በኢትዮጵያ አስተናጋጅነት በአዲስ አበባ ቴኒስ ክለብ እየተካየሄደ የሚገኘው የዓለም ከ18 ዓመት በታች ቴኒስ ቻምፒዮና ነገ ፍፃሜ ያገኛል። ውድድሩ ከ28 አገራት የተውጣጡ በርካታ ተጫዋቾች ሲፎካከሩ ቆይተዋል። ቻምፒዮናው በኢትዮጵያ ሲዘጋጅ ከ17 ዓመት በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ ሲሆን፤ ላለፉት ሁለት ሳምንታት የተለያዩ የማጣሪያ፣የጥሎ ማለፍና የግማሽ ፍጻሜ ውድድሮች አስተናግዷል።
በኢትዮጵያ መዘውተር ከጀመረ ረጅም እድሜና ታሪክ እንዳለው የሚነገርለት የቴኒስ ስፖርት ባለፉት ሁለት አስርት ዓመታት ገደማ ተዳክሞ ቆይቷል። በአሁኑ ወቅት ግን ስፖርቱ ላይ በተሰሩት ተስፋሰጪ ስራዎች የዓለም አቀፉን የቴኒስ ፌዴሬሽን ትኩረት መሳብ በመቻሉ የአዘጋጅነቱን እድል ከ17 ዓመት በኋላ ወደ ኢትዮጵያ ማምጣት እንደተቻለ ተገልጿል።
በቻምፒዮናው ኢትዮጵያን ጨምሮ ከ28 በላይ የዓለም አገራት ከተወጣጡ ከ50 በላይ ተጫዋቾችን በአራቱም የአዲስ አበባ ቴኒስ ክለብ ሜዳዎች እያፋለመ ቆይቷል። በውድድሩ 14 ኢትዮጵውያን ወጣትና ተስፈኛ የቴኒስ ተጫዋቾች የተካፈሉ ሲሆን፤ ከነዚህም ውስጥ ሶስቱ (ሁለት ወንድና አንድ ሴት) በታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ አሸንፈው ነጥብ ማስመዝገብ እንደቻሉ ታውቋል። ይህም ኢትዮጵያውያኑ ተጫዋቾች ከራሽያ፣ ከአሜሪካና ፖርቹጋልን ከመሳሰሉ አገራት በቀዳሚ ስፍራ እንዲቀመጡ አድርጓቸዋል። በዚህም ውጤት ኢትዮጵያውያን ተጫዋቾች ዓለም አቀፍ ደረጃን መያዝ ስለሚችሉ በውጪ አገራት ጭምር ሄደው የመወዳደር እድል እንደሚያገኙ ታውቋል።
መሰል የውድድር አይነቶች በአገር ውስጥ መዘጋጀታቸው ለአገር ውስጥ ተጫዋቾችና ለቴኒስ ተመልካቾች ጥሩ ልምድ ከመሆኑ ባሻገር ስፖርቱ በሌላው ዓለም የደረሰበትን ደረጃ ለመከተል መልካም አጋጣሚ እንደሚሆን ተጠቁሟል።
በተጨማሪም በቴኒስ ስፖርት ውስጥ ለሚሳተፉ ተጫዋቾች ፣ አሰልጣኖችና ዳኞች ልምዶችን ለመቅሰም ጥሩ እድልን የፈጠረ ውድድር መሆኑ ተገልጿል።
እንዲህ አይነት ውድድሮችን ማዘገጀት ለአገር ኢኮኖሚ አስተዋጽኦን ከማበርከት በተጨማሪ የስፖርት ቱሪዝምን በማስፋት ከዘርፉ የሚገኘውን ውጭ ምንዛሬ በማሳደግ ጥቅም እንደሚኖረው ታምኖበታል። የአገር ገጽታን በመገንባትም ፋይዳ እንዳለው ተገልጿል።
ለዚህም ተቀዛቅዞ የነበረውን የቴኒስ ስፖርትን ለማነቃቃትና አለም አቀፍ ውድድሮችን የማዘጋጀት ቁመና ላይ ለመድረስ ከሶስት ዓመታት ጀምሮ በርካታ ስራዎች መሰራታቸውን የኢትዮጵያ ቴኒስ ፌዴሬሽን ገልጿል። ፌዴሬሽኑ ለስፖርተኛው የውስጥ ውድድሮችን በማብዛት፣ አዳዲስ የአሰለጣጠን ሂደቶችን ከውጭ ባለሙያ በመጋበዝ ሲሰጥ የቆየ ሲሆን፣ ከዩኒቨርሲቲዎች ጋር በመቀናጀት በመጀመሪያ ዲግሪ ለሚማሩ ተማሪዎች ስልጠና እየተሰጠ መሆኑን ገልጿል።
ስፖርቱን በዩኒቨርሲቲ ደረጃ ለማስፋፋት እንዲያስችል ከኢትዮጵያ ዩኒቨርሲቲዎች ስፖርት ማህበር ጋር ስምምነት በመፈራረም ላለፉት ሁለት ዓመታት በሁለት ዙር ስልጠናዎችን መስጠት እንደቻለም ጠቁሟል። በዋናነት ከባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ ጋር በተገባው ስምምነት መሰረት ዩኒቨርሲቲው ሰላሳ ልጆችን በባለሙያ ድጋፍ በማሰልጠን ላይ ይገኛል። በተጨማሪም ስፖርቱን ለማስፋት በቅርቡ ከአርባ ምንጭና ድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲዎች ጋር ስምምነት ለመፈራረም ፌዴሬሽኑ በዝግጅት ላይ እንደሚገኝ አሳውቋል።
የኢትዮጵያ ቴኒስ ፌዴሬሽን ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ይልማ ከፈለኝ ለአዲስ ዘመን በሰጡት አስተያየት፤ በፌዴሬሽኑ ስር የሚዘጋጁ የአዋቂዎች ውድድር አራት መሆናቸውን ጠቁመው፤ ክለቦችና ክልሎች የራሳቸውን የውስጥ ውድድሮች እንደሚያደርጉ አስረድተዋል። በባህልና ስፖርት ሚኒስቴር ከተያዙ የውድድር መርሃ ግብሮች ውጪ በቴኒስ ፌዴሬሽን የክለብ ቻምፒዮና፣ የኩነት ውድድሮችንና ሌሎች ውድድሮችን ጨምሮ በማዘጋጀት ብዙ የማበረታቻ ሽልማቶች መገኘታቸውንም ጠቁመዋል።
ከአገር ውጪ በሚደረጉ የምስራቅ አፍሪካ ዞን አምስት ውድድሮች ላይ ከ12 ዓመትና ከ14 ዓመት በታች ባሉ የዕድሜ እርከኖች እየተሳተፉ እንደሆነ የገለጹት አቶ ይልማ፤ ፌዴሬሽኑ ከ15 ዓመታት በላይ ተቋርጦ በነበረው የዴቪስ ካፕ ባለፈው ዓመት ለመጀመሪያ ጊዜ ሲካሄድ ተሳትፎ ጥሩ ውጤት እንዳስመዘገበ ገልጸዋል። በመጪው ሰኔ በሚደረገው ውድድር ላይም ለመሳተፍ በመዘጋጀት ላይ መሆናቸውን ጠቁሟል። “እንደዚህ አይነት ውድድሮች መሳተፋችን እና ቻምፒናውን ማዘጋጀታችን በጎ የሆኑ ልምዶችን እንድንቀስም ይረዳናል” በማለትም ተናግረዋል።
ስፖርቱ በባህሪው የዕድሜ ገደብ እንዳለው የገለጹት አቶ ይልማ፣ ተተኪ ላይ መስራት አማራጭ የሌለው መፍትሔ መሆኑን ተናግረዋል። ጁኒር ኢኒሼቲቭ ፕሮግራም ከዓለምአቀፉ ቴኒስ ጋር በመተባበር 14 ዓመትና ከዛ በታች ያሉ ተዳጊዎችን ብቻ መሰረት ያደረገ ስራ በጋራ እንደሚሰራም አክለዋል። ለዚህም የገንዘብ፣ የቁሳቁስና ሙያ ድጋፎችን እንደሚያገኙ ጠቁሟል። እንደ አቶ ይልማ ገለጻ፣ ሌሎች ዓለም አቀፍ ውድድሮችን በቅርቡ ወደ ኢትዮጵያ ለማምጣት ንግግሮች እየተደረጉ እንደሆነና ከተቻለ በዚህ ዓመት ካልሆነ ግን በሚቀጥለው ዓመት ለማምጣት ተስፋሰጪ ምላሽ መገኘቱን ተናግረዋል። “ውድድሩን ከማዘጋጀቱ አስቀድሞ የውድድር ቁመና ላይ ስለመገኘታችን የማዘወተሪያ ስፍራዎች መጠን አይቶ ስላጸደቁልን አሁንም ውድድሩን ለሚያዘጋጀው አካል ዕድሉ እንዲሰጠን ከመጠየቅ አንቦዝንም” ሲሉም አስረድተዋል።
የቴኒስ ስፖርት በኢትዮጵያ መዘውተር የተጀመረው በአጼ ምኒልክ ዘመነ መንግስት በፈረንሳውያን የባቡር ሃዲድ ዝርጋታ ሰራተኞች እንደሆነ መረጃዎች ይጠቁማሉ።
አለማየሁ ግዛው
አዲስ ዘመን ዓርብ የካቲት 17 ቀን 2015 ዓ.ም