መነሻዋ ጠንካራ ከሆኑ ነጋዴ ቤተሰቦች ነው። ወላጅ አባቷ የረጅም ጊዜ ቡና አቅራቢ እንዲሁም ቆዳ ነጋዴ ናቸው። ‹‹ባልና ሚስት ከአንድ ወንዝ ይቀዳል›› እንዲሉ ታዲያ ወላጅ እናቷም የባለቤታቸውን ፈለግ ተከትለው በንግዱ ዘርፍ ከላይ ታች ብለዋል። በቡና፣ በቆዳና በሌሎች የንግድ ዘርፎች በመሰማራት ረጅም ጊዜን ካስቆጠሩት ከነጋዴ ወላጆች የተገኙት ልጆችም አብዛኞቹ ነጋዴዎች አይደሉም። የቤቱ አምስተኛ ልጅ ግን የወላጆቿን ፈለግ ተከትላ ብርቱ ነጋዴ ሆናለች። ከዚህች ብርቱ ነጋዴ ጋር ቆይታ ያደረገው የዝግጅት ክፍላችንም ከሕይወት ልምዷ የተካፈለውን እንካችሁ ብሏል።
የንግድ ሥራ በቤት ውስጥ ሲሰራ እያየችና ወላጆቿን እያገዘች ያደገችው የዛሬ የስኬት እንግዳችን የኔወርቅ ቢወጣ ለዓለም ትባላለች። ተወልዳ ያደገችው በአዊ ዞን አዲስ ቅዳም ከተማ ነው። ቤተሰቦቿ በዋናነት በተሰማሩበት የቡና ሥራ ውስጥ ጉልህ አበርክቶ የነበራት በመሆኑ ዛሬ ብርቱ ነጋዴ መሆን ችላለች። እርግጥ ነው ማንኛውም ልጅ ወላጆቹን በቤት ውስጥ በሥራ እንደሚያግዝ ሁሉ እርሷን ጨምሮ እህት ወንድሞቿ ቤተሰቡን በሥራ አግዘዋል። ከእህት ወንድሞቿ በተለየ ግን የኔወርቅ ቢወጣ ለዓለም እገዛዋ ከውስጥ በመነጨ ፍላጎት ጭምር ነበር።
የልጅነት ግዴታዋን ከፍላጎት ጋር በማዋደድ የንግድ ሥራን በቤት ውስጥ ሆና ከወላጆቿ ተምራለች። ከትምህርቷ የሚተርፋትን ጊዜ ሁሉ ቤተሰቦቿን በንግድ ሥራ እያገዘች አድጋለች። ትምህርቷን ሳትዘነጋ ከልጅነት ዕድሜዋ ጀምሮ በሥራ ያደገችው የኔወርቅ፤ ታላላቆቿ በትምህርት ባይገፉም እርሷ ግን በንግድ ሥራው ወላጆቿን ከማገዝ ጎን ለጎን ለትምህርቷ ትኩረት ትሰጥ ነበር። እርግጥ ነው ተወልዳ ባደገችበት በአዊ ዞን አካባቢ ሴት ልጆችን ገና በጠዋቱ ለትዳር መስጠት የተለመደ ቢሆንም፤ የኔወርቅ ግን ወደ ትዳር ሳይሆን ወደ ትምህርት ቤት የመሄድ ዕድል አግኝታለች።
ከታላላቅ እህት ወንድሞቿና ከአካባቢው ማህበረሰብ በተለየ መንገድ ከትዳር ይልቅ በትምህርቷ መግፋት የቻለችው የኔወርቅ፤ የመጀመሪያ ደረጃን ተወልዳ ባደገችበት አዊ ዞን አዲስ ቅዳም ከተማ ተከታትላለች። በወቅቱ ታዲያ በአዲስ ቅዳም ከተማ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት አልነበረም። ያም ቢሆን የኔወርቅን ከህልሟ ሊያሰናክላት አልቻለም። በአካባቢው ወደሚገኙ ቡሬና ፍኖተ ሰላም ከተማ በማቅናት የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቷን ተከታትላለች።
የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቷን አጠናቅቃ ወደ ጎንደር ዩኒቨርሲቲ ያቀናችው የኔወርቅ፤ በአካውንቲንግና ፋይናንስ የመጀመሪያ ዲግሪዋን ይዛለች። የአካውንቲንግና ፋይናንስ ትምህርቷን ካጠናቀቀች በኋላ ሥራ ፍለጋ ማስታወቂያ አላገላበጠችም። መረጃዎቿን ይዛም ወዲህ ወዲያ አላለችም። በቀጥታ የቤተሰቦቿን የንግድ ሥራ ተቀላቀለች እንጂ። ቀድሞውኑ ያደገችበትንና የምታውቀውን የንግድ ሥራ ተምራ በተማረችው የትምህርት መስክ ለማገልገል ከፍተኛ ፍላጎት አደረባት።
የቤተሰብ በሆነው የንግድ ሥራ ውስጥ የሒሳብ ባለሙያ በመሆን ወደ ሥራ የተቀላቀለችው የኔወርቅ፤ በአዲስ ቅዳም ከተማ በቤተሰቦቿ የንግድ ሥራ ውስጥ ለወራት ከሰራች በኋላ ሙያዋን የሚፈልጉ በርካታ የሥራ ዘርፎች አዲስ አበባ ላይ በመሆናቸው ወደ አዲስ አበባ አቅንታለች። ቤተሰቡ የተሰማራበት የንግድ ሥራ በዋናነት ቡናና ቆዳ ቢሆንም የተለያዩ ጥሬ ዕቃዎች ወደ አዊ ዞን አዲስ ቅዳም ከተማ የሚላከው ከዚሁ ከአዲስ አበባ በመሆኑ አገልግሎቷን ለማስፋት አዲስ አበባ ከተመች።
ከቡናና ከቆዳ ንግድ በተጨማሪም በህንጻ መሳሪያ፣ በህዝብ ትራንስፖርት፣ በጅምላ ንግድና በሌሎችም ሥራዎች የተሰማራው ቤተሰቡ የኔወርቅ በተለያዩ የሥራ ዘርፎች እንድትሰማራ ዕድል ከፈተላት። በመሆኑም በዋናነት ከምትሰራው የሂሳብ ሥራ በተጨማሪ ጉዳይ በማስፈጸም፣ ዕቃ በመግዛትና በሌሎች የሥራ ዘርፎች ጭምር ተሳትፋለች።
ከልጅነት ዕድሜዋ ጀምሮ በሥራ ያደገችው የኔወርቅ፤ በተለያየና ሰፊ በሆነ የንግድ ሥራ መሳተፍ አልከበዳትም። ይልቁንም በሌሎች የሥራ ዘርፎች ለመሰማራት ያላት ጉጉት በከፍተኛ መጠን እያደገ ሄዶ ለንግድ ሥራ ተሰጠች። እናም ቤተሰቦቿ ከጀማመሯቸው የንግድ ሥራዎች በተጨማሪ በሂደት የሆቴል ኢንዱስትሪን ተቀላቀለች። በትውልድ አካባቢዋ በሀዊ ዞን አዲስ ቅዳም ከተማ የመጀመሪያውን አሀዱ ሆቴል በማቋቋም የሆቴል ኢንደስትሪውን አንድ ብላ ጀመረች።
አንድ ተብሎ የተጀመረው ሆቴልም በከፍተኛ ትጋት ሁለት ሊባል ሆነ፤ ሁለተኛውን ሆቴል በዳንግላ ከተማ መገንባት ቻለች። ‹‹ዳንግላ ከተማ ለአዲስ ቅዳም ከተማ ቅርብ ከመሆኗ የተነሳ እንደ ሁለተኛ ከተማችን ናት›› የምትለው የኔወርቅ፤ ሁለተኛውንና ባለ ሶስት ኮከብ ጋሹና ሆቴልን ዳንግላ ከተማ ላይ ስትከፍት ትልቅ ትጋት ጠይቋታል። ከምስረታ ጀምሮ ሆቴሉን በማደራጀትና በመክፈት ጉልህ ድርሻ ቢኖራትም እያንዳንዱ የቤተሰቡ አባላት አሻራው ያረፈበት መሆኑንም ትናገራለች።
ጋሹና ሆቴል በዳንግላ ከተማ ውስጥ ቀዳሚ ሆቴል ሲሆን በወቅቱ 27 አልጋዎች የነበሩት ሲሆን በአሁን ወቅት 54 አልጋዎች አሉት። ሆቴሉ የተሟላ አገልግሎት የሚሰጥ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ የተለያዩ ስብሰባዎች ይካሄዱበታል።
የተማረችው ትምህርት አግዟት ከእህት ከወንድሞቿ በተለየ መንገድ በቢዝነስ ሥራ ውስጥ ገፍታ የገባቸውና በትምህርትም ቀዳሚ የሆነችው የኔወርቅ፤ ከዕለት ዕለት የንግድ ሥራ እየገባት በመሄዱ ውጤታማ መሆን ችላለች። ቤተሰቡ ከለመደው አሰራርና የሥራ ባህሪ ወጣ በማለትም በተለያዩ የንግድ ዘርፎች ለመሰማራት ሌት ተቀን ተግታለች። ለሥራ ባላት ከፍተኛ ፍላጎት ውጤታማ ያደረጋትን ትጋት በማከል ሁለት ሆቴሎችን ማቋቋም ችላለች።
በአዲስ ቅዳም ከተማ እንደስሙ ቀዳሚ የሆነውን አሀዱ ሆቴል እንዲሁም በዳንግላ ከተማ ባለሶስት ኮከብ ጋሹና ሆቴልን ያቋቋመችው የኔወርቅ፤ ሆቴሎቹ በሁለት እግራቸው መቆም መቻላቸውን ስታረጋግጥ ፊቷን ወደ ሌላ የንግድ ሥራ አዙራለች። ወላጅ አባቷ በስፋት ይሰሩት የነበረው የቡና ንግድን ጠንቅቃ ታውቀዋለችና ቡናን እሴት ጨምሮ በአገር ውስጥና በውጭ ገበያ ለማቅረብ ተሰናድታ ወደ ሥራው ገብታለች።
ወላጅ አባቷ በቡና ንግድ ሰፊ ልምድ ያላቸው ቢሆንም እስካሁን ቡናን ማልማት እንዳልጀመሩ ያነሳችው የኔወርቅ፤ ወደፊት ቡናን በማልማት የመሰማራት ፍላጎት እንዳላትና ‹‹ከልማት እስከ ኩባያ›› የሚል እቅድ ያላት መሆኗን ተናግራለች። ይህም ማለት ቡናን ከማልማት ጀምሮ ተፈልቶ እስኪጠጣ ድረስ ባለው ሂደት ተሳታፊ በመሆን በእያንዳንዱ ሰው ቤት ተደራሽ መሆን ነው።
በአሁን ወቅት በየካ አባዶ አካባቢ ጋሹና የቡና ማቀነባባሪያ ፋብሪካ በማቋቋም ቡናን እሴት በመጨመር ቆልታና ፈጭታ ለገበያ ታቀርባለች። ጥሬ ቡናውን ከኢትዮጵያ ምርት ገበያ የምታገኝ መሆኑን ያነሳችው የኔወርቅ፤ ወላጅ አባቷ በኢትዮጵያ ምርት ገበያ ባላቸው ወንበር እንደሆነም አስረድታለች። ይሁንና ወደፊት የቡና ልማት እንደሚኖራት ትልቁ ምኞቷ ነው። ከምርት ገበያ የምታገኘውን የተለያየ ጣዕም ያላቸውን የቡና አይነቶች በጋሹና ቡና ማቀነባበሪያ ፋብሪካ እሴት በመጨመር በጥንቃቄ ተቆልቶና ተፈጭታ በአገር ውስጥ እንዲሁም በውጭ ገበያ ተደራሽ ታደርጋለች።
‹‹ኢትዮጵያ ውስጥ ለቁጥር የበዙ የተለያየ አይነት ጣዕም ያላቸው የቡና ዝርያዎች አሉ›› የምትለው የኔወርቅ፤ ጋሹና ቡናም እነዚህን ኢትዮጵያዊ ጣዕም ያላቸውን የቡና አይነቶች በመጠቀም ለገበያ ተደራሽ ያደርጋል። የይርጋ ጨፌ እንዲሁም የሲዳማ ቡናን ለአገር ውስጥ ገበያ በስፋት የምትጠቀም ሲሆን፤ አልፎ አልፎም የጅማ ቡናን ትጠቀማለች። የውጭ ገበያውን በተመለከት ሁሉንም የቡና አይነቶች በመጠቀም በጥሬውና እሴት በመጨመር ተቆልቶና ተፈጭቶ እንደገበያው ፍላጎት ታቀርባለች።
ጋሹና ቡና በአሁን ወቅት በአገር ውስጥ ገበያ በስፋት እየገባ መሆኑን ያነሳችው የኔወርቅ፤ ፍላጎቷም ከውጭ ገበያ በበለጠ በአገር ውስጥ ገበያ በስፋት መግባት ነው። ምክንያቱም ጥሩ ጣዕም ያለው ቡና ማህበረሰቡ መጠቀም አለበት የሚል ጠንካራ ዕምነት ያላት በመሆኑ ነው። ‹‹ሰዎች ጥሩና ተመራጭ የሆነውን የአገራቸውን ቡና በመጠጣት የተፈጥሮን ጣዕም ማጣጣም እንዳለባቸውና ቆንጆ ጣዕም ያለውን የኢትዮጵያ ቡና ባህላዊ እሴቱን ሳይለቅ ሁሉም ሰው ደርሶት ይጠጣ›› የምትለውም ለዚሁ ነው።
ጋሹና ቡና ኢትዮጵያዊ ጣዕም ያላቸውን የተለያዩ የቡና አይነቶች ከአገር ውስጥ ባለፈ ወደ ውጭ ገበያ በመላክ የተሰማራ ቢሆንም ቅድሚያ ለአገር ውስጥ ገበያ ይሰጣል። የአገር ውስጥ ገበያውን ተደራሽ በማድረግ ገበያው በፈለገው መጠን ቡናን በጥሬውና እሴት ጨምሮ የተቆላው ቡናን ወደ ውጭ ገበያ እየላከ ይገኛል።
በመላው አገሪቱ ተደራሽ የመሆን ፍላጎት አለኝ የምትለው የኔወርቅ፤ ሁሉም ሰው የኢትዮጵያን ቡና ቢያጣጥመው ትወዳለች። እንደ አገር ደግሞ የውጭ ምንዛሪ እጥረትን ለመሸፈን በኤክስፖርት ላይ በስፋት ቢሠራ መልካም ነው በማለት የአገርን ገቢ በማሳደግ ረገድ ጉልህ ድርሻ ያለው የቡና ዘርፍ ገና ብዙ ያልተሰራበትና ሊሰራበት የሚገባው ዘርፍ እንደሆነም አጽንኦት ሰጥታ ትናገራለች።
ጋሹና ቡና በስፋት ገበያ ውስጥ ከገባበት አዲስ አበባ ከተማ በተጨማሪ አዳማና ደብረዘይት በመጠኑ ተደራሽ መሆን ችሏል። ይሁንና ድርጅቱ ብራንዲንግ ላይ ወይም ደግሞ መለያ ስም ላይ የሚሰራ በመሆኑ አጠቃላይ ማህበረሰቡ ጋሹና ቡናን በካፌ ደረጃ ማጣጣም የሚችልበትን ዕድል የመፍጠር ዕቅድም አላት። ጎን ለጎንም ሰዎች እንደየፍላጎታቸው ቡናውን በጥሬው፣ እንዲሁም ተቆልቶና ተፈጭቶ መጠቀም እንዲችሉ ይቀርባል።
ከአገር ውስጥ ባለፈ ለውጭ ገበያ የሚቀርበው ጋሹና ቡና በአሜሪካ ቨርጅኒያ፣ ሜኒሶታና ሜሪላንድ ተደራሽ ሲሆን በአፍሪካ ደግሞ ማሊና ባማኮ እንዲሁም በአረብ ኢምሬትስ ሳውዳረቢያ የገበያ መዳረሻዎቹ ናቸው። የውጭ ገበያውን በስፋት ለመቀላቀል በተለይም ጥራት ላይ ትኩረቱን በማድረግ እየሠራ ያለው ጋሹና ቡና በቀጣይም በዓለም አቀፍ ገበያው ተወዳዳሪ ለመሆን የማቀነባበር ሥራውን በተሻለ ጥራት ይሰራል በዚህም ጥሩ ተከፋይ ይሆናል።
ጋሹና ቡና በቀጣይ ያስቀመጣቸው ሰፋፊ እቅዶች እንዳሉ ሆነው በአሁን ወቅት 32 ዜጎች ለሚደርሱ የአካባቢው ዜጎች የሥራ ዕድል መፍጠር ችሏል። እነዚህ ሰራተኞችም ቡናውን ከመልቀም ጀምሮ እስከ ማሸግ ያሉትን ሥራዎች ያከናውናሉ። አብዛኞቹ ሠራተኞች ሴቶች መሆናቸውን ያነሳችው የኔወርቅ፤ ሴቶች ለሥራ ትጉና ጠንቃቃ በመሆናቸው ምክንያት ቅድሚያ መስጠቷን ትናገራለች።
በጋሹና ቡና ማቀነባባሪያ ከተፈጠረው 32 የሥራ ዕድል በተጨማሪ በሀዊ ዞን ዳንግላ ከተማ በሚገኘው ጋሹና ባለ ሶስት ኮከብ ሆቴል ከ55 በላይ የሥራ ዕድል መፍጠር የቻለችው የኔወርቅ፤ ሆቴሉም ለአካባቢው ማህበረሰብ የተሟላ አገልግሎት እየሰጠ ይገኛል። ከመደበኛው አገልግሎት በተጨማሪም አካባቢዎች እየመጡ ለሰርግ፣ ለልደትና ለተለያዩ ፕሮግራሞች የሚጠቀሙ ደንበኞችም አሉት።
ጋሹና ቡና ማቀነባባሪያ ፋብሪካ የሚገኘው የካ አባዶ ኮንዶሚኒየም አካባቢ በከተማ ኢንዱስትሪ ስር እንደመሆኑ ማህበራዊ ኃላፊነትን በመወጣት ረገድ የአካባቢውን መንገድ ማሰራት ችላለች። የሚፈጠረው የሥራ ዕድልም ከአካባቢው ማህበረሰብ ውጭ አይሆንም። ከዚህ በተጨማሪም በበዓላት ወቅት በአካባቢው የሚገኙ አቅመ ደካሞችን በመጎብኘት እንዲሁም መንግሥት በሚያቀርበው ማንኛውም አገራዊ ጥሪ ምላሽ በመስጠት ማህበራዊ ኃላፊነቱን እየተወጣ ያለ ተቋም ነው።
በቀጣይም ጋሹና ቡና የተነሳበትን ዓላማ ለማሳካት በቡና ልማት በመሰማራት ኢትዮጵያዊ የሆኑና የተለያየ ጣዕም ያላቸውን የቡና አይነቶች በማልማት ከምርት እስከ መጠጥ እንዲደርስ በትጋት መሥራት የየዕለት ተግባሯ እንደሆነ ትናገራለች። ‹‹የኢትዮጵያ ቡና ልንኮራበት የሚገባ ትልቁ ሀብታችን ነው›› የምትለው የኔወርቅ፤ ከላይ ካለው አካል ጀምሮ እስከታች ያለው አርሶ አደር የኢትዮጵያ ቡና በኩራት ቢያስተዋውቅና ቢሰራበት ሕዝቡም አገሪቷም ከዘርፉ ተጠቃሚ መሆን እንደሚችሉ ይችላሉ። ቡና ለአገሪቷ ኢኮኖሚ የጀርባ አጥንት ሆኖ ከማገልገሉም ባለፈ በቀጣይም ትልቅ ተስፋ የሚጣልበት ዘርፍ በመሆኑ ትኩረት ያሻዋል።
ፍሬሕይወት አወቀ
አዲስ ዘመን የካቲት 18 ቀን 2015 ዓ.ም