በአገሪቱ የማህበራት ታሪክ ውስጥ ከቀዳሚዎቹ ተርታ የሆነው የቀድሞው የኢትዮጵያ ቡና ላኪዎች ማኅበር ያሁኑ የኢትዮጵያ ቡና ማህበር ግብይትን በማሳለጥ ረገድ አበርክቶው የጎላ ነው። ቡና ከአገር ውስጥ ገበያ ባለፈ በውጭው ዓለም እንዲታወቅና እንዲሸጥ በማድረግ ከ50 ዓመት በላይ ልምድ ያለው የኢትዮጵያ ቡና ማህበር ዛሬም በቡና ግብይት ሂደት ውስጥ ጉልህ ሚና አለው።
በ1961 ዓ.ም በ12 አባላት የተቋቋመው የኢትዮጵያ ቡና ማህበር የኢትዮጵያ ቡናን ወደ ውጭ ገበያ ለማቅረብ ያላሰለሰ ጥረት ሲያደርግ መቆየቱን የዘርፉ ባለሙያዎች ይናገራሉ። ከዛሬ 50 ዓመት በፊት ማህበሩ ሲቋቋም ወደ ውጭ ገበያ ይቀርብ የነበረው የቡና መጠን ከ10ሺ ቶን ያልበለጠ እንደሆነ መረጃዎች ያሳያሉ። ይሁንና ማህበሩ ወደ ውጭ ገበያ የሚላከው የቡና መጠን ከፍ እንዲልና የግብይት ሂደቱ የተሳለጠ እንዲሆን በርካታ ሥራዎችን ሲሰራ ቆይቷል።
የኢትዮጵያ ቡና በአገር ውስጥና በዓለም አቀፍ ገበያ እንዲታወቅ የዘርፉ ምሁራን፣ ዓለም አቀፍ ገዢዎች፣ ታላላቅ ኩባንያዎችንና ታዋቂ ሰዎችን በማሳተፍ ማህበሩ ከፍተኛ ጥረት አድርጓል። በመሆኑም በአሁን ወቅት ከሶስት መቶ ሺ ቶን በላይ የኢትዮጵያ ቡና ወደ ውጭ ገበያ እየተላከ እንደሆነ ከኢትዮጵያ ቡና ላኪዎች ማህበር የተገኘው መረጃ ያመለክታል።
የኢትዮጵያ ቡና ማኅበር ፕሬዘዳንት አቶ ደሳለኝ ጀና እንደሚሉት የኢትዮጵያ ቡና ማህበር በግል ዘርፉ መካከል ድልድይ ሆኖ ሲያገለግል ቆይቷል። በተለይም በ50 ዓመታት ጉዞ ውስጥ የኢትዮጵያ ቡና ገበያ መዳረሻ እንዲሰፋ በማድረግ ዘርፈ ብዙ ተግባራትን ሲያከናውን ቆይቷል። በመሆኑም በአሁን ወቅት ከ60 በላይ የሚሆኑ አገራት የኢትዮጵያን ቡና እየተቀበሉ እንደሆነ ይናገራሉ።
ከጊዜ ወደ ጊዜ ውጤታማ እየሆነ የመጣው ማህበር የኢትዮጵያ ቡናን ወደ ውጭ ገበያ በማቅረብ ጉልህ ሚና ሲጫወት ቆይቷል። በተለይም በቀደመው ጊዜ ገበያውን የሚመራ አካል ባልነበረበት ወቅት የኢትዮጵያ ቡናን በዓለም ገበያ ሲያስተዋውቅ ቆይቷል። በተለያዩ የዓለም አገራት ኤግዚብሽኖችን በማዘጋጀት የኢትዮጵያ የቡና ማህበረሰብንና ዓለም አቀፍ ገዢዎችን በማቀራረብ በድልድይነት ሲያገለግል እንደነበርም አንስተዋል።
ማህበሩ ከቡና ዘርፍ ጋር ተያያዥነት ያላቸውን የመንግሥት ፖሊሲዎች፣ ህጎችና መመሪያዎች ያስተዋውቃል። የአፍሪካና ዓለም አቀፍ የቡና ማህበራት አባል በመሆንም የቴክኒክና የልምድ ልውውጥ ሲያደርግ ቆይቷል። በዚህም የአባላትን አፈጻጸም አቅም በማጎልበትና ወቅታዊ የሆነ ዓለም አቀፍ የቡና ገበያና የዋጋ መረጃ በመስጠት አባላቱ ጥራት ያለው ቡና በብዛት ለዓለም ገበያ እንዲያቀርቡ የማበረታታት ሥራ ሲሰራ ቆይቷል። በቀጣይም የኢትዮጵያ ቡና ዓለም አቀፍ ተደራሽነቱ እንዲሰፋ በሚያስችሉ ተግባራት ላይ ትኩረት አድርጎ የሚሰራ መሆኑን አቶ ደሳለኝ አስረድተዋል።
የቡና ላኪዎች ቁጥርን ከማሳደግ ባለፈ የገበያ መዳረሻን በማስፋት የኢትጵያ ቡና በዓለም ገበያ ሰፊ ተደራሽነት እንዲኖረው እየሰራ ያለው ማህበሩ፤ በተለይም በግብይት ሂደት ውስጥ በርካታ ችግሮች ሲገጥሙት እንደነበርና መፍትሔ ሲሰጥበት እንደቆየም አስታውሰዋል። ከዚህ ቀደም ፊት ለፊት በግልጽ ጨረታ ይከናወን የነበረው የቡና ግብይት ችግሮች የነበሩት በመሆኑ መንግሥት ችግሩን በመረዳት ቡና ወደ አንድ ማዕከል እንዲገባ አድርጓል።
በመሆኑም የቡና በግብይት ስርዓት ተበጅቶለት በምርት ገበያ በኩል ግብይቱ እንዲሳለጥ ተደርጓል። ይሁንና በምርት ገበያ በኩል የሚከናወነው የቡና ግብይት ሂደትም እንደታሰበው አርሶ አደሩን ተጠቃሚ ማድርግ ባለመቻሉ መንግሥት ሪፎርም ማድርጉን ያስታወሱት አቶ ደሳለኝ፤ በዚህም ቡና ላኪውና አርሶ አደሩ በቀጥታ ትስስር ግብይት እንዲያከናውን በማድረግ በቡና ግብይት ሂደት ውስጥ የነበሩ ችግሮችን መቅረፍ እንደተቻለ ነው ያብራሩት።
የቡና ግብይት በየዘመኑ የገጠሙት ችግሮች ቢኖሩም በአሁን ወቅት በተለይም አምራቹን ተጠቃሚ ማድርግ የሚችል የግብይት ስርዓት ተፈጻሚ መሆኑን የጠቀሱት ደግሞ የኢትዮጵያ ቡና ማህበር ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ግዛት ወርቁ ናቸው። እሳቸው እንዳሉት በደርግ ዘመነ መንግሥት ማህበሩ ተዳክሞ የነበረ ቢሆንም፤ የግሉ ዘርፍ እንዳይዳከም ሲሰራ መቆየቱን አስታውሰው በወቅቱ በመጠን ያነሰ ቢሆንም በግሉ ዘርፍ ቡና ሲላክ እንደነበር ተናግረዋል። በቡና የግብይት ሰንሰለት ውስጥ ይስተዋሉ የነበሩ ችግሮች ደረጃ በደረጃ እየተፈቱ የመጡ መሆኑን የሚጠቅሱት ፕሬዚዳንቱ፤ ከዘርፉ ተጠቃሚ መሆን የሚቻለው ግን በዋናነት ጥራት ላይ ሲሰራ እንደሆነ ያስረዳሉ።
‹‹ከቡና ገበሬውም ሆነ ላኪው ተጠቃሚ መሆን የሚችለው ጥራቱ ሲሻሻል ነው›› የሚሉት አቶ ግዛት፤ ከመቼውም ጊዜ በበለጠ በአሁን ወቅት “ካፕ ኦፍ ኤክሰለንስ” ትልቅ ድጋፍ እያደረገ መሆኑን ተናግረዋል። በተለይም ምንም አይንት አሴት የማይጨምረውን ደላላ ከገበያ ሰንሰለት ውስጥ እንዲወጣና ቁጥሩ እንዲቀንስ ማህበሩ ከፍተኛ ጥረት ሲያደርግ መቆየቱን ይገልፃሉ። ጥራት ሲሻሻል ቡና የተሻላ ዋጋ ያወጣል። በአሁን ወቅትም የኢትዮጵያ ቡና ዓለም አቀፍ ገበያው ላይ የተሻለ ዋጋ እንዲያወጣ እንደ “ካፕ ኦፍ ኤክሰለንስ” በሂደት ውስጥ እየገቡ ያሉ አዳዲስ አሰራሮች አሉ። እነዚህ መግባታቸው ገበሬውና ላኪው ተጠቃሚ እንዲሆን እንዲሁም የቡና ጥራት እንዲሻሻልና የኢትዮጵያ ቡና በዓለም አቀፍ ገበያ የተሻለ ዋጋ እንዲያወጣ ያርጋል። ለዚህም ማህበሩ የተለያዩ ስልጠናዎችን በመስጠት ከፍተኛ ጥረት ሲያደርግ መቆየቱን አስረድተዋል።
የቀርጫንሼ ቡና ላኪ ድርጅት ባለቤትና የኢትዮጵያ ቡና ማህበር የቦርድ አባል አቶ እስራኤል ደገፋ በበኩላቸው፤ በግብይት ሂደት ውስጥ የነበሩ ችግሮች ከሶስት ዓመታት በፊት መቅረፍ እንደተቻለ አንስተዋል። እሳቸው እንዳሉት በአሁን ወቅት ገበሬውና ላኪው በቀጥታ የገበያ ትስስር ፈጥሮ መገበያየት እንዲችል ሆኗል። በዚህም የደላላን ሰንሰለት መስበር እንደተቻለና አርሶ አደሩ እንዲሁም ላኪው ከዘርፉ ተጠቃሚ መሆን ችሏል።
ይሁንና በዓለም አገራት በነጻ ገበያ ተወዳዳሪ ሆኖ ለውጭ ገበያ በሚቀርበው የኢትዮጵያ ቡና በተለይም የቡና ባለቤት የሆነው አርሶ አደር በሚገባው ልክ ተጠቃሚ አልነበረም። አገሪቷም ከዘርፉ ማግኘት የሚገባትን ውጤት እያገኘች እንዳልሆነ አንስተዋል። ለዚህም በዋናነት አርሶ አደሩ ቡናን እያለማ ያለበት መንገድ ዘመናዊና የተሻሻለ ባለመሆኑ ነው ይላሉ። ይሁንና በአሁን ወቅት ጥራት ያለውን ምርት ይዞ ወደ ዓለም ገበያ መቅረብ እንዲቻል በማህበሩ በኩል የተለያዩ ሥራዎች እየተሰሩ ሲሆን በዚህም አበረታች ውጤት እየተመዘገበ ይገኛል።
‹‹ጥራት ያለው ምርት ይዞ መቅረብ ተወዳዳሪ ያደርጋል›› የሚሉት አቶ እስራኤል፤ በተለይም ከሪፎርሙ ወዲህ ትርጉም ያለው ለውጥ መመዝገብ እንደተቻለ አንስተዋል። በተለይም የስፔሻሊቲ ቡና ዝግጅቶች ቁጥራቸው እየተበራከተ በመምጣቱ የኢትዮጵያ ቡና የተሻለ ዋጋ እንዲያገኝ አድርጓል። ባለፈው በጀት ዓመትም ኢትዮጵያ በታሪኳ አንድ ነጥብ አራት ቢሊዮብ የአሜሪካን ዶላር ማግኘት ችላለች። ለዚህም በዋነኛነት ግብዓት ሆኖ ያገለገለው የስፔሻሊቲ ቡና ዝግጅትና የኤክስፖርት መጠን መጨመር ነው ብለዋል።
የኢትዮጵያ ቡና በተፈጥሮ ልዩ ቢሆንም በአዘገጃጀት ችግር ምክንያት ከደረጃ እየወረደ መሆኑን በማንሳትም፤ ወደፊት መንግሥትን ጨምሮ ከግብርና ሚኒስቴር ጋር በጋራ በመሆን የአዘገጃጃት ችግሮችን በመቅረፍ ጥራት ያለው ቡና በተሻለ ዋጋ ለዓለም ገበያ ለማቅረብ ጥረት ይደረጋል በማለት ቡና ብቻውን ውጤት ሊያመጣ የማይችል መሆኑንም ተናግረዋል። አገር ከቡና የምታገኘውን ውጤት ለማሳደግም ሆነ የቡናው ባለቤት የሆነውን አርሶ አድር ተጠቃሚ ለማድረግ የሚመለከታቸው አካላት በጋራ መሥራት ያለባቸው መሆኑን አጽንኦት ሰጥተው ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ ቡና ባለቤት የሆነው አርሶ አደር ላይ ሰፊ ሥራ መሠራት እንዳለበት ያነሱት አቶ እስራኤል፤ አርሶ አደሩ ዛሬም በትናንሽ መሬት ላይ በተለመደው መንገድ ቡናን እያለማ እንደሆነ ነው የተናገሩት። በመሆኑም ኢትዮጵያ በቡና ምርቷ ያላትን አቅም ሁሉ ተጠቅማለች ማለት አይቻልም። ቡና በዓለም አቀፍ ገበያ የሚቀርብ ምርት በመሆኑ የገበያ ተጽዕኖ ቢኖርም በሚገባው ልክ ያልተጠቀምንበት ዘርፍ እንደሆነ ነው ያስረዱት።
ኢትዮጵያ የቡና አምራች አገር እንደመሆኗ ዋጋ ተቀባይ እንጂ ዋጋ ሰጪ አይደለችም የሚሉት አቶ እስራኤል፤ ይህም በመሆኑም ባለፈው ዓመት በዓለም አቀፍ ደረጃ ለቡና በተሰጠው ከፍተኛ ዋጋ እንዲሁም በሌሎች ምክንያቶች የኢትዮጵያ ቡና የተሻለ ዋጋ ማምጣት ችሏል። አሁን ደግሞ የቡና ባህሪ ሆኖ ዋጋው ዝቅ እያለ እንደሆነ አንስተው ለዚህም መፍትሔው የምርት መጠኑን ማሳደግ እንደሆነ ነው የሚናገሩት።
ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ ከእያንዳንዱ ማሳ ውስጥ ገብቶ የኤክስቴንሽን አገልግሎት በመስጠት ውጤት ማምጣት ይቻላል። ምርትና ምርታማነትን ማሳደግ ከተቻለም አሁን ላይ ተመዘገበ ከተባለው ከፍተኛ ውጤት በበለጠ ሶስትና አራት ቢሊዮን የአሜሪካን ዶላር በዘርፉ ማምጣት ይቻላል። ኢትዮጵያ ሰፊ አቅም ያላት በመሆኑም በዘንድሮ ዓመትም የታቀደው ዕቅድ የሚሳካ እንደሚሆን ያላቸውን ዕምነት ሲገልጹ ከምርታማነት ጎን ለጎን በግብይት ስርዓቱ ላይም ሰፊ ሥራ መሰራት ያለበት መሆኑን ጠቁመዋል።
የቡና ግብይት እረጅም ሰንሰለት ያለው ከመሆኑ ጋር ተያይዞ ቡና ላኪዎች ወጣ ገባ የሚሉበት ሁኔታ መኖሩን ያነሱት አቶ እስራኤል፤ እንደ አገር የሚጠቅመን አርሶ አደሩና ላኪው በቀጥታ ተገናኝቶ መገበያየት ሲችል ነው። ይህም ቡናን በተሻለ ዋጋ ለገበያ ማቅረብ አስችሏል። ከዚህም በተጨማሪ ቀጣይነት ያለው ሥራ ለመሥራት ዕድል ይሰጣል። ሪፎርሙም ለዚህ ጥሩ ምላሽ በመስጠት በግብይት ስርዓት ሂደት ውስጥ ትርጉም ያለው ውጤት መመዝገብ ተችሏል። በመሆኑም ከዚህ ቀደም ላለፉት ዘጠኝና አስር ዓመታት በቡና ግብይት ስርዓት ውስጥ ፈታኝ የነበሩ ችግሮች በዚህ ሁለትና ሶስት ዓመታት ውስጥ ችግሩ ተቀርፏል ነው ያሉት። በቀጣይም የምርቱ ባለቤት የሆነው አምራቹ ልዩ ተጠቃሚ መሆን እንዲችል ይሰራልም ብለዋል።
የኢትዮጵያ ቡና በዓለም አቀፍ ደረጃ ከሚገኙ የቡና አይነቶች ጋር ሲወዳዳር በዓለም ገበያ የተሻለ እንደሆነ ይታወቃል። በዓለም ከሚታወቁና ስም ከወጣላቸው የቡና አይነቶች መካከልም የጃማይካ ቡና ብሉ ማውንቴን፣ ኮና፣ የአሜሪካ ሱማትራ እና የኢንዶኔዥያ ቡናዎች በዓለም ገበያ በፍተኛ መጠን የሚሸጡ ቢሆንም የኢትዮጵያ ቡና ሲቀመስ ከእነዚህ አገራት ያነሰ እንዳልሆነ መረጃዎች ያሳያሉ።
ኢትዮጵያ የቡና መገኛ አገር እንደመሆኗ እንዲሁም በቡና ኤክስፖርት ውስጥ ረዥም ዕድሜን ያስቆጠረች ቢሆንም ከመነሻው ጀምሮ በተገቢው መንገድ የተሰራበት ባለመሆኑ በዓለም ገበያ የሚጠበቅባት ደረጃ ላይ መድረስ አልቻለችም። ከመንግሥት ስርዓት ጀምሮ በርካታ ችግሮች ዘርፉ ሲፈትኑት የቆየ በመሆኑም ቡናን በሚፈለገው ልክ ለዓለም ገበያ ማስተዋወቅ አልተቻለም። ይሁንና በአሁን ወቅት መንግሥት ከማህበሩ ጎን በመሆን በጋራ እየሠራ በዘርፉ የሚያጋጥሙ ችግሮችን ደረጃ በደረጅ መፍታት በመቻሉ የቡና ግብይት ከዓመት ዓመት የተሻለ እንቅስቃሴ እያደረገ የኤክስፖርት መጠኑም ሆነ የውጭ ምንዛሪ ግኝቱ እየጨመረ መጥቷል። ይህንኑ በቀጣይነት ዘላቂ ለማድረግና የበለጠ ለማሻሻል በተለይም ምርትና ምርታማነትን ማሳደግና ጥራቱን ማስጠበቅ ምርጫ የሌለው አማራጭ መሆኑን የዘርፉ ባለሙያዎች ይናገራሉ።
ፍሬሕይወት አወቀ
አዲስ ዘመን የካቲት 15 ቀን 2015 ዓ.ም