የ12ኛ ክፍል ፈተና እና ቀጣይ እድሎቹ

የተማሪዎች በ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና ወቅት የእርስ በእርስ መኮራረጅ፤ ስርቆት፤ አስተዳደራዊና ብልሹ አሠራሮች እንዲሁም የፈተና አሰጣጥ ሂደት የትምህርቱን ዘርፍ ለዓመታት ሲፈትኑ የቆዩ ተግዳሮቶች መሆናቸው በተለያየ ጊዜ ይጠቀሳል። ይህም የተማሪ እና የወላጅ ሥነ ልቦናን እየጎዳ ዘመናትን ተሻግሯል። አልፎ ተርፎም ለትምህርት የሚመደበውን ሀብት ለድግግሞሽ ወጪ ሲዳርግ ቆይቷል። የሀገርን ሥራ ከእቅድ ውጭ አድርጎ ተጨማሪ ጊዜያትን በመውሰድ የጊዜ ብክነትን ፈጥሯልም።

ዛሬ ላይ ግን ነገሮች እየተቀየሩ የመጡ ይመስላል። ከትምህርት ጥራት ጋር ተያይዞ የዘርፉ ብሎም የ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና ትክክለኛ መመዘኛ የሚሆኑ ጉዳዮች ተግባራዊ በመደረግ ላይ በመሆናቸው ነገሮች እንደተቀየሩ ይነገራል። የለውጡ ዘመን የትምህርት አመራሮች ችግሩን በዋዛ ሳይመለከቱ ለመፍትሄው መፋጠናቸው ደግሞ መፍትሄው እንዲመጣ ማስቻሉም ይገለጻል።

ትምህርት ለማህበራዊ፤ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ብልጽግና ያለውን ቁልፍ ሚና በአግባቡ እንዲወጣ ጥራት ያለው መሆን የግድ ነው። በተለይ የ12ኛ ክፍል ሀገር አቀፍ ፈተና የምዘና ሥርዓት ተማሪዎችን ማዘመንም እንዲችሉ የሚያስችላቸው፤ ራሳቸውን መለወጥ የሚችሉበትና ለሀገራቸው አበርክቶ እንዲኖራቸው የሚያደርግ መሆን እንደሚገባው ማንም ይገነዘበዋል። ከዚህ አንጻርም በትምህርቱ ዘርፍ በተቀናጀ መልኩ በርካታ ሥራዎች ተከናውነዋል። ሥራው ሲጀመር ሁሉን አቀፍ ሪፎርሞች ቀዳሚ ተደርጎ ነው።

የትምህርት ሚኒስትሩ ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ እንደተናገሩት የ2017 ትምህርት ዘመን የ12ኛ ክፍል ሀገር አቀፍ ፈተና በተጠናቀቀበት ማግስት እንደተናገሩት፤ በትምህርት ዘርፉ ላይ ከፍተኛ ችግር የነበረው የ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና የአፈታተን ሥርዓት ነበር። በመሆኑም ችግሩን ከሥር መሠረቱ ለይቶ በማውጣትና የአፈታተን ሥርዓቱን በማሻሻል ሥራውን ላለፉት አራት ዓመታት ሲከናወን ቆይቷል።

ችግሩን ከስር መሠረቱ ለመፍታት የተመረጠው የመፍትሄ ሃሳብ የፈተና ሥርዓቱን ከኩረጃ እና ስርቆት ነፃ በሆነ ሁኔታ በበይነ መረብ እንዲፈተኑ ማድረግ ነው። ይህ ሁኔታ ደግሞ ሩቅ ሳይኬድ አምና ብቻ ብዙ ለውጦችን ያሳየ እንደነበር መመልከት ይቻላል። በወቅቱ ትምህርት ሚኒስቴር 29 ሺህ 727 ተማሪዎች ፈተናውን በበይነ መረብ እንዲወስዱት አድርጓል። ዘንድሮ ፈተናውን በበይነ መረብ የወሰዱት ተማሪዎች ቁጥር ከአራት እጥፍ በላይ በማሳደግ ወደ 134 ሺህ 25 እንዲያሻቅብ ማድረጉን አስረድተዋል። ይሄም ችግሩ በብርቱ እንዲቀረፍና ተማሪዎች ከኩረጃ እንዲጸዱ እያደረገ እንዲመጣ አብራርተዋል።

በዘንድሮው የ12ኛ ክፍል ሀገር አቀፍ ፈተና የመጣውን ውጤት በማሳያነት የጠቀሱት ሚኒስትሩ፤ ፈተናው በበይነ መረብ መሰጠቱ አጠቃላይም የፈተና አሰጣጥ ሥርዓተ ሂደቱን ለውጦታል። የፈተና ኩረጃን እና ስርቆሽን ብቻ ሳይሆን ሌሎች ተጨማሪ ችግሮችንም ፈትቷል። ለአብነት ኢንተርኔት በፈተና ማዕከላቱ ሆን ተብሎ ከማቋረጥ ጀምሮ ቁሳቁሶች ተደብቀው የሚገቡበት በር የዘጋ ነበር። ደብቀው ይዘውት የሚገቡትንም ማንኛውንም ነገር ያስቀረ ነው። ሂደቱ ካለፉት ዓመታት ጋር ሲነፃፀር ተማሪዎች ኢትዮጵያዊ ጨዋነት በተላበሰ እንዲሁም በራስ በመተማመን መንፈስ ፈተና መፈተንን ተሞክሮ ያዳበሩበት ከስርቆትና ኩረጃ የፀዳ ሰላማዊ የነበረ ስለመሆኑም አንስተዋል።

ትምህርት ሚኒስቴር ከፈተናው ጋር ተያይዞ ይገጥም የነበረውን ችግር በበይነ መረብ ፈተና አሰጣጥ አሠራሩ እየቀነሰ ይመጣል የሚል ተስፋ እንዲያደርግም ስለማስቻሉ ሳይገልፁ አላለፉም። በአጠቃላይ የፈተና ሂደቱ የታለመለትን ዓላማ ያሳካ ነበርና ተስፋችን ትከክል ነውም ብለዋል።

ፕሮፌሰር ብርሃኑ በመግለጫቸው እንደተናገሩት፤ የበይነ መረብ ፈተና አሰጣጥ ሥርዓት ሂደት ዘርፈ ብዙ ፋይዳዎች አሉት። በተለይ እንደ ትምህርት ሚኒስቴር ተማሪዎች ከቤታቸው ወጥተው ዩኒቨርሲቲዎች በመሄድ የሚፈተኑበትን ቀስ በቀስ እንዲቀንስ የሚደረግበትን ሁኔታ በብርቱ ያፋጥናል። ፈተናው በወረቀት ሲሰጥ በአንድ ተማሪ የሚወጣውን ወጪም በከፍተኛ ሁኔታ ይቀንሳል። ለምሳሌ እስከ ዛሬ በአንድ ተማሪ ለወረቀት የ3ሺህ 500 ብር ወጪ ይደረግ ነበር። በበይነ መረብ በመሰጠቱ ደግሞ ይህ ቁጥር ወደ 1 ሺህ 500 ብር ዝቅ ማድረግ ተችሎበታል። ከጥቂት ዓመታት በኋላ ፈተናውን ከእዛው ከሚማሩበት ትምህርት ቤት ሳይወጡ መደበኛ፤ ወጪና ጊዜ ቆጣቢ እንደሚያደርገውም ተስፋ ተጥሎበታል።

ትምህርት ሚኒስቴር ወደፊት ተማሪዎች በአንዴ የሚፈተኑበትን ሁኔታ በማስቀረት እና የፈተና ባንክ በማቋቋም ተማሪዎች በሚመቻቸው ጊዜ ፈተናውን የሚፈተኑበት ሁኔታ ላይ እደርሳለሁ ብሎ እንደሚያስብ የገለጹት ሚኒስትሩ፤ አሁን ላይ ትምህርት ሚኒስቴር ፈተናውን በበይነ መረብ የሚሰጥበት ሂደት ሩብ ወይም በቁጥር 23 ነጥብ 2 በመቶ ላይ የደረሰ ነው። ከእዚህ አንጻርም በቀጣይ ዓመት ፈተናውን በበይነ መረብ የመስጠት ሂደት ግማሽ የማድረስ እቅድ ተይዞ እየተሠራ ስለመሆኑም አውስተዋል። የፈተና አሰጣጥ ሂደቱ ፈተናውን በበይነ መረብ ቴክኖሎጂ የመስጠቱ ልምድ በእጅጉ እየዳበረ እንዲሄድ ስለመርዳቱም ገልፀዋል።

የትምህርት ምዘና እና ፈተናዎች አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር እሸቱ ከበደ (ዶ/ር) በበኩላቸው ትምህርት ሚኒስቴር ቅድሚያ ትኩረት ከሰጣቸው መስኮች አንዱ የትምህርት ምዘና እና ፈተናዎች አስተዳደር ሥርዓትን በዚህ መልኩ ማሻሻል ስለመሆኑ አመላክተው፣ ይህ የትኩረት ሥራም ፈተናው በሰላም እንዲጠናቀቅ እንዳስቻለ ያስረዳሉ።

እንደ ዋና ዳይሬክተሩ ማብራሪያ፣ ከ2014 ዓ.ም ጀምሮ ባለፉት ዓመታት የተወሰደው ይሄው ፈተናውን የበለጠ የማዘመን ሥራና በበይነ መረብ ፈተናን የመስጠት ርምጃ ዘንድሮ ትርጉም ባለው መልኩ ተከናውኗል። ተጨባጭ ለውጥም እያመጣ ይገኛል። ከእዚህ በኋላ በስርቆት እና ኩረጃ የሚገኝ ምንም ነገር እንደሌለ በሁሉም የትምህርት ማህበረሰብ ዘንድ መተማመን መፍጠርም ተችሏል።

ዋና ዳይሬክተሩ እንደተናገሩት፤ ዘንድሮ ከሰኔ 2017 ዓ.ም ጀምሮ እስከ ሀምሌ 8/2017 ሲሰጥ የቆየው የ 12ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና በተሳካ ሁኔታ መጠናቀቁም ማሳያ ይሆናል። የዘንድሮውን ፈተና ለመውሰድ 608 ሺህ 742 ተማሪዎች ተመዝግበው ነበር። ከእነዚህ ውስጥም 581 ሺህ 905ቱ በሁሉም ክልሎች እና ከተማ አስተዳደሮች በተቋቋሙ 216 የመፈተኛ ማዕከላት በመገኘት ፈተናውን መውሰድ ችለዋል። ፈተናው ከተሰጠባቸው ማዕከላት 139ኙ ከዩኒቨርሲቲ ውጭ በበይነመረብ ብቻ በተሳካ ሁኔታ ፈተና የተወሰዱባቸው ናቸው።

ፈተናውን ከወሰዱት ተማሪዎች ውስጥ 134ሺህ 828ቱ ፈተናውን በበይነ መረብ መውሰዳቸው የትምህርት ምዘናና ፈተናዎች አስተዳደር ሥርዓት በሪፎርሙ ምን ያህል እየተሻሻለ መምጣቱን በግልጽ ያሳያል የሚሉት ዋና ዳይሬክተሩ፣ ኩረጃ እና ስርቆትን በመቀነሱ ረገድ በበይነ መረብ የሚሰጥ የፈተና ሂደት ያለው አበርክቶ መጉላቱንም ያብራራሉ። ቀሪዎቹ 447 ሺህ 77 ተማሪዎች ፈተናውን በወረቀት ከመፈተናቸው አንፃር በዘርፉ ገና ብዙ ርቀት መጓዝ እንደሚጠበቅም ዋና ዳይሬክተሩ እሸቱ (ዶ/ር) አልሸሸጉም።

እሸቱ (ዶ/ር) በማብራሪያቸው እንደጠቀሱት፣ ባለፈው 2016 የትምህርት ዘመን በበይነ መረብ ይሄንኑ የ 12ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና ለመፈተን የተመዘገቡት ተማሪዎች ቁጥር 701 ሺህ 774 ነበር። ከእነዚህ ተፈታኞች መካከል ፈተናውን በበይነ መረብ የተፈተኑት ተማሪዎች ቁጥር 29ሺህ 727 ብቻ ናቸው። ዘንድሮ ይሄ የበይነ መረብ ተፈታኞች ቁጥር ከአራት እጥፍ በላይ በማሳደግ በበይነ መረብ የሚፈተኑ ተማሪዎችን ቁጥር ወደ134 ሺህ 828 ከፍ ማድረግ ችለናል። ይህ ቁጥር ማደጉ ደግሞ የፈተና አሰጣጥ ሂደት በቴክኖሎጂ መዘመኑ እያመጣ ያለውን ለውጥ በተጨባጭ ያሳየን ሆኗል።

በዘንድሮ 2017 የትምህርት ዘመን የ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና የፈተናውን የአሰጣጥ ሥርዓት በበይነ መረብ ቴክኖሎጂ የዘመነ ከማድረግ ጎን ለጎን ለዚሁ ስኬት ሲባል በርካታ የፈተና አስፈፃሚዎች እንዲሳተፉ የተደረገበትም ሂደት ነበር። በሂደቱ 27 ሺህ 106 የፈተና አስፈፃሚዎች መሳተፋቸው ፈተናው በስኬት ለመጠናቀቁ የነበረው ድርሻ በቀላሉ ሊታይ የሚችል እንዳልሆነም ተናግረው፤ ምንም እንኳን የበይነ መረብ ቴክኖሎጂው ለፈተና ኩረጃ እና ስርቆት በምንም መልኩ ዕድል የሚሰጥ ሆኖ ባይዘጋጅም ተማሪዎች ስርቆትና ኩረጃ ለመፈፀም የማያስችላቸውን ቁሳቁስ ደብቀው የሚገቡበትን ሁኔታ ስለሚኖር ይህንን በመከላከሉ ረገድ ከፍተሻ ሠራተኞች ጀምሮ ፈተና አስፈፃሚዎች በሂደቱ ቀላል የማይባል ሚና ተጫውተዋል ሲሉም በመግለጫቸው አስረድተዋል።

እሸቱ (ዶ/ር) እንደሚሉት፤ በ2017 ትምህርት ዘመን የ12ኛ ክፍል ተማሪዎች መልቀቂያ ፈተና ሂደት በተለያዩ የሀገሪቱ መፈተኛ ማዕከላት ያጋጠሙ ተግዳሮቶች ነበሩ። በተለይ ከፈተና ስርቆት እና ኩረጃ ጋር ተያይዞ በአንዳንድ ተማሪዎች ላይ የፈተና ሥነ-ምግባር መጓደል የታየበት ሁኔታ ነበር። ለምሳሌ፦ የተወሰኑ ተፈታኞች በተለያዩ ቁሳቁሶች ውስጥ በመደበቅ እና ልዩ ልዩ ዘዴዎችን በመጠቀም ተንቀሳቃሽ የእጅ ስልክ ወደመፈተኛ ክፍል ይዘው ለመግባት የሞከሩበት ሁኔታ ተስተውሏል። ሆኖም ለፈተናው ሂደት የተደረገው ጥብቅ ቁጥጥርና ክትትልን መሠረት ያደረገ የአካል ፍተሻ ያማከለ ጥንቃቄ ሙከራቸው ከሽፏል። ፈተናው ፍፁም ሰላማዊ ከኩረጃ እና ስርቆት ነፃ በሆነ መልኩ ተሰጥቶም ለመጠናቀቅ በቅቷል።

ዋና ዳይሬክተሩ እሸቱ (ዶ/ር) እንደተናገሩት፤ ሌላው በፈተናው ሂደት ወቅት ያጋጠመ ችግር ተፈታኝ ተማሪዎች ፈተናውን ለመውሰድ ሲንቀሳቀሱ ከነበረው ጋር በብርቱ ይሰናሰላል። ተፈታኝ ተማሪዎች ወደ መፈተኛ ማዕከላት በሚሄዱበት እና በሚመለሱበት ወቅት አምስት ቀላል የትራፊክ አደጋዎች አጋጥመዋል። ሆኖም ምንም የሞት አደጋ አላጋጠመም። ከባድ የተፈታኝ ተማሪዎች የአካል ጉዳትም እንዲሁ አልተፈጠረም። እነዚህ ቀላል የትራፊክ አደጋ የደረሰባቸው ተፈታኞች የመጀመሪያ ደረጃ የሕክምና ርዳታ ተደርጎላቸው ፈተናቸውን የወሰዱበት ሁኔታም አለ።

በተጨማሪም አምስት ተፈታኞች የመጀመሪያውን ዙር ፈተና ያልተፈተኑበት ችግር ገጥሞ ነበር። ይሄም ችግር ፈተናው ያመለጣቸው ተማሪዎች ፈተናውን በሁለተኛው ዙር እንዲወስዱ በማድረግ በፈተና ሂደቱ የጊዜ ሰሌዳም ሆነ በተማሪዎች የፈተና ጊዜ ላይ ምንም ዓይነት አሉታዊ ተጽዕኖ ሳያሳድር ማለፍ መቻሉን አብራርተዋል።

ከዚሁ በፈተና ወቅት ከአጋጠመ ችግር ጋር ተያይዞ ዋና ዳይሬክተሩ እንዳሉት በአማራ ክልልም የተከሰተ ችግር ነበር። በክልሉ ተፈታኝ ተማሪዎች ከሰቆጣ ወደ ወልዲያ ዩኒቨርሲቲ ሲጓጓዙ ሮቢት ላይ አደጋው እንዲደርስ ሆኗል። አደጋውን በተማሪዎች ላይ ያደረሱት ታጣቂ ኃይሎች ሲሆኑ ደፈጣ ይዘው ሁለት ጥይት በተኮሱበት ወቅት ነው። በዚህም ሁለት ሴት ተፈታኝ ተማሪዎች ላይ ቀላል የመቁሰል አደጋ ደርሷል። ሆኖም በሁለቱ ሴት ተማሪዎች ላይ የደረሰው ጉዳት ቀላል እና ፈተናውን ለመውሰድ የማይከለክል በመሆኑ ተፈታኝ ተማሪዎቹ በዩኒቨርሲቲው ሕክምና ማዕከል ሕክምና ከተደረገላቸው በኋላ ፈተናቸውን ተፈትነው ወደ መኖሪያቸው እንዲመለሱ መደረጉን አንስተዋል።

በአጠቃላይ በግል ችግር ምክንያት ካልሆነ በስተቀር የ2017 የትምህርት ዘመን የ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና በበይነ መረብ ቴክኖሎጂ ሲስተም መቆራረጥም ሆነ በማንኛውም ተግዳሮት ፈተናውን ሳይወስድ የቀረ አንድም ተማሪ የለም ብለው፤ በአማራ ክልል አንዳንድ አካባቢዎች ላይ ያሉና የተወሰኑ የሕግ ታራሚዎች በድምሩ 4ሺህ 966 የሚሆኑት በቀጣይ በሁለተኛ ዙር በተዘጋጀ ፈተና በወረቀት ፈተና ነሐሴ ከ 26 እስከ 28 ድረስ እንደሚወስዱም አስረድተዋል። መልካም ሳምንት!

ሰላማዊት ውቤ

አዲስ ዘመን ሰኞ ሐምሌ 14 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You