አንጋፋ ስፖርተኛ ናቸው። ለተሳተፉበት የስፖርት ዘርፍ በኢትዮጵያ እንዲሁም በዓለም ኦሊምፒክ ፈር ቀዳጅ ናቸው። ይሄ ግነት ሳይሆን ታሪክ ቁልጭ አድርጎ በገፆቹ የከተበው እውነት ነው። እኚህ ሰው ለአገር ባለውለታ ናቸው። ስፖርቱ አሁን ካለበት አንፃር ከተመለከትነው የእርሳቸው ሚና የእውነትም ገኖ ሊታየን ይችላል። ለመሆኑ እኚህ ስፖርተኛ ማን ናቸው? በኢትዮጵያ የመጀመሪያው ዓለም አቀፍ የብስክሌት ስፖርት ተወዳዳሪ፣ የኦሊምፒክ ተሳትፎ ፈር ቀዳጅ፣ አሰልጣኝ እንዲሁም የጠንካራ ስብእና ባለቤት ጋሽ ገረመው ደንቦባ።
በኢትዮጵያ የብስክሌት ስፖርት እንዲሁም የኦሊምፒክ ተሳትፎ ታሪክ ደማቅ አሻራቸውን ካሳረፉ ድንቅና ግንባር ቀደም ስፖርተኞች አንዱ የሆኑት ብስክሌተኛ ገረመው ደንቦባ በሕክምና ሲረዱ ቆይተው ከቀናት በፊት በ90 ዓመታቸው ከዚህ ዓለም በሞት ተለይተዋል፡፡ ስርአተ ቀብራቸውም ከትናንት በስቲያ በብርሃናተ ዓለም ጴጥሮስ ወጳውሎስ ቤተ-ክርስቲያን ተፈፅሟል፡፡
አዲስ ዘመን በአንድ ወቅት ከእኚህ ታላቅ የስፖርት ሰው ተነግሮ የማያልቅ ስፖርቱ ዓለም ትዝታ፤ የሕይወት ጉዟቸውን እንዴት እንዳሰመሩት እንዲሁም ለሚወዱት ስፖርት እድገት ያላቸውን ልምድ ለትውልድ እንዲያጋሩ ሰፋ ያለ ቃለ መጠይቅ አድርጎላቸው ነበር። በዚህ ቃለምልልስ ወቅት ጠንካራው ሰው ህመም አሸንፏቸው ከቤት ውለዋል። በህክምና ላይ እንደነበሩ ለመረዳትም አያዳግትም። በአፍንጫቸው ላይ ኦክስጂን ሰክተዋል። እግራቸው ላይ ያጋጠማቸው ጉዳት ብዙም አያራምዳቸውም። እንደዚያም ሆኖ ግን እኛን በእንግድነት መቀበል አላቃታቸውም። እንዳደጉበት ባህል ኖር አሉን። ለጥያቄያችንም ሳይሰስቱ ከታሪክ ባህራቸው እየጨለፉ አጫወቱን። ብዙ የመውጣት እና የመውረድ የሕይወት ሂደቶች ላይ ያወጉንን ጨምረን ረጅሙን የስፖርት ታሪካቸውን ከብዙ በጥቂቱ እንዳስሳለን።
ጋሽ ገረመው በእርሳቸው ዘመን ባላቸው ጥንካሬ ለአገር በብስክሌት ስፖርት ፈር ቀዳጅ ውጤቶችን አስመዝግበዋል። እነ አበበ ቢቂላን፣ ማሞ ወልዴ፣ ይድነቃቸው ተሰማ ለዚህች አገር ከሰሩት ውለታ በማይተናነስ በብስክሌት ስፖርት ላይ ተጠቃሽ ስራን የሰሩ ታላቅ ባለውለታ ናቸው። ለዚህ ደግሞ የታሪክ ዶሴዎችን በቀላሉ መግለጥ በቂ ነው።
ዘመነ ጣሊያን ወረራ እና የጋሽ ገረመው
የጋሽ ገረመው የትውልድ ከተማ አዲስ አበባ ነው። አንዋር መስጊድ ፊት ለፊት ሀብተ ጊዮርጊስ ድልድይ እየተባለ በሚጠራው ሰፈር ነው ተወልደው ያደጉት። ጣሊያን አይኑን በጨው አጥቦ ኢትዮጵያን በድጋሚ ለመውረር ሲገባ የያኔው እምቦቃቅላ ኋላም አንጋፋ ስፖርተኛ ጋሽ ገረመው ከተወለዱ የአንድ አመት እድሜ አስቆጥረው ነበር። በወቅቱ ለኢትዮጰያውያን መርገምትን ይዞ ከተፍ ያለው ፋሽስት ጣሊያን ግን ለርሳቸው የወደፊት ህልም ፈር የቀደደ አጋጣሚን ፈጥሮ ነበር። መቼም ሁሉም ነገር መጥፎ አይሆንም። ወራሪ ወታደሮቹ ወደ ኢትዮጵያ ሲገቡ የጣሊያን ስሪት የሆኑትን እነ ቢያንኪሊ፣ባርታሊ እንዲሁም ቦንሲት የሚል ስያሜ ያላቸው ብስክሌቶችን ይዘው ገብተው ነበር። ታዲያ እነዚህ ብስክሌቶች ፋሽስት በጀግኖች አርበኞች ድል ተደርገው ከኢትዮጰያ ጨርቃቸውን ጥለው ሲወጡ በምርኮነት አገር ውስጥ ቀርተው ነበር።
ፋሽስት በአምስት ዓመት የቆይታ ጊዜው ወታደሮቹ በአዲስ አበባ ብስክሌቶችን በጎዳናዎች ላይ በመንዳት፣ ሰዎችን በማለማመድ እና ውድድር በማካሄድ የኢትዮጵያውያንን ልብ ለመማረክ ጥረት ያደርግ ነበር። በወቅቱ በዓለም ላይ በተለይ በፈረንሳይ፣ ቤልጂየም እንዲሁም ሆላንድ የመሳሰሉ አገራት ብስክሌት ተወዳጅ እና ቀዳሚው ስፖርት ነበር። ለዚህ ስፖርት ኢትዮጰያውያኑ እንግዳ ቢሆኑም በቀላሉ እውቀቱን በመቅሰም ጥሩ ችሎታን አዳብረው ነበር። በጎዳናዎች ላይ አንደ ድንገት ከወራሪዎቹ ጣሊያኖች ጋር ሲገናኙ እንኳን በቀላሉ እያለፏቸው ይጓዙ ነበር። በዚህ ሁኔታ ላይ እንዳለ ፋሽስት ከአገሪቷ ሳይወድ በግዱ ተባረረ። የብስክሌት ስፖርት ግን በኢትዮጰያ ተወዳጅነቱ ቀጠለ። ድሮውንም ኢትዮጵያውያን ከፋሽስት እንጂ ከስፖርቱ ቂም አልነበራቸውም። የወደፊቱ ባለታሪክ ጋሽ ገረመውም ጣሊያን ሲወጣ ስድስት አመት ሞላቸው። እድሜያቸው ለአስኳላ ደርሶ ዘመናዊውን ትምህርት ተያይዘውት ነበር።
የጋሽ ገረመው የብስክሌት ወዳጅነት ጅማሮ
የጋሽ ገረመው ብስክሌትን የተዋወቁት ገና በጨቅላ እድሜያቸው ውድድሮችን በመመልከት ነው። በአምስት እና ስድስት አመታቸው እነ ካሳ ፈዲር፣ ኤርትራዊው ካሳ ርእሶም፣ ሙሉጌታ ካሳ፣ታዬ ክፍሌ የሚባሉ ብስክሌተኞች ከአንዋር መስጊድ ፊት ለፊት እነኡስማን ኪኪያ ሱቆች አካባቢ እነ እራስ ሃይሉን የመሳሰሉ ታላላቅ መሳፍንት እና መኳንንቶች በክብር ቦታቸው ላይ ተቀምጠው ውድድር ሲያደርጉ ሲመለከቱ ጋሽ ገረመውም በራፋቸው ላይ ሆነው በደረታቸው ተኝተው ይከታተሉ ነበር። ከስፖርቱ ጋር ወዳጅነት የጀመሩትም በዚያን ወቅት ነበር።
ጋሽ ገረመው በአንዋር መስጊድ ቢያጆ ተራ ብስክሌት እያከራዩ የሚያለማምዱ ልጆች ጋር በሰባት ዓመታቸው ግንኙነት ጀመሩ። አምስት እና አስር ሳንቲም ከቤተሰቦቻቸው እየወሰዱ በመክፈል ልምምዳቸውን አጧጧፉት። ቁመታቸው ገና ቢሆንም እግራቸውን በፔዳሉ መካከል እያሾለኩ ቆመው በመንዳት ተለማመዱ። በዘጠኝ ዓመታቸው ግን የብስክሌቱ ኮርቻ ላይ መቀመጥ ቻሉ። እድሜያቸው እየጨመረ ሲሄድ ግን ከብስክሌቱ ጋር ግንኙነታቸው እየጠነከረ መጣ። ጋሽ ገረመው ለቤተሰቦቻቸው አስራ አንደኛ ልጅ ናቸው። ሆኖም እናታቸው ወይዘሮ ቶላ ኢጀሬ ለእርሳቸው የተለየ ፍቅር ነበራቸው። በኮከበ ፅባሕ ትምህርት ቤት በእግራቸው እየተመላለሱ ይማሩ ስለነበርም ለልጃቸው ብስክሌት በ30 ብር ገዝተው ለመስጠት አላመነቱም ነበር። የግል ብስክሌት ገና በልጅነታቸው በእጃቸው በማስገባት ከቤት ወደ ትምህርት ቤት፣ ከትምህት ቤት ወደ ቤት ጓደኞቻቸውን እያፈናጠጡ ( ከኋላ እየጫኑ) ይመላለሱ ጀመር። ይሄ ደግሞ የብስከሌት የመንዳት ብቃታቸውን እና ጥንካሬያቸውን እየጨመረው መጣ።
ጊዜው 1943 ዓ.ም ነው። በአካባቢያቸው የታዳጊዎች እና ወጣቶች የብስክሌት ውድድሮች ይካሄዱ ነበር። ታዲያ የያኔው ታዳጊ ጋሽ ገረመው በዚህ ውድድር ላይ በመሳተፍ ድል ማድረግን አሀዱ አሉ። ለተራ የትራንስፖርት አገልግሎት በሚጠቀሙባት ብስክሌት ጓደኞቻቸውን ከኋላ አስከትለው ውድድሩን ሰባተኛ ደረጃ በመያዝ አጠናቀቁ።
70 የሚደርሱ ተወዳዳሪዎች ተሳታፊ ነበሩ። በጊዜው ለእርሳቸው ጥሩ ውጤት ቢሆንም እንዴት አንደኛ መውጣት አልችልም የሚል ቁጭት ውስጥ ግን ከቷቸው ነበር። ጓደኞቻቸውን እያፈናጠጡ የጀመሩት የብስክሌት ስፖርት በውድድሮችም እየተገነባ ከጊዜ ወደ ጊዜ የስፖርት ተክለ ሰውነታቸው እና ጡንቻቸው እየፈረጠመ መጣ። ከተራ ፍቅር ቅልጥ ወዳለው የብስክሌት ሱስ ውስጥ ተንደርድረው ገቡ።
ጋሽ ገረመው በታላቁ የኦሊምፒክ መድረክ
ታላቁ ብስክሌተኛ ጋሽ ገረመው በኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ታሪክ በመጀመሪያ ተሳትፎ በሆነው እኤአ 1956 የሜልቦርን ኦሊምፒክ ከመሳተፍቸው በፊት ብዙ ውጣ ውረዶችን አሳልፈዋል። ኦሊምፒኩን ወዳዘጋጀችው አውስትራሊያ ጋሽ ገረመውና የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ቡድን ያደረገው የጉዞ ውጣ ውረድ በራሱ አንድ መጻሐፍ ይወጣዋል።
ለንጉሰ ነገስት ቀዳማዊ ኃይለስላሴ በሜልቦርን በኦሊምፒክ ኢትዮጵያ ወደ ውድድር ከፍታ እንድትመጣ ጥያቄ ያቀረቡት ገረመው ደንቦባ ነበሩ። በወቅቱ ታታሪው ወጣት ወደ ቢሾፍቱ ለልምምድ የሚወጡበት እሁድ ቀን ነው። ኦሊምፒያን ገረመው ደንቦባ ሁሌም በዚህ ቀን 42 ኪሎ ሜትሮችን በቢያንኪ ብስክሌታቸውን ይጋልባሉ።
የወጣት ፍላጎታቸው እና አገርን የማስጠራት አላማቸው ገንፍሎ ወጥቶ “ለምን በዓለም አልሳተፍም” የሚል ጥያቄ በውስጣቸው ይመላለስ ነበር። ግን ይህን ብቻቸውን ማድረግ እንደማይችሉ ያውቁታል። ምክንያቱም ኢትዮጵያ በወቅቱ የዓለም ኦሊምፒክ ኮሚቴ የሚባል አልነበረችም። ወቅቱም ገና 1946 ዓ.ም ነው። የስፖርት ተቋማት አልተገነቡም። በመንግስት ተቋማት ላይ ተፅእኖ አልፈጠሩም። ስለዚህ ተናጥላዊ ጥያቄ እንጂ ከተቋም የሚመጣ የእንሳተፍ አላማ የለም።
ይህንን የእንሳተፍ ጥያቄ ኦሊምፒያን ገረመው ደንቦባ አነሱት። ንጉሰ ነገስቱን ቢሾፍቱ መስመር ላይ አገኟቸው።
“የእሳቸው መኪና እንደሆነ ገብቶኛል። የተረዳሁት እሱን ነው። ይህንን አጋጣሚ ደግሜ እንደማላገኘው አውቃለሁ። ስለዚህ መጠቀም አለብኝ። በቀኝ እጄ ብስክሌቱን ይዤ፣ ግራ እጄን ወደላይ ከፍ አድርጌ አወጣሁት። ንጉሱ ይህንን ያዩ ኖሯል። ትንሽ ጠበቁኝ እና መኪናቸውን አቁመው ምን እንደምፈልግ ለሾፌሩ ሙሴ ነሲብ ጠየቁት” በማለት ያንን ጊዜ ያስታውሱታል።
ከዚህ በኋላ ብዙም ሳይቆይ ከንጉሱ እንዲህ የሚል ጥሪ ደረሳቸው “የሚመጣው ሳምንት ገነተ ልዑል ቤተመንግስት እንድትገኝ”። ብስክሌተኛው ጊዜ አላባከኑም ለንጉሱ ጥሪ እጅ ነስተው ስራቸውን ቀጠሉ።
ታሪክ አዋቂው ገረመው ደንቦባ በቀጠሮው ቀን ተገኙ። ንጉሱ የየሳምንት ችሎት፣ ጥያቄዎች የሚመለሱበት አዳራሽ ውስጥ ሲገቡ ሁሉም የክብር ሰላምታ ሰጥቷቸው ካባቸውን ነስንሰው ተቀመጡ።
ያንን አጋጣሚም ሲያስታውሱ “የእኔ ጥያቄ ከትንሽ ቆይታ በኋላ አዳራሹ ውስጥ ተነበበ። ፍላጎቴ ኢትዮጵያ በዓለም (ኦሊምፒክ) እንድትሳተፍ ነው። ይህንን ተሳተፉ የሚለውን ምላሽ ነው የምጠብቀው። ተነቦ ካለቀ በኋላ ጥያቄውን ንጉሱ እንደተቀበሉት ተናገሩ። የተሰማኝ ደስታ በልጅነቴ ኤሌክትሪክ ሲይዘኝ የነዘረኝን አስታወሰኝ። እንደዛን ቀን ደስተኛ ሆኜ አላውቅም። በጉልበቴ ተንበርክኬ አመስግኘ ከአዳራሹ ወጣሁ” በማለት በአንድ ወቅት ተናግረዋል።
ከዚህ በኋላ ብስክሌተኛ ገረመው ኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ በተሳተፈችበት የሜልቦርን ኦሊምፒክ በብስክሌት ስፖርት ኢትዮጵያ ወክለው በመሳተፍ እና ሰንደቅ አላማዋን በመያዝ ቀዳሚው አትሌት ለመሆን አውስትራሊያ ሜልቦርን ተገኙ። በሜልቦርን ኦሊምፒክ ተሳትፏቸውም ኢትዮጵያ ከዓለም ዘጠነኛ ደረጃን ይዛ እንድታጠናቅቅ ታላቅ የጀግንነት ፍልሚያ አድርገዋል። ይህም ውጤታቸው በታሪክ በስፖርቱ ትልቅ ውጤት ሆኖ ይጠቀሳል።
ቀጣዩ የ1960 የሮም ኦሊምፒክም ታሪክ ነው። በዚህ ኦሊምፒክ ጠንካራው ኢትዮጵያዊ የብስክሌት ተወዳዳሪ ከውድድሩ አስቀድሞ ትልቅ የአሸናፊነት ግምት የተሰጣቸው ሰው ነበሩ። ለዚህ ደግሞ አቅሙም እድሉም ነበራቸው። ግን ቀዳሚ የማሸነፍ እድል የተሰጣቸው ኢትዮጵያዊ ውድድር ላይ እያሉ ያልተጠበቀ አደጋ አጋጠማቸው። ከ11 ዙር ውስጥ 9ኙን በአንደኝነት እየመሩ ያሸንፋሉ ተብሎ ሲጠበቅ በድንገት ከኋላ ተገጭተው በመውደቃቸው ውድድሩን አቋርጠው ለመውጣት ተገደዱ። ይህም በወቅቱ አንጋፋው ብስክሌተኛ ገረመው ተገቢ ያልሆነ ግጭት ባያስተናግዱ ማሸነፍ ይችሉ እንደነበር በዓለም ጋዜጦች ጭምር ተዘግቦላቸዋል። በዚህም ለ9 ዙር የሮሙን የብስክሌት ውድድር በመምራት ሰፊ ሙገሳ እና ክብርን በማግኘት ታሪክ ይዘክራቸዋል። በዚያ ኦሊምፒክ ጋሽ ገረመው በድንገተኛው አጋጣሚ ከውደድሩ በጉዳት ቢወጡም፤ አበበ ቢቂላ በባዶ እግሩ ሮምን ወሮ የጓደኛውን ሀዘን በደስታ አካካሰው።
ገረመው ደንቦባ በቀጣዩ 1964 የቶኪዮ ኦሊምፒክም በዋና አሰልጣኝነት የኢትዮጵያን የብስክሌት ቡድን መምራት የቻሉ ሲሆን፣ በተወዳዳሪነት ዘመናቸው በተለያዩ ዓለም አቀፍ መድረኮች ከ30 በላይ ዋንጫ እና 32 የወርቅ ሜዳሊያዎች ማስመዝገብ እንደቻሉ ከሕይወት ታሪካቸው ማህደሮች መረዳት ይቻላል።
ጋሽ ገረመው በኢትዮጵያ ብስክሌት ስፖርት ታሪክ ውስጥ የአንበሳውን ድርሻ ይወስዳሉ። በቶኪዮ ኦሎምፒክ ላይም የብስክሌቱን ልኡካን ቡድን በአሰልጣኝነት በመምራት አገልግለዋል። ከዚያም በኋላ ለረጅም ዓመታት በአሰልጣኝነት ለአገር ውለታ ሰርተዋል። በምላሹ ግን ለአገራቸው ክብር እግራቸው ተሰብሮ ብረት ሲያጠልቁ «አባ ከና» ያላቸው የለም።
ገረመው ደንቦባ በኢትዮጵያ ብስክሌት ስፖርት ታሪክ ውስጥ ትልቅ አሻራን ከማሳረፋቸው ባሻገር አቅማቸው ደክሞ እቤት መዋል እስከጀመሩበት ቅርብ ጊዜ ድረስ በተለያዩ መድረኮች እየተገኙ ልምዳቸውን በማካፈል ይታወቃሉ። ከእሳቸው በኋላ በኢትዮጵያ ብስክሌት ስፖርት ታሪክ ጎልተው መውጣት ለቻሉት እንደ ለተሰማ አሞሳ፣ አድማሱ መርጋ፣ አላዛር ክፍሎም፣ ጆቫኒ ማሶላ፣ ጀማል ሮጎራና ጽጋቡ ገብረማርያም ለመሳሰሉ ብስክሌተኞች አርአያ መሆን ችለዋል።
ዳግም ከበደ
አዲስ ዘመን የካቲት 19 ቀን 2015 ዓ.ም