መረጃና ከመረጃ ጋር የተያያዙ ጉዳዮች ለአንድ ማኅበረሰብ ያላቸው ጠቀሜታ የሕልውና ያህል ሊሆን እንደሚችል ይገመታል ፤ ከዚህ የተነሳም ባለንበት የመረጃ ዘመን ቀርቶ ቀደም ባሉት ዘመናት ዓለም ለመረጃ ከፍተኛ ትኩረት ሰጥታ ለመንቀሳቀስ የተገደደችበት እውነታዎች ከፍተኛ ነበሩ።
ለዚህም በተለያዩ የዓለም ክፍል ያሉ የማኅበረሰብ ክፍሎች ዘመናት ያስቆጠሩ የመረጃ ማስተላለፊያ ሥርዓት ባለቤት መሆናቸው፤ ዛሬም ቢሆን በእነዚህ የመረጃ ማስተላለፊያ ሥርዓታቸው በመታገዝ ሕይወታቸውን እየገፉ መገኘታቸው ለእውነታው ተጨባጭነት ማሳያ ተደርጎ ይወሰዳል።
ከሰው ልጆች የዕለት ተዕለት ሕይወት ጋር ተነጥሎ የማይታየው የመረጃ ጉዳይ ፤ ባለንበት ዘመን/ በመረጃ ዘመን/ለሰው ልጆች ነገዎች አልፋና ኦሜጋ መሆን ወደሚያስችለው ታሪካዊ ምዕራፍ ለመሸጋገር በመንደርደር ላይ እንዳለ በስፋት ይነገራል፤ በርግጥም እየሆነ ያለው ከዚህ የተለየ አይደለም።
በተለይም ዓለም ወደ አንድ መንደርነት እየተለወጠች ባለችበት አሁናዊ ዓለም አቀፋዊ ዐውድ፤የመረጃ ማሰራጫ ቴክኖሎጂዎች ላይ እየታየ ያለው ፈጣን እድገት፤ እድገቱ በሰዎች የአኗኗር ዘይቤ ላይ እያሳደረ ያለው ተጽዕኖ እውነታውን አምኖ ለመቀበል በራሱ በቂ ነው።
የመረጃ ማሰራጫ ቴክኖሎጂዎች በከፍተኛ ሁኔታ እየዘመኑ ባሉበት ፤ ከዚህ የተነሳም ግለሰቦችን በያዟቸው ተንቀሳቃሽ ስልኮች በቀላሉ ዓለም አቀፍ የመረጃ ማሰራጫ የቴክኖሎጂ ሥርዓት ውስጥ የመግባታቸው እውነታ ትክክለኛ ሚዛናዊ መረጃዎችን ለሕዝብ የማሰራጨቱን ሂደት ፈታኝ አድርጎታል።
ይህ ዓለም አቀፋዊ እውነታ ቀደም ባለው ጊዜ መረጃ ሰብስቦ በማሰራጨት ወቅት የነበረውን ሂደት ተዓማኒ ለማድረግ በሙያ ሥነ ምግባርና በሕግ አግባብ ለመግራት ይደረግ የነበረውን ጥረት ፈተና ውስጥ ጨምሮታል። በዚህም ዓለም ያልተገባ ዋጋ ለመክፈል እየተገደደች ነው።
ትክክለኛ ፣ግልጽ እና ሚዛናዊ መረጃ ለሕዝብ እንዲሰራጭ ፤መረጃ የማሰብሰብና በማሰራጨት ሥራ ባለቤት የሆነው የጋዜጠኝነት ሙያ ሳይቀር ለተቀመጡለት ሙያዊ ሥነ ምግባሮችና የሕግ አግባቦች ለመገዛት እየተቸገረ ለአደጋ ተጋላጭ እየሆነ ነው።
ችግሮቹ በተለይም እንደ ኢትዮጵያ ባሉ የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ጡቦች በአግባቡ ባልተሰደሩባቸው ሀገራት ፤ ሥርዓቱን ለመገንባት ለሚደረጉ ጥረቶች ተግዳሮት ሆነው መታየት ከጀመሩ ውለው አድረዋል። እያስከተሉት ያለውም አደጋ የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታውን ወደኋላ እስከ መጎተት የደረሰ ነው።
አንድም ሕዝቡ ይዞት ከመጣው የመረጃ አጥርቶ የማድመጥና የመውሰድ ክፍተት ጋር በተያዘ ፤በሚሰማው ሁሉ የመወሰድ አደጋ ውስጥ መውደቁ ፤ ከዚያም በላይ ሕዝቡን በተሳሳቱ መረጃዎች ግራ በማጋባት የለውጡ አቅም እንዳይሆን የሚደረጉ እኩይ ተግባሮች ሕዝቡ በቴክኖሎጂዎቹ በተገቢው መንገድ ተጠቃሚ እንዳይሆን እያደረጉት ነው።
የፖለቲካ ባሕላችን ሀሳብ ከመሞገት ይልቅ ስድድብና ብሽሽቅ ላይ የሚንጠላጠል ፤ለዚህም ማኅበራዊ ሚዲያውን ጨምሮ አዳዲስ ዘመናዊ የመረጃ ማሰራጫ ቴክኖሎጂዎችን ሳይቀር ኃላፊነት በጎደለው መንገድ የሚጠቀም፤ይህንንም አንድ የፖለቲካ ስትራቴጂ አድርጎ የሚወስድ መሆኑ የአደጋው አንዱ መገለጫ ሆኗል።
አንዳንድ የማኅበረሰብ አንቂ ነኝ የሚሉ አካላትም ቢሆን ራሱ በአግባቡ ሳይነቃ ሌሎችን ለማንቃት እየሄደበት ያለው መንገድ “በአይነስውር በቅሎ ቃጭል ተጨምሮ “ እንደሚባለው ሕዝባችን ትክክለኛ ፣ ግልጽ እና ሚዛናዊ መረጃ የማግኘት መብቱን ከማሳጣት ባለፈ በተሳሳተ መረጃ የእራሱን እና የሀገሩን ነገዎቹን ለአደጋ እንዲያጋልጥ እያስገደዱት ነው።
ይህንን ሃገራዊ ችግር ተሻግሮ ለማለፍ ከሁሉም በላይ ሕዝባችን መረጃዎችን ወስዶ የራሱ ከማድረጉ በፊት መረጃውን የማጥራት ባሕል ማዳበር እንዲሁም ትዕግስትና ስክነት መፍጠር ይጠበቅበታል። በተለይም ከፖለቲከኞች እና ከማኅበረሰብ አንቂዎች ከሚለቀቁ መረጃዎች ጀርባ ያሉ ድብቅ ዓላማዎችን በአግባቡ መገንዘብ የሚያስችል እርጋታ ሊኖር ያስፈልጋል ።
በተለያዩ የመንግሥት መዋቅር ውስጥ የሚገኙ የመንግሥት ኃላፊዎችም ፤ኅብረተሰቡን ውዥንብር ውስጥ የሚጥሉ መረጃዎች ሲለቀቁ ፤ ፈጥነው ትክክለኛ መረጃዎቹን በማውጣት ሕዝቡ በተሳሳቱ መረጃዎች ያልተጋባ ዋጋ እንዳይከፍል መታደግ ይጠበቅባቸዋል። በዚህም ሕዝቡ የለውጡ አቅም ሆኖ የሚዘልቅበትን የመረጃ ሥርጭት ሥርዓት መፍጠር ይቻላል!
አዲስ ዘመን የካቲት 19 ቀን 2015 ዓ.ም