
አዲስ አበባ፡- ዘንድሮ ለ13ኛ ጊዜ የብሄር ብሄረሰቦችና ህዝቦች በዓል ከመከበሩ አስቀድሞ የህዝብ ለህዝብ ትስስሩን ወደነበረበት ለመመለስ በተለያዩ አካባቢዎች ተንቀሳቅሶ ያደረገው ውይይት ተስፋ ሰጪ መሆኑን የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ወይዘሮ ኬሪያ ኢብራሂም አስታወቁ፡፡
አፈ ጉባኤ ወይዘሮ ኬሪያ ኢብራሂም ከአዲስ ዘመን ጋዜጣ ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ እንደተናገሩት፤ ፌዴሬሽኑ በዓሉ ከመከበሩ በፊት የህዝብ ለህዝብ ትስስርን ለማዳበርና አንድነትና መቻቻሉን ወደነበረበት ለመመለስ በተለያዩ አካባቢዎች ተንቀሳቅሶ ከህዝቡ ጋር ውይይት አካሂዷል፡፡ ከህዝቡም ተስፋ ሰጪ ምላሽ ተገኝቷል ፡፡
ፌዴሬሽኑ ያዘጋጀው የጋራ መድረክ የሲቪክ ማህበራት አመራር፣ የሴቶችና የወጣቶች አደረጃጀቶች፣ የሃይማኖት አባቶች፣ የአገር ሽማግሌዎች፣ አባገዳዎች፣ የጎሳ መሪዎች እንዲሁም በህዝብ ዘንድ ተቀባይነትና እውቅና ያላቸው አካላት
የተካተቱበት መሆኑን አፈ ጉባኤዋ ተናግረዋል፡፡
እርሳቸው እንዳሉት፤ በአሁኑ ወቅት በብዙ አካባቢ የእርስ በእርስ መጠራጠርና ቅሬታ አለ፤ መተማመንም የተሸረሸረበት ሁኔታ ታይቷል፡፡ በርካቶችም ከቀያቸው ተፈናቅለዋል፤ ጥቂት የማይባሉ ዜጎችም በማንነት ሳቢያ ህይወታቸው አልፏል፡፡ ይህ በመሆኑም ቀላል የማይባል የህብረተሰብ ቁጥር በሀዘን ውስጥ መሆኑ ተስተውሏል፡፡ ከእነዚህ መካከል አብዛኛዎቹ ጥቃት የደረሰባቸው በማንነታቸውና በብሄራቸው ምክንያት ነው፡፡
በዚህ ችግር ውስጥ ያለውን ህዝብ በደፈናው በዓሉን አክብር ብሎ ማለቱ ፌዴሬሽኑ የሚከብድ ሆኖ አግኝቶታል ያሉት አፈ ጉባኤ ኬሪያ፣ ከበዓሉ አስቀድሞ ከህዝቡ ጋር ውይይት ማድረግ አስፈላጊ ሆኖ መገኘቱን አስታውቀዋል፡፡ በህዝቡ መካከል የተፈጠረውንም ቁርሾ ለመፍታት እየተሰራ መሆኑን ጠቅሰው፤ በዚህም ጉዳይ በቁርጠኝነት ተከታታይነት ያለው ስራ መስራት ማስፈለጉንም ገልጸዋል፡፡
እርሳቸው እንዳሉት፤ የመንቀሳቀሳቸው ዋና ግብ በተቻለ ሁሉ ሰላምና መረጋጋትን ለመፍጠር ነው፤ ብዝሃነት ስጋት እንዳልሆነና ማንነትም ወደግጭት የሚያመራ አለመሆኑን ግንዛቤ ለማስጨበጥ ነው፡፡ ማንነትን ትውልድ የሚቀባበለው እንጂ ማንም ሊያጠፋው እንደማይችልም ለማስታወስም ነው፡፡
በህዝቡ መካከል ያለው መቻቻል እንዲሸረሸር ያደረገው ምክንያት ምን እንደሆነም በመቻቻል ዙሪያ የሚያጠነጥን ጽሁፍ ተዘጋጅቶ መቅረቡንም አፈ ጉባኤዋ አስረድተዋል፡፡
ውይይቱ ቀጣይነት እንደሚኖረውም ጠቁመዋል፡፡ በውይይቱ ወቅት ከህዝቡ ይነሳ የነበረው ምላሽ የሚያበረታታ መሆኑንም ተናግረው፤ ውይይቱ ቀደም ሲል መደረግ የነበረበት እንደሆነ መናገራቸውን አመልክተዋል፡፡ ብዙ የሚፈታ ችግር መኖሩንና የህግ የበላይነት መከበር እንዳለበትም ህዝቡ በውይይቱ ወቅት ማንሳቱን አስታውቀዋል፡፡ ህዝብ ለህዝብ አለመጋጨቱን ከተሳታፊዎች እንደተነሳም አመልክተው፤ በኃላፊነት ላይ ያሉ አካላት የፈጠሩት ችግር እንደሆነ በግልጽ መናገራቸውን ጠቅሰዋል፡፡
ወይዘሮ ኬሪያ እንዳሉት፤ በዓሉ የመከበሩ ምስጢር አንድ ነን፤ አንለያይም ለማለት ነው፡፡ ስለዚህ ግጭት በተፈጠረበት አካባቢ እርቅና ሰላም በመፍጠር በጋራ በዓሉን ማክበር ተገቢ ነው፡፡ የፌዴሬሽኑ ሃሳብ እርቅ ከተፈጸመ በኋላ ህዝቡ ለምሳሌ በሁለት ክልል መሃከል አጎራባች ያሉ የተኳረፉ ህዝቦች ካሉ ታርቀው ደስታቸውን በጋራ እንዲያደርጉት ነው፡፡
አዲስ ዘመን ህዳር 25/2011
አስቴር ኤልያስ
The topics covered here are always so interesting and unique Thank you for keeping me informed and entertained!