዓይነቱ የሳይበር ጥቃት ሲፈጸም በግለሰብም ሆነ በአገር ደረጃ ከፍተኛ ጉዳት ሊያደርስ ይችላል። አንድ መረጃው የተጠለፈበት ሰው ላይ የሚደርሰው ጉዳት በጊዜው በግለሰቡ ላይ ከፍተኛ ድንጋጤን የሚፈጥር ሲሆን፤ በአገር ላይ የሚደርሰው ጉዳት ደግሞ አገርን ከባድ ችግር ውስጥ ሊከት የሚችል ጉዳቶችን ያስከትላል።
የሳይበር ጥቃት በኮምፒዩተርና የኮምፒዩተር መሠረተ ልማትን በመጠቀም አገልግሎት በሚሰጡ ተቋማት ላይ የተደቀነው አደጋ ከባድ እንደመሆኑ መጠን ተቋማት ላይ በየጊዜው አያሌ የሳይበር ጥቃቶች የሚቃጡበት ሁኔታዎች ይታያሉ። የሳይበር ጥቃት እንዲህ አሳሳቢ ከሆነ ዘመኑን የሚመጥኑ ቴክኖሎጂዎችን በመጠቀም ትኩረት ሰጥቶ የመሥራትን አስፈላጊነት ያመላክታል። በሳይበር ዘመን እየፈረጠመ ያለውን የሳይበር ጡንቻ መመከት የሚያስችል ሥራ መሥራት ካልተቻለ የሳይበር ጥቃት በእጅጉ እየጨመረ በርካታ አገርን ሊጎዱ የሚችሉ ጥቃቶች ሊደርሱ እንደሚችሉ የዘርፉ ምሁራንም ምክረ ሃሳባቸውን ይለግሳሉ።
አዲስ ዘመን የካቲት 21 ቀን 2015 ዓ.ም