የሰላምን ዋጋ ለመግለጽ፤ ሰላም ከሌለ በሰላም ወጥቶ መግባት የማይታሰብ ነው ማለት ብቻ ዋጋውን በእጅጉ ያሳንሰዋል። ምክንያቱም ሰላም በዋጋ አይተመንምና ነው። ሰላም ለሰው ልጆች ብቻ አይደለም ለእንስሳት አራዊቱ ሁሉ የግድ አስፈላጊ ነው። በተለይም ለሰው ልጆች የመኖር ዋስትና ነው። በዕለት ተዕለት ተግባር ውስጥ ከምንተነፍሰው አየር ያልተናነሰ ዋጋም አለው። በጠፋ ጊዜ ታድያ ሰዎች በተስፋ መቁረጥ ድባቴ ውስጥ ይወድቃሉ። ተስፋ በመቁረጥ፣ በፍርሃትና በጥርጣሬም ይሸበባሉ።
እርግጥ ነው አገራት በተለያየ ምክንያት ሰላም ሲያጡ ማስተዋል የተለመደ ነው። ብዙዎቹም ያጡትን ሰላም ለመመለስ ጦርነትን ብቸኛ አማራጭ በማድረግ ጦር መዘው ቃታ ስበው ሲጨራረሱ ማየት የተለመደ ነው። የሰላም አስፈላጊነት ከማንኛውም የግል ጥቅም፣ ፍላጎት እና የጦር መሳሪያ ኃይል የሚበልጥ ሆኖ ሳለ ብዙዎች ጦር ይመዛሉ።
ብዙ አገራት ለሰላማቸው መደፍረስ አይነተኛ ምክንያት ቢኖራቸውም ሰላማቸውን የማረጋጋጥ ኃላፊነትም በእጃቸው መዳፍ ላይ መሆኑ ሳይታለም የተፈታ ነው። ይሁን እንጂ ብዙዎቹ ለሰላም ዋጋ ሲከፍሉና ቅድሚያ ሲሰጡ አይስተዋልም። እንደሌሎች አገራት ሁሉ ኢትዮጵያም ሰላሟን ማደፍረስ የሚችሉ ከበቂ በላይ ምክንያቶች አሏት።
አንዱን ችግር ተሻገርኩ ስትል እግር በእግር ተከታትለው ከልማት ጉዞዋ የሚያስተጓጉሏት ግን ደግሞ ፍጹም ሊያስቀሯት የማይችሉ ብዙ ችግሮች በዙሪያዋ አሉ። በውል ተለይተው እየናጧትና እየተጋሏት ካሉ ችግሮቿ በተጨማሪ ነገ ከነገ ወዲያ ሊፈነዱ የሚችሉ ፈንጂዎች ላለመኖራቸውም ማረጋገጫ የለም።
ኢትዮጵያን በየጊዜው ከሚፈትናት ችግር፣ ድርቅ፣ ረሃብና ሰቆቃ ባሻገር ጦርነትም እጣ ፈንታዋ እስኪመስል ኖራበታለች አሁንም አለችበት። እርግጥ ነው ሁሌም ቢሆን ጥፋት፣ ውድመትና ኪሳራን ብቻ የሚያስከትለውን ጦርነትን መምረጥ የግድ የሚሆንበት ጊዜ አለ። ጦርነት አማራጭ ጠፍቶ የግድ የሚገባበት ቢሆንም ቅሉ መጨረሻው መስማማትና መደራደር እንደሆነም ይታመናል።
በተግባርም እየሆነ ያለው ይኸው ነው። የኢትዮጵያ መንግሥት ከሕወሓት ጋር የግድ ሆኖበት በገጠመው ጦርነት የሆነው ይሄው ነው። ጦርነት ያው ጦርነት ነውና ዜጎች በጦርነቱ ሰላም አጥተዋል፤ ብዙ ዋጋም ከፍለዋል። ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ምስቅልቅሎሽ ተፈጥሯል።
ሁለት ዓመታትን ያስቆጠረው የሰሜኑ ጦርነት ባስከተለው ምስቅልቅሎሽ በሕይወትና በንብረት ላይ ከደረሰው ውድመት በተጨማሪ የሕዝቦችን ችግር ተመልክተን እንደ ሰው በተለይም እንደ ኢትዮጵያዊ በብዙ ታመናል ቆስለናል።
ከቁስላችን እንድንሽር አልያም ከህመማችን እንድንፈወስ ታድያ ሰላም የግድ በመሆኑ ሰላም እንዲሰፍን ሆኗል። ጦርነትን አስወግዶ ሰላምን ለማምጣት ቆም ብሎ ማሰብና መስከን ቀዳሚው ጉዳይ በመሆኑ መንግሥት ‹‹ሰላምን ለማስፈንና ብልጽግናን ለማስቀጠል ብቸኛው አማራጭ ጦርነቱን ማቆም ነው›› ብሎ በማመኑ የሰላም እጆቹን መዘርጋቱ ይታወቃል።
ለሰላም የተዘረጉት የመንግሥት እጆችም ዛሬ ለተፈጠረው ሰላም የነበራቸው ሚና ጉልህ ነው። ከጦርነት ወጥተን የሰላም አየር መተንፈስ መቻላችንም ለዚሁ ነው። ለተፈጠረው ሰላም ተግባራዊነቱና አፈጻጸሙ ምንም ይሁን ምን ጦርነት መቆሙ ለብዙዎች እፎይታን ሰጥቷል።
‹‹ጦርነት ቆመ›› የሚለውን ዜና በመስማት ብቻ የብዙ የእናቶች እንባ ታብሶ ጭንቀታቸው ረገብ ብሏል። በጦርነት ቀጠና ውስጥ የሚገኙ ዜጎችም ዛሬ ከባሩድ ሽታ ከተኩስ ሩምታ ነጻ ወጥተው የሰላም አየር መተንፈስ ጀምረዋል። ይህ ለብዙዎች እፎይታን የሰጠ ትልቅ ተግባር ነው።
ትልቅ ዋጋ ያለውን ሰላም ማረጋገጥ ለመንግሥት ብቻ የሚተው ተግባር አይደለም። እያንዳንዱ ዜጋ ጉልህ አበርክቶ ያለው በመሆኑ ለሰላሙ ዘብ ሊቆም ይገባል። በአካል ከሚከናወነው ጦርነት ውጭ ዛሬም የኢትዮጵያን ሰላምና ደህንነት ለማደፍረስ የተዘጋጁ እዚህም እዚያም የተቀበሩ ፈንጅዎች ስለመኖራቸው ለቁጥር የበዙ ማሳያዎች አሉ።
ቁምነገሩ ግን እነዚህ ፈንጂዎች እንዲፈነዱ ዕድል የመስጠትና ያለመስጠት ጉዳይ ነው። መሽቶ በነጋ ቁጥር ሰላማችንን የሚያደፍርሱና እርስ በርስ እንድንጋጭና እንድንፋጭ አጀንዳ የሚቀርጹልን እልፍ ናቸው። እኛም ‹‹የዋህዎች የተቀባበሉ ሽጉጦች ናቸው›› እንደሚባለው አንድ ጊዜ እንኳ ቆም ብለን አናስብም። ክፉዎች ባዘጋጁልን የጥፋት ወጥመድ ዘው ብለን ገብተን ሰላማችንን ለጠላቶቻችን አሳልፈን ስንሰጥ ይታያል።
በዚህም የጠብ፣ የጦርነትና የመገዳደል ምንጭ የሆነውን ጥላቻ እናረግዛለን። እርስ በእርስ እንገፋፋለን። ነገር ግን ቆም ብለን ብናስብና ሰከን ብለን ብናሰላስል ዛሬ ብሔርተኝነትና ጽንፈኝነት መሬት ረግጦ ሊውጠን ባልተገዳዳረ ነበር። አሁን ላይ በዙሪያችን የምናስተውላቸው ለቁጥር ብዙ ግራ መጋባቶችም ባለመስከናችን የመጡ ችግሮቻችን ናቸው።
እርግጥ ነው የእኔ ብቻ የሚል አስተሳሰብን ያነገበ ቡድን በጉልህ ተንሰራፍቶ ቀፎው እንደተነካ ንብ ግር እያለ እዚህም እዚያም ፈንጂውን ማፈንዳት ጀምሯል። ይሁንና “አንድ እንጨት አይነድም…” እንዲሉ አበው ህዝቡ በአንድነት፣ በፍቅር፣ በይቅርታና በመቻቻል ስሜት የጋራ በሆነችው አንድ አገር ውስጥ በሰላም ተጠልሎ ለመኖር ግርታውን ማጽዳት ከህዝብ ይጠበቃል።
ህዝብ ሁሌም ቢሆን ነገሮችን በሰከነ መንገድ ሊያስተውልና ሀቅን አንጥሮ ሊረዳ ይገባል። ከጦርነት ወጥተን ኡ…ፈ…ይ ስንል ሌላ ችግር እየተፈጠረ የሰላም እጦት አየሩን እንዳይሞላው ሃይ ማለት ይገባል። ይህ ካልሆነ ግን ፍርሃት፣ ጥርጣሬና ስጋት ሸብቦ በመያዝ ከብልጽግና ጉዟችን ያዘናጋናል።
ከዚህም ባለፈ የህዝቡ የልማት ፍላጎትና የሥራ ዕድል ፈጠራ ገና ብዙ የሚቀር ሆኖ ሳለ፣ በሁከት ምክንያት የልማት ተቋማት መውደማቸው ቀሪ የቤት ሥራዎቻችንን ያበዛዋል፤ የውጤቱን ጊዜም ያርቀዋል። የአገሪቱ እድገትም የውድመቱን ያህል ወደኋላ ይጎተታል።
ስለዚህ የህዝብን ሰላም ከሚያውኩ ማናቸውም ድርጊቶች በመጠበቅ የሁሉም ነገር መሰረት የሆነውና ትልቅ ዋጋ ላለው ሰላም ዋጋ ከፍለን የአገርን አንድነት፣ ሰላምና ፍቅር፤ ዕድገት ብልጽግናን ማረጋገጥ ከእያንዳንዳችን ይጠበቃል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ በአንድ ወቅት ባደረጉት ንግግር ስለ አገር የተናገሩትን ልዋስና ላብቃ “አገር እንደሰው ናት፤ እኛ እንደሆነው ትሆናለች። ብንፋቀር ፍቅር ታዘንባለች፣ ይቅር ከተባባልን ፈውስ ታፈልቃለች፣ ብንተጋ ብልፅግናን ታጎርፋለች፣ ብንማር ትሰለጥናለች፣ ብንከባበር ብንተባበር ትከብራለች፣ ትገዝፋለች፣ ትልቃለች…”
ፍሬሕይወት አወቀ
አዲስ ዘመን የካቲት 16 ቀን 2015 ዓ.ም