በአንድ ማኅበራዊ ግንኙነት አጋጣሚ ከንባብ ጋር በተነሳ ርዕሰ ጉዳይ ላይ አንድ ግለሰብ እንዲህ ሲል ሃሳቡን ሲሰጥ ሰማሁ፤ «ማንበብ ምን ይሠራል? መጻሕፍት በተለያዩ ሰዎች ሃሳብ የተሞሉ ናቸው። ታሪክም ቢሆን በጸሐፊው እይታ የሚጻፍ ነው። እኔ ደግሞ በነዛ ሰዎች መንገድ ማሰብ ስለማልፈልግ ነው መጽሐፍ የማላነበው…» አለ። ይህን ሃሳብ ምን ያህል ሰዎች ሊጋሩት እንደሚችሉ አላውቅም፤ ነገር ግን መጻሕፍትን ማንበብ በዛ መልክ የሚታይ ጉዳይ ነው?
በዚህ ሰው ሃሳብ ላይ ከዚህ የተሻለ ጥያቄ አንስተው የሚጠይቁ፤ አልፈውም መርታት የሚችሉና ሃሳቡን ከደካማ ሃሳብ ተራ ሊከቱት የሚችሉ ተናጋሪዎች እንደሚኖሩ አልጠራጠርም። ግን ይህኛው ይቆየንና በአስተሳሰብ ልቀው የተገኙና ዓለማችን አሁን ያላትን መልክ ያስያዟት ሰዎች ከመጻሕፍት ምን ተጠቅመዋል ብለን እንጠይቅ።
በኢትዮጵያ ብሔራዊ ቤተመዛግብትና ቤተመጻሕፍት ኤጀንሲ የሥልጠናና ምርምር ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ መኮንን ከፋለ «ንባብ የወለዳቸው ልሂቃን» በሚል ርዕስ አንድ የዳሰሳ ጥናት አዘጋጅተዋል። ከላይ ላነሳሁት ጉዳይም ይህ የዳሰሳ ጥናት የተለያዩ ሃሳቦች የሚያቀብል በመሆኑ በዚህ ላቀርበው ወደድኩ።
በዚህ የዳሰሳ ጥናት መሰረት ንባብ እንዲሁ በቀላል ልንገምታቸው ከምንችላቸው በላይ ጥቅሞች እንዳሉት ተጠቅሷል። እነዚህም ምን አልባት አንድ መንገደኛ «ንባብ ለምን ይጠቅማል?» ተብሎ ቢጠየቅ በምላሹ ሊሰጣ ቸው ከሚችላቸውና ብዙዎቻችን በጋራ ከምንስ ማማባቸው ላቅ ያሉ ናቸው። ለምሳሌ አንዱ ንባብ ለጤና ጥቅም እንዳለውና ራስን ከበሽታ ለመከላከል ጭምር እንደሚጠቅም ነው።
ይህ እንዴት ይሆናል? ተመራማሪዎች ንባብ የአንድን ሰው ጭንቀት ያስወግዳል፤ የዓይናማውን የዓይን ጡንቻ እንዲጠነክር ያደርጋል፤ ዕድሜን ያራዝማል ይላሉ። ጥናቱ እንደሚያመለክተው ደግሞ ከዛ በተጓዳኝ የአእምሮ ንቃትን ይጨምራል፤ መርሳትን ይቀንሳል ብሎም ያስወግዳል። በተለያየ ጊዜ እንደምንሰማውና እንደምናየውም ማንበብ
ጠያቂ እና ሞጋች ስብዕና ያላብሳል፤ ልበ ሙሉ እና ባለ ርቱዕ አንደበት ያደርጋል።
ታድያ በዚህ መሰረት በብዛት ከንባብ የማይርቁ ሰዎች አእምሯቸው ፈጣንና ብሩኅ፣ መንፈሰ ጠንካራ፣ ትዕግስተኛና አስተዋይ ሆነው እናገኛቸዋለን። ከዚህም አልፎ ዓለምን መምራት የቻሉት ያነበቡትና የጻፉት መሆናቸውን እንረዳለን። በዙሪያችን የምናየው እያንዳንዱ ለውጥም ከመጻሕፍትና መጻሕፍትን ካነበቡ ሰዎች የመነጨና የተገኘ ነው።
በዳሰሳ ጥናቱ እንደተጠቀሰው፤ ዴል ካርኒግ የተባለ አሜሪካዊ ጸሐፊና መምህር በንባብ ዙሪያ «ከውስጣችን ታላላቅ ሃሳቦች እንዲወጡ ከፈለግን በቅድሚያ ታላላቅ ሃሳቦችን ወደ ውስጥ ማስገባት አለብን» ብሏል። ታድያ ይህን ብሂል በመግቢያችን ላይ ጠቀስ ላደረግሁትና «ሰዎች የጻፉትን ማንበብ ጭንቅላትን በሰዎች አስተሳሰብ መሙላት ነው።» ላለው ሰው እንደ አንድ ሃሳብ ጣል አድርገን ወደነገራችን እንጠልቃለን።
የዳሰሳ ጥናቱ የንባብን ጥቅም ጠቃቅሶ በንባብ ታላላቅ ሃሳቦችን ወደ ራሳቸው አስገብተው የላቁ ሃሳቦችን ማካፈል ስለቻሉ ኢትዮጵያውያን አንስቷል። እነዚህ ሰዎች በአንድ በኩል ዘመናዊ በሚባለው የቀለም ትምህርት ብዙ ያልገፉ ናቸው። ነገር ግን በንባብ ራሳቸውን አስተምረውና እይታቸውን አስፍተው ሰፊውን አድማስ ለብዙዎች ማሳየት ችለዋል።
ቀዳሚው ክቡር ዶክተር ሀዲስ ዓለማየሁ ናቸው። ደራሲ ሀዲስ ዓለማየሁ በልጅነታቸው በቤተክርስቲያን ትምህርት ተኮትኩተው ያደጉ ሲሆን ዘመናዊ በሚባለው የቀለም ትምህርት ግን ከሰባተኛ ክፍል በላይ የዘለሉ እንዳልሆነ ታሪካቸው ያስረዳናል። በእርግጥ በቀደመው ጊዜ በቤተክርስቲያን የሚሰጠው ትምህርት በአንድ በኩል የንባብ ክህሎትን ሲያዳብር በተጓዳኝ የሰላ አስተሳሰብና የተባ ብዕር ያላቸው ልሂቃን እንዲፈጠሩ ምክንያት መሆኑ የሚዘነጋ አይደለም።
አገራችንም የቀደመውን ስልጣኔዋን ልታገኝ የቻለችው ከእነዚህ ከሃይማኖት ትምህርት ቤቶች በወጡ ሊቃውንት ነበር እንጂ የትምህርት ስርዓትና የትምህርት ዓይነት ከባህር ማዶ የተቀዳበት ዘመን አልነበረም። ታድያ በጥቅሉ ኮርተን «ይመለሳል!» የምንለው የኢትዮጵያ የቀድሞ ቁመና ራሳቸውን በንባብ ባበለጸጉ ሰዎች የተገኘ ነው ማለት እንችላለን። ይህም ይቆየንና ወደ ዳሰሳ ጥናቱ እንመለስ።
ታድያ ደራሲ ሀዲስ ዓለማየሁ በዚሁ መልክ በቀለም ትምህርት የገፉ አልነበሩም። ይሁንና ከመምህርነት ጀምሮ ከፍተኛ በሆኑ የመንግሥት የስልጣን ደረጃዎች ላይ ማገልገል የቻሉ ሰው ናቸው። ብዙዎችም በሚያውቁት «ፍቅር እስከ መቃብር» ረጅም ልብወለድ መጽሐፍና በሌሎች ልቦለዳዊ ድርሰቶችም ቀዳሚውን ስፍራ ይዘው ይገኛሉ። ለአገራችን የሥነ ጽሑፍ እርምጃ አንድ አስተዋጽኦ የነበራቸውና የድርሻቸውን ያራመዱ እንደሆኑም ይታወቃል።
ሌላው ደራሲና ጋዜጠኛ ማሞ ውድነህ ናቸው። ደራሲ ማሞ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህር ታቸውን ቢያጠናቅቁም፤ በግልጽ ባልተለየ ምክንያት የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን መከታተል እንዳልቻሉ የተለያዩ ታሪካቸው የሰፈረባቸው መዛግብት ያስረዳሉ። ይሁንና በቁጥር 53 የሚደርሱ መጻሕፍትን ከእንግሊዝኛ ወደ አማርኛ ተርጉመው አስነብበዋል። በተለያዩ የኃላፊነት ቦታዎችም ላይ ለዓመታት አገልግለዋል።
ልክ እንደ ማሞ ውድነህ ሁሉ ደራሲና ጋዜጠኛ ጳውሎስ ኞኞ ይነሳል። ጳውሎስ ኞኞ የቀለም ትምህርትን እስከ አራተኛ ክፍል ድረስ ብቻ ነው የተማረው። ነገር ግን አነሰ በዛ ሳይልና ሳይንቅ ያገኘውን ሁሉ ያነብ የነበረ ሰው ነው። እናም ተምረዋል ከሚባሉት በላይ ስሙ ዛሬም ድረስ የሚነሳው እርሱ ነው። እንዴት?
ጳውሎስ ኞኞ በጋዜጠኝነት አንቱ የተባለ ከመሆኑ ባሻገር አሥራ ዘጠኝ መጻሕፍትን ለአንባብያን አድርሷል። በአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንኳ «አንድ ጥያቄ አለኝ» የሚለው አምድ ላይ ሳይታክት ለጥያቄዎች ሁሉ መልስ ይሰጥ የነበረውና አድናቆትንም ያገኘው ከዚሁ ከንባብ ልምዱ በመነጨ እንደሆነ ይኸው ዳሰሳ ጥናት ያስረዳል።
ከእነዚህ ሰዎች በተጨማሪ ዘመናዊ የሚባ ለውን የቀለም ትምህርት ወደጎን ትተን፤ በንባብ ራሳቸውን በማሳደግ የበለጠውን በረከት ስላካፈሉት ሌላ ሰው እናንሳ። እኚህም ብላቴን ጌታ ኅሩይ ወልደሥላሴ ናቸው። ኅሩይ ከቤተክህነት ትምህርት ዘልቀው ራሳቸውም የቅኔና የመጻሕፍት መምህር ሆነው እንዳገለገሉ ታሪካቸው ያስረዳል። እኚህ ሰው አገራቸውን በተለያየና በብዙ መንገድ የሠሩም ጭምር ናቸው። የሕይወት ታሪካቸውን ያነበበና የሚያውቅ ደግሞ እኚህ ሰው ምን ያህል እንደሚልቁ ያውቃልና ይህ አንቀጽ ዋጋ ቢስ ቅንጣት እንደሆነ ሊያስተውል ይችላል።
ብላቴን ጌታ ኅሩይ በቁጥር 245 የሚሆኑ የኢትዮጵያ ነገሥታትና ምኁራንን ታሪክ እንዲሁም ሌሎች መጻሕፍትን አዘጋጅተዋል፤ ጽፈዋል። እንደውም እርሳቸው የጻፏቸው መጻሕፍት በኢትዮጵያ ዘመናዊ ትምህርት ሲጀመር ለማስተማሪያነት ያገለገል እንደነበር የአቶ መኮንን ጠናት ይገልጻል። ታድያ ይህ ሁሉ ተግባራቸው ለንባብ መስፋፋትና አንባቢ ትውልድን ለመፍጠር ትልቁን ድንጋይ ያቀበሉ አድርጓቸዋልና፤ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቤተመዛግብትና ቤተመጻሕፍት ኤጀንሲ የንባብ አዳራሹን «የብላቴን ጌታ ኅሩይ አዳራሽ» ብሎ መሰየሙ አይረሳም።
አናሲሞስ ነሲብ ሌላው በዚህ አውድ የሚነሱ ሰው ናቸው። እኚህ ሰው ከልጅነታቸው ጀምሮ የሃይማኖት መጻሕፍትን አብዝተው ያነቡ የነበሩ ናቸው። እኚህ ሰው ለኦሮምኛ ሥነ ጽሑፍ ጅማሮና እርምጃ ብዙ ያበረከቱ መሆናቸውም ይነሳል። የብሉይና ሀዲስ ኪዳን መጻሕፍትን ወደ ኦሮምኛ ቋንቋ ተርጉመው በመጻፍም ይታወቃሉ።
አቶ መኮንን ከፋለ ባቀረቡት ዳሰሳ ላይ እነዚህን አንጋፎች ልሂቃን ይጥቀሱ እንጂ ሌሎች በርካቶች መኖራቸው እሙን ነው። ታድያ እንደ መጠቆሚያ ቢሆኑ ተብለው የተጠቀሱ ከንባብ የተወለዱ ልሂቃን፤ ማንበብ ለብቻው የት እንደሚያደርስ ምስክር ይሆናሉ። ጥናቱም መዝጊያው ላይ እንደሚለው አገራዊ ኃላፊነቶችን በብቃት መወጣት የቻሉትና ዘመን ተሻጋሪ የሥነ ጽሑፍ ሥራዎችን ማበርከት የቻሉት እነዚሁ ንባብ የወለዳቸው ልሂቃን ናቸው።
ትምህርት አሁን ላይ በአገራችን ተስፋፍቷል፤ ሁሉም ሰው ልጁን ወደ ትምህርት ቤት እየላከ ነው። ይህ የትምህርት ስርዓት ንባብ ላይ ምን ያህል ትኩረት አድርጓል? ብለን እንጠይቃለን። ተማሪዎች «አጥኑ» እንጂ «አንብቡ» ሲባሉ ብዙ ጊዜ አንሰማም። ምንአልባት የሁለቱ ቃላት ትርጓሜ ተቀራራቢ ሊሆን ይችላል፤ በየትኛውም ደረጃ የሚገኙ ተማሪዎች ግን በየእለት የተማሩትን ለፈተና እንዲሸመድዱ ሳይሆን አእምሯቸው እንቅስቃሴ እንዲያደርግ የሚያግዘውን ንባብን እንዲለማመዱ ማድረጉ ላይ ብዙ ይቀራል።
ጋዜጦች፣ መጽሔቶች፣ መጻሕፍትና የመሳሰሉ የህትመት ውጤቶች በገበያው ላይ ስርጭታቸው እጅግ አነስተኛ ነው። ይሁንና እጅግ ብዙ ተማሪዎች በርካታ በሆኑት የመንግሥትና የግል የትምህርት ተቋማት ሲመላለሱ ይታያል። ሁለቱን ስናነጻጽር ግን እጅግ ሰፊ ልዩነት አለ። ጥሩ የተባሉ መጻሕፍት የህትመት ቁጥራቸው አንድ የከፍተኛ ትምህርት ተቋም ተማሪዎችን ብዛት እንኳ አያክልም።
በ21ኛው መቶ ክፍለ ዘመንና ትምህርት በተስፋፋበት ጊዜ ንባብ ላይ ከቤተሰብ በተጓዳኝ ትምህርት ቤቶች ትልቅ ድርሻ ይኖራቸዋል ማለት ነው። ለምን ቢባል ከመጻሕፍትና ከንባብ ልሂቃን ይወለዳሉ። ወደ ጥናቱ መለስ ስንል፤ አጥኚው አያይዘው ምንም እንኳ ዘመናችን ከመጻሕፍት ሊያርቁን የሚችሉ አዳዲስና ሳቢ ቴክኖሎጂዎችን እያሳየን ቢሆንም፤ እነርሱንም በመጠቀም ከንባብ ላለመራቅ መጣር ያስፈልጋል። ይህም በአገራችንም ሆነ በሌላው ዓለም ካሉ ታላላቅ ሰዎች ተርታ ሊያሰልፈን የሚችል ነው ብለዋል። ሰላም!
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 13/2011
ሊድያ ተስፋዬ