መንግስት ከፍተኛ ትኩረት ሰጥቶ ሲንቀሳቀስባቸው ከነበሩ ትላልቅ ፕሮጀክቶች አንዱ ሀገራዊ የስንዴ ምርትን በመጠን እና በጥራት በማሳደግ፤ ሀገርና ሕዝብን በተሻለ ሁኔታ ተጠቃሚ ማድረግ ነው። በዚህም እስካሁን ባለው አፈጻጸም እየተመዘገበ ያለው ውጤት አበረታችና ዓለም አቀፍ እውቅና የተቸረው ነው።
መንግስት መላው ሕዝባችንን አስተባብሮ የጀመረውንን ይህን ፕሮጀክት በቁርጠኝነት ማስቀጠል ከቻለ ፤ ብዙ የትናንት የተመፅዋችነት ታሪኮቻችን እና እነዚሁ የፈጠሩት የልብ ስብራቶች የሚፈወሱበትና አዲስ የታሪክ ትርክት የሚጀመርበት ጊዜ ሩቅ እንደማይሆን ይታመናል።
ሀገራችን ለስንዴ ምርት ካላት ተስማሚ የአየር ንብረት እና በቂ የውሃ አቅርቦት አንጻር፤ እስካሁን የዚህ ተፈጥሮ ሀብት ተጠቃሚ አለመሆኗ በብዙ መልኩ የሚያስቆጭ ነው፤ ይህም ሆኖ ግን አሁንም ዓይናችንን ከፍተን ሀብቱን መጠቀም በሚያስችል ቁመና ላይ መገኘታችን የሚበረታታ ነው።
በተለይም በስንዴ ማምረት ላይ የተሰማራው አርሶ አደር ፕሮጀክቱ የእርሱን ሕይወት በመለወጥ፤ ሀገርን ወደ አዲስ የታሪክ ምእራፍ የማሻገር ራእይ ያነገበ መሆኑን ተገንዝቦ፤ ለልማቱ ልዩ ትኩረት በመስጠት እያደረገ ያለው ተሳትፎና እያስመዘገበ ያለው ውጤት ከፍ ያለ እውቅና የሚቸረው ነው።
ይህን ተሳትፎውን ምርቱ ለውጪ ገበያ ማቅረቡን ተከትሎ በተለያዩ መንገዶች እየተካሄዱ ካሉ የሴራ ፕሮፓጋንዳዎች እና ውዥንብሮች በመጠበቅ፤ መንግስት የጀመረውን ይህን ትውልድ ተሻጋሪ ፕሮጀክት በተሻለ መልኩ ውጤታማ እንዲሆን በትጋት መንቀሳቀስ ይጠበቅበታል።
ፕሮጀክቱ ከፍ ባለ የውጪ ምንዛሬ / የመንግስት የግብርና ኢንቨስትመንት /የሚካሄድ ነው፤ ፕሮጀክቱን ለማስቀጠል ሆነ አሁን ካለበት ከፍ ወዳለ ደረጃ ለማሸጋገር ተጨማሪ የውጪ ምንዛሬ ይጠይቃል፤ ይህን እውን ለማድረግ ደግሞ ቢያንስ ቢያንስ የተወሰነውን ምርት ወደውጭ በመላክ የውጪ ምንዛሬ አቅምን ማሳደግ የግድ ነው።
ይህን ማድረግ ካልተቻለ በቀጣይ የስንዴ ልማቱን በተጀመረበት ልክ ለማስቀጠል የሚያስችል አቅም ሊኖር አይችልም ፤ ይህ ደግሞ በተለይ ምርቱን በማምረት የተሻለ ተጠቃሚ ለሆነው፤ ነገ ላይም የላቀ ተጠቃሚነት ተስፋ ለሚያደርገው ገበሬ ታይቶ እንደሚጠፋ ብርሃን / ተስፋ/ ያህል ሆኖ ማለፉ የማይቀር ነው።
እንደ ሀገርም በብዙ ቁርጠኝነትና ከፍ ያለ ዋጋ “አይቻልምን ወደ ይቻላል” የለወጠውን ታሪካዊ ክስተት ሊያደበዝዝ የሚችል፤ መጪውም ትውልድ ነገዎቹን በተሻሉ ዛሬዎች ላይ እንዳያዋቅርና በተለመደውና በተመጣበት የአይቻልም መንገድ እንዲቀጥል የሚያስገድደው ይሆናል።
በርግጥ ላለፉት ግማሽ ምእተ አመታት በላይ የስንዴ ፖለቲካ ዓለምን ካስከፈለው ዋጋ አንጻር፤ ዛሬ በስንዴ ምርት ራሳችንን ችለን ምርቱን ለውጭ ገበያ ለማቅረብ እየሄድንበት ያለው መንገድ አልጋ በአልጋ ይሆናል ብሎ መገመት የዋህነት እንደሚሆን ይታመናል።
ከዚህ አንጻር ስንዴ ለውጭ ገበያ ማቅረባችንን ተከትሎም ሆነ ሀሳቡ ከተነሳ ጀምሮ እየተካሄደ ያለው የፕሮፓጋንዳ ዘመቻ፤ በብዙ መልኩ ተጠባቂ ነው፤ ጉዳዩን የፖለቲካ አጀንዳ አድርጎ ለመውሰድ የሚደረገው ጥረት ግን ፈጽሞ ተቀባይነት የሌለውና፤ የሀገርንና የሕዝብን ጥቅም አሳልፎ እንደመስጠት የሚቆጠር ነው።
ሀገራት ሁሉ ምርቶቻችውን ለውጭ ገበያ የሚያቀርቡት፤ ምርቱ ተርፏቸው፤ ተትረፍርፏቸው ነው ተብሎ አይታመንም። በተለይም ራሳቸውን ለመለወጥ በብዙ መልኩ ደፋ ቀና የሚሉ ሀገራት ስለነገዎቻቸው አምጠው ያለሟቸውን ሕልሞች እውን ለማድረግ ከጉድለታቸውም ቢሆን ያላቸውን ይዘው የዓለም ገበያን መደባላቃቸው የተለመደ ነው። የኛም ቢሆን ከዚሁ እውነታ የተለየ አይደለም።
ለሀገር ጠቃሚው መንገድ ኢትዮጵያን የሚመጥን ታላቅ ራዕይ መሰነቅ፤ ለዚሁ ራዕይ መሳካት መተባበርና ፈተናዎችንና ተግዳሮቶችን በጥበብ እያለፉ መጓዝ ነው። ከዚህ አንጻር የስንዴ ልማቱም ሆነ የኤክስፖርት ጅማሬው ይበል የሚሰኝና ተጠናክሮና ይበልጥ ውጤታማ ሆኖ ሊቀጥል የሚገባው ነው!
አዲስ ዘመን የካቲት 17 ቀን 2015 ዓ.ም