ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ለመካከለኛና ረጅም ርቀት ጀግናዋ አትሌት ሰንበሬ ተፈሪ በመድረኩ ላስመዘገበቻቸው አንጸባራቂ ድሎቿና አርያነቷ ዕውቅና አበርክቶላታል። አትሌቷ ዕውቅናው የተሰጣት ከትላንት በስትያ በአያት ሬጀንሲ የ2015 ዓ.ም ሳፋሪኮም ቅድሚያ ለሴቶች የ5 ኪሎ ሜትር ውድድር ምዝገባ ማስጀመሪያ ስነስርዓት ላይ ነው።
በአፍሪካ ቀዳሚ የሆነው ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ በርካታ አትሌቶችን ለዓለም አቀፍ ዕውቅና በማብቃት ይታወቃል፡፡ በመድረኩ የተሻለ ተሳትፎና ውጤት ያላቸውንም የሚያበረታታ ሲሆን፤ አትሌት ሰንበሬ ተፈሪ ከእነዚህ መካከል አንዷ ሆናለች፡፡ አትሌቷ በሶስት ተከታታይ የቅድሚያ ለሴቶች 5 ኪሎ ሜትር ውድድሮች ያለ ጣልቃ ገብነት ክብረወሰኖችን መሰባበሯ ለዕውቅና አብቅቷታል። ቅድሚያ ለሴቶች የ5 ኪሎ ሜትር ውድድር እአአ ከ2004 ከተጀመረ አንስቶ ለሶስት ተከታታይ ጊዜ ከሰንበሬ ተፈሪ ውጪ ያሸነፈ አትሌት እንደሌለም በመድረኩ ተገልጿል። ይህም አትሌቷ ለሴቶች የመቻል ምልክት ሆና ላበረከተችው ትልቅ አስተዋጽኦ በታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ የዕውቅና ሽልማት እንዲበረከትላት አስችሏል፡፡
ሽልማቱ የተሰጣት ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ በየዓመቱ በሚያዘጋጀው የቅድሚያ ለሴቶች ሩጫ የ2015 ዓ.ም ምዝገባ ማስጀመሪያና 20ኛ ዓመት ክበረ በዓልን ምክንያት በማድረግ መሆኑም ተጠቁሟል። ለአትሌቷ ዕውቅናውን ያበረከቱትም በክብር እንግድነት የተገኙትና በዚህ መድረክ ድልን መቀዳጀት የቻሉት አትሌት ብርሃኔ አደሬ እና አትሌት አሰለፈች መርጊያ ናቸው፡፡
በመድረኩ እውቅና ከመስጠትም ባሻገር የ2015 ዓ.ም የሳፋሪኮም ቅድሚያ ለሴቶች 5ኪ.ሜ የጎዳና ላይ ሩጫ የምዝገባ ቀንና ቦታም ይፋ ተደርጓል። ተሳታፊዎች ምዝገባውን ከመጪው ሰኞ የካቲት 20/2015 ዓ.ም ጀምሮ በዳሽን ባንክ እንዲሁም በአሞሌ ሞባይል መተግበርያ አማካኝነት 450 ብር በመክፈል መመዝገብ እንደሚችሉ ተጠቁሟል። ውድድሩ መጋቢት 17/2015 ዓ.ም የሚካሄድ ሲሆን፤ 15ሺ ተሳታፊዎች እንደሚካፈሉበትም ተጠቁሟል። ውድድሩ እንደተለመደው መነሻና መድረሻውን ቦሌ አትላስ አድርጎ እንደሚካሄድ ተገልጿል።
የምዝገባውን መጀመርም የታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ስራ አስኪያጅ ወይዘሮ ዳግማዊት አማረ በይፋ አብስረዋል። ‹‹ሳፋሪኮም ወደ ኢትዮጵያ ከገባ ወዲህ የሴቶችን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ጠንክሮ እየሰራ ይገኛል፤ ለዚህም ከነሱ ጋር አብረን በአጋርነት መስራት ጥሩ አጋጣሚ ነው። እንደዚህ ያለ የስያሜ አጋር በማግኘታችንም ደስተኞች ነን›› ሲሉም ወይዘሮ ዳግማዊት ሃሳባቸውን አጋርተዋል።
የሩጫው መልዕክት ከተባበሩት መንግስታት ድርጅት ጋር በመተባበር ‹‹ቦታዬ፣ መብቴ፣ ድምጿ›› የሚል እንደሚሆንም ተገልጿል። የ20ኛ ዓመት ቅድሚያ ለሴቶች ክብረ በዓልና የ2015 ዓ.ም መክፈቻ ዝግጅት ላይም በክብር እንግድነት ሻለቃ አትሌት ኃይሌ ገብረስላሴን ጨምሮ የውድድሩ አምባሳደር አትሌት መሰረት ደፋርና የአዲስ አበባ ሴቶች፣ ህጻናት ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ ኃላፊ ዶክተር ሃና የሺንጉስ መታደም ችለዋል።
የታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ መስራች ሻለቃ ኃይሌ ገብረስላሴ በውድድሩ ትልቅ የሆነ ለውጥ መምጣቱን ገልጾ፤ ‹‹ለሴቶች የምንሰጠው ክብር ለቤተሰባችን የምንሰጠው ክብር ነው›› በማለት ተናግሯል። አክሎም ‹‹ለሴቶች ሩጫ ማወዳደር ብቻ ሳይሆን ቀጥሬ በማሰራው መስሪያ ቤት ውስጥም 60 በመቶ ሰራተኞች ሴቶች በመሆናቸው ለሴቶች በሚሰጠው ልዩ ትኩረት ለሌሎች እንደተሞክሮ ሊወሰዱ ይገባልም›› በማለት አሳስቧል። አትሌት መሰረት ደፋር በበኩሏ ሴት ሆኖ አትሌት መሆን ልምምድ ስለሚያስፈልግ እነዚህን ነገሮች በማድረግ ውጤታማ ስለሆንኩ ኩራት ይሰማኛል በማለት ስሜቷን ገልጻለች። በቀጣይም ውድድሩን ወደ ተሻለ ደረጃ ለማድረስ ድርሻዋን እንደምትወጣ ቃል ገብታለች።
የታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ራዕይ የሆነውን ‹‹ሩጫን የአኗኗር ዘይቤያችን እናድርግ›› ለማጉላት ከውድድሩ በፊት ለ4 ሳምንት የሚቆይ የአካል ብቃት ልምምድ በተለይም በሩጫው ለመሳተፍ ለተዘጋጁ እና የታላቁ ሩጫ አባላት ለሆኑ የስልጠና መርሃ ግብር መዘጋጀቱም ተጠቅሷል። ይህም በነገው ዕለት የካቲት 19/2015 ዓ.ም እንደሚጀመርም ተነግሯል።
የታላቁ ሩጫ የሴቶች ውድድር እአአ በ2004 መካሄድ የጀመረ ሲሆን፤ በ4ሺ500 ሴት ተሳታፊ አትሌቶች ነው፡፡ በአሁኑ ወቅት ቁጥሩ በከፍተኛ ደረጃ ጨምሮ በዘንድሮው ውድድር 15ሺ ሴቶች እንደሚሳተፉም ይጠበቃል።
አለማየሁ ግዛው
አዲስ ዘመን የካቲት 18 ቀን 2015 ዓ.ም