ሀገራችን በተለያዩ ወቅቶች ባጋጠሟት የድርቅ አደጋዎች ከፍ ላሉ ሰብዓዊ፣ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ኪሳራዎች ተዳርጋለች። በአደጋዎቹ በሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎቻችን ለሞትና ለስደት ተዳርገዋል፤ በመቶ ሚሊዮኖች የሚቆጠር የሀገር ሀብትና ንብረት ለውድመት ተዳርጓል፤ በዜጎች ላይ የተፈጠሩ የስነ ልቦና ጠባሳዎችም ዛሬም ቢሆን ገና አላገገሙም።
በ1966 እና በ1977 ዓ.ም በሰሜኑ የሀገሪቱ ክፍሎች በተከሰቱ የድርቅ አደጋዎች ካደረሱት ከፍተኛ ሰብዓዊ፣ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ውድመት ባለፈ ሀገሪቱን በዓለም አቀፍ መድረክ የሀገራችንን ገጽታ በእጅጉ ጎድተዋል፤ የረሀብ ተምሳሌት ተደርጋ እንድትሳልም ነበር። በወቅቱም እንደ ሀገር የከፈልነው ዋጋ የጥቁር ታሪካችን አንድ አካል ተደርጎም ይወሰዳል።
ይህ የታሪካችን ጥቁር ነጥብ አንገት አስደፍቶናል፤ ዛሬ ላይ ሆነን ሳይቀር ወቅቱን ከፍ ባለ የልብ ስብራት እንድናስብ አድርጎናል፤ በተለይም ፈጥነን በመንቀሳቀስ ልንታደጋቸው እንችል የነበርናቸውን ወገኖቻችንን በእኛ የዝግጅትና የአቅም ማነሰ፤ በችግሩ የፖለቲካ ትርፍ /የፖለቲካ ቁማር / አስልተው የተንቀሳቀሱ ቡድኖች ያስከፈሉን ዋጋ ሌላው አስከፊ ገጽታ ነው።
ይህ ጥቁር ታሪክ የፈጠረውን የልብ ስብራትም ሆነ ዓለም አቀፍ ትርክት ለመለወጥ እንደ ሀገር ከፍ ባለ ቁርጠኝነት መንቀሳቀስ በጀመርንበት ማግስት፤ ከተረጂነት ወጥተን በምግብ እህል ራሳችንን ለመቻል ያለንን አቅም እያሰባሰብን ባለበት አሁን ዛሬ ላይ ተመሳሳይ የድርቅ አደጋ በቦረና ዞን ተከስቶ በወገኖቻችን ላይ ከባድ አደጋ ደቅኖ ይገኛል።
መረጃዎች እንደሚያመለክቱት ፤ በዞኑ ባለፉት ሦስት ዓመታት ለተከታታይ አምስት ዙር ዝናብ ሳያገኝ ቆይቷል። በዚህም የተነሳ በዞኑ የሚገኙ 13 ወረዳዎች በድርቅ ተጠቅተዋል፤ በድርቁ ከሁለት ሚሊዮን ሁለት መቶ ሺህ በላይ እንስሳት ሞተዋል፤ 807 ሺህ ሰው ድጋፍ ያስፈልጋቸዋል። ከእነዚህም ውስጥ 167 ሺህ የሚሆኑ ደግሞ አስቸኳይና ተከታታይ ድጋፍ የሚፈልጉ ናቸው።
መንግሥት በአንድ ዙር ብቻ ከ600 ሺህ በላይ ለሚሆኑ ሰዎች ከ90 ሺህ ስድስት መቶ ኩንታል በላይ ስንዴ፣ ሁለት ሺህ 66 ሊትር ዘይት እና 22 የውሃ ቦቴዎች ርዳታ አቅርቧል፡ ከመንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶችና አጋር አካላት ወደ 750 ሚሊዮን የሚጠጋ ገንዘብ ተገኝቷል። ይህም ሆኖ ግን እየቀረበ ያለው ርዳታ ከችግሩ ስፋት አንጻር በቂ አይደለም፤ እንደ ሀገር ፈጥነን መንቀሳቀስ ካልቻልን ሊያስከፍለን የሚችለው ዋጋ የከፋ ሊሆን እንደሚችል መገመት የሚከብድ አይደለም።
በርግጥ አሁንም ቢሆን እንደ ሀገር በቦረና እንስሳት ላይ የደረሰው ጥፋት፤ ከቦረና እንስሳት የዝርያ ተፈላጊነት አንጻር በቀላሉ የሚሰላ አይደለም። የተቀሩትን ለመታደግ ሊኖር የሚችለውን አማራጭ ሁሉ መጠቀምን የሚጠይቅ ነው። የአካባቢው ማኅበረሰብ አርብቶ አደር ከመሆኑም አንፃርም እንስሳቱን መታደግ ማለት ነገዎቹን ከዛሬ ጽልመት አላቆ የብርሃን ተስፋ ማልበስ ያህል ነው።
ለዚህ ደግሞ መንግስት እንደ መንግስት ያለበትን ኃላፊነት ለመወጣት የሚያደርገው ጥረት የሚበረታታ፤ ከፍ ባለ ደረጃ ተጠናክሮ ሊቀጥል የሚገባ ነው። በተለይም የአስቸኳይ ጊዜ ርዳታዎችን በማቅረብም ምንም አይነት ሰብዓዊ ቀውስ እንዳይፈጠር በትኩረት መስራት ይኖርበታል።
በተለይም የሚመለከታቸው የመንግስት አካላት የችግሩን ስፋትና ጥልቀት ለመላው ሕዝባችንንና ለዓለም አቀፉ ሕብረተሰብ በማሳወቅ፤ በችግሩ ዙሪያ ያሉ ብዥታዎችን ማጥራትና የርዳታ አቅርቦቶች በስፋት ለተረጂዎች የሚደርሱበትን አስቸኳይ ሁኔታ ማመቻቸት ይጠበቅባቸዋል።
መላው ሕዝባችንም ያጋጠመን ችግር ከእኛ አቅም በላይ ያልሆነ፤ በኃላፊነት መንፈስ በአንድነት መንቀሳቀስ ከቻልን በቀላሉ ፈጥነን ልንቆጣጠረው የምንችለው መሆኑን በመረዳት “ለወገን ደራሽ ወገን ነው” በሚል መርህ ማዘጋጀት ይኖርበታል። በዚህም ራሱን ከታሪክ እና ከትውልዶች ተወቃሽነት መታደግ ይችላል!
አዲስ ዘመን የካቲት 18 ቀን 2015 ዓ.ም