የአገራት እድገት ዘላቂነትና አስተማማኝነት የሚረጋጋጠው ባላቸው እምቅ የተፈጥሮ ሀብት አልያም ባከማቹት የጦር መሳሪያ ልክ ሳይሆን ባላቸው የማህበረሰብ ንቃተ ህሊና ደረጃ ነው። ለግለሰብም ሆነ ለማህበረሰብ ንቃተ ህሊና መበልጸግ ደግሞ ትምህርት ዋነኛ መሳሪያ ነው። ትምህርት ከግለሰብ አስከ ማህበረሰብ ብሎም በአገረ አቀፍ ደረጃ ለሚመዘገቡ የኢኮኖሚ እድገት ሰላምና ብልጽግና ዋነኛ መንገድ ነው። በቅርቡ የዓለም ታሪክ የምናስታውሳቸው ከነዳጅ እስከ የከበሩ መአድናት በጉያቸው ታቅፈው በምድራቸው ከድህነት ወለል በታች የሚኖሩ ዜጎችን የያዙና በውስጥ ችግሮቻቸው እየታመሱ ያፈሩትን ጥሪታቸው በጦርነት ያወደሙ አገራት ለዚህ ሁነኛ ማሳያ ናቸው።
ትውልድ የሚቀረጸው በትምህርት እንደመሆኑ በትውልድ ላይ የማይሰራ አገርም ካለመበት የመድረሱ ጉዳይ አጠራጣሪ ብቻ ሳይሆን የማይታሰብም ነው። ይህን እንደመንደርደሪያ ያስቀመጥኩት በቅርቡ የተማሪዎችን ውጤት አስመልክቶ ስለተለቀቁት ዜናዎችና ስለተባሉት ሁሉ አንዳንድ ነገር ለማለት ስለወደድኩ ነው። በቅድሚያ 2014 ዓ.ም የ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና ከፍተኛ ውጤት (666) በማስመዝገብ ካመጣው የደሴ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪ አድናቆቴን እየገለፅኩ ወደ ዩኒቨርሲቲ ለሚገቡት ዕድሉ የገጠማችሁን ሁሉ እንኳን ደስ ያላችሁ ለማለት እወዳለሁ። ተፈትናችሁ ለጊዜው ወጤት ያላመጣችሁ ነገ ሌላ ቀን መሆኑን ተረድታችሁ በአዲስ ሞራል፣ የስነ ልቦና ዝግጅት አይቻልም የሚለውን ተስፋ አስቆራጭ ሃሳብ ከአእምሯችሁ ገለል ማድረግ ይጠበቅባችኋል። ለቀጣይም ከአለፈው ስህተቶቻችሁ በመማርና በርትቶ በመስራት የከፍተኛ ትምህርት ተቋማትን የማትቀላቀሉበት አንዳችም ምክንያት አይኖርምና በርቱ ለማለት እወዳለሁ፡፡
ወደዋናው ጉዳዬ ስገባ ግን የትምህርት ጥራት መጓደልም ሆነ የተማሪዎች ፈተና መውደቅ የልጆቹ ጉዳይ ብቻ ሳይሆን አገራዊ ችግር እንደመሆኑ ሁሉም በየደረጃው ኃላፊነቱን መውሰድ ብሎም ለማስተካከል የሚጠበቅበትን መወጣት እንዳለበት ይሰማኛል። በመሆኑም በአገራችን በሚገኙ ትምህርት ቤቶች ለተማሪዎች ውጤት ማሽቆልቆልና የትምህርት ጥራት አለመምጣት ዋነኛ ተጠያቂ ናቸው የምላቸውን ከሚጠበቅባቸው ተግባር ጋር እንደሚከተለው ለማቅረብ እወዳለሁ። በመንግስት በኩል ያለውን የትምህርት ጥራት ችግሮች በማጥናት ሰፊ ክትትል በማድረግ መፍትሔ መስጠትና በየአካባቢው ያሉ የሰላም ችግሮችን በወቅቱ መፍታት። ትምህርት ሚኒስቴር የትምህርት ፖሊሲና እና ስርዓተ ትምህርቱን የአገሪቱን ተጨባጭ ሁኔታዎችን ያገናዘቡና ችግር ፈች ብሎም ስራ ፈጣሪ ትውልድ የሚያፈሩ እንዲሆኑ ማስቻል። የትምህርት ባለድርሻ አካላት የሚባሉትም ሁሉም በአንድነት በመቆም አገራዊ እሳቤን በመያዝ ለአጠቃለይ የመማር ማስተማሩ ሂደት እኩል በመነሳት በህብረት መስራት።
የትምህርት ቤት ኃላፊዎች ዘወትር ራሳቸውን እያበቁና ከግዜ ጋር እየተራመዱ ተቋሞቻቸውን በብቃት ማስተዳደር። በትክክለኛው፣ ሰዓት፣ ጊዜ፣ ቦታ በመገኘትና ከሙስና በቡድን ከማሰብ፣ ከጎጠኝነት፣ ከብሄርተኝነት፣ ከመንደርተኝነት፣ ፅንፍ መውጣት ይጠበቅባቸዋል። እያንዳንዱ መመህር በቅድሚያ ለሙያው ፍቅር ኖሮት ራሱን በስነ ምግባር በማነፅና በየጊዜው በማብቃት ቴክኖሎጂ በመጠቀም ለፈጠራ ምርምር በመዘጋጀት ትውልድ አሻጋሪ ዜጋ በእውቀት ለመፍጠር መነሳት፡፡ የፈተና በሚወጣበት ወቅትም ሆነ የፈተና አሰጣጣ ተማሪውን በዕውቀት መገንባት የሚያችል ደንብና የፈተና ህጉን የተከተለ ማድረግ፡፡ የመምህራን ማህበራት አሁን ለተፈጠሩት ዘመን ተሻጋሪ ችግሮች መፍትሄና ምላሽ ከመስጠት አኳያ እየሰሩት ስራ የሚበረታታ ነው። ይህ እንደተጠበቀ ሆኖ የተወከሉበትን ኃላፊነትና ተግባር ቅድሚያ በመስጠት በመምህሩ የሚቀርቡ አያሌ ችግሮች በየደረጃቸው መፍትሄ እንዲያገኙ መስራት ይጠበቅባቸዋል፡፡
ተማሪው ከሁሉም በላይ በትምህርት ቤት ውስጥ ትልቁ የተማሪ ድርሻ መማር መሆኑን ተገንዝቦ ለትምህርቱ ሰፊ ዝግጅትና ጥናት በማድረግ ሌት ከቀን ቤተሰብና ማህበረሰቡ በሚጠበቅበት ስነምግባር በመታነፅ ኩረጃን በመጥላት በአላማ እና ዕቅድ በመስራት ለሚጠበቅበት ራሱን አሳልፎ መስጠት ይገባዋል ፡፡ ማህበረሰቡ ትምህርት ቤቶችንና ተማሪዎችን የራሱ ሀብቶች መሆናቸውን በመገንዘብ እና በመረዳት ከመንግስት፤ ከሚመለከታቸው ተቋማት ጋር በህብረት በመስራት የትምህርት ቤቶችን አቅም ማጎልበትና ለመማር ማስተማሩ ሂደት ምቹ ሁኔታ በመፍጠር የትምህርትን ጥራት ለማስጠበቅ ለሚደረገው ርብርብ የድርሻውን መወጣት ይኖርበታል።
ከሁሉምና ከምንም በላይ እያንዳንዱ ቤተሰብ ልጁን ወደትምህርት ገበታ ለምን እንደሚልክ ማወቅ፤ አውቆም መከታተል ይጠበቅበታል። በየእለቱ የልጆቹን ውሎ ከመከታተል ባለፈም ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በቅርበት መወያያትና ክትትል ማድረግ አለበት። ባጠቃላይም በአገራዊ ዕሳቤዎች ኢትዮጵያውያን ዲያስቦራዎች፣ አክትቪስቶች፣ በጎ አድራጊ ተቋማት የሚታየውን የትምህርት ጥራት ችግር፤ እንዲሁም ከዚሁ ጋር ተያይዘው የሚፈጠሩትን ችግሮች ቀድሞ በመረዳት አገራዊ ኃላፊነትን በመውሰድ የግል የጋራ ድርሻቸውን ሊወጡ ይገባል። በመጨረሻም ትምህርትን በብቃትና በጥራት ለሁሉም የምናደርገው ስራ ሀሳብ ከወረቀት በዘለለ ወደ መሬት ለማውረድ ተግባራዊ ለማድረግ ሁላችንም እንነሳ እላለሁ።
መምህር አረሩ አዴሳ
ይህ አምድ በተለያዩ ፖለቲካዊ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ጉዳዮች ዙሪያ ዜጎች ነፃ ሀሳባቸውን የሚሰጡበት ነው። በዓምዱ ላይ የሚወጡ ጽሁፎች የዝግጅት ክፍሉን አቋም አያመለክቱም።
አዲስ ዘመን ሰኞ የካቲት 20 ቀን 2015 ዓ.ም