ምርምር የአንድ አገር መሰረታዊ ለውጥ ምሰሶ እንደሆነ ማንም ይረዳዋል፡፡ በዚህም በከፍተኛ ትምህርት፣ ምርምር ተቋማትና በሙያ ማህበራት እንደአገር የተለያዩ ምርምሮች ይሰራሉ፡፡ ሥራውም በተለያየ መልኩ ጥቅም ላይ እንዲውል ይደረጋል፡፡ ሆኖም እንደአገር ያለንበት ደረጃ ግን ከዓለም ብቻ ሳይሆን ከአፍሪካም ጭምር ዝቅተኛ ነው፡፡ በተለይም በዓለም አቀፍ ደረጃ የምርምር ጆርናሎች ጥራትና ቅቡልነት ብዙ መስራትን የሚጠይቀን ነው፡፡ ታዲያ ይህንን ክፍተት ለመሙላት ምን እየተከናወነ ነው፤ አሁን ያለው የምርምር ሥራ እንደአገር እንዴት ይታያልና መሰል ጉዳዮችን በማንሳት በትምህርት ሚኒስቴር የምርምር ጉዳዮችና ማህበረሰብ ጉድኝት ዋና ስራ አስፈጻሚ ዶክተር ሰለሞን ቢኖርን አናግረናል፡፡
አዲስ ዘመን፡- እንደ አገር አሁን ባለንበት ወቅት ዩኒቨርሲቲዎች የምርምር ተቋማት ጭምር ተብለው ተለይተዋል።በምን መስፈርት ነው፤ ለምንስ አስፈለገ?
ዶክተር ሰለሞን፡- በነበረን የ70 ዓመት ታሪክ ውስጥ አንዳንድ ዩኒቨርሲቲዎች ከልምዳቸውና ከቆይታቸው አንጻር ተለይተው የሚሰሩበት ሁኔታ ቢኖርም ሳይንሳዊ ዘዴን ተከትሎ ሁሉም ተለይተው እንዲሰሩ የተደረገበት ሁኔታ የለም።በነበራቸው የሥራ ሁኔታና አቅም ልክ በትኩረት መስክ የመለየት እድልም አልነበራቸውም።ሐሮማያን ብንወስድ የግብርና ኮሌጅ ሆኖ ዓመታትን መሻገሩ፤ ኮተቤን ብንወስድም እንዲሁ የመምህራን ትምህርት ኮሌጅ ሆኖ መቆየቱ ባይካድም ዩኒቨርሲቲዎች እስከ አራተኛው ትውልድ ድረስ በተስፋፉበት ልክ የትኩረት መስክ ተለይቶላቸው እንዲሰሩ አልተደረጉም።ከዚያ ይልቅ ሁሉንም የትምህርት መስክ አካተው እንዲያስተምሩ ነው የተደረጉት።ይህ ደግሞ የሀብት ብክነትን ያመጣል።ሌሎች ተጨማሪ ስራዎች እንዳይከናወኑም ያደርጋል።ስለዚህም ከሦስት ዓመት በፊት ይህ ታሳቢ አድርጎ ወደመሥራቱ ተገብቷል።ዩኒቨርሲቲዎች ዓለምአቀፍ መስፈርትን ተከትለውና አለማ ቀፋዊ ሳይንሳዊ ይዘት ኖሯቸው በትኩረት መስክ እንዲሰሩ ሆኗልም።
በተልዕኮና በትኩረት መስክ ተለይተው እንዲሰሩ ደግሞ የ 10 ዓመቱ ፍኖተ ካርታ ወሳኝ ነበር።አዲሱ የትምህርት ስርዓት ወደ ትግበራ መግባቱም እንዲሁ።በዚህም መስፈርት መሰረት የተለዩ ዩኒቨርሲቲዎች አምስት ሲሆኑ፤ ዓለምአቀፍ ተሞክሮን ያገናዘቡት በምርምር፣ በአፕላይድ፣ በአጠቃላይ (ኮምፕሬንሲቨ) የተከፈሉት እና መንግስት በራሱ በተጨማሪ ትኩረት ይደረግባቸዋል ብሎ የመረጣቸው ሁለት መስኮች ማለትም የሳይንስና ቴክኖሎጂ የትምህርት ዩኒቨርሲቲ የሚባሉት ናቸው።ወደፊት እየታየም የሚጨመርና የሚለዩ ዩኒቨርሲቲዎች ይኖራል።
እንዴት ተለዩ ሲባል የምርምሩን ብቻ እንኳን ብናነሳ አንድ የምርምር ዩኒቨርሲቲ የምርምር ዩኒቨርሲቲ ነው ለማለት ማሟላት ያለበት አነስተኛ መስፈርት አለ።ይህም የመምህራን ወይም የተመራማሪዎች ብዛት፣ የፕሮፌሰሮች ስብጥር ወይም የሰው ኃብት ቁጥሩ፣ ያለው የግብዓት አቅርቦት ሁኔታ፣ ጆርናሎችን የማሳተም ብቃትና መሰል ነገሮች ታይተው ነው።ነገር ግን እንደአገር እነዚህን አነስተኛ መስፈርቶች እንኳን ማሟላት የሚችሉ ዩኒቨርሲቲዎች አልነበሩም።ሆኖም የሉም ብሎ ሥራዎችን ከማቆም በመንግስት በኩል የቅርብ ክትትልና ድጋፍ ቢሰጣቸው ወደመስመሩ ሊገቡ ይችላሉ የተባሉትን መምረጥ ተችሏል።ዩኒቨርሲቲዎቹ ነባሮቹ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ፣ ሐዋሳ ፣ ጅማ ፣ መቐሌ ፣ ጎንደር ፣ ባህርዳር ፣ ሐሮማያና አርባምንጭ ዩኒቨርሲቲዎች ናቸው።
አዲስ ዘመን፡- እነዚህ የምርምር ተቋማት ተብለው የተለዩት ዩኒቨርሲቲዎች ምርምር ብቻ ነው የሚሰሩት ወይስ ዩኒቨርሲቲዎች ከዚህ ቀደም የተሰጣቸውን ሦስቱን ዋና ዋና ተልዕኮዎችንም ይፈጽማሉ ?
ዶክተር ሰለሞን፡- እርሱ ግድ ነው።ምክንያቱም አንድ ዩኒቨርሲቲ ምሉዕ እንዲሆን ዩኒቨርሳል የሆነ ሥራ መስራት አለበት። ለዚህ ደግሞ መማር ማስተማር፣ ምርምርና የማህበረሰብ አቀፍ አገልግሎት ማከናወን ወሳኝ ናቸው።ይህንን መስራት ካልተቻለ ምንም መተግበር አይቻልም።ስለሆነም የማይቀሩ ጉዳዮች ናቸው።ይሁን እንጂ ከእነዚህ ውስጥ ተለይቶ የተሰጠውን ሥራ ልዩ ትኩረት ሰጥቶ ማከናወን ይጠበቅበታል።ማለትም የምርምር ተቋማቱ ምርምር መለያቸው ነውና እርሱን ተኮር ሥራዎች በስፋት ያከናውናሉ። በድህረ ምረቃ ላይ ያተኮረ ምርምር በዋናነት ይሰራሉ ምርምር ደግሞ ሁለቱን ዋና ዋና ተልዕኮዎችን ካልያዘ ስኬታማ ሊሆን አይችልም። የምርምር ተቋማት የሚሰሩት ምርምር የአገሪቱን አጀንዳ የሚያስፈጽም ነው።የመንግስትን ፖሊሲ አቅጣጫዎችንና ምክረ ሀሳቦችን ያመጣል፤ ወደ መሬት እንዲወርድና በአግባቡ እንዲታይም ያደርጋል። ስለዚህም በእነዚህ ዩኒቨርሲቲዎች የምርምር ሥራዎች ልዩ ትኩረት ያገኛሉ ማለት እንጂ ዋና ተልኮውን አይተገብሩም ማለት እንዳልሆነ መወሰድ አለበት።
አዲስ ዘመን፡- በየዓመቱ እንደሀገር ምን ያህል ጆርናሎች ይታተማሉ፤ ችግር ፈቺነታቸውስ በምን ይለካል?
ዶክተር ሰለሞን፡- በዓመት ብቻ ሳይሆን በወራትም ጭምር የሚቋቋሙ አዳዲስ ጆርናሎች አሉ።ምክንያቱም አሁን በዚህ ጊዜ ስንነጋገር በምርምር ተቋማት፣ በዩኒቨርሲቲዎች አዳዲስ የሚቋቋሙ ይኖራሉ።ስለዚህም መናገር የሚቻለው እስካሁን ባለው መረጃ ነው።እናም እስካሁን በኢትዮጵያ ውስጥ ከ 185 እስከ 200 የሚደርሱ ጆርናሎች አሉ።እንዴት በቁጥር ተለይተው ታወቁ ከተባለ ደግሞ የምርምር ጆርናሎችን ማነው የሚያስተዳድረው፤ ማነው የሚያቋቁመው የሚለውን መመለስ ያስፈልጋል።ከዚህ አንጻርም ይህንን የሚያደርጉ ተቋማት በዋናነት ዩኒቨርሲቲዎች፣ የምርምር ተቋማትና የሙያ ማህበራት ናቸው። ስለዚህም እነርሱ በሚያመጧቸው መረጃዎች ይታወቃል።
አዲስ ዘመን፡- እንደ ማሳያ ችግር የፈታ የምር ምር ሥራ በየትኛው ተቋም ተሰራ፤ ያስገኘው ውጤትስ ምንድን ነበር ?
ዶክተር ሰለሞን፡- እዚህ ላይ ልብ ሊባሉ ከሚገባቸው ጉዳዮች መካከል አንዱ ምርምር ችግር ፈቺ ብቻ ነው ወይ የሚለው ነው።ምርምር አንድ ተመራማሪ ሳይንሱን አውቆ በምርምር የተለዩ ዘርፎችን ወዲያውኑ ማህበረሰብን የሚጠቀምበት ወይም ደግሞ ቆይቶ በሂደት ግኝት በማግኘት፤ ንድፈ ሀሳቦችን በማምጣት፤ ግምታዊ ትንታኔዎችን በመስጠት በሂደት ማህበረሰቡ እንዲጠቀምበት የሚያደርግ ነው።ስለዚህም ምርምር በይዘቱ መሰረታዊ አለያም ችግር ፈቺ (አፕላይድ)ና በእነዚህ በሁለቱ መካከል የሚሰራ ሊሆን ይችላል።እናም ምርምሮች በሙሉ ችግር ፈቺ ናቸው ተብሎ መወሰድ የለበትም።ሀሳብ አመላካች፣ መረጃ ሰጪ፤ እውቀት አሻጋጋሪና መሰል ጉዳዮችን በማመላከትም የሚተገበሩ ናቸው።
አዲስ ዘመን፡- ዩኒቨርሲቲዎች እንደ አገር፤ እንደ አፍሪካ በምርምር ሥራቸው የቱ ጋር ናቸው ብሎ ማስቀመጥ ይቻላል?
ዶክተር ሰለሞን፡- ኢትዮጵያውያን ከአፍሪካ በሕዝብ ብዛታችን ከናይጀሪያ ቀጥለን እንገኛለን።በዚህም ችግሮቻችን ብዙ ናቸው። እናም ምርምሮቻችን በሙሉ ችግር ፈቺ ብቻ እንዲሆኑ እንፈልጋለን።ምርምር ግን ከችግር ፈቺነቱ ባሻገር በሳይንስና በንድፈ ሀሳብ አዲስ እውቀት፣ አዲስ ፈጠራ፣ አዲስ እይታና አዲስ መረጃ ማምጣትና መስጠት ነበር አላማው።ይህ ግን እንደ አገራችን በስፋት ሲሰራበት አይታይም። በዚያው ልክ ኢትዮጵያ በምርምር ስራ የሚሳተፉ በርካታ ምሁራንና ተመራማሪዎች፤ ብዙ ዩኒቨርሲቲዎችና ከፍተኛ ተቋማት አሏት።በሀብት ደረጃም እንዲሁ በቂ ሀብት ይገኝባታል።ሆኖም ከአፍሪካውያን ጋር ስትነጻጸር እጅግ ዝቅተኛ የምርምር ሥራን ነው ለዓለም የምታበረክተው።
ደረጃችን የት ነው የሚለውን ስንመልሰው እንዳለን የከፍተኛ ተቋማት ብዛት፤ እንዳለን የምርምር ተቋም ብዛት መስራት ያለብንን ያህል አልሰራንም።ለምሳሌ 57 የሚሆኑ ዩኒቨርሲቲዎች አሉን።አምስቱ የግል ዩኒቨርሲቲዎች ሲሆኑ፤ ዩኒቨርሲቲ ኮሌጆች ናቸው።ከ250 በላይ ኮሌጆች አሉን።ዩኒቨርሲቲና ኮሌጅ ከተባለ ደግሞ ሦስቱን ተልዕኮዎች ይዞ ማስቀጠል ግድ ነው።በግል ተቋማት ላይ ግን ይህ ይደረጋል ወይ የሚለው መልሱ የሚታይ ነው። ትኩረታቸው ትምህርትና ማስተማር ላይ ብቻ እንደሆነ ይታወቃል።ከዲፕሎማ እስከ ሦስተኛ ድግሪ ድረስ ትምህርት እየሰጡ ቢቀጥሉም ምርምር ላይ ግን ሲሰሩ አይታይም።ይህና መሰል ችግሮች ከአፍሪካ ጋር ስንነጻጸር ብዙ ይቀረናል ። ለአብነት በምርምር ጆርናሎችን ብቻ ብናነሳ ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ ላይ እውቅና ያገኘችባቸው እስከ 2022 ድረስ ባለው መረጃ አራት ብቻ ናቸው።በህዝብ ብዛትም ሆነ በዩኒቨርሲቲዎች ብዛት የምታንሰን ደቡብ አፍሪካ ግን ከ125 በላይ በሆኑ ጆርናሎች አለማቀፋዊ እውቅናን አግኝታለች።የሳይንቲፊክ መስፈርቱን አሟልተውም አገርን በመወከል ሌሎች እንዲጠቀሙባቸው ሆነዋል።ለዚህ ያበቃቸው ደግሞ የምርምር አሰራር ምህዳራቸው ነው።ስለዚህም እንደአገር ዩኒቨርሲቲዎቻችን እውቅና ከማግኘቱ አንጻር ያሉበት ደረጃ እጅግ ዝቅተኛ ነው።ብዙ ክፍተቶች አሉባቸውም።
አዲስ ዘመን፡- ክፍተቶቻቸውን ለመሙላት ከማን ምን ይጠበቃል?
ዶክተር ሰለሞን፡- ሥራው ከግለሰብ ይጀምራል። ተመራማሪው በዓለም ጭምር በሥራው ታውቆ አገሩን ለማስጠራትና ሕዝቡን ለመጥቀም ብሎ መስራት ይኖርበታል። ከዚያ ደግሞ ተቋማት የድርሻቸውን መወጣት አለባቸው። ማለትም ዩኒቨርሲቲዎች፣ እነርሱን የሚያስተዳድረው ትምህርት ሚኒስቴር እንዲሁም መንግስት የየራሳቸውን ድርሻ ወስደው መስራት ይገባቸዋል። በተለይ እንደመንግስት ዩኒቨርሲቲዎችን በማስፋቱ ደረጃ ብዙ እንደሰራ ሁሉ የምርምር ጥራት ላይም ስርዓቶችን አስፍቶ መስራት ይኖርበታል። ስለዚህም ተመራማሪዎችን ሊያሰራ የሚችል የአሰራር ስርዓት መፍጠር እንደአገር እጅግ ያስፈልጋል።
ደቡብ አፍሪካ ከአፍሪካ በምርምር የላቀች የሆነችው በመንግስት ደረጃ ምርምር እንዴት መመራት አለበት ተብሎ ብሔራዊ ተቋም በማቋቋማቸው ነው።ተቋሙ የሚተዳደረው ከመንግስት በሚሰጠው በጀት ብቻ ሳይሆን ከምርምሮች በሚያገኘው ገንዘብ ነው።የዓለምን የምርምር የሳይንስ አካሄድ እያየ ከመንግስት በጀት በላይ እየተወዳደረ የራሱን ገቢ ያመነጫል።ሩቅ ሳንሄድ ዩጋንዳ የዚህ አይነት አሰራር አላት። በኢትዮጵያ ግን ይህ ሁኔታ አልተፈጠረም። የምርምር ተቋማትና ዩኒቨርሲቲዎችን የሚያስተባብር ብሔራዊ የምርምር ተቋም የለም። እስካሁን ባለው መረጃ ምርምሮች የሚመሩት በኮሚቴ ነው።ምርምር ደግሞ በኮሚቴ አይመራም።ምክንያቱም የምርምር ተቋማት በስብጥር ነው ያሉት።እነዚህን ለማሰባሰብ የግድ አገራዊ ተቋም ያስፈልጋል።
በሳይንስና ቴክኖሎጂ ኢኖቬሽን ፖሊሲ ምርምር ላይ ትኩረቱን የሚያደርግ ምክር ቤት አለ።ነገር ግን እርሱ ሁሉንም አሰባስቦ የሚሰራ አገራዊ ተቋም አይደለም።እናም ይህንን ተረድቶ ኢትዮጵያ ውስጥ ያለውን ውስን ሀብት ለምርምር በጀት ከማዋል ይልቅ ምርምሮች በራሳቸው የገቢ ምንጭ እንዲፈጥሩ ማድረግ የመንግስት ሥራ ሊሆን ይገባል።ይህ መሆኑ ያለውን ጠቀሜታ ለማሳየት አንድ ምሳሌ ብቻ ልጥቀስ።በአውሮፓ ህብረት ስር ያለው ሆራይዞን 100 ቢሊዬን ዶላር ለአፍሪካ አገራት ለምርምር ሥራ ይሰጣል።ሆኖም የእኛ ተደራሽነት በጣም አናሳ በመሆኑ አገራዊ ተቋምም ስለሌለን ተበታትኖ ይቀራል።ስለሆነም እንደነዚህ አይነት በጀቶችን መጠቀም ካስፈለገ ብሔራዊ የምርምር ተቋም እንዲኖር ማድረግ ያስፈልጋል።
አዲሱ የሳይንስና ቴክኖሎጂ ፖሊሲም ይህንን እንዲያይ በተደጋጋሚ ተነጋግረንበታል።ተቋሙ ደግሞ የሚመራውም በተመራማሪው እንጂ በፖለቲከኛ አይደለም።ከዚያ ባሻገር የአገር ውስጥ ጆርናሎችን ቁጥር ማብዛት ላይ ሳይሆን ጥራታቸው የተጠበቀ እንዲሆን ማስቻል ላይ መስራት ይገባል።ለዚህም የፍተሻና የእውቅና አሰጣጥ ስርዓት መዘርጋት ይገባልና ትምህርት ሚኒስቴር ከሦስት ዓመት በፊት ጀምሮታል። በዚህም በመጀመሪያው ዙር ጥሪ ተላልፎ ወደ 16 ጆርናሎች እውቅና እንዲያገኙ ሆነዋል። በሁለተኛው ዙርም እንዲሁ 23 ጆርናሎች እውቅና አግኝተዋል።በድምሩ 39 ጆርናሎች እውቅና ተሰጥቷቸዋል።እንደሚባለው ምንም አልተሰራም የሚያስብለን ላይ ግን አይደለንም። በምስራቅ አፍሪካ እንኳን ሲታይ የጆርናል ህትመታችን ደረጃ ጨምሯል። አሁንም ይህንን ሁኔታ ከፍ ለማድረግ በብሔራዊ ደረጃ ተሰርቷል የሚለውን ጆርናል ለማሳየት ከመጋቢት 28 እስከ 30 አገርአቀፍ የምርምር አውደጥናት በሳይንስ ሙዚዬም ይካሄዳል።አላማውም ኢትዮጵያ ውስጥ ምን ምርምር ተሰራ፤ እነማን ሰሩት፣ እንዴት እናሻሽለው፣ ክፍተቶቹ ምን ይመስላሉና መሰል ጉዳዮችን ማመላከት ነው።
አዲስ ዘመን፡- በየዓመቱ እውቅና ይሰጣል። እውቅናው ደግሞ ምርምር ተኮር ነው።ለመሆኑ ምን አይነት ውጤት ስለአመጡ ነው በዚህ ደረጃ እውቅና እንዲያገኙ የሆነው፤ መለያውስ ምን ነበር ?
ዶክተር ሰለሞን፡- መለያው የህግ ማዕቀፍ ነው። ጥራታቸው እንዴት ይፈተሻል የሚለውን በዓለምአቀፍ መስፈርት (ስታንዳርድ) መሰረት ታይቷል።አንድ ጆርናል ለመምረጥ ቢያንስ አነስተኛ መስፈርቱን ማሟላት ይኖርበታል። ለምሳሌ ኤዲቶሪያል ይዘቱ ምን ይመስላል፣ የምርምር ልምዱስ፣ የምርምር አርታኢው እንዲሁም በትንሹ ሦስት ዓመት አገልግሏል ወይ የሚሉት ይገመገማሉ።ውስጡ ያለው ቴክኒካል ይዘትም (ኮንቴንትም) ይመረመራል።ከዚያ እውቅናውን ይሰጠዋል። እስካሁንም ለ39 ጆርናሎች እውቅና ተሰጥቷል።ይህ ማለት ግን ምንም እንኳን አለማቀፋዊ የሳይንስ መስፈርትን ይዘን ብንለየውም በአገር ውስጥ ያለውን መስፈርት ያሟሉ መሆናቸውን ብቻ ነው እኛ ልናረጋግጥ የምንችለው። በአለማቀፋዊው ደረጃ ምን እንደሚባሉ አይታወቅም። ሳይንቲፊክ የሆነ ልዩነት የመፍጠሪያ ዘዴም ያለው በመሆኑ ከአፍሪካ እንኳን ተወዳድረው የተለዩ አይደሉም።ይህ እውቅና በአለማቀፉ ደረጃ ውስጥ ገብተው እንዲወዳደሩ እድል የሚሰጥ ብቻ ነው።
አዲስ ዘመን፡- ይህ የእውቅና መርሃግብር ምንን ታሳቢ አድርጎ የሚሰጥ ነው?
ዶክተር ሰለሞን፡- እውቅናው አንድ የአገር ገጽታ መገንቢያና ማሻሻያ ነው።ክፍተት መሙያና ከፍታን ማሳያም ነው። በሌላ በኩል እውቅና የምርምር ቱሩፋቶችን ማግኛና ዓለምአቀፍ ተወዳዳሪነትን መጨመሪያ ነው።አሁን የተለያዩ ጆርናሎችን በጥራታቸው እየጨመርን ሄድን ማለት አለምላይ እያስቀመጥን የምንመጣው ሥራ ይሰፋል ማለት ነው።ለምሳሌ በተባበሩት መንግስታት ድርጅት ዋይፖ( ወርክ ኢንተሌክችዋል ፕሮፐርቲ) የሚባል ኦርጋናይዜሽን ኢትዮጵያ በምርምርና ጥናት የት ላይ እንዳለች ሲያስቀምጥ ሁልጊዜ መጨረሻ ያደርጋታል።እናም ይህንን ለመቀየር እንደነዚህ አይነት እውቅናዎች ግድ አስፈላጊ ናቸው።በዓለም አቀፍ ደረጃ ጆርናሎችን የማወዳደርና የማለፍን እድልን ይጨምራልና። የተመራማሪዎችን ተነሳሽነትም ይጨምራል።የምርምር ባህላችንም ይዳብራል።ኢትዮጵያ በምርምር ላይ ያላት ተሞክሮም ይሰፋል።የመንግስት የፖሊሲ አቅጣጫንም መልካም ተጽዕኖዎችን በመፍጠር ሊያስቀይር ይችላል። ምርምርና ልማት ላይ ትኩረት መስጠት የአንድ አገር የሰለጠነ አካሄድን መምራት እንደሆነ ይታወቃልና አገር በዚህ እንድትመራ ያደርጋታል።
አዲስ ዘመን፡- ስለሰጡን ማብራሪ እናመሰግናለን
ዶክተር ሰለሞን፡- እኔም አመሰግናለሁ።
ጽጌረዳ ጫንያለው
አዲስ ዘመን ሰኞ የካቲት 20 ቀን 2015 ዓ.ም