እኛ ኢትዮጵያውያን በየዘመኑ ከፍያሉ መስዋዕትነቶችን የጠየቁ ተጋድሎዎችን በማድረግ የነፃነታችን
ባለቤት በመሆን በዓለም አቀፍ ደረጃ የገዘፈ ታሪክ ባለቤት መሆን የቻልን ሕዝቦች ነን። ይህ የተጋድሎ
ታሪካችን ከእኛም አልፎ በአፍሪካና ካረቢያን የሚገኙ ጥቁር ወንድሞቻችን የአልገዛም ባይነትን መንፈስ
አምጠው እንዲወልዱ ሁነኛ የአቅም ምንጭ ሆኗቸዋል፤ ዛሬ ላይ ለሚያጣጥሙት ነፃነታቸውም ፈር ቀዳጅ
መሆናችን የተረጋገጠ ነው።
የዓድዋ ድል ከነዚህ የነፃነት የተጋድሎ ታሪካችን ውስጥ በዋነኛነት የሚጠቀስ ነው። በጥቁር ሕዝቦች
ታሪክ ውስጥም እንደ አንድ ታላቅ ዓይን መግለጫ ክስተት፤ የአይቻልምን የገዘፈ ቀንበር ከጥቁር ሕዝቦች
ትከሻ ላይ አሽቀንጥሮ መጣል የሚያስችል መነቃቃትን የፈጠረ፤ ለእነዚህ ሕዝቦች የአዲስ የነፃነት ትግል
ታሪክ ምዕራፍ መክፈቻ ተደርጎ የሚወሰድ ነው ።
ኢትዮጵያውያን ለአገራቸው ካላቸው ጥልቅ ፍቅር የተነሳ ዘር እና ሃይማኖት ሳይለያቸው ቀፎው
እንደተነካበት ንብ በአንድነት በመንቀሳቀስ ስለአገራቸው ከፍ ያለ መስዋዕትነት በመክፈል የቀደሙ አባቶች
በብዙ መስዋዕትነት ያቆይዋትን በነፃነቷ የተከበረች አገር በሌላ ተጨማሪ የተጋድሎ ታሪክ ለመጪው ትውልድ
ማስረከብ የቻሉበት ነው።
ጥልቅ የአገር ፍቅር ስሜትና ከዚህ የሚመነጭ ለአገር መስዋዕት ሆኖ የማለፍ መነቃቃት የታየበት የዓድዋው
ጦርነት፤ ሁኔታዎች ወራሪው ኃይል እንዳሰበው ሳይሆን መልካቸው ተቀይሮ ዓለም አቀፍ አጀንዳ
እንዲሆኑ ያደረገና ዓለም ስለ ጥቁር ሕዝቦች የነበረውን የተሳሳተ አመለካከት መልሶ እንዲያጤነው አስገዳጅ
ሁኔታ መፍጠር ያስቻለ ነው።
ከሁሉም በላይ ኢትዮጵያውያን በየትኛውም ሁኔታ ውስጥ ቢሆኑምና ማንም ወራሪ የቱንም ያህል የገነገነ
ቢሆን፤ ለነፃነታቸው ካላቸው ቀናኢነት አንጻር፤ ነፃነታቸውን ከእጃቸው ፈልቅቆ ማውጣት በቀላሉ የማይታሰብ
መሆኑን ከፍ ባለ የተጋድሎ መስዋዕትነት ያሳየ፤ ለዚህ የሚሆን አዲስ የታሪክ ትርክት የፈጠረ ነው።
ኢትዮጵያውያን ለአገር በሆነ ጉዳይ ለሚቀርብ ብሔራዊ ጥሪ ጨርቄን ማቄን እንደማይሉ፤ በየትኛውም
ሁኔታ ለኢትዮጵያውያን ለአገር መሞት ትልቅ ክብር እንደሆነ በወቅቱ የነበረው ትውልድ በተግባር ማሳየት
እንዲችል ያደረገ፤ በዚህም ጉዳይ ዓለም አቀፉ ኅብረተሰብ ከታሪክ ባለፈ ተጨባጭ ማኅበረሰባዊ እውነታውን
በዓይኑ መታዘብ የቻለበትን ዕድል የፈጠረ ነው።
መላው የአገሪቱ ሕዝብ ለነፃነቱ ካለው ቀናኢነት የተነሳ ከነበረው የጦርነት ተሳትፎ ጎን ለጎን፤ ጦርነቱ
የተመራበት አገር በቀል ስትራቴጂ በርግጥም ኢትዮጵያውያን ጦርነትን የመምራትና በድል የማጠናቀቅ
አቅም ባለቤት መሆናቸውን በአደባባይ መመስከር ያስቻለ ነው። አገሪቱን በኃይል ለማንበርከክ የሚደረጉ
ጥረቶች ዋጋ እንደሚያስከፍሉም በተግባር ማሳየት ያስቻለ ክስተት ነው።
ይህ የሕዝባችን ፍጹም አንድነት የታየበት፤ አንድነት የድል መሠረት መሆኑ በተጨባጭ ትልቅ አገራዊ
ተሞክሮ የሆነበት የዓድዋ ጦርነትና በጦርነቱ የተገኘው ድል፤ ዛሬም ድህነትን አሸንፈን የበለጸገች አገር
ለመመስረት ለምናደርገው እልህ አስጨራሽ ትግል ትልቅ ተሞክሮ ስለሚሆን ከዚህ ድል ዛሬ ላይ ብዙ ልንማር
እንደምንችል ይታመናል።
አባቶቻችን በብዙ መስዋዕትነት ያስረከቡን ነፃነታችን በዚህ ዘመን ከሚኖረው ያልተሟላ ትርጉም
አንጻር፤ ይህንን ነፃነት ምሉእ ለማድረግ የጀመርነውን ድህነትን አሸንፎ የመውጣት እልህ አስጨራሽ ትግል
በዓድዋ አባቶቻችን እንዳደረጉት ሁሉ ጨርቄን ማቄን ሳንል ተቀብለን ለመጪው ትውልድ የተሟላ ነፃነት
የማስረከብ ኃላፊነታችንን ልንወጣ ይገባል።
ዛሬ ላይ አገራዊ ነፃነታችንን የተሟላ በማድረግ በዓለም አቀፍ መድረኮች አንገታችን አቅንተን፤ በልበ
ሙሉነት ለመመላለስ፤ መንግሥት ድህነትን ለማሸነፍ ያቀረበውን አገራዊ ጥሪ መቀበል፤ ለዚህ የሚሆን
ተነሳሽነትና ቁርጠኝነት መፍጠር ይጠበቅብናል።
በአጠቃላይ ኅብረብሔራዊ አንድነታንን በማጽናት የዓድዋው ድል ቀጣይ የሆነውን የኢኮኖሚ ድል
በተባባረ ክንድ እውን በማድረግ እንደቀደመው ዘመን ለሌሎች ወንድሞቻችን የይቻላል መንገድን ማመላከት
ከአሁኑ ትውልድ የሚጠበቅ አገራዊ ኃላፊነት ነው።
አዲስ ዘመን የካቲት 21 ቀን 2015 ዓ.ም