ሰላም ልጆች እንዴት ናችሁ:: ሳምንቱ እንዴት አለፈ? ትምህርት እንዴት ነበር? እንደተለመደው ሳምንቱን በትምህርት እና በጥናት እንዳሳለፋችሁ እርግጠኛ ነኝ:: ምክንያቱም እናንተ ጊዜያችሁን በአግባቡ የምትጠቀሙና በትምህርታችሁ የማትደራደሩ መሆናችሁን ስለማምን ነው::
ሀገራችን በምን ውስጥ አልፋ ለዛሬ እንደደረሰች መረዳት ባህሏን ማወቅ ማክበርና ለሌሎች ማስተዋወቅ ሀገሩን ከሚወድ ልጅ የሚጠበቅ ትልቅ ቁም ነገር ነው:: በዛሬው ፅሁፌ ኢትዮጵያን በዓለም ዙሪያ ጎልታ እንድትታይና እንድትከበር ያደረጋትን እንዲሁም የአፍሪካም ኩራት የሆነውን የዓድዋ ድልን እንመለከታለን::
በ1882 ዓ.ም ጥቅምት ወር ንጉሠ ነገሥት ዘኢትዮጵያ ተብለው የነገሱት ዳግማዊ አፄ ምኒልክ በዓድዋ ጦርነት የኢትዮጵያን ስም በዓለም አስጠሩ። ምኒልክ ንግሥናቸውን እንዳገኙ የመጀመሪያው የውጭ ጉዳይ ውል ከኢጣልያ ጋር የተደረገው ነበር። ይህም የስምምነት ውል የውጫሌው ውል በመባል የሚታወቀውና ለዓድዋ ጦርነት መነሻ የሆኑ አንቀጾችን የያዘው ስምምነት ነው። የውጫሌ ውል አንቀጽ አሥራ ሰባት የጣሊያንኛው እና የአማርኛው የተለያየ ትርጉም ነበረው፤ የጣሊያንኛው “ኢትዮጵያ ከአውሮፓ መንግሥታት ጋር ማድረግ የምትፈልገውን ግንኙነት በኢጣሊያ መንግስት በኩል ማድረግ አለባት” ሲል፤ የአማርኛው ደግሞ “ኢትዮጵያ ከአውሮፓ መንግሥታት ጋር ማድረግ የምትፈልገውን ግንኙነት በኢጣሊያ መንግሥት በኩል ማድረግ ትችላለች “ይላል::
ልጆች ይህ የውጫሌ ስምምነት የአማርኛው ትርጉም የኢትዮጵያን ሉዓላዊነትና ልዕልና ሲያስከብር በተቃራኒው የጣሊያንኛው ትርጓሜ የኢትዮጵያን ሉዓላዊነትና ልዕልና መድፈር ብቻ ሳይሆን ብሔራዊ ክብሯንና ጥቅሟን ይነካል:: ዳግማዊ ምኒልክ አርቆ በማሰብ ኢትዮጵያ በኢጣሊያ መንግሥት ቁጥጥር ስር እንዳትገባ ጥረት በማድረግ ነፃነታቸውን ጠብቀው ከሌሎች ሀገራት ጋር ግንኙነትንና ምክር መቀበል ቀጠሉ። በዚህም የተነሳ ኢጣሊያንም ኢትዮጵያን ለመያዝ በኤርትራ በኩል ትግራይን መውረር ጀመረች። ምኒልክም ሕዝቡን ለጦርነት ክተት አሉ።
ልጆች አፄ ምኒልክ በወቅቱ ያስነገሩት አዋጅ ምን የሚል መሰላችሁ፤ “እግዚአብሔር በቸርነቱ እስካሁን ጠላት አጥፍቶ አገር አስፍቶ አኖረኝ፤ እኔም እስካሁን በእግዚአብሔር ቸርነት ገዛሁ:: ከእንግዲህ ብሞትም ሞት የሁሉም ነውና ስለእኔ ሞት አላዝንም:: ደግሞ እግዚአብሔር አሳፍሮኝ አያውቅም፤ ወደፊትም ያሳፍረኛል ብዬ አልጠራጠርም:: አሁንም አገር የሚያጠፋ፤ ሃይማኖትን የሚለውጥ፣ በፊት እግዚአብሔር የወሰነልንን ባህር አልፎ መጥቷል:: እኔም የአገሬን ከብት ማለቅ፤ የሰውን መድከም አይቼ እስካሁን ዝም ብለው ደግሞ እያለፈ እንደፍልፈል መሬት ይቆፍር ጀመር:: አሁን ግን በእግዚአብሔር ረዳትነት አገሬን አሳልፌ አልሰጠውም:: የአገሬ ሰው ከአሁን ቀደም የበደልሁህ አይመስለኝም:: አንተም እስካሁን አላስቀየምኸኝም:: ጉልበት ያለህ በጉልበትህ እርዳኝ። ጉልበት የሌለህ ለልጅህ፣ ለምሽትህ፣ ለሃይማኖትህ ስትል በሃዘንህ እርዳኝ:: ወስልተህ የቀረህ ግን ኋላ ትጣላኛለህ:: አልምርህም:: ማርያምን ለዚህ አማላጅ የለኝም። ዘመቻዬ በጥቅምት ነውና የሸዋ ሰው እስከ ጥቅምት እኹሌታ ወረይሉ ከተህ ላግኝህ።” የሚል አዋጅ ነበር:: በዚህ አዋጅ መሰረት ጀግናና ቆራጥ የነበሩት የጥንት አባቶቻችን ሁሉን ነገር ጥለው ቅድሚያ ሀገሬን ብለው ለዘመቻ ወጡ::
ጣሊያኖች በጄኔራል ባራቲዬሪ የሚመራውን 20 ሺህ ወታደሮቻቸውን ይዘው በ1888 ዓ.ም የካቲት 23 ቀን ዓድዋን ወጉ። ከ 80 ሺህ እስከ 120 ሺህ የሚገመተው የኢትዮጵያ ሠራዊትም በሚገባ ሲዋጋ የሀገሪቱ ተፈጥሯዊ አቀማመጥና ሀገሬን ብሎ በቁርጠኝነት ስሜት ቀፎው እንደተነካ ንብ የተነቃነቀው ኃይል የጠላትን ጦር አደናግጦ መግቢያ መውጫ በማሳጣት ቀኑን ሙሉ ጦርነቱ ከተካሄደ በኋላ በሚያስደንቅ አኳኋን ድሉ የኢትዮጵያ ሆነ። ልክ የዛሬ 127 ዓመት። ሃያ ዘጠኝ ሺህ ፈረሰኞችን ጨምሮ ከመቶ ሺህ እስከ መቶ ሃያ ሺህ የሚገመት አንድ ሺህ ኪሎ ሜትር በባዶ እግሩ የተጓዘ የኢትዮጵያ የገበሬ ሠራዊት በወታደራዊ አካዳሚ የሠለጠነውን የአውሮፓ ወራሪ ጦር የካቲት 23 ማለዳ አሥራ አንድ ሰዓት ግድም ገጥሞ ከረፋዱ አራት ሰዓት ላይ ማሸነፉን አረጋግጧል:: ቅኝ አገዛዝ እግሬ አውጪኝ ሲል ነፃነት በኢትዮጵያ ምድር ላይ ከፍ አለ። ለጥቁር ሕዝብ የነጻነት ተጋድሎ ጮራው ፈነጠቀ። ኢትዮጵያ በልጆቹዋ ደምና አጥንት ሉዓላዊነቷን አረጋገጠች። በቅኝ ግዛት ለተያዙ ሌሎች የአፍሪካ ሀገራትም ምሳሌ ሆና የተስፋ ብርሃንን አበራችላቸው::
ልጆች እቴጌ ጣይቱ በጡል ለዓድዋ ጦርነት መንስኤ የሆነውን የውጫሌ ውል አንቀጽ 17 ኢጣሊያኖች ትርጉሙን አዛብተው ኢትዮጵያን በመዳፋቸው ስር ለማስገባት የሸረቡትን ሴራ ቀድመው ማጋለጣቸው ይነገርላቸዋል፤ በተለያዩ የታሪክ መፃህፍት ላይ ሰፍሮ እናገኘዋለን:: እቴጌ ጣይቱ ከባለቤታቸው ከአፄ ምኒልክ፣ ከኢትዮጵያውያኑ የጦር አዝማችና ሠራዊታቸው ጋር በመሆን ከተፋፋመው የዓድዋው ጦር ግንባር ላይ በመገኘት ጦሩን ከማበረታታት በላይ የመቀሌን ምሽግ በውኃ የሰበሩ ጀግና ናቸው። የመቀሌው የጣሊያን ጦር ምሽግ ጠንካራነት ጣይቱን ለፈጣን መላ ጋበዘ። ለአጃቢ ወታደሮቻቸው የመስዋዕትነት ግብዣ አቀረቡ። እነዚያ ወታደሮች የመቀሌውን የጣሊያን ጦር የመጠጥ ምንጭ ያዙ። ጣሊያን የሆዱ ነገር አሸነፈውና የመቀሌው ምሽጉ ባስደናቂ ሁኔታ ተሰበረ። የጣይቱ ብልህነት ወራሪውን ጣሊያን ድል መታ::
እንግዲህ ልጆች ኢትዮጵያ ታላቅ ክብርና ያገኘችበትና ነፃነቷን አላስነካም ያለችበትና በየአመቱ የካቲት 23 ቀን የሚከበረው የዓድዋ ድል ታሪክ ይህንን ይመስላል:: ጦርነት ጥሩ ባይሆንም አባቶቻችን ሀገራችንን ከጠላት ለመጠበቅ የሕይወት መሰዋዕትነት ከፍለው ለዚህ አድርሰዋል:: እናንተ ደግሞ ጠንክራችሁ በመማር ሀገራችሁን ከኋለ መቅረት ጦርነት ነፃ ልታወጧት ይገባል እያልኩ በዚሁ አበቃሁ መልካም ሳምንት::
በለጥሻቸው ልዑልሰገድ
አዲስ ዘመን የካቲት 19 ቀን 2015 ዓ.ም