ለተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ ሥራዎች ከፍያለ ትኩረት ሰጥቶ መንቀሳቀስ ኢኮኖሚያቸውን በግብርና ላይ መሰረት ላደረጉ አገራት ትልቁ የቤት ስራ ነው። በተለይም እንደ ኢትዮጵያ ላሉ ነገዎቻቸውን ባላቸው የተፈጥሮ ሀብት ላይ ተስፋ አድርገው ለሚንቀሳቀሱ ሕዝቦች ጉዳዩ የህልውና ያህል አደጋ ሊሆን የሚችልበት አጋጣሚ ሰፊ ነው። እነዚህ ሕዝቦች በትንሹ የእለት ምግባቸውን አምርተው፤ ዛሬን ለመሻገር በተፈጥሮ ሀብታቸው /በአፈር፣በአየር እና በውሀው/ ላይ ያላቸው ቁርኝት የህልውናቸው ያህል ነው። ይህም ለተፈጥሮ ሀብታቸው ሊሰጡት የሚገባው ትኩረት የቱን ያህል ወሳኝ እንደሆነ አመላካች ነው። እንደ ሕዝብ ዛሬ ላይ በዘርፉ የሚፈጥሩት መዘናጋት ከነሱ አልፎ መጪዎቹን ትውልዶ ቻቸውን የከፋ አደጋ ላይ ሊጥል ይችላል፤ ጊዜው ካለፈ በኋላ ከችግሩ ለመውጣት የሚያደርጉት ጥረትም ያልተገቡ ዋጋዎችን ከመክፈል መታደግ የሚያስችል አቅም ሊኖረው አይችልም።
በእኛም አገር ቢሆን ከግንዛቤ እጥረት ምክንያት የቀደሙት ትውልዶች በተፈጥሮ ላይ ካደረሱት መጠነ ሰፊ ውድመት የተነሳ፤ አሁን ያለው ትውልድ ከፍ ያሉ ዋጋዎችን ለመክፈል ተገድዷል፤ እየተገደደም ነው። ለዚህም ከግማሽ ምእተ ዓመት በላይ በአገሪቱ በየአስር ዓመቱ እየተከሰቱ ያሉ፤ የድርቅ አደጋዎች እና እያስከተሉት ያለው ጥፋት የዚሁ እውነታ አንድ ተጨባጭ ማሳያ ናቸው። ዛሬም በአንዳንድ የአገሪቱ አካባቢዎች የሚሰማው የድርቅ እና የድርቅ አደጋ ወሬ የዚሁ እውነታ አንድ ተጨባጭ ማሳያ ነው።
ይህንን ተጨባጭ እውነታ በአግባቡ በመረዳት አገራችንም ላለፉት ሁለት አስርት ዓመታት በተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ ዙሪያ ሰፊና ቀጣይነት ያላቸው ስራዎች ሰርታለች፤ በዚህም ከፍተኛ መጠን ያለው የተፈጥሮ ሀብት እንዲያገግም በማድረግ በዓለም አቀፍ ደረጃ ሳይቀር ተጠቃሽ ልትሆን ችላለች። በተለይም በተፋሰስ ልማት ፕሮጀክቶች ስር አርሶ አደሮችን በስፋት በማሳተፍ ሰፊ መሬት እንዲያገግም አድርጋለች። በዚህም የአካባቢ አየር ንብረት ለውጥን ከመከላከል ባለፈ ለግብርና ስራዎች ምርታማነት የተሻለ አቅም መፍጠር ችላለች።
በአሁኑ ሰአት በተለያዩ አካባቢዎች የሚኖረው ሕዝባችን እያስገኘለት ካለው ጠቀሜታ አንጻር፣ በተፈጥሮ ሃብት ጥበቃ ስራዎች ላይ የመሳተፍ የደን ችግኞችን የማልማትና የመጠበቅ ባህሉን እያዳበረ መጥቷል።ከዚህ ጎን ለጎንም ለእንስሳት መኖና ለምግብ ፍጆታ የሚውሉ ችግኞችን በመትከል የተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ ስራው የበለጠ በህይወቱ ትርጉም እንዲኖረው እየሰራ ነው። ይህም የተጠቃሚነቱን ደረጃ እያሳደገው ይገኛል። ይህም ሆኖ ግን መረጃዎች እንደሚያመ ለክቱት፤ በአሁኑ ወቅት ሰባት ሚሊየን ሄክታር መሬት በአፈር አሲዳማነት የተጠቃ ነው፤ ከዚህ ውስጥ ሶስት ሚሊየን ሄክታር መሬቱ የአሲዳማነት ደረጃ ከፍተኛ ነው።
በተለይ ትርፍ አምራች ከሚባሉት ክልሎች በምዕራብ አማራ፣ በአብዛኛው ኦሮሚያ፣ ሲዳማ፣ ደቡብና ደቡብ ምዕራብ አካባቢዎች የአፈር ሆምጣጤነት በከፍተኛ ደረጃ እየተስፋፋ ይገኛል፡፡ ይህ ከደን መመናመን /ጭፍጨፋ/ ጋር በተያያዘ እየተከሰተ ያለ ችግር፤ ምርታማነት ላይ ከሚያሳድረው ተጽእኖ ባለፈ፤ በቀጣይ በምግብ እህል እርሳችንን ለመቻል ለምናደርገው ጥረት ስኬት ዋነኛ ተግዳሮት መሆኑ የማይቀር ነው።
ችግሩን ለመቅረፍ በዋነኛነት በአገር አቀፍ ደረጃ ተግባራዊ እየሆነ ያለውንና ዓለም አቀፍ ዕውቅና ያተረፈውን የአረንጓዴ አሻራ መስፋት ማስቀጠል ያስፈልጋል፤ ቀደም ብለው የተጀመሩ የተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ ስራዎችን አጠናክሮ መቀጠል ይገባል። በተለይ የተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ ስራዎችን በተሻለ መልኩ ውጤታማ እንዲሆኑ፤ ሥራውን አገራዊ ንቅናቄ አድርጎ ማስቀጠል ያስፈልጋል። ለዚህ ደግሞ የፖለቲካ አመራሩን ጨምሮ ሁሉም የሚመለከታቸው አካላት ቀጥተኛ ተሳትፎ ወሳኝ ነው!
አዲስ ዘመን ሰኞ የካቲት 20 ቀን 2015 ዓ.ም