ፓን አፍሪካኒዝም መላውን የዓለም ጥቁር ሕዝብ እንደ አንድ አፍሪካዊ ቤተሰብ የሚመለከት አስተሳሰብ ወይም ንቅናቄ ነው። ንቅናቄው በዋነኝነት የቅኝ ግዛት መስፋፋትን ወይም የነጭ የበላይነትን ለመዋጋት እና አፍሪካዊ አንድነትን ለማጠናከር የታለመ ነበር። ፓን አፍሪካኒዝም በፖለቲካ፣ በሥነጽሑፍ፣ በሙዚቃ፣ በባህል እና በመሳሰሉት ዘርፎች የተቃኘ ሰፊ ንቅናቄ ነበር። ይህ ንቅናቄ መሠረቱን በአገረ አውሮፓ እና አሜሪካ ያድርግ እንጂ የንቅናቄው መንፈስ እና ብርታት ኢትዮጵያ ነበረች። በዚህም ኢትዮጵያ በፓን አፍሪካኒዝም እንቅስቃሴ ውስጥ የጥቁር ሕዝቦች ሁሉ ኃይል እና ኩራት ተደርጋ ትወሰዳለች። የዚህ አስተሳሰብ እና እምነት ገፊ ምክንያት ደግሞ ኢትዮጵያ በማንኛውም የቅኝ ገዥ ኃይል ያልተንበረከከች ብቸኛ አፍሪካዊት አገር መሆኗ ነው።
ኢትዮጵያ እና ፓን አፍሪካኒዝም ያላቸውን ትስስር ብሎም በፓን አፍሪካኒዝም ጽንሰ ሐሳብ ዙሪያ ማብራሪያ እንዲሰጡን ካነጋገርናቸው ምሁራን መካከል በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካል ሳይንስ እና ዓለምአቀፍ ግንኙነት መምህር እና ተመራማሪ ዶክተር ደመቀ አጭሶ ናቸው። እርሳቸው እንደሚናገሩት፤ ፓን አፍሪካኒዝም በዋናነት ግቡ አንድ እና አንድ ነው፤ ይኸውም የአፍሪካን ውህደት ማምጣት ነው። ውህደት ስንል የመንፈስ፣ የሥነልቦና፣ የፖለቲካ፣ የኢኮኖሚ ውህደት ማምጣት እና በጋራ እንደ አንድ አህጉር በመቆም በዓለም ላይ አፍሪካ ያላትን ተፅዕኖ ከፍ ማድረግ ነው። በተጨማሪም በግሎባል ፖለቲካል ኢኮኖሚ ላይ ያላትን ሚና ማላቅ ነው። በቴክኖሎጂ፣ በንግድ ትስስር አፍሪካ እርስ በእርስ ያለው ውህደት ፀንቶ ሌሎች አገራት የደረሱበት ደረጃም ማድረስ ነው። አፍሪካ አሁንም በ21ኛው ክፍለ ዘመን በርካታ የጥይት ድምጽ የሚሰማባት አህጉር ናት፤ እነዚህን ሁሉ ችግሮች ለመቅረፍ በርካታ ግቦችን ይዞ የሚንቀሳቀስ ነው፤ ዋናው ነገር ግን አፍሪካ በዓለም ላይ ጫና የመፍጠር ብሎም የመደራደር አቅሟን ከፍ እንዲል ግብ ይዞ የሚንቀሳቀስ ታላቅ ርዕይ እና ዓላማ ያለው ነው።
ዶክተር ደመቀ ለዚህ ራዕይ አለመሳካት ተግዳሮት ነው የሚሉትን ሲያነሱ እንዳብራሩት፤ አንደኛ እንደ አህጉር ያሉት በርካታ አገራት ናቸው። የሕዝብ ቁጥሩም አንድ ነጥብ አራት ቢሊዮን ይደርሳል ተብሎ ይገመታል፤ እነዚህን ሁሉ አገራት አንድ ላይ ማምጣት በራሱ ፈተና ነው። ሁለተኛ በቅኝ ግዛቱ ምክንያት የቅኝ ገዢዎቻቸው ባህል እና ተጽእኖ የተቋማት ግንባታ ሒደቱ ላይ ጫና አሳድሮባቸዋል። ይህንን ሁሉ ክፍፍል አንድ ላይ አምጥቶ የሚፈለገውን ርቀት ለመሄድ አሁንም የሥነልቦና ዝግጅት ያስፈልጋል። ሦስተኛው ኢኮኖሚ ነው፤ የአፍሪካ ውህደት በዓለም ላይ ያለው የተደማጭነት ሥነልቦና ከፍ እንዲል ማድረግ የተግባር እንቅስቃሴ ይፈልጋል። በተግባር ካልሆነ እውን ሊሆን አይችልም። ለዚህ ደግሞ የኢኮኖሚ አቅም ያስፈልጋል፤ ከውጭ እርዳታ ጥገኝነት መላቀቅ የግድ ይላል። ስለዚህ እነዚህን መሠረታዊ ችግሮች መቅረፍ እና የአፍሪካን ትስስር የፓን አፍሪካኒዝም መንፈስ ማምጣት እንደመናገር ቀላል አይደለም። በመሆኑም ሒደት እና ጽናት ይፈልጋል።
የፓን አፍሪካኒዝም ንቅናቄ ምክንያት ከሆነው አንዱ በ19ኛው ክፍለ ዘመን አፍሪካውያን በዓለም ኢኮኖሚ ላይ በደንብ የተዋሃዱ ስላልሆኑ እና በተለይ በቴክኖሎጂ ወደ ኋላ በመቅረት እንዲሁም ከሰው ኃይል አኳያ በባርነት ሥርዓት ብዙ ቦታ ተበትነው በመኖራቸው እንደሆነ ተመራማሪው ዶክተር ደመቀ ይናገራሉ። በመጀመሪያ አፍሪካውያኑ በሄዱበት ቦታ ሁሉ እንደ ሰው ሰብዓዊነታቸው ተጠብቆ ከሌላው ዓለም ጋር በደንብ የተዋሃዱ ሆነው ሌላው የሰው ልጅ የሚያገኘውን ክብር አያገኙም ነበር ይላሉ።
አፍሪካውያን በአስተሳሰብም በሌላም በሚሠሩት ሥራ ከሌላው በተለየ አፍሪካዊ በመሆናቸው ብቻ መድልዎ ይፈፀምባቸው ነበር። ስለሆነም ፓን አፍሪካኒዝም በበርካታ የአፍሪካ ምሁራን በዓለም ዙሪያ በተለይ በአውሮፓ እና አሜሪካ የተጠነሰሰ እንቅስቃሴ መሆኑን ዶክተር ደመቀ ያስረዳሉ። በዚህ በፓን የአፍሪካኒዝም እንቅስቃሴ አፍሪካውያን ይህንን መገለል ለማስቀረት ባሉበት ቦታ ሁሉ የመንፈስ እና የተግባር አንድነትን አምጥተው መቆም እንዳለባቸው እና በዚሁ መንፈስ ሲቆሙ ደግሞ እንደ አንድ አህጉር ብሎም አንድ ድምፅ ተደማጭነታቸውን ለመጨመር እንደሆነም ይናገራሉ። በዓለም ፖለቲካል ኢኮኖሚ ላይ ያላቸው ተጽዕኖ ከፍ እንዲል በአንድነት የመቆም እንቅስቃሴ እንደነበርም ነው ታሪካዊ ዳራውን አውስተው የሚያብራሩት።
እንደ ተመራማሪው ዶክተር ደመቀ አባባል፤ ይህ እንቅስቃሴ በ19ኛው ክፍለ ዘመን መጨረሻ እና በ20ኛው ክፍለ ዘመን መጀመሪያ አካባቢ ጠንከር ብሎ ቀጥሏል፤ ከዚያ በኋላ እንቅስቃሴው እያደገ እና እየሰፋ መጥቶ ወደ 1960ዎቹ በቅኝ ግዛት ተገዝተው የነበሩ አገራት ከቅኝ ግዛት እራሳቸውን ማላቀቅ የጀመሩበት ጊዜ ነበር።
በአፍሪካ ብቸኛዋ በቅኝ ያልተገዛች አገር ኢትዮጵያ ናት ያሉት ዶክተሩ፣ ሌሎቹ በቅኝ ግዛት ውስጥ ማለፋቸውን ተናግረዋል። እስቴቶቹም አገራቱም የተመሠረቱት ከቅኝ ግዛት ጋር ተያይዞ ስለነበር በኢትዮጵያ ዙሪያ ያሉ አገራትም የቅኝ ግዛት ውጤት እንደሆኑ ጠቅሰው፤ ኢትዮጵያ ከጎረቤት አገራት ጋር ያላትን ጉዳይ ስታካሂድ የቆየችው ከጎረቤቶቿ ጋር ሳይሆን እነርሱን በቅኝ ከገዙ የቅኝ ገዥዎቻቸው ጋር እንደነበር አውስተዋል። ስለዚህ በ1960ዎቹ አፍሪካን መልሶ ነፃ ማውጣት የሚሉ እንቅስቃሴዎች ብሎም የነፃነት ትግሎች በየቦታው ነበሩ ሲሉ አስረድተዋል።
ዶክተር ደመቀ፣ ኢትዮጵያ ተምሳሌት የሆነችበትን ምክንያት ሲያብራሩ፤ ኢትዮጵያን ለመውረር ከፈረንሳይ፣ ከእንግሊዝ እንዲሁም ከጣሊያን በኩል ፍላጎት ነበር። አገራቱ ኢትዮጵያን በመውረር እንደ ሌሎቹ የአፍሪካ አገራት እናንበረክካታለን የሚል እሳቤ ነበር፤ በሰዓቱ የነበሩ መሪዎች በተለይ ምኒልክ የነበራቸው ቁመና ከአውሮፓውያን ጋር እኩል ባይሆንም ዘመናዊ ዲፕሎማሲ የገባቸው ስለነበር ኢትዮጵያን በዙሪያዋ የከበቡ ኃይላት እርስ በእርስ እንዲጠባበቁ በማድረግ የኢትዮጵያ ሉአላዊነት እንዳይደፈር በማድረግ ትልቅ የዲፕሎማሲ ሥራ መሥራት ችለዋል። በዚህም ኢትዮጵያ በቅኝ ግዛት እንዳትገዛ ማድረግ በመቻላቸው ታላቅ ድል አስመዝግበዋል። የኢትዮጵያ የፓን አፍሪካኒዝም አስተዋፅኦ የጀመረውም ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ሲሆን፣ በአድዋ ድል ምክንያት ኢትዮጵያ የአፍሪካ የነፃነት ቀንዲል ተደርጋ የምትወሰድ አገር መሆን ችላለች። ድሉ በመሪ ደረጃ ብቻ የተገኘ ሳይሆን እንደ አገርም እንደ ሕዝብም ለአፍሪካ ያበረከትነው አስተዋፅኦ ጉልህ መሆኑንም የሚያሳይ ነው። ይህ ደግሞ ዓለም ያወቀው ሃቅ መሆኑ አይካድም።
ያንኑ ይዞ በ1960ዎቹ ላይ ብዙ የአፍሪካ አገራት ነፃ በወጡበት ወቅት ኢትዮጵያ ስትሠራ የነበረው ‹‹አፍሪካ በአንድነት መቆም አለባት›› በሚል እሳቤ ነበር። ብዙዎች የአፍሪካ አገራት ከቅኝ ግዛቱ በኋላ የተከፋፈለ መንፈስ ነበራቸው፤ ከዚህም የተነሳ የአፍሪካን አንድነት እውን እንዲሆን ለማድረግ ከመግባባት ላይ መድረስ አልቻሉም። በመሆኑም በወቅቱ የነበሩት የኢትዮጵያ መሪ አጼ ኃይለሥላሴ በቅኝ እንዳልተገዛ አገር ለአፍሪካውያን ተምሳሌት በመሆን እርስ በእርስ እንዲግባቡ በማድረግ በ1963 ዓ.ም የአፍሪካ አንድነት ድርጅት በአዲስ አበባ እንዲቋቋም በማድረግ ኢትዮጵያ ለፓን አፍሪካኒዝም መሠረት መጣሏን ዶክተር ደመቀ አስረድተዋል።
እንደ ዶክተር ደመቀ ገለጻ፤ የደርግ ሥርዓትም ለፓን አፍሪካኒዝም በርካታ ሥራዎችን ሠርቷል፤ ቅኝ ግዛቱ ስላለቀ በ1970ዎቹ የተለያዩ አፍሪካውያንን በማሰልጠን ነፃነታቸውን ማግኘት እንዲችሉ የተጫዋተው ሚና ትልቅ ነው። ይህ አካሄድ ቀጥሎ በዘመነ ኢህአዴግ የወቅቱ የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር የነበሩት አቶ መለስ ዜናዊ የአፍሪካ ኅብረት መቀመጫ ከአዲስ አበባ ለማንሳት እንቅስቃሴ በነበረበት ወቅት ለኅብረቱ ኢትዮጵያ ያበረከተችውን አስተዋፅኦ በማውሳት የኅብረቱ መቀመጫ ኢትዮጵያ ሆና እንድቀጥል አድርገዋል።
በአሁኑ ወቅት ያሉትም የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር፣ ለፓን አፍሪካኒዝም መነቃቃት የራሳቸውን ሚና እየተወጡ ነው፤ በተለይ በጎራቤት አገራት የሰላም ሂደት፣ በአረንጓዴ አሻራ፣ በተባበሩት መንግሥታት አፍሪካ ተገቢውን ቦታ እንድታገኝ፣ ለአፍሪካ ችግሮች አፍሪካዊ መፍትሔ እንዲኖር በማድረግ እየሠሩት ያለው ሥራ የኢትዮጵያ የአፍሪካ ተምሳሌትነት ዛሬም እንዲቀጥል ያስቻለ እንደሆነ ዶክተር ደመቀ ገልፀዋል።
በአርሲ ዩኒቨርሲቲ የሥርዓተ ትምህርት እና ፖሊሲ ጥናት መምህር እና ተመራማሪ የሆኑት ዶክተር እንዳለው ፉፋ በበኩላቸው፤ ኢትዮጵያን በየጊዜው የመሩ መሪዎች በአገራቸው ዴሞክራሲ በማስረፅ ሂደት ብዙም የተሳካላቸው ባይሆንም ለአፍሪካ አንድነት እና ለፓን አፍሪካኒዝም መርህ የነበራቸው ቁርጠኝነት ትልቅ እንደነበር አስታውሰዋል። በሌላ ጎኑ የአገራት ሥርዓት እና መሪዎች በየጊዜው መቀያየር እና ከዜሮ የመጀመር ዝንባሌ መብዛቱ ብሎም ግጭት መበራከቱ የፓን አፍሪካኒዝሙን እንቅስቃሴ በሰከነ መልኩ ሄዶ ውጤታማ እንዳይሆን አድርጎታል ይላሉ። አፍሪካውያን የሚያጋጥሟቸውን ችግሮች በውስጥ ተነጋግሮ የመፍታት ባህል አናሳ መሆን ለውጭ ኃይላት ጣልቃ ገብነት ዳርጓቸዋል። በጥናት ላይ የተደገፈ ተቋማዊ ሥራ አለመሠራቱ እና በሁሉም ዘርፍ ችግሮችን በጋራ የመቋቋም ሁኔታ በማህበራዊ ብሎም በኢኮኖሚያዊ ጉዳይ የጋራ አተያይ የመፍጠር ችግር አለባቸው። የውስጥን አካሄድ፣ የመበልፀግ እንዲሁም እርስ በእርስ በጋራ የመሥራት ልምዱ ገና ጥሬ ነው። ሁሉም በሩን ዘግቶ ይቀመጣል፤ ለፓን አፍሪካኒዝሙ ስኬት በጋራ የመሥራት ቁርጠኝነት አሁንም አነስተኛ ነው ብለዋል።
ስለዚህ በተለያዩ ቀጣናዎች በአንድ አንድ አገራት መካከል ያለው ጅምር በመሠረተ ልማት የመተሳሰር እንቅስቃሴ መስፋት በመንገድ፣ በንግድ እንዲሁም ሕዝብ ለሕዝብ ያለውን ግንኙነት እንዲዳብር ማድረግ ይገባል፤ ይህ እንዳይሆን ደግሞ በየጊዜው ሥርዓት እና መንግሥታት በተለዋወጡ ቁጥር እርስ በእርስ ያለው ግንኙነት የሰከነ አለመሆን ተግባራዊነቱ ላይ የራሱን አሉታዊ አስተዋፅአ አበርክቷል ይላሉ። በየአገራቱ ከሥርዓት ለውጥ በኋላ ያለፈውን ሥርዓት በመውቀስ ብቻ መጠመድ እንዲሁም ጉድለቶችን በማረም መልካም ነገሮችን ማስቀጠል አለመቻል ሌላው ችግር እንደሆነም ዶክተር እንዳለው አስረድተዋል።
ዶክተር ደመቀ፣ ለፓን አፍሪካኒዝሙ ስኬት የአህጉሪቱ መሪዎች ሚና የመጀመሪያው የውስጥ የፖለቲካ ሥርዓታቸውን ማዘመን መቻል ነው። ሥርዓቱ ተጠያቂነት ያለው እንዲሆን ማድረግና የሕግ የበላይነት የሰፈነበት የፖለቲካ ሥርዓት መገንባት ወሳኝ ነው። የኢኮኖሚ አቅማቸውን ማሳደግ፣ የዴሞክራሲ ተቋማትን በደንብ ማዘመን እና መገንባት በጣም አስፈላጊ ጉዳይ ነው። ስለዚህ ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ፖለቲካዊ ለውጦች በውስጥ የፖለቲካ ሥርዓት ላይ መምጣት መቻል አለባቸው። ሁለተኛው አፍሪካ የጥሬ ዕቃ አቅራቢ ብቻ ሆና መቀጠል የለባትም። ርካሽ የጥሬ ዕቃ እና የሰው ኃይል እየፈሰሰ ያለው ከአፍሪካ አህጉር ወደ ሌሎች አህጉራት ነው። ደሴት ሆኖ መኖር ስለማይቻል ከዓለም ጋር ትስስር መፍጠር ጥሩ ነው። ነገር ግን ጥቅም እና ጉዳቱን ማስላት አስፈላጊ ነው።
ዶክተር ደመቀ እንደሚሉት፤ ጥሬ ዕቃ ወደ ውጭ ከመላክ ይልቅ እሴት ጨምሮ መሸጥ የሚቻልበትን የአሠራር ዘዴ መፍጠር፣ የቴክኖሎጂ አቅምን ማዳበር እና የአፍሪካ አገራት ከሌላው ዓለም ጋር እንዲኖራቸው የሚፈልጉትን ያህል ግንኙነት እርስ በእርስ በተለይ የንግድ ትስስር እንዲኖራቸው በርትተው መሥራት አለባቸው። ሌላው የአፍሪካ መሪዎች በየጊዜው ግንኙነት በማድረግ ተቋማት እየተገነቡ ነው ወይ? የሚለውን በመገምገም ሌሎች የደረሱበት የውህደት ደረጃ በአፍሪካ ውስጥም እንዲመጣ በተለይ ነፃ የንግድ ቀጣና ለማስፋፋት ቁርጠኝነት በመውሰድ መሥራት ያስፈልጋል። አህጉሪቱ ዛሬም በእርዳታ ሰጪ አገራት የእጅ አዙር ቅኝ ግዛት ውስጥ እንዳትወድቅ በፋይናንስ እራስን ለመቻል በትጋት መስራት የግድ ይላል።
ክብረአብ በላቸው
አዲስ ዘመን የካቲት 21 ቀን 2015 ዓ.ም