በአገሪቱ ዘመናዊ ትምህርት በ19ኛው መቶ ዘመን በነገሡት በዳግማዊ ምኒልክ ዘመን በአሁን ዘመን ዳግማዊ ምኒልክ ተብሎ የሚጠራውና ዘመናት የተሻገረው ተቋም መቋቋሙ ይወሳል። እንደ ፕሮፌሰር ጆን ማርካኪስ አገላለጽ ‹‹… ምኒልክ ዘመናዊ ትምህርት ቤትን በመክፈት በኢትዮጵያ ውስጥ ዘመናዊ የትምህርት ዘር የዘሩ ናቸው። … ትምህርት ቤቱም የተሠራው ንጉሠ ነገሥቱ በሰጡት የግል ገንዘብ ነው። …››። በፕሮፌሰር ባሕሩ ዘውዴ የዘመናዊት ኢትዮጵያ ታሪክ ድርሳን አገላለጽም፣ የመደበኛ ትምህርት በኢትዮጵያ ለመስፋፋት እንደ አንድ ዐቢይ ክስተት የሚቆጠረው ድርጊት በዳግማዊ ምኒልክ ዘመን የተከናወነው በንጉሠ ነገሥቱ ስም የሚታወቀው ትምህርት ቤት በ1900 ዓ.ም. መከፈቱ ነው። ‹‹የዘመናዊ ትምህርት›› ፍላጎት እያደገ መምጣት የጀመረው በ19ኛው መቶ ዓመት መሆኑን ከዓድዋ ድል በኋላ ኢትዮጵያ ከአውሮፓና ከአውሮፓውያን ጋር ያላት ግንኙነት እየተጠናከረ ሲሄድ ዘመናዊ ትምህርት ለማስፋፋት አመቺ ሁኔታዎች መፈጠራቸውን የታሪኩ ድርሳን ያመለክታል።
ይሁን እንጂ ነባሩ የኢትዮጵያ ትምህርት ሥርዓት የሚጀምረው ግን በዘመነ አክሱም ከአራተኛው መቶ ዘመን ጀምሮ መሆኑም ይገለጻል። የተለያዩ ጸሐፍትና የሥነ ትምህርት ምሁራን ነባሩን የትምህርት ሥርዓት ባህላዊ የትምህርት ሥርዓት፣ የቤተክህነት ትምህርት ቢሉትም ደስታ በርሀ ስብሐቱ በአንድ ጥናታቸው እንዳመለከቱት፣ ነባሩ የትምህርት ሥርዓት ‹‹የኢትዮጵያ ትምህርት ሥርዓት›› መባል አለበት ይላሉ።›› ለዚህም ማገናዘቢያቸው እስከ 20ኛው መቶ ዓመት መባቻ ድረስ የኢትዮጵያ ትምህርት በተማከለ ወይም ባልተማከለ መልኩ በተለያዩ አካላትና ተቋማት አስተዳደርና ሥር መከናወኑ ነው፡
ዘመናዊ ትምህርት በሀገራችን ከመጀመሩ በፊት ታዳጊዎችን የሚያስተምሩት የሃይማኖት ትምህርት ቤቶች ነበሩ። በእስልምና አሽር ቤት፣ በክርስትና ቄስ ትምህርት ቤት በሚባል ይጠራሉ። ተማሪዎቹም በቅደም ተከተል ደረሳዎችና የቆሎ ተማሪዎች ይባላሉ። የጠቀስናቸው የሃይማኖት ትምህርት ቤቶች ታዳጊዎችን እያስተማሩ ለወግ ለማዕረግ ያበቁ ነበር።
ትምህርቱ ሃይማኖት ተኮር ቢሆንም በግብረ ገብ የታነፀ በስነ ምግባር የበለፀገ ትውልድ የሚፈራባቸው ነበሩ። አሁን አሁን ደብዛቸው እየጠፋ ቢመጣና በአጸደ ሕፃናት ቢዋጥም፤ በከተሞች የቄስ ትምህርት ቤቶችም በብዛት ነበሩ። በዚህም ከፊደል ቆጠራ ጀምረው እስከ ንባብ ድረስ ይማሩ ነበር። ትምህርት ቤቶቹም በአዲስ አበባ እንኳ እንደነገሩ የነበሩ ናቸው። የተወሰነ ፀሀይ መከላከያ ያለው መኖሪያ ቤት ተዘጋጅቶ ልጆች ተሰብስበው ይማሩበታል። እኔ ስማር የተወሰኑ መቀመጫዎች የአጠና እንጨት ተረብርቦ የተሰራባቸው ጎናቸው ረጃጅም ቁመታቸው አጫጭር አግዳሚዎች ከፊሉ ደግሞ ጠፍጣፋ የሚመስሉ ድንጋይ ወደ ጎን ተደርድረው እንቀመጥባቸው እንደነበር አስታውሳለሁ።
የኔታ (ቄሱ) ድርሻቸው ትልቆቹን ማስተማር ነበር። ጀማሪዎችን ደግሞ እንደደረጃቸው የተወሰነ ፊደል የሚያውቁ ተማሪዎች ያስጠናሉ። የሚያስጠኑትን ደግሞ ሌሎች ከፍ ያለ ደረጃ የደረሱ በተራቸው ያስጠናሉ። ፊደሎቹን መገንዘብ ሲጀምሩ በየኔታ ጥያቄ ይቀርብላቸዋል። ካወቁ ወደ ቀጣይ ከሀሁ ወደ አቦጊዳ፤ መልዕክተ፤ ወንጌል ወዘተ እያሉ ይሄዳሉ። ካላወቁ በአለንጋ ተገርፈው በደንብ እንዲያጠኑ ይደረጋል። እንዲህ እያለ እስከ ዳዊት ማንበብ የሚዘልቅ አለ። በከተሞች ቄስ ትምህርት ቤት ተማሪዎች እረፍት ሲወጡ መጫወቻው የትምህርት ቤቱ ሠፈር ነበር እንጂ የራሱ ግቢ የለውም። ውሃ ከጠማችሁ በረፍታችሁ በአካባቢው ካሉ ቤቶች ሄዳችሁ ውሃ ትላላችሁ ይሰጣችኋል። የጠማውም ያልጠማውም ለመጠጣት ይረባረባል።
ትምህርታችን በመደዳ ተቀምጠን ተቃቅፈን እንደዥዋዥዌ እየተወዛወዝን ፊደላችንን ይዘን በዜማ እንለው ነበር። ፊደሉን ስንጨርስ ‹‹ በየኔታ ጉሮሮ ጠጅ ይንቆርቆር፣ በጠላት ጉሮሮ አጥንት ይሰንቀር›› ስንል ይታወሰኛል። ወር በገባ በ21 ማርያም ይባልና 10 ሳንቲም ከቤት አምጥተን አምባሻ ተገዝቶ ተቆርሶ በልተን ወደ ቤታችን እንሄዳለን። እረፍት ስለምንሆን ጊዜውን በደስታ እንራገጥበታለን። በቄስ ትምህርት ቤት፤ የትምህርት ጅማሪ ጉዞ እንዲህ አሃዱ ብሎ ህግና ሥርዓት ማክበር ነው። የኔታ! እንደ ጨረቃ ያድምቆ፣ እንደ ሰርዶ ያለምልሞዎ፣ ብሎ መመረቅና ጉልበት መሳም የተለመደ ነበር። እየተማርን የኔታ የሚገቡ ከሆነ ሁላችንም ብድግ ብለን እንነሳ ነበር። ሌሎች እንግዶችም ቢመጡ ታላላቆችን አክብሮ መነሳት ሥርዓት ነበር። ቁጭ በሉ ስንባል እንቀመጣለን።
በከተሞች የቄስ ትምህርት ቤት የሚባለውን በገጠር የቆሎ ትምህርት ቤት ይሉታል። መምህራኑ ግን የአብነት ትምህርት ሲሉ ይጠሩታል። ከአባት የተገኘ ከአበው የተወረሰ ማለት ነው። በዚህም እንደከተሞች ፊደል ቆጥሮ መሰናበት ብቻ ሳይሆን ሀሁ፤ አቡጊዳ ፤ መልዕክተ ዮሐንስ የዮሐንስ ወንጌል ዳዊት ይማሩበታል።
የአብነት ትምህርት ቤቶች ‹‹ሃይማኖታዊና ባሕላዊ እሳቤዎችን፤ ዕሴቶች እና ትውፊቶችን ለታዳጊዎች እንዲሁም ለአዋቂዎች ›› ለማስተማር የተወጠኑ የቤተ ክርስቲያን የትምህርት ተቋማት ናቸው ሲል በዚሁ ርዕስ ላይ ጥናት ያከናወኑት አሰለፈች ገብረኪዳንን ጠቅሶ ቢቢሲ በአንድ ወቅት ዘግቦ ነበር።
አሰለፈች ከአብነት ትምህርት ልዩ መገለጫዎች መካከል ታዳጊ ተማሪዎቹ በራሳቸው ለወላጅ ፈቃድ ብዙም ሳይጨነቁ ወደ አዳዲስ ስፍራዎች የሚንቀሳቀሱ መሆናቸው፤ ተማሪዎቹ ይህንን በሚያደርጉበት ጊዜም ለትምህርት ያቀኑበት ማኅበረሰብ ምግብ በመቸር የሚደግፋቸው መሆኑ፤ ትምህርቱ በጥቅሉ እስከ አርባ ዓመታት ያህል ሊወስድ መቻሉ እና በአብዛኛውም በአፋዊ አስተምህሮ ላይ የተንጠላጠለ መሆኑ ተጠቃሽ ናቸው ይላሉ።
የአብነት ትምህርት ጉባዔ ቤቶች በሚባሉ የትምህርት ዘርፎች የተከፋፈለ ነው። ፕሮፌሰር ስርግው ሀብተሥላሴና ፕሮፌሰር ታደሰ ታምራት የአብነት ትምህርት ቤት ንባብ ቤት፣ ዜማ ቤት፣ አቋቋም ቤት፣ ቅኔ ቤት፣ ቅዳሴ ቤት እና መፃሕፍት ቤት እንደሚከፈል በጽሁፎቻቸው ጠቅሰዋል። እነዚህ ዘርፎች ከስነ-ኃይማኖታዊ ትምህርት በተጨማሪ የንባብ፣ የሙዚቃ፣ የስነ ግጥም፣ የፈጠራ እንዲሁም የስነ ጽሑፍ ዕውቀትን ለአጥኚዎቻቸው ያበረክታሉ። ደራሲ ሀዲስ አለማየሁ ዮፍታሔ ንጉሤ፣ ፕሮፌሰር መስፍን የዚህ አሻራ ያላቸው ነበሩ።
ጋዜጣ ሲጀመር ጸሐፌ ትዕዛዝ ገብረሥላሴ፣ ዐጥሜ፣ አለቃ ታዬ፣ ብላቴን ጌታ ኅሩይ ወልደሥላሴ፣ሌሎችም አሻራቸው ነበረ። ይህም በወቅቱ በተማሩት ሀገርኛ ትምህርት ነው። ፊደልን፣ የቁጥር ቀመርን፣ ስነ ጽሕፈትና ስነ ጽሑፍን የተወረሰው ከአብነት ትምህርት ነው። በዘመናቸው የቁም ጽሑፍ የሚጽፉ መጽሐፍ የሚደጉሱ ይገኙ ነበር። ቀደም ባሉት መንግሥታት የአስኳላ ትምህርትን ለመመስረትም ሆነ በመንግሥት ተቋማት ለማገልገል ሲፈለግ ግለሰቦች የተወሰዱት ከአብነት ትምህርት ልሂቃን ነበር። ለዚህም እንደ ምሳሌ እነ ሀዲስ አለማየሁና ዮፍታሄ ንጉሴ ይጠቀሳሉ። ትምህርቱን ሲማሩ ከክፉ ምኞት ይርቃሉ፤ (ከሴሰኝነትና ሱሰኝነት፣ ከጭፈራና ዳንኪራ) የዕውቀት ሰይፍ ይታጠቃሉ፣ ሃይማኖታቸውን ያውቃሉ፣ የበቁ የነቁ ሆነው ይገኛሉ።
ወደ ደረሳዎች ደግሞ እንምጣ ደረሳ በእስልምና ልክ እንደ ቆሎ ተማሪዎች ከቦታ ቦታ እየሄዱ ቁራንን የሚቀሩ ተማሪዎች ናቸው። አሽር ቤት ደግሞ የቁርአንን ትምህርት የሚቀስሙበት ነው። በቅርቡ ደራሲ እና ጋዜጠኛ ሐውለት አሕመድ አሽር ቤት በሚል መጽሐፍ አስመርቃ ነበር።
እኔም አማተር ጋዜጠኛ ሆኜ የሚያውቀኝ የክበቤ አባል የነበረው የአሰላው ወዳጄ ሳዲቅ ሐጐስ መጽሐፉን ገዝቶ አበረክቶልኝ ስለነበር የመጽሐፉን ኮድ በኪስ ስልኬ ልኮ በሀገር ፍቅር አዳራሽ በተካሔደው ምርቃት ተገኝቼ መጽሐፉን ወስጃለሁ። ከታች ያለውም ለዚሁ ጽሑፌ ከመጽሐፉ ያገኘሁትን መረጃ ነው፤ ለግብዓት የወሰድኩት እንደሆነ ይታወቅልኝ።
በአሽር ቤት ረጃጅም አግዳሚ የእንጨት ርብራብ ወንዶቹ የሚቀመጡበት ሲሆን የሴቶቹ ደግሞ ከፊት ለፊት የሚገኝ ሆኖ አጫጭር አግዳሚ እንደሆነ የጠቀስኩት መጽሐፍ ያስረዳል። እንደዚያም ሆኖ ስለማይበቃ ጠፍጣፋ ድንጋዮች በማስገባት ለመቀመጫ ይገለገሉበት እንደነበርና እሱም ካነሰ መሬት ላይ መቀመጥ የተለመደ እንደነበር ሐውለት አሕመድ በአሽር ቤት መጽሐፍ የልጅነት ትዝታዋን ታወጋለች።
የአሽር ቤቱ መምህር አሽር ጌታ ነው የሚባሉት። የቄስ ትምህርት ቤቱ መምህር የኔታ እንደሚባሉት ስሙ መሳ ለመሳ የሚመሳሰል ይመስላል። የደስታ ተክለወልድ አዲስ የአማርኛ መዝገበ ቃላት የኔታ የሚለውን ቃል የኔ (የእኔ) ጌታ፣ ጌታዬ፣ አስተማሪዬ፣ መምህሬ ማለት ነው በሚል ይፈታዋል።
በአሽር ቤት አዳዲስ ገቢዎችን ከፍ ያሉ ልጆች የሚያቀሯቸው ሲሆን የእነሱን አቅሪዎች ደግሞ ሌላ ከእነርሱ በቁርአን ደረጃ ከፍ ያለው ያቀራቸውዋል። እንዲህ እንዲህ እያለ የመጨረሻውን ደግሞ አሽር ጌታ ያቀራሉ። ይሁንና በየትኛውም ደረጃ የሚገኝ ደረሳ ወደሚቀጥለው ለማለፍ የአሽር ጌታን ማረጋገጫ /ይሁንታ ማግኘት አለበት ስትል ሐውለት አሕመድ በጻፈችው መጽሐፍ ታስረዳለች።
በጠዋቱ ክፍለ ጊዜ ትንንሽ ልጆች ሰልፍ ይዘው ቂርአታቸውን ለአሽር ጌታ ያሰማሉ። በሚጠበቀው ደረጃ ካልቀሩ ተኮርኩመው በደንብ እንዲከርሩ (ደጋግሞ መቅራት) ይደረጋል። ከሰዓት በኋላ ወይም በማግስቱ ሊሃክሙ (የአሽር ጌታን ይሁንታ ማግኘት) ይችላሉ። የአሽር ጌታችን እያንዳንዱ ደረሳ ከሕፃን እስከ ታዳጊ ወጣቶች ያለንበትን የቁርአን ደረጃ ያውቃሉ አንድ መስመር እዘላለሁ ብንል በራሳችን ላይ ነው የምንፈርደው፤ ሲል መጽሀፉ ይገልፃል።
ከላይ የጠቀስናቸው ሀገርኛ ትምህርት ቤቶች ዕውቀት እምነትን ስነ ምግባርን ለዜጋው የሚያስተምሩ ነበሩ። ትምህርቱ ደግሞ አፋዊ (በቃል የሚጠና በቃል የሚያዝ ነው።) በጥንቱ ዘመን መጽሐፍ እንደልብ ስለማይገኝ ያነበቡትን በቃል መያዝ ግድ ነበር። አሁንም ይህ ባህል በጠቀስናቸው ትምህርት ቤቶች ይታወቃል። በደርግ ዘመን የእስልምና ጉዳዮች አመራር የነበሩት እና በክርስቲያኑ በሙስሊሙ የሚወደዱት ሐጂ ሙሐመድ ሳኒ ሀቢብ የወጡት በጠቀስነው አሽር ቤት ውስጥ መሆኑን መናገር ለቀባሪ ማርዳት ይሆንብናል።
ዘመናዊ ትምህርት ሲመጣ ሀገርኛውን ዕውቀት ገለል ስላደረገው ሰው ጥላቻ ሰባቂ ጦር ነቅናቂ ዘር/ፓርቲ እየቆጠረ መነቋቆር ሥራው አደረገ። ይህ ሀገርኛ ባህላችን በዘመናችን ዘመናዊ ትምህርት እንዳይኮላሽ፤ ሰው ፈጣሪውን የሚፈራ፤ በሀገሩ በእምነቱ የሚኮራ እንዲሆን፤ ዘመናዊ ትምህርቱንም እየተማረ ጎን ለጎን በትርፍ ሰዓቱ እንዲማር ማድረግ ተገቢ ነው።
ኃይለማርያም ወንድሙ
አዲስ ዘመን የካቲት 18 ቀን 2015 ዓ.ም