ባለንበት ወቅት በፈጣን ሁኔታ ከማደግ ባለፈ ፤ ነገዎቻቸው ላይ ተስፋ ሰንቀው ለመሮጥ ለሚንደረደሩ ህዝቦች እንደ አንድ ትልቅ አቅም ሆነው ከሚያገለግሉ አገራት መካከል አንዷ ቻይና ነች ። በዚህም እያገኘችው ያለው ዓለም አቀፍ እውቅና እለት እለት እየጨመረ ይገኛል።
በተለይም በቀደሙት ዘመናት በነበሩ የቅኝ አገዛዝ ሆነ ከዛም በኋላ በተፈጠሩ የእጅ አዙር ቅኝ አገዛዝ ስርአቶች ውስብስብ በሆኑ ውጪያዊ ችግሮች ብዙ ዋጋ ለመክፈል ለተገደዱት የአፍሪካ ሕዝቦች እያደረገችው ያለው ድጋፍ በታሪክ ውስጥ ትልቅ ስፍራ የሚኖረው ነው።
ከአስገዳጅ የፖለቲካ ጫና በወጣ፤ የጋራ ተጠቃሚነትን መሰረት ባደረገ፤ ከሁሉም በላይ የአህጉሪቱን ህዝቦች ነገዎች ተስፋ ሰጭ በሚያደርግ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ አስተሳሰብ የተቃኘው የቻይና አሁነኛ አካሄድ በብዙ መልኩ ዘመኑን የዋጀ እንደሆነም ይታመናል።
የአህጉሪቱን ህዝቦች በተሻለ መንገድ በባቡር ትራንስፖርት ለማቀናጀት የያዘችው ፕሮጀክት ዋን ቤልት ዋንሮድ ስትራቴጂን / One Belt One Road Strategy/ ጨምሮ ፤ የልማት ስራዎችን በገንዘብና በቴክኖሎጂ በመደገፍ፤ ለልማት የሚሆን የገንዘብ ብድሮችንና እርዳታዎችን በመስጠት እያደረገች ያለው ድጋፍ የአህጉሪቱ ህዝቦች ለመሻታቸው አማራጭ እንዲያገኙ አስችሏቸዋል።
ከዛም ባለፈ ከነጻነት ማግስት ያለሟትን የበለፀገች አፍሪካ የመፍጠር ራእይ፤ በአዲስ ተስፋና መነቃቃት ለመተግበር የሚያስችል አቅም መፍጠር እያስቻላቸው ነው። ድምጻቸው በዓለም አቀፍ መድረኮች የተሻለ ተደማጭነት የሚያገኙበትንም እድል እየፈጠረ ነው ።
የአህጉሪቱ ህዝቦች አህን አሁን በሀብታቸው መደራደር ፤ ተደራድረው ተጠቃሚ የሚሆኑበት ዓለም አቀፍ ሁኔታዎች እየታዩ ነው፤ በዚህም በቀደሙት ዘመናት አማራጭ አ ጥተው / ተስፋ ቢስ ሆነው/ ያጧቸውን ፤ ፖለቲካዊ ፣ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ መብቶቻቸውን በተሻለ አማራጭ በእጃቸው እንዲያስገቡ ተጨማሪ አቅም እየሆነ ነው ።
ኢትዮጵያም በነገዎቻቸው ተስፋ አድርገው ለመለወጥ ከሚተጉ አገሮች እንዷ እንደ መሆኗ፤ በአጭር ጊዜ ሁለንተናዊ እድገት እያስመዘገበች፤ በዚህም ለብዙዎች ተስፋ እየሆነች ካለችው ቻይና በብዙ መልኩ ተጠቃሚ የመሆኗ እውነታ የአደባባይ ሚስጥር ነው።
በተለይም ባለፉት ሁለት አስርት ዓመታት የቻይና መንግስት በኢትዮጵያ የተጀመረውን ልማት በሁለንተናዊ መልኩ ለመደገፍ የሄደበት መንገድ፤ በሁለቱ አገራት የነበረውንና ዘመናት ያስቆጠረውን ግንኙነት ከማደስ ባለፈ በአዲስ መልክ በተጠናከረ መልኩ እንዲቀጥል አስችሏል።
በለፉት ሁለት አስርት በአገሪቱ የተከናወኑ የልማት ስራዎች በአብዛኛው ከቻይና መንግስት በተገኙ በረጅም ጊዜ በአነስተኛ ወለድ በሚከፈሉ ብድሮች እና የልማት ድጋፎች ነው። በዚህም አገርን እንደአገር ተጠቃሚ ያደረጉ ብዙ እድሎች ተፈጥረዋል።
ከቴክኖሎጂና ከእውቀት ሽግግርም አንፃር ቻይና እንደ አንድ አቅም ሆና እያገለገለችን ነው። በዚህም አገሪቱ ዘመኑን የሚመጥን እውቀት ባለቤት የምትሆንበት መልካም አጋጣሚዎች ተፈጥረዋል። የእድሉ ተጠቃሚ የሆኑ ዜጎቻችን ቁጥር ቀላል አይደለም።
ከዚህም ባለፈ ከነገ በስቲያ ጀምሮ 80 የሚጠጉ የኢትዮጵያ ምርቶች በቻይና ገበያ ከቀረጥ ነጻ እንዲገቡ የቻይና መንግስት የደረሰበት ውሳኔ ፤ አገሪቱ ለኢትዮጵያና ለኢትዮጵያውያን ያላትን ከፍያለ ከበሬታ በአደባባይ ያመላከተ ነው።
የፕሬዚዳንት ጆ ባይደን አስተዳደር ባልተገባ መንገድ ኢትዮጵያን አሜሪካ ለአፍሪካ ከሰጠችው የቀረጥ ነጻ እድል /አግዋ / ባገደችበት፤ እገዳው የራሱን የሆነ ችግር ይዞ በመጣበትና አገርን እየተፈታተነ በሚገኝበት በዚህ ወቅት፤ የቻይና መንግሥት የሰጠው ይህ የቀረጥ ነጻ እድል ለኢትዮጵያውያን ከእድል በላይ ነው።
አዲስ ዘመን የካቲት 16 ቀን 2015 ዓ.ም