የመጀመሪያ ልጇ ነውⵆ ሲወለድ ጭንቅላቱ ከሌሎች ህፃናት ለየት ማለቱንም ቀድማ አላስተዋለችም ነበር፡፡ ‹‹ከዚህ በፊት ወልጄ ስለማላውቅና ህፃኑ የመጀመሪያ በመሆኑ ገና የተወለዱ ህፃናት ጭንቅላት መጠን ምን እንደሚመስል አላውቅም›› የምትለው መስተዋት ወሰኑ (የተለወጠ ስም) ሁለት እና ሦስት ወር ሲሞላው ጭንቅላቱ ከተለመደው መጠን የተለየ መሆኑን በደንብ እየተገነዘበች መምጣቷን ታስረዳለች፡፡
በሴት አዳሪነት ሥራ ለተሰማራችው መስተዋት ይሄ የልጇ ሁኔታ ኑሮዋን የበለጠ አክብዶባትና አወሳስቦባታል፡፡ ልጇ በተለይ ከሁለት ወር እስከ አንድ ዓመት ባለው ጊዜ በጣም ይወራጭ ስለነበር ምን እንደፈለገ ለማወቅ ስትቸገር ቆይታለችⵆ አሁን ድረስም አብዝቶ ያለቅስና ይወራጫል፡፡ ስታቅፈውና ስታባብለው ዝም ይላል፡፡ አንድ ዓመት ሁለት ዓመት እያለ የጭንቅላቱ መጠን ሲጨምር ታድያ የበለጠ ግራ መጋባቷንም ታነሳለች፡፡ የሕፃኑ ጭንቅላት ላይ የነበረው ለስላሳ ቦታ እብጠት ያለው መስሏት ነበር፡፡ በእርግጥም እብጠቱ እየጨመረ በመምጣቱ ትክክል ነበረች መስተዋት፡፡ ይዛው ሆስፒታል ስትሄድ የህክምና ባለሙያዎቹ የጎደጎደው በኋላም ያበጠው ለስላሳው የሕፃኑ ጭንቅላት ክፍል (እርግብግቢት) የሰውነት ፈሳሽ ማነስ ምልክት መሆኑ ነገሯት፡፡ ‹‹ይሄኔ የሚወስድልኝ ሰው ባገኝ ልሰጠው ነበር፡፡ ነገር ግን እንኳን ለመውሰድ ገና ጭንቅላቱን ሲያዩት ሰዎች ይደነግጣሉ፡፡ አሁን ድጋፍ እያደረገልኝ ያለ ድርጅትም እንዲወስድልኝ ሞክሬ ነበር ፡፡ ግን አልቀበለም አለኝ›› ትላለች በምሬት፡፡ መስተዋት ይሄን የምትለው ልጇን ጠልታው ሳይሆን የኑሮ ሁኔታ አስገድዷት እንደሆነም ትናገራለች፡፡ ‹‹እኔ ቀንም ሆነ ማታ ወዲያ ወዲህ ተሯሩጨ የዕለት ጉርሴን የምፈልግ ሴት አዳሪ በመሆኔ በፍፁም እሱን አቅፌ መቀመጥ አልችልም›› ስትልም ምክንያቷን ትገልፃለች፡፡
ማርዋ እያሉ ሲያቆላምጧት የሰማነውና ስሟ ይሄው መሆኑን ብቻ የነገረችን ሌላዋ በተለያዩ ቤቶች ልብስ በማጠብ የምትተዳደረው እናት እንደምትለው ልጇ ሁለት እግሩን የተጎዳው በወቅቱ የፖሊዮ ክትባት ስላላስከተበ መሆኑን የሰማችው ከህክምና ባለሙያዎች ነው፡፡ አሁን ዕድሜው ገና በመሆኑ ዝም ብሎ በእንፍቅቁና በዳዴ ቢሄድም እያደገ ሲመጣ መሄድ የሚችለው በክራንች ታግዞ እንደሆነም ባለሙያዎቹ ነግረዋታል፡፡ ግን ደግሞ ሊድን ይችላል በሚል ሕክምና መከታተሉ ተስፋ እንድታደርግ አድርጓታል፡፡ ይህችም እናት በጉዳቱ ምክንያት ህፃኑ ስለሚያስቸግራት ወስዶ የሚያሳድግላት ብታገኝ ደስተኛ እንደሆነችም ትናገራለች፡፡
‹‹የአካል ጉዳት ያላቸው ህፃናት ወላጆች በአብዛኛው ልጆቻቸውን አይፈልጓቸውም›› የምትለው በኢትዮጵያ አካል ጉዳተኞች ማህበራት ፌዴሬሽን ውስጥ የአካል ጉዳተኞች የፕሮግራም አስተባባሪ ወጣት ስምረት ዝናቡ ወደስራው ከመግባቷ በፊት ለአምስት ዓመታት አካል ጉዳተኛ ህፃናት ላይ ስለሰራችም ግንዛቤ እንዳለት ትናገራለች፡፡ ፕሮግራም አስተባባሪዋ እሷ የምትሰራበት ተቋም አንዲወስድላቸው የሚፈልጉና የጠየቁም እናቶች አሉ፡፡ ምክንያቱን ስትገልጽም በአብዛኛው የህፃናቱ ወላጆች በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ ያሉ߹ አብዛኞቹ በሴተኛ አዳሪነትና በየሰው ቤት ልብስ በማጠብ የዕለት ጉርሳቸውን የሚሸፍኑ መሆናቸው ነው፡፡ ይሄን ታሳቢ አድርጎ ለልጆቻቻው በምግብ አቅርቦትና በሌሎች በሚያስፈልጋቸው ጉዳዮች ይደግፋቸዋል፡፡
የአካል ጉዳተኛ ህፃናቱ በአካላቸው ጉዳት ምክንያት በእናቶቻቸው ላይ ከሚያሳድሩት ከፍተኛ ጫና አንፃር ድጋፉ በቂ አይደለም፡፡ በመሆኑም ጫናቸውን ለመቀነስ የሚያስችላቸውን ሌሎች ተጨማሪ ድጋፎች ማለትም ልጆቻቸውን ማዋያ፤ ለራሳቸው መጠለያ የሚሰጥበትም ሁኔታ አለ፡፡ ‹‹እኔ ከዚህ በፊት በአካል ጉዳተኛ ህፃናት ላይ ስሰራ ቆይቻለሁ›› የምትለው ወጣቷ የአካል ጉዳተኛ ህፃናት ጉዳታቸውንና በጉዳታቸው ምክንያት በሚንቀሳቀሱበት ወቅት የሚገጥማቸውን ህመም ወይም ችግር እንደ አዋቂ በአንደበታቸው መግለጽ አለመቻላቸው መሆኑን ታወሳለች፡፡
ህፃናት ስሜታቸውን ወይም ህመምና የተቸገሩባቸውን ጉዳቶች የሚገልጹት በተለያየ መንገድ መሆኑንም ገልጻ ፍላጎታቸው ምን እንደሆነ የሚያስደስታቸውን የሚያስከፋቸውን ላናውቅና ላንረዳላቸው እንችላለን፡፡ በዚህ ወቅት ደግሞ ወደ መጮህ߹ ማልቀስ ነው የሚሄዱት፡፡ የእጅ ጉዳት የሌለባቸው ከሆኑ ያገኙትን ነገር ይደበድባሉ፡፡ ራሳቸውን ከግድግዳ ጋር የሚያጋጩም አሉ፤ መሬት ላይ የሚፈጠፍጡበትና መሬት ላይ እየወደቁ በመነሳት የሚንፈራፈሩበትም ሁኔታ ይፈጠራል፡፡ በዚህ ሁኔታ ደግሞ ለተጨማሪ ጉዳት ሊዳረጉ ይችላሉ፡፡ እንደ ፕሮግራም አስተባባሪዋ ይሄ ሁኔታቸው እጅግ አደገኛ ነው፡፡ ነገር ግን ወላጆቻቸው ወደ ሕክምናም ሆነ ሕክምና የሚያገኙበትን ሁኔታ ወደሚያመቻቸው ማህበር የሚያመጧቸው በጣም ዘግይተው ነው፡፡ እናቶች መስማት የተሳነው ህፃን ልጅ ቢኖርሽ መቼ ነው መስማት ያለመቻሉን ያወቅሽው ቢባሉ ላይመልሱ ይችላሉ፡፡ ምክንያቱም ከፍ እስኪሉ ድረስም ጉዳታቸውን የማያውቁላቸው ብዙ ናቸው፡፡ የአእምሮም ሆነ ሌላ የአካል ጉዳት ያላቸው ህፃናት በተለይ ተናግረው ያለባቸውን ችግር ለማስረዳት ይቸገራሉ፡፡ ስለዚህ አካል ጉዳተኛ ህፃናት የወላጅን ትኩረት ማግኘት አለባቸው፡፡
ሁሉም ወላጅ ምን ዓይነት ልጅ አለኝ የሚለውን ማስተዋል እንዳለበትም ታሳስባለች፡፡ በእኛ አገር ለአካል ጉዳተኝነት ያለው ግንዛቤ ዝቅተኛ ስለሆነ ጉዳቱ የመጣው በወላጆቻቸው ሀጢያት߹ በመርገምትና ሌሎች ብዙ ዓይነት አመለካከቶችም አሉ፡፡ ነገር ግን አንዳንዱ የአካል ጉዳት ፈጥነው ወደ ሆስፒታል ካለመሄድ ሌላውም ቢሆን በተመሳሳይ ቸልተኝነት የሚፈጠር ሊሆን ስለሚችል ሁሉም ወላጅ የወለዳቸውን ልጆች የቀን ተቀን ሁኔታ መከታተል የተለየ ነገር ሲያይ ደግሞ ፈጥኖ ወደሆስፒታል መውሰድ ያስፈልጋልⵆአንዳንድ ችግሮች በመዘግየት ብቻ ታክሞ መዳን ወደማይችልበት ደረጃ ላይ ሊደርስ ይችላል ⵆ ይህ ከሆነ በኋላ ደግሞ ልጆቹን ማገዝ ያስቸግራል፡፡
የአካል ጉዳተኞች ስምምነት መብት በዚህ በኩል መተግበር አለበት፡፡ መንግስትም ለህፃናት በተለይም ለአካል ጉዳተኛ ህፃናት በጀት መመደብ ይገባዋል ትላለች፡፡
ሰላማዊት ውቤ
አዲስ ዘመን የካቲት 16 ቀን 2015 ዓ.ም