‹‹ … አረቄ ቤት ቺርስና ዲጄ የለም። 32 እና 34ን አያውቋቸውም? ጐጃም በረንዳን አልፈው፤ በሜይ ዴይ ትምህርት ቤት ገባ ብሎ ያሉት መንደሮች። ወይንም ከአዲስ ከተማ ትምህርት ቤት ጀርባ። 32 ቀበሌና 34 ቀበሌ ይባላሉ። ወዳጄ፤ በዚህ መንደር ያሉት ቤቶች ፍቅረኛሞች ይመስላሉ። እፍግፍግ ብለው፤ ትስርስር ያሉ ፍቅረኛሞች። ፍቅራቸው ግድግዳ እስከ መጋራት የሚዘል የምስኪኖች መኖሪያ። መንደሩን ሾፍ ሲያደርጉ እነዚህ ቤቶች በዓይንዎ መቅረፀ ምስል ላይ እርፍ ይላሉ። ድንገት ሣት ብልዎት ብረት ጊቢ ሊያዩ ይችላሉ። ፐ! የሀብታም ቤት ካሉ ተሳስተዋል። ብረት በሩ ሽፋን ነው። በሩን ተሻግረው ሲገቡ ነፍ ማዘር ቤቶች፣ አረቄ ቤቶች፣ ማደሪያ ቤቶች…ያገኛሉ።
ቤቶቹ በጠቅላላ ማለት ይቻላል G+1 ናቸው። መቼም በእርሶ ቤት G+1 ማለት ቤት በቤት ላይ የተደረበበት ነው። ለመንደሩ ግን ይሄ አይደለም – ሌላ ነው። አራት በአራት የሆነች ጠባብ ቤት በጣውላ ወይም በአጣና ለሁለት ተከፍላ ላይዋ ቆጥ፣ ታቿ ሣሎን ማለት እኮ ነው – G+1። …እያንዳንዱን ሙድ እነሆ:- ድንገት እግር ጥልዎት ከምሽቱ አስራ ሁለት ሰዓት በኋላ 32 እና 34 ቢመጡ በየሁለት ሜትር ርቀት “አልጋ አለ … አልጋ ትፈልጋለህ … ንፁህ አልጋ … ክፍል ለብቻ…ንፁህ ፍራሽ አለ…ወለል ትፈልጋለህ…” የሚልዎት ልጅ እግር፣ ሴቶችና እናቶች ያጋጥምዎታል።
መሄጃ ከሌለዎትና በኪስዎ ውስጥ ያለው ብር ከተመናመነ አልጋ በአስራ ሁለት ብር፣ ክፍል ለብቻ ብለው ተነጋግረው ወደ መኝታዎ (አልጋዎ) ይሄዳሉ። ልክ ቤቱን ሲያዩ ክው ይላሉ። ጠባብ ቤት፤ 2በ2 ወይም ከሰፋ 3በ2 የሆነ። ቆይ አልጋዎን ላሣይዎት ብላ ያመጣችዎት ልጅ በመሠላል ወደ ቆጥ ወጥታ ክፍል ለብቻው ያለችዎትን ቤት ታስረክብዎታለች። ክፍል ለብቻው ያለችዎ’ኮ ቆጥ ላይ/ምድር (ሣሎን) ውስጥ ስድስት ሰባት አልጋ ተደርድሮ አልጋዎቹ በመጋረጃ ወይም በካርቱን የተከፈሉትን ነው።
ንድድ ይሉና መቼስ ምን ይደረጋል ብለው ብርድ ልብሱን ገልጠው አረፍ እንዳሉ፤ “የእንኳን ደህና መጣህ” አቀባበል የሚያደርጉልዎ የደለቡ ትኋኖች ናቸው። ገና ከማረፍዎ አፍታ እንኳን ሳይቆዩ ውርር ያደርግዎታል። አከክ አከክ ቢያረጉም እነሱ አይቀንሱም። ንድድ ብለው ብርድልብስዎትን ቢገልጡ ሰውነትዎ ሁላ በተባይ ተሞልቷል። ብሽቅ ብለው እዚህ አላድርም፣ የፈለገ ነገር ይምጣ ይሉና ሱሪዎትን ታጥቀው እግርዎትን መሬት ሊያስረግጡ ቢሞክሩ መሬት ይናፍቅዎታል። አልጋ ስሩና ወለሉ በጠቅላላ “በኬሻ በጠረባ” ተከራዮች ተወሯል። (ኬሻ በጠረባ – ወለል ላይ ኬሻ ተነጥፎ እሚተኛበት ነው።) ይቅርታ ጠይቀው… ተለማምጠው …የተረፈረፈውን ሰው እንዳይረግጡ እየተጠነቀቁ ተራምደው እንደምንም ቤቱን ለቀው ላጥ!›› ይላል ፒያሳ ሙሀሙድ ጋር ጠብቂኝ የሚለው መጸሐፍ ደራሲ መሃመድ ሰልማን ስለ አልጋ ቤቶቹ ምንነትና ማንነት ሲያስረዳ።
ወደኛ ባለታሪኮች ስንመጣ ደግሞ ይህንኑ የሚደግሙልን በርካቶች ናቸው። በክፉ አጋጣሚ አዲስ አበባን የተቀላቀለው ማስረሻ አያሌው አንዱ ሲሆን፤ የእነዚህ መኝታ ቤቶች ጉዳይ እጅግ ከፈተኑትና የየቀን ሮሮ ከሆኑበት መካከል ነው። ማደሪያ አጥተው ከተቸገሩትና ውሎ አዳራቸውን በኬሻበጠረባ ካደረጉት ሰዎች መካከል ስለሆነም ስለመኝታዎቹ ምንነት ስለ ሰፈሩ ሁኔታ ጥንቅቅ አድርጎ ያውቃል።
ማስረሻ ገና በልጅነቱ በምች ምክንያት የዓይን ብርሃኑን አጥቷል። ይባስ ብሎ በሰሜኑ በነበረው ጦርነት ጦስ ይኖርበት የነበረውን ቀዬና ምቾት ትቶ እንዲወጣ ተገዷል። ኑሮው በሰሜን ወሎ ዞን፣ ዳውንት ወረዳ ነበር። የነገ ተስፋውን ለማለምለም በቤተሰብ እገዛም ሲማር ቆይቷል። አዲስ አበባ ከመጣ በኋላ ግን ሁሉ ነገር አልጋ በአልጋ ሊሆንለት አልቻለም። የማያውቀውን አካባቢና ኑሮ በቀላሉ ሊለምደው አልቻለም። ምክንያቱም ዛሬም አካል ጉዳቱ ከ ኑሮ ደረጃው ጋር ተዳምሮ ከጦርነት ያልተናነሰ ህይወት እንዲገፋ አድርጎታል።
አዲስ አበባ ሲመጣ የሚያርፍበትም ሆነ የሚጠጋበት ዘመድ የለውም። የአይነስውራን ማህበር ድጎማ ቢያደርግለትም ለቀን ቤት ኪራዩ እንኳን አይበቃውም። ስለዚህ ምርጫው አንድና አንድ ብቻ ነው። የእናት ቤት (ኬሻ በጠረባ) የሚባሉትን ማደርያዎች ተከራይቶ ቀን እስኪያልፍ ህይወትን መግፋትና የጀመረውን ትምህርት ማጠናቀቅ ዋነኛው ህልሙ ነው።
የኬሻ በጠረባ ቤቶች ለማስረሻ ቤቶቹ ተስፋ ሰጪዎች ቢሆኑም ስቃዩም ናቸው። ኬሻ በጠረባ የሚባሉት ማደርያዎች በቱሃን፤ በቁንጫ፤ ቅማልና ሌሎች ተባዮች የተሞሉ ከመሆናቸውም በላይ እነርሱን ተቋቋምኩ ሲል ሌላ ፈተና ያመጡበታል። ይህም የተከራዩዎች እንቅስቃሴና ማንኮራፋት እረፍት ይነሳዋል። አናት የሚበጠብጥ የጫማና የላብ መጥፎ ጠረንም የነዚህ ቤቶች ዋነኛ መለያዎች ናቸው። በዚያ ላይ ደግሞ ለማደር የሚገቡት ሰዎች ባህሪ የተለያየ በመሆኑ ጩኸቱ እንደአይነስውርነቱ እንኳን በመቅረጸ ድምጹ የቀዳውን ትምህርት ለማዳመጥ አያስችለውም። የቤት ሥራም እንዲሁ እንዲሰራ እድሉ የለውም። ምክንያቱም እያነበበለት የሚያሰራው ሰው አያገኝም። ይህ አልተሳካም ብሎ እንኳን እንቅልፍ ልተኛ ቢል አይችልም።
ቤቱ ሰካራም አለያም ወንበዴን መርጦ የሚያሳድር ባለመሆኑ የተነሳም ሁልጊዜ ንብረቱን በእጁ አቅፎ እንዲተኛ ያስገድደዋል። አስቀምጦ የሚሄድበትም ቤት ስላልሆነ ንብረቱን በሻንጣው ተሸክሞ ትምህርት ቤት እንዲመላለስ ያደርገዋል። ይህም ሆኖ ግን ንብረቱን ማትረፍ አልቻለም። በተደጋጋሚ ትራንስፖርት ላይ ተወስዶበታል። ዩኒፎርሙ ሳይቀር ተዘርፏል። ትምህርት ቤቱ መልካም ፈቃዱን ባይቸረው ኖሮ ዛሬ ትምህርቱን አቋርጦ ነበር። የ12ኛ ክፍል ተማሪም ለመሆን አይበቃም ነበር።
የኬሻ በጠረባ ኪራይ ጉዳይ ይህ ብቻ አይደለም። ኬሻ በጠረባ ተከራይቶ እንደልብ መገላበጥ ማርና ወተት እንደመጠጣት የሚናፈቅ ነው። ኬሻ በጠረባዎች በሰው ስለሚሞሉ ወለሉ ሁሉ መኝታ ይሆናል። ስለዚህም በአንድ ጎን ከተኙ ሳይገላበጡ ማንጋት ግድ ነው። ለሌላኛው መገላበጫ ቦታ የለም። አንዱን ከነኩ ድብድብ መግጠምዎ አይቀርም። ስለዚህም ምርጫዎ የሚሆነው እግሮት እንደታጠፈ አለያም እንደተዘረጋ ማንጋት ብቻ ነው። በዚህም አይነስውሩ ማስረሻም ምንም እንኳን ባያያቸውም እረግጣቸዋለሁ በሚል ስጋት ከተቀመጠበት ሳይንቀሳቀስ ነው ቀናትን፣ ወራትን አሳልፏል። አሁንም በዚህ ሁኔታ እያደረ ነው የ12ኛ ክፍል ትምህርቱን እየተማረ ያለው።
እነርሱ ግን እንደፈለጋቸው ይረጋግጡታል። በተለይ አልፈውት አልጋ የተከራዩት ሲመጡ አንድም ቀን ሳይረግጡትና ሳይጨፈልቁት አይሻገሩም። በዚያ ላይ ደግሞ አንዳንድ ቤቶች መብራት የላቸውምና ስቃዩ ይበረታበታል። መብራቱ ለእርሱ ሳይሆን ወደ ቆጡ አለያም ወደ ኬሻ በጠረባው ላይ የሚያርፉትን እንዲተያዩ ያግዛልና ቢያንስ መረገጡን ይቀንስለታል። እናም ዛሬ የመረጠው ደህና ቢሆን ነገ ደግሞ አዳሩ ሰቆቃ የሚሆንበት አጋጣሚ ብዙ ነው።
የኬሻ በጠረባ ነገር ሲነሳ በጣም የሚገርመው በሰፈሩ ያሉት ልጆች ጉዳይ ነው። ቀን ከትምህርት መልስ ይተኛሉ። ሌት አልጋቸው ስለሚከራይባቸው ሰፈሩን በጨዋታ ሲያቀልጡት ያድራሉ። ከዚያም አልፈው ቤታቸው እንዲከራይላቸው “አልጋ አለ…ክፍል ለብቻ አልጋ አለ…ወንድም አልጋ ትፈልጋለህ…”›› እያሉ ሲጮሁ ያነጋሉ። ቀን ቀን ትምህርት ቤት እየተማሩ እንቅልፍ ጭልጥ አድርጎ የሚወስዳቸው በርካቶች ናቸው።
ወደ ሌላኛዋ ባለታሪካችን ስንገባ ደግሞ ከማስረሻ የተለየ ነገር ያላቸው ናቸው። እንደእርሱ ተከራይ አይደሉም። አከራይ እንጂ። ስለዚህም ይህ ሥራ ለእርሳቸው ልዩ ትርጉም ያለው ነው። የኑሯቸው ምሶሶና የችግራቸው መውጫ ነው። እናም በልዩ ፍቅር ነው የሚሰሩት። ስራው ግን አድካሚና ከብዙዎች ጋርም ለጭቅጭቅና ለዱላ የሚዳርግ ነው። በእርግጥ ሥራውን የገቡበት በአጋጣሚ ነው። ባለቤታቸው ሲሞት፣ ከቋሚ ሥራቸው ሲቀነሱና ልጆቻቸው ታመው ማሳከሚያ ሲያጡ ዘው ብለው አልጋ ማከራየት ውስጥ ገቡ።
የቤት ኪራዩ ልክ እንደአውቶቢስ ተራ ኬሻ በጠረባ የሚባል ነገር የለበትም። ቦታው በተለምዶ ሀዲድ እየተባለ የሚጠራው አካባቢ ላይ ያለ ሲሆን፤ የአልጋ ኪራይ ብቻ ነው ያለው። ስለዚህም በዝቅተኛ ዋጋ ማለትም በ30 ብር አንድ ሰው አንድ አልጋ ይዞ ማደር ይችላል። ተደራራቢ ቆጡ በG+8 ድረስ ያለ ሲሆን፤ ክፍያው እንደ ከፍታው ይለያያል። እንደኮንደሚኒየሙ አይነት ግን እዳይመስላችሁ። ምክንያቱም ኮንደሚኒየም ውሃ ከፍ ያለ ቦታ ላይ መውጣት ስለማይችልና ሰዎችም በከፍታው ምክንያት ስለሚሰቃዩ ላይኛው ላይ ያለው ተከራይ ዋጋ ይቀነስለታል። በእነዚህ ቤቶች ግን ከፍ ካለው ቆጥ ላይ የሚተኛ ሰው ከፍ ያለ ዋጋ መክፈል ይጠበቅበታል። ምክንያቱም ለመሰረቅ፣ አደጋ ውስጥ ለመግባት ቶሎ አይጋለጥም። ሁሉ ነገሩ ሴፍ ነው።
ወይዘሮ ገበያነሽ አልጋ ሲያከራዩ መራጭ ናቸው። ልክ በትላልቅ ሆቴሎች እንደሚደረገው ዕቃዬ ይሰረቃል የሚል ስጋት ያለው ሰው ንብረቱን ለሪስፕሽን እንደሚያስረክበው በሃዲድ መንደርም ስጋት የገባው ሰው ንብረቱን ለወ/ሮ ገበያነሽ አስረክቦ ያለስጋት እንቅልፉን መለጠጥ ይችላል። ከዚያ ባሻገር የእነ ወይዘሮ ገበያነሽ ቤት ተከራይ ሌሎች መልካም እድሎችም አሉት። ለምሳሌ በዓል ሲሆን አብሮ ማሳለፍና ያለውን አብሮ መቋደስ ይፈቀድለታል። በሃዲድ መንደር አልጋ ተከራይ ማለት ቤተሰብ ነው።
‹‹እነዚህ ቤቶች የአከራዮች የእለት ጉርስ የተከራዮቻቸው ደግሞ የደከመ ጎን ማሳረፊያ ናቸው። መውደቂያ ላጡ ምስኪኖች ደግሞ መደጋገፊያ ይሆናሉ። ምክንያቱም ለድሆች የቀን እፎይታቸው የሌሊት ረፍታቸው ናቸው። በድካም የዛለ ሰውነታቸውን ያሳርፉባቸዋል።›› የሚሉት ወይዘሮዋ፤ ይህን ሥራ ልክ እንደልጃቸው ያዩታል። ምክንያቱም የሞቱባቸው ልጆቻቸውን ባይድኑም አሳክመውበታል። በዚያ ላይ የልጃቸው ማስታወሻ ነው። እርሷ በሕይወት በነበረችበት ወቅት ልጆቿን ተንከባክባበታለች። ዛሬም ቢሆን ለልጅልጆቻቸው ሕይወት መቀጠል ጭምር ዋነኛው ምሰሶ የዚህ ሥራ ገቢ ነው። እናም ደንበኞች ክቡር ናቸውና መደረግ ያለበት ሁሉ መደረግ ይኖርበታል ብለው ያምናሉ፤ ያደርጉታልም።
አሁን ላይ በላይ ክፍል ሰርተው የሚያከራዩት ቤት በለስ ቀንቷቸው በደርግ ጊዜ ቀበሌ የሰጣቸው ቤት ነው። እናም አነስተኛ ክፍያ ለመንግሰት እየከፈሉ መኝታ ክፍል ሳያምራቸው ሳሎናቸውን መኝታ አድርገው የገቢ ምንጭ የሚሆናቸውን ተደራራቢ አልጋ በአንዱ ክፍል ውስጥ በማስቀመጥ የገቢ ምንጫቸውን ፈጥረዋል። ቤቱ ለደህንነታቸው ሲባል በግርግዳ የተለየ ሲሆን፤ የራሱ የሆነ በር አለው። ክፍሉ ግን እጅግ ጠባብ ነው:: በአንዱ ክፍል የሚሰራው በሌላው ክፍል በቀላሉ ይሰማልና እንቅልፍ ይናፍቃል። ከዚያም ከፍ ሲል አዳሪዎቹ የተለያዩ ሰዎች በመሆናቸው መጥፎ ጠረኖች አይጠፉም። ሆኖም እርሳቸው ይህ እንዳይከሰት የቻሉትን ያህል ያደርጋሉ። ለአብነት ውሃ በገፍ ያቀርባሉ፤ ካልሲያቸውን የሚያጥቡበት፤ እግራቸውን የሚታጠቡበት ሳሙናም እንዲሁ ይሰጧቸዋል።
አልጋ ተከራዮቹ የሚመጡበት ሰዓት የተወሰነ ሲሆን፤ ወደ አልጋ የመግቢያ ሰዓት እስከ ምሽቱ አራት ሰዓት ብቻ ነው። ከዚያ በኋላ የሚመጣ ሰው ቦታ የለውም። በዚህም መጀመሪያ የተከራዮቹን ከዚያም የራሳቸውን በር ዘግተው ይተኛሉ። ጠዋት 12 ሰዓት በር ይከፍታሉ። ከዚያም ቀደም ብሎ መውጣት የሚፈልግ ካለ አይከለክሉትም። ላርፍድ ያለ ሰውም እንዲሁ እስከ ሁለት ሰዓት እንዲተኛ ይፈቀድለታል። ለሁሉም ወጪዎች ቀድመው በመነሳት እንደተለመደው ውሃና ሳሙና በር ላይ ያስቀምጣሉ። ይህንን በማድረጋቸው ቋሚ አዳሪዎችን ጭምር የፈጠሩበት እድል መኖሩን ያነሳሉ።
‹‹መልካምነት ይከፍላል፤ ከገንዘብ በላይ ቤተሰባዊነት ይበልጣል። ኑሮን ጎዶሎን ለመሙላት ሲባል እንጂ ሰውን ሁሉ በነጻ ማሳደር ይቻል ነበር። ምክንያቱም ቤት የእግዚአብሔር ነው። ግን ወቅቱ ይህንን አይፈቅድም። አሁን ባለው ሁኔታ ሰዎችን አምኖ በራሱ ማሳደር ትልቅ መልካምነት ነው።›› ይላሉ ያለውን የሥራ ሁኔታ ሲያስረዱ። ምክንያቱም እርሳቸውን ባይገጥማቸውም በዚህ ስራ የሚተዳደሩ ሰዎች በመጥፎ ሰዎች ድርጊት ቤተሰባቸው፤ ኑሯቸውና ማንነታቸው ተነጥቀዋል። እናም ሥራው መልካምም መጥፎም ስጦታ አለው ይላሉ።
ጽጌረዳ ጫንያለው
አዲስ ዘመን የካቲት 18 ቀን 2015 ዓ.ም