አገራችን ኢትዮጵያ ለዘመናት ጦርነትን እንደ ትልቅ የሰላም ምንጭ ስትጠቀመው ቆይታለች። ያለፉትንም ሆነ የቅርብ ጊዜ የጦርነት ትዝታዎቻችንን መለስ ብለን ብንቃኝ አገር ከማውደም ባለፈ ያተረፉልን አንዳች ነገር እንደሌለ እንደርስበታለን። እያንዳንዱ አገራዊ ጉዳያችን ለጦርነት በር ከፋች ከመሆኑም በላይ የመፍትሄ ሀሳቦችን መለስ ብለን እንዳናይ ያደረገም ነበር። ከሁሉ በላይ በፖለቲካው ምህዳር የተለማመድናቸው አጉል ልምምዶች የሰላም አማራጮችን እንዳናይ ከማድረጋቸውም ባለፈ ለጦርነት መንገድ የሚጠርጉ እንደነበሩ ትላንትን ማስታወሱ በቂ ነው። የአሁኗን ኢትዮጵያ ጠፍጥፈው ያበጇት እነዚህ ለሰላም የሚሆን ልዕልና የሌላቸው አስተሳሰቦች ናቸው ።
ከትላንት እስከ ዛሬ እኔ ያልኩት ካልሆነ በሚል እሳቤ አሸናፊ በሌለው የብኩርና ግፊያ ለንክሻና ለመለያየት ተዳርገናል። ሀሳብን በሀሳብ ማሸነፍ ተስኖን፣ ልዩነትን በጋራ እውነት መርታት አቅቶን ቅራኔዎቻችንን ሁሉ ወደ ጦርነት ሲወስዱን ቆመን አይተናል። አሁን ጊዜው በሀሳብ ልዩነት ስንሞት ቆመን የምናይበት ሳይሆን ተቀምጠን የምንወያይበት ነው። በብሄራዊ ምክክር መሪነት ተቀምጠን የምንነ ጋገርባቸው አጀንዳዎቻችን ያንን አዳፋ ታሪካችንን ይቀይሩታል ብዬ በጽኑ አምናለው። ጦርነት የጠፈጠፋትን አገራችንንም እንደ አዲስ ለመፍጠር እድል እናገኛለን። በአለመግባባትና በተለያዩ ልዩነቶች አገራችን ውጥንቅጧ በወጣበት በዚህ ሰዐት ይሄ የምክክር መድረክ እንደ አገር እውቅና አግኝቶ መቋቋሙ አገራችንንን ወደ ፊት የሚያራምድ ድንቅ ተግባር ነው ብዬ ማወደስ እሻለው።
ከዚህ ሁሉ በላይ ደግሞ ችግሮቻችን በምክረ ሀሳብ መፍትሄ አግኝተው ሰላማዊት አገር ስንፈጥር እስከዛሬ ባለመነጋገራችን የከፈልነውን ዋጋ እያሰብን የምንቆጭበት ጊዜ ይመጣል ባይም ነኝ። ኢትዮጵያዊነት የአንድነት ድር ነው..ሸማኔውም እኔና እናንተ ነን። በአንድ አይነት እጅ፣ በአንድ አይነት እንዝርት ተሹረን ጋቢና ቡሉኮ የሆንን ህዝቦች ነን። በዚህ እንዳይለያይ ሆኖ በተሰናሰለ ማንነት ውስጥ የሌለን ልዩነት እየመዘዙ ማውጣት ለማንም የማይበጅ እኩይ ተግባር ነው። የሚያምርብን እንዴትና መቼ እንደሆነ እናውቀዋለን። የሚያምርብን አንድ ላይ ስንቆም ነው።
የሚያምርብን ኢትዮጵያዊነት ከሰማኒያ መልክና ቀለም ተፈልቅቆ ህያው የሆነ ማንነት እንደሆነ ሲገባን ነው። ያለፉ ታሪኮቻችንን መለስ ብለን ብናጤን ከተለያየንባቸው ይልቅ አንድ የምንሆንባቸው የበዙ እንደሆኑ እንደርስበታለን። ነገር ግን ከዛ ሁሉ እልፍ አንድነታችን ውስጥ ጥቂት ልዩነቶችን እየቆጠርን ለመለያየታችን የምንገፋፋ ነን። እንደ አገር ልዩነት ሊኖረን ይገባል..አይደለም ሰው ከሰው እግር ከእግርም ይጋጫል ትልቁ ጥበብ ግን ልዩነቶቻችን ወደጦርነት ከማምራታቸው በፊት በውይይት መፍታት ነው። ለውይይትና ለምክክር ክፍት ባልሆነ ፖለቲካ ውስጥ የምትፈጠር ውጤታማ አገር የለችም። ኢትዮጵያን የመሩና እየመሩ ያሉ ብዙዎቹ ፖለቲከኞች ኢትዮጵያ እንድታድግና እንድትለወጥ ጽኑ ፍላጎት ያላቸው ናቸው ነገር ግን ችግሮቻቸውን በውይይት ሲፈቱ አልታዩም። አብዛኛው ችግራችን ከፖለቲካው ተነስቶ ወደማህበረሰቡ የሚፈስ ነው።
ከማህበረሰቡ ተነስቶ ወደፖለቲከኞቻችን የደረሰ ችግር ኢትዮጵያ የላትም። ችግሮቻችን ሁሉ ከፖለቲከ ኞቻችንና ከፖለቲካው መንጭተው አገርና ህዝብ የሚጎዱ ናቸው። እንደ አገርም ሆነ እንደ ፖለቲከኛ ውይይትን የችግር መፍቻ ቁልፍ አድርገን ልንቀበል ይገባል። አንድ አይነት ከሆነ የፖለቲካ አስተሳሰብ ወጥተን ዘመኑን የዋጀ የንግግርና የምክክር ስርዐትን ማምጣት ይጠበቅብናል። በችግሮቻችን ላይ ሳንወያይና የጋራ ተግባቦት ሳይኖረን የምንመኘው ህልም ህልም እልም ከመሆን ባለፈ ፋይዳው አይታየኝም። ሰው የእድሉ ፈጣሪ ነው..ይሄን እውነት ወደአገርና ህዝብ ስናመጣው ህዝብ የአገሩ ፈጣሪ ነው የሚል ይሆናል። እንደ ኢትዮጵያ እድሎቿን በጦርነትና ባለመግባባት ያባከነች አገር አላውቅም። ..ወደጦርነት የወሰዱንን ችግሮቻችንን በሰላማዊ መንገድ ፈተናቸው ቢሆን ኖሮ ዛሬ ላይ በዚህ ልክ በድህነትና በኋላቀርነት ባልተሰቃየን ነበር እላለሁ።
ድህነትና ኋላቀርነት በተፈጥሮ የሚሰጡ አይደሉም የሰው ልጅ በራሱ መንገድ፣ በራሱ የአኗኗር ዘይቤ የሚስባቸው ናቸው። ከትላንት እስከዛሬ የተቆራኘናቸውን ድህነትና ነውሮቻችንን በራሳችን መንገድ የፈጠርናቸው እንደሆኑ እማኝ አያሻንም። ከነዚህ ነውሮቻችን ለመውጣት አዲስ አገራዊ አስተሳሰብን መጀመር አለብን..እሱም ከመነጋገርና ችግሮችን በውይይት ከመፍታት የሚጀምሩ መሆን አለበት። ሰው ሳይወያይና ሳይነጋገር አይደለም ከሌሎች ጋር ከራሱ ጋር እንኳን አብሮ መኖር አይቻለውም። እንደ አገር እድሎቻችንን የሰወርነው ራሳችን ነን። የምንናፍቃት ኢትዮጵያ እንድትፈጠር የመሳሪያ ድምጽ የማይሰማበት ፖለቲካ ያስፈልገናል። የምንፈልገው አገራዊ ልማትና ብልጽግና እንዲመጣ ውይይትን ያስቀደመ ችግር ፈቺ ምክረ ሀሳብ ያስፈልገናል።
ጀግንነት ያለው በፍቅር ውስጥ ነው። ጀብደኝነት ያለው በይቅርታ ውስጥ ነው። አገራችንን በፍቅርና በይቅርታ ጀግንነት ውስጥ ካልሆነ ካቀረቀረችበት ቀና ልናደርጋት አንችልም። እየሱስ ጠላቶቹን የረታው በፍቅር ነው። በሰማይም በምድርም ጦር ማዝነብ የሚችል ልዕለ ሀያል ጌትነት እያለው ግን በፍቅር ማሸነፍን መረጠ። አሁን የሚያስፈልገን የይቅርታ ልብ ነው። አሁን የሚያስፈልገን በምክክር የነበሩና ያሉ የሚኖሩም ችግሮቻችንን መፍታት ነው። ጀግና ማለት ስለሀገሩ እያሰበ ስለሀገሩ የኖረ ነው። የጎደለን ነገር ትንሽ ነው፤ ዋጋ እያስከፈለን ያለው ግን ብዙ ነው። ትንሽ ዞር ብለን ምን እንደጎደለን ማየት አለብን። የጎደለን ሰላም ብቻ ነው..የጎደለን ሰላምን በውይይት ማምጣት ነው። ለአገራችን ውለታ ለመዋል አንድ መንገድ ብቻ ነው ያለን እርሱን የሰላም መንገድ ነው።
አገራዊ የምክክር መድረኩ ለአገራችን ትልቅ ተስፋ ይዞ እንደመጣ አምናለው። በጦርነትና በመገፋፋት የዳበረ ጡንቻችንንም ያለዝብልናል ብዬ ተስፋ አደርጋለው። የእድሎቻችን መፈጠሪያ፣ የተስፋዎቻችን መነቃቂያ እንደሆነ አምነን መቀበል አለብን። እኛ ካልተሳተፍንበት፣ እኛ የመፍትሄው አካል ካልሆንን ግን ብቻውን ምንም ሊያመጣ አይችልም። መድረኩ በእኛ ለእኛ የቆመ ነው። ከእኛ ውጪ ምንም ኃይል የለውም። ለውይይት ቢቀርቡ የምንላቸውን፣ ትላንትም ይሁን ዛሬ የተፈጠሩ የመገፋፋት ቁርሾዎቻችንን በማንሳትና በመምከር በመወያየትም የጋራ እውነት ላይ የምንደርስበት መድረክ እንጂ ፊት አይቶና አእምሮ አንብቦ በመንካት መፍትሄ የሚሰጠን አይደለም። በነቃ ተሳትፎ ዘላቂ መፍትሄ የምናገኘው ነው። በብሄራዊ ምክክሩ ላይ የምንጠብቀው አካል፣ መፍትሄ እንዲሰጠን የምንተማመነው ኃይል የለም። እኛው ተነጋግረን እኛው የምንግባባበት የእኛው መድረክ ነው።
በሰከነ አእምሮ ማሰብ ከቻልን ብሄራዊ ምክክሩን የለውጥና የመነሳት ምዕራፍ አድርገን ልንወስደው እንችላለን። ችግሮቻችን በምክክር ተፈቱ ማለት አብረው መፍትሄ የሚያገኙ ብዙ ነገሮች አሉን። በአንዲት ትንሽ ችግር ውስጥ የገቡ ብዙ ችግሮች ያሉን ህዝቦች ነን። የዛ ቀዳዳ መደፈን የብዙ ችግሮችን ቀዳዳ ነው የሚደፍንልን። በምክክሩ ትውልድ እንቀርጽበታለን፣ ሰላም እናመ ጣበታለን፣ ያለፈ እኩይ ታሪካችንን እናድስበታለን። ወደ ፊት ለመሄድ በምናደርገው ጉዞ ላይ ኃይል ሆኖ የሚያራምደን፤ በዚም በዛም የተደቀኑብንን ችግሮች እያጠራን እንድንሄድ በብርቱ የሚያግዘን ይሆናል። ዓለም ላይ አንድ አይነት አስተሳሰብ ያላቸው ማህበረሰቦች የሉም። እንደ መልካችን አመለካከታችንም የዛኑ ያክል የተራራቀ ነው። ግን ደግሞ በልዩነት ውስጥ መግባባት ይቻላል። እኛ ያቃተን በልዩነት ውስጥ መግባባት ነው። ባለመስማማት ውስጥ ያለውን መስማማት እስካሁን አልደረስንበትም። ብዙ ነገሮቻችን ዋጋ ያጡት ለዚህ ነው።
በምክክር ያልተፈታ ችግር በጦርነት አይፈታም። ጦርነት መነሻና መድረሻው ውድመት ነው። ችግሮቻችን ወደ ጦርነት የሚወስዱን ለውይይት የሰፋ ልብና የዳበረ አእምሮ ስለሌለን ነው። የሰላም ምንጫችንን እያወቅን ሰላም ማምጣት አለመቻላችን ሁሌም የሚያሳዝን፤ የሚያስቆጭ ነው። ሰላም ውይይት ውስጥ እንዳለ እናውቃለን..ማወቅ ብቻ አይደለም እናምናለንም። ግን እምነትና ድርጊታችን ለየቅል ነው። ሰው አርነት የሚወጣው በእውቀት ነው። እውቀታችን ሰላምና ስለሰላም ካልሆነ ስለጦርነት እያሰብን መሽቶ በሚነጋ ፖለቲካችን ውስጥ አገር መፍጠር አንችልም። አገራችንን ከገጠሟት የሰላም ጠንቆች ለመታደግ የሰላም እውቀት ቀዳሚው መርሀችን መሆን አለበት በሰላም እውቀት ተነጋግረን መግባባታችን ለኢትዮጵያ የምንከፍለው የመጨረሻው ውለታችን ነው። ሰላም ወደ ፊት ለመሄድ ወደ ኋላ የምንደረደርበት መስፈንጠሪያችን ነው..ያልተስፈነጠርነው ሰላምን ሳንይዝ ስለተንደረደርን ነው።
ሰላምን መሰረት ያደረገ ሁሉን አቀፍ አገራዊ ተግባቦት ያስፈልገናል። የሰላም ዋጋው ምን ያክል እንደሆነ የገባንን ያክል ምንም ነገር ገብቶን እንደማያውቅ አምናለው። ባለፉት ዓመታት ውስጥ በሰላም እጦት የከፈልናቸው መስዋዕቶች ዛሬም ድረስ እንደሚያሙን ይሄንንም እናውቃለን። ትልቁ ጥያቄ የሚሆነው ትላንታችን እንዳይደገም ዘሬ ላይ ምን እናድርግ የሚለው ነው። ትላንታችን እንዳይደገም ትላንት ላይ የሌሉ የውይይት መድረኮች ያስፈልጉናል። ትላንታችን እንዳይደገም ልዩነቶችን በእርቅና በምክክር መፍታትን መልመድ ይኖርብናል። እኚህና የመሳሰሉ ገፊ ታሪኮቻችን ናቸው ዛሬ ላይ ይሄን አገራዊ ምክክር እንድናቋቁም እድል የሰጡን። በሰላማዊ መንገድ ሰላማዊ አገር መፍጠር እንደሚቻል ዛሬ ስለገባን በግሌ አዝናለው። ትልቋ አገር..በውብ ቀለም ዓለምን የቀለመች ጦቢያ ዛሬ ላይ የሠላም ሀሳብ አጥታ ሰላም ርቋት ሳይ ይከፋኛል። ከዓለም በፊት በቅላ ከዓለም ኋላ መጽደቋ እንደ ዜጋ ይቆረቁረኛል። ቀላል ነገሮች ናቸው ከባድ ዋጋ እያስከፈሉን ያሉት።
የምኞታችንን ያክል ለአገራችን አንዳች አላደረግንም። ምኞት በተግባር የሚጸድቅ እንጂ በወሬ የሚለማ አይደለም። ጎራዴአችንን ለስየፋ እየሳልን፣ መትረየሳችንን ለመግደል እያነጣጠርን የምንመኘው ሰላም ከኪሳራ ባለፈ ትርፍ አያመጣልንም። ጦራችንን ለበቀል፣ ቀስታችንን ለሞት እያነሳን የምንፈልገው ስልጣኔ ከወሬ ባለፈ መሬት ጠብ አይልም። ትርፋችንን በምኞታችን መጠንና ብዛት ሳይሆን ለውይይት በከፈትነው ልባችን ልክ ማስላት አለብን። አዲስ ማንነት የአዲስ ህይወት መጀመሪያ ነው። አዲሷን አገራችንን በአዲስ ፖለቲካና በአዲስ ህዝባዊ እርቅ ብንፈልጋት አዋጪ መንገድ ነው። ለዚህ ደግሞ ብሄራዊ ምክክር ኮሚሽን በሚያነሳቸው የህዝብ አጀንዳዎች ላይ አስተያየት በመስጠትና የመፍትሄ አካል በመሆን አንድ ርምጃ መራመድ እንችላለን።
አንድ ቀን ትውልዱ ይጠይቀናል..ዛሬም ድረስ በአባቶቻችን ኢትዮጵያ ስር ነን። የእኛን ኢትዮጵያ መፍጠር አልቻልንም። አንድነትና ወንድማማችነት ያቆማትን የአባቶቻችንን ኢትዮጵያ ሸርፈንና ገምሰን ለማንም እንዳትሆን የፖለቲካና የዘረኝነት ካባ እየደረብንባት ነው። ይሄ ደግሞ ሁላችንንም ከመጉዳት ባለፈ ነጥሎ የሚጎዳው የማህበረሰብ ክፍል የለም። እመኑኝ አንድ ቀን ትውልዱ ይጠይቀናል..ሁላችንም ተጠያቂዎች ነን። ለዚህ ትውልድ መልስ ለማዘጋጀት ያልተከፋፈለችና ጦርነትን የሰላም ማምጫ ያላረገች አገር ታስፈልገናለች። ከአባቶቻችን እንደተረከብነው ሁሉ ለልጆቻችን የምናስረክባት በአንድነቷና በነጻነቷ የቆነጀች አገር መስራት ይጠበቅብናል። በታደሰ ፖለቲካና ለእርቅ በቆመ ማህበረሰብ ታጅበን ወደፊት መሄድ ካልቻለ ከነበርንበት የሚያንቀሳቅሰን ምንም ኃይል አይኖርም። በመሸነፍ ውስጥ ማሸነፍን አይነት፣ በመተው ውስጥ ማትረፍን አይነት፣ በይቅርታ ውስጥ መራመድን የመሰለ አዲስ ማንነት ያስፈልገናል። መሄድ ከሚገባን ርቀን ለመሄድ እነዚህ የዘመናዊነት ርሾ በፖለቲካችን ላይ ሊነሰነሱ ግድ ነው።
በትረ ሙሴ (መልከ ኢትዮጵ)
አዲስ ዘመን ሰኞ የካቲት 20 ቀን 2015 ዓ.ም