አሜሪካ የአየር መከላከያ ሚሳኤሎችን ለዩክሬን ልትሰጥ ነው

አሜሪካ የፓትሪየት ሚሳኤሎችን ለዩክሬን እንደምትልክ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ተናግረዋል። ፕሬዚዳንቱ ዩክሬን በእጅጉ የምትፈልጋቸው የፓትሪየት የአየር መከላከያ ሚሳኤሎች ከአሜሪካ እንደሚቀርቡላት ገልጸዋል።

ትራምፕ ከሜሪላንድ ለጋዜጠኞች ሲናገሩ፤ ‹‹ዩክሬኖች በጣም የሚፈልጓቸውን ፓትሪዮት ሚሳኤሎችን እንልክላቸዋለን። ምክንያቱም ፑቲን ብዙ ሰዎችን ያስገርማል። ጥሩ ይናገራል፤ ከእዚያ ሌሊት ሌሊት ሁሉንም ሰው በቦምብ ይደበድባል። ስለዚህ እዚያ አካባቢ ችግር አለ። ያን ነገር አልወደውም፤›› ብለዋል።

ፕሬዚዳንቱ ምን ያህል መሣሪያዎችን ለዩክሬን እንደሚልኩ ባይገልጹም፣ ዩክሬን ራሷን መከላከል ስላለባት መሣሪያዎቹን እንደምታገኝ ተናግረዋል። ‹‹አክሲዮስ›› (Axios) ሁለት ስማቸው ያልተገለጸ ምንጮችን ጠቅሶ እንደዘገበው፣ አሜሪካ ለዩክሬን ከምታቀርባቸው የአየር መከላከያዎች በተጨማሪ ጥቃት ለመሰንዘር የሚውሉ መሣሪያዎች ይገኙበታል።

ትራምፕ ባለፈው ሳምንት አውሮፓውያን የሰሜን አትላንቲክ የጦር ቃል ኪዳን ድርጅት (ኔቶ) አጋሮች መሳሪያዎቹን ለኪዬቭ እንዲያስተላልፉ አስተዳደራቸው መወሰኑን አስታውቀው ነበር። ፕሬዚዳንቱ መሣሪያዎቹ ለዩክሬን ስለሚቀርቡበት ሁኔታ በእዚህ ሳምንት ከድርጅቱ ዋና ጸሐፊ ማርክ ሩተ ጋር ይወያያሉ ተብሎ ይጠበቃል።

ለዩክሬን ከሚቀርበው የጦር መሣሪያ በተጨማሪ በሩሲያ ላይ የሚጣሉ ማሕቀቦች ስለመኖራቸው የተጠየቁት ፕሬዚዳንት ትራምፕ፤ ስለማሕቀቦቹ ባይናገሩም፤ በሩሲያው አቻቸው ቭላድሚር ፑቲን መበሳጨታቸውን ግን ገልጸዋል። ‹‹በፕሬዚዳንት ፑቲን በእጅጉ አዝኛለሁ። ፑቲን ቃሉን የሚያከብር ሰው ይመስለኝ ነበር። በጣም በጥሩ ሁኔታ ይናገራል፤ ሌሊት ግን ሰዎችን ይገድላል። ያን ድርጊቱን አንወደውም›› በማለት ተናግረዋል።

ትራምፕ ተባብሶ በቀጠለው ደም አፋሳሹ የሩሲያ-ዩክሬን ጦርነት በሩሲያው አቻቸው ቭላድሚር ፑቲን ደስተኛ ባለመሆናቸው እና ጦርነቱን ለማስቆም የሚደረጉ ሙከራዎች እስካሁን ውጤት ባለማስገኘታቸው፣ በሩሲያ ላይ ማዕቀብ ለመጣል እያሰቡ እንደሆነ ባለፈው ሳምንት ተናግረው ነበር። በወቅቱ ትራምፕ በሩሲያ ላይ ተጨማሪ ማዕቀብ ስለመጣል ጉዳይ ተጠይቀው፣ ‹‹ጠንከር አድርጌ እያሰብኩበት ነው›› የሚል ምላሽ ሰጥተው ነበር።

ከሁለት ሳምንታት በፊት አሜሪካ ለዩክሬን ከምትሰጣቸው የጦር መሣሪያዎች መካከል አንዳንዶቹን ማቋረጧን አስታውቃ ነበር። ውሳኔው የተወሰነው የመከላከያ ሚኒስቴር አሜሪካ ለሌሎች ሀገራት የምታደርገውን ወታደራዊ ድጋፍ መገምገሙን ተከትሎ የአሜሪካንን ጥቅም ለማስቀደም እንደሆነ ዋይት ሃውስ ገልጾ ነበር።

ርምጃው የተወሰደው የአሜሪካ ወታደራዊ መሣሪያዎች ክምችቶች እየቀነሱ መምጣታቸውን ተከትሎ መሆኑን ተዘግቦ ነበር። ይህ ውሳኔ የተላለፈው የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ከዩክሬኑ አቻቸው ቮሎድሚር ዘሌንስኪ ጋር ከሁለት ሳምንታት በፊት በኔዘርላንድስ በተካሄደው የ‹ኔቶ› ጉባኤ ላይ ከተገናኙ በኋላ ነበር። በወቅቱ ትራምፕ አሜሪካ ተጨማሪ የፀረ ሚሳኤሎችን ለዩክሬን ትሰጥ እንደሆን ተጠይቀው ‹‹አንዳንዶቹን ማቅረብ እንችል እንደሆነ የምናየው ይሆናል›› ብለው ነበር። ይህ የአሜሪካ ውሳኔ ሩሲያ በዩክሬን ላይ የምትፈጽመውን ጥቃት አጠናክራ በቀጠለችበት ወቅት መወሰኑ ዩክሬንንና አጋሮቿን ክፉኛ አስጨንቆ ነበር።

ትራምፕ ይህን በተናገሩ በቀናት ልዩነት ደግሞ ሀገራቸው ተጨማሪ የጦር መሣሪያዎችን ለዩክሬን እንደምትልክ አስታውቀዋል። ለዩክሬን ከሚላኩት መሣሪያዎች ውስጥ ዋናዎቹ የአየር መከላከያ መሣሪያዎች እንደሆኑ ጠቁመው ነበር። ‹‹ተጨማሪ መሣሪያዎችን እንልካለን። ዩክሬኖች ራሳቸውን መከላከል አለባቸው›› ማለታቸው ይታወሳል።

የመከላከያ መሥሪያ ቤቱ ፔንታገንም፣ አሜሪካ ለዩክሬን ተጨማሪ መሣሪያዎችን እንደምትልክ አረጋግጧል። የፔንታገን ቃል አቀባይ ሾን ፓርኔል በሰጡት መግለጫ፣ ዩክሬናውያን ራሳቸውን መከላከል መቻላቸውን ለማረጋገጥ አሜሪካ ተጨማሪ የመከላከያ መሣሪያዎችን እንደምትልክ ገልጸዋል። ጦርነቱ ቆሞ ዘላቂ ሰላም እንዲሰፍንም ጥረቷን እንደምትቀጥል ቃል አቀባዩ ተናግረዋል። ፕሬዚዳንት ትራምፕ አሜሪካ ወደ ሌሎች ሀገራት የምትልካቸው የጦር መሣሪያ አቅርቦቶች የአሜሪካንን ጥቅም የሚያስከብሩ መሆናቸውን የማረጋገጥ ሥራቸውን እንደሚቀጥሉም ፓርኔል ገልጸዋል።

ሩሲያ በዩክሬን ላይ የምትፈጽመውን ጥቃት አጠናክራ ቀጥላለች። ባለፉት ሳምንታት ጦርነቱ ከተጀመረበት ጊዜ አንስቶ በዩክሬን ላይ ከፈጸመቻቸው ጥቃቶች ሁሉ ትልልቅ ናቸው የተባሉ የአየር ጥቃቶችን ፈጽማለች። በጥቃቶቹ በመቶዎች የሚቆጠሩ የጦር መሣሪያዎችን ማለትም ሰው አልባ አውሮፕላኖችን፣ ባሊስቲክ እና የክሩዝ ሚሳኤሎችን ተጠቅማለች።

የሩሲያው ፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑቲንም ሀገራቸው ከዩክሬን ጋር ወደ ጦርነት ያስገባት መሠረታዊ ችግር ካልተወገደ ጦርነቱን እንደማታቆም ተናግረዋል። ፑቲን ከቀናት በፊት ከፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ጋር ባደረጉት የስልክ ውይይት፤ ሞስኮ ከኪዬቭ ጋር ወደ ጦርነት ያስገቧት መሠረታዊ ምክንያቶች ሳይወገዱ እና የጦርነቱ መሠረታዊ መነሻ እልባት ሳያገኝ ጦርነቱ እንደማይቆም ነግረዋቸዋል። ከእዚህ በተጨማሪም ለጦርነቱ ፖለቲካዊ መፍትሔ ለመፈለግ ዝግጁ መሆናቸውን እና ሩሲያ ከአሜሪካ ጋር የምታደርጋቸውን ውይይቶች ለመቀጠል ፈቃደኛ ብትሆንም፤ ማንኛውም የሰላም ድርድር መደረግ ያለበት ጉዳዩ በቀጥታ በሚመለከታቸው በሩሲያና ዩክሬን መካከል እንደሆነ ገልጸውላቸዋል።

‹‹ልዩ ወታደራዊ ዘመቻ›› ተብሎ ተሰይሞ የነበረውና በጥቂት ጊዜያት ውስጥ እንደሚጠናቀቅ ተነግሮለት ከሦስት ዓመታት በፊት የተጀመረው የሩሲያ-ዩክሬን ግጭት፤ ዛሬም ሕይወት እየቀጠፈና ንብረት እያወደመ ቀጥሏል። ጦርነቱን ለማስቆም የተሞከሩት ጥረቶች ሁሉ ትርጉም ያለው ውጤት ማስገኘት አልቻሉም። ሁለቱም ሀገራት የሚፈጽሟቸውን ጥቃቶች በየፊናቸው አጠናክረው ቀጥለዋል። ሩሲያ ተኩስ ለማቆም ያስችላል ባለችው ዝርዝር እቅድ ውስጥ የተካተቱት ቅድመ ሁኔታዎቿም በዩክሬንና በምዕራባውያን አጋሮቿ ተቀባይነት ያገኛሉ ተብሎ አይታሰብም። ለእዚህም ነው ብዙ የጂኦ-ፖለቲካ ተንታኞች ‹‹ሩሲያና ዩክሬን የመስማማት ተስፋ አላቸው? ዘላቂ የተኩስ አቁም ብሎም የሰላም ስምምነትስ ይፈራረሙ ይሆን…?›› ብለው አበክረው የሚጠይቁት።

በጋዜጣው ሪፖርተር

አዲስ ዘመን ማክሰኞ ሐምሌ 8 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You